Map St Joseph Cistercians

Top Panel

የዐቢይ ጾም 18ኛ ቀን

የዐቢይ ጾም 18ኛ ቀን

the-dark-night-of-the-soulእምነት

የጸሎት የመጀመርያው ደረጃ እምነት ነው። ስለዚህ ስለ እምነት ያለን ግንዛቤ የተንሸዋረረ ከሆነ የጸሎት ሕይወታችንም ሸውራራ መሆኑ ግልጽ ነው፤ እምነት ስሜት አይደለም፤ እምነት የሆነ ሰሞን ሞቅታ  አይደለም፤ እምነት ወደ አንዳች መልዕልተ ባህርያዊ ነገር መሳብ አይደለም፤ እምነት እንደው ዝም ብሎ በሰው ልጅ መንፈስ ውስጥ የተቀመጠ ቁም ነገር አይደለም፤ እምነት “እግዚአብሔር አለ” የሚል ዝንባሌ አይደለም፤ እምነት አንድ ሰው “ድኛለሁ” ወይም “ጸድቄያለሁ” ብሎ ለራሱ የሚያውጀው እና ከራሱ ዐዋጅ በስተቀር ሌላ ምንም ተጨባጭ ማስረጃ የሌለው የግል የጽድቅ ስሜት አይደለም፤ እምነት ከማናቸውም አይነት ውጫዊ ነገሮች ጋር ግንኙነት የሌለው ግላዊ እና ውስጣዊ አቋም አይደለም፤ እምነት “የነፍስ ኃይል” አይደለም፤ እምነት ከነፍሳችን ስር የሚነሳ እና መላ ማንነታችንን ወርሮ ነገር ሁሉ ለበጎ መሆኑን የሚያረጋግጥልን ምናብ አይደለም፤ እምነት ይዘቱ ከሌሎች ጋር ልካፈለው የማይቻለኝ የእኔ ብቻ የሆነ ነገር አይደለም፤ እምነት ስለ እግዚአብሔር ያለኝ መላ ምት ወይም ግምት አይደለም፤ እምነት ምክኒያታዊ ጥናት ላይ የተመረኮዘ የሐሳቦቼ ትክክለኛነት ማረጋገጫ ማኅተም አይደለም፤ እምነት የሳይንሳዊ ምርምር ፍሬ አይደለም፤ ምክኒያቱም እምነት እርግጠኝነትን አይጠይቅም፤ የምታምነው ነገር በተመሳሳይ ጊዜ በምልዐት የማታውቀው ነገር ነው። ያንን ነገር በምልዐት ባወቅኸው ቅጽበት ማመን ታቆማለህ፤ ወይንም ደግሞ ከማወቅህ በፊት በነበረህ አይነት መረዳት ነገሩን አትመለከተውም።

እምነት ልብን እና አእምሮን ፍጹም የሚያደርግ እውቀት ነው፤ እምነት ፈቃድን እና እውቀትን ፍጹም ያደርጋል እንጂ አያጠፋቸውም። እምነት አእምሮ በአመክንዮ ኃይል ሊደርስበት ወደማይችል እውነት ከፍ ይል ዘንድ ፈቃድን እና ዕውቀትን ወደዚህ እውነት የሚያጠጋጋ ኃይል ነው። እግዚአብሔርን በእርሱነቱ እናውቀው ዘንድ እግዚአብሔርን የሚያውቅ ብርኀን  የምናገኘው በእምነት ነው፤ እምነት ሕያው ከሆነ አምላክ ጋር የሚያገናኘን መለኮታዊ ኃይል እንጂ የተፈጠሩ ነገሮችን በመመልከት እና የፍጥረታቸውን ሰንሰለታዊ ምንጭ ለማግኘት በሚደረግ ስልታዊ ቀመር ስለ መጀመርያው ምንጭ (the first principle) ወይንም ስለማይንቀሳቀሰው አንቀሳቃሽ (the unmoved mover) ያለን እውቀት አይደለም። በመሆኑም እምነት የሚታየው ግዙፉ ነገር ማንነት እና የኅልውናው ምንጭ የሚረጋገጥበት ውስጣዊ ማስረጃ አይደለም።

መለኮታዊ የሆነውን ነገር በሚመለከት ማመን የሚለው ቃል በሰብዓዊ ማንነታችን ልንረዳው የማንችለው ሁለት የተለያዩ ነገር ግን እውነተኛ ማንነቶች መልዕተ ባሕርያዊ በሆነ ምህዋር ፊት ለፊት የሚተያዩበት እና የሚገናኙበት ኃይል ነው፣ ይህም ግንኙነት ከአንዳች ውስጣዊም ይሁን ውጫዊ ማስረጃ በላይ የሚዘልቅ፣ እንዲህ ነው ተብሎ ማስረጃ ሊጠቀስለት የማይችል፣ ምሥጢራዊ እና መልዕልተ አመክንዮ ያለበት፣ ነገር ግን በተወሰነ ጥልቀት አእምሮ ሊያሰላስለው የሚችል ምሥጢራዊ ውሕደት ነው። የዚህ ምሥጢር እውነት ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚገለጥ ሲሆን እንደ ግልጠቱ በጎ ፈቃድ ልግሥና የተገለጠውን እውነት እናውቃለን።

እምነት በባሕርዩ የአእምሮን ምክኒያታዊ ምሕዋር የሚሻገር እውነታ በመሆኑ ለአእምሮአዊ እውቀት አጥጋቢ ምላሽ ሊሰጥ አይጠበቅበትም። እምነት አእምሮ በአመክንዮ ሊደርስበት ወደማይችለው እና ጥልቀቱ ወደሚፈተንበት ብርኀን መቅረብ ይችላል፤ በመሆኑም እምነት የሚደርስበትን ብርኀን አእምሮ ሙሉ በሙሉ ተጨባጭ እና ምክኒያታዊ ነው ብሎ ሊረዳው አይቻለውም። ነገር ግን በእምነት የሚታነጽ አእምሮ የእምነትን ብረኀን ለመመልከት እና ለመቀበል ከራሱ ምክኒያታዊ ጉልበት የሚበልጥ የጸጋ ኃይል ሊሞላ ይችላል። ማመን እግዚአብሔርን ማፍቀርን ይጠይቃል፤ ፍቅር የፈቃድ እና የእውቀት ውሳኔ በመሆኑ አእምሮ እግዚአብሔርን በሚያፈቅር እምነት በኩል ወደ እውቀት እና ወደ ብርኀን ደስታ ሊደርስ ዐቅም ያገኛል። በመሆኑም እግዚአብሔርን በማወቅ እና ያንን ያወቀውን እግዚአብሔርን በማፍቀር አእምሮ ዕረፍት ያገኛል። በመሰረቱ አእምሮ እንደተረዳበት የዕውቀቱ ጥልቀት ብቻ ሳይሆን እንዳመነበት እና ከእግዚአብሔር ጸጋ ጋር እንደተባበረበት ነጻ ፈቃድ መጠን እግዚአብሔርን እንደተገለጠበት ልግሥና ልክ ሊያውቀው ይችላል።

ነገር ግን እግዚአብሔርን በማንነቱ ለማወቅ አይቻልም፤ እርሱ ሊታወቅ፣ ሊደረስበት፣ ሊታሰብ፣ ሊገመት፣ ሊነጻጸር፣ በሕብረ አምሳል ሊገለጽ ከሚችለው ከየትኛውም ነገር በላይ ነው። እርሱ ራሱን ሊገለጥ እና እርሱነቱን ሊያሳይ በወደደበት መጠን ማወቅ እንችል ዘንድ የአእምሮ እና የፍቃድ ዕወቀት ልሂቅነት ብቻ ሳይሆን ከሁሉ በፊት እምነት ያለበት ትህትና ያስፈልጋል። እግዚአብሔር ጥበብ ነው እንላለን እንጂ ጥበብ የሆነበትን ልክ እና ጥልቀት ልናውቅ በፍጹም አንችልም፤ እግዚአብሔር ፍቅር ነው ስንል ፍቅር ምን እንደሆነ ከምንገነዘብበት መረዳት ተነስተን እንናገራለን እንጂ እግዚአብሔር ፍቅር የሆነበትን ጥልቀት ማየት፣ መለካት፣ ማሰላሰል፣ ማወቅ አንችልም። ምሕረት እና ይቅርታ ምን እንደሆኑ ካለን መረዳት እና ግንዛቤ በመነሳት እግዚአብሔር መሐሪ ነው እንላለን እንጂ እግዚአብሔር በእግዚአብሔርነቱ ሁሉ ምሕረት የሆነበትን የይቅርታውን ፍጽምና ሊሰፍር እና ሊረዳ የሚችል አእምሮ የለም። ይህንን ለመረዳት በእግዚአብሔር አእምሮ ማሰብ እና እግዚአብሔር ራሱን በሚያውቅበት ዕውቀት ማወቅ ያስፈልጋል፤ ይህ ደግሞ አእምሮ እና ዕውቀት ሳይሆን እግዚአብሔርን ራሱን መሆንን ይጠይቃል።

እምነት አእምሮአዊ ነገር ብቻ ሳይሆን እምነት የፈቃድ መዋሃድ ጭምር ነው። እምነት እግዚአብሔር እኛን የሚናፍቅበት እና እኛ እግዚአብሔር ጋር ለመድረስ የምንናፍቅበት የጋራ ተስፋ ነው፤ እግዚአብሔር በነጻ ፈቃዳችን እሺታ ወደ እርሱ እንመጣ ዘንድ የሚጠባበቅበት ትዕግሥት እና እኛ እግዚአብሔርን ለማግኘት የምንናፍቀው ናፍቆት በእኛ እና በእግዚአብሔር መካከል ያለ የፈቃድ ውህደት እና የጋራ ተስፋ ነው። እምነት የተገለጠውን መለኮታዊ እውነት በሙሉ ልባችን መቀበል እና በዚያ እውነት መሰረት ሕይወታችንን መምራት ማለት ብቻ አይደለም፤ እምነት ከሐሳብ ይልቅ ግንኙነት ነው፤ በመሆኑም እምነት ስለ እግዚአብሔር ከማወቅ ባሻገር ወደ እግዚአብሔር ከፍ ማለት እና ከርሱ ጋር ሕብረት ማድረግን የሚጠይቅ ሕይወት ነው። እምነት የተገለጠውን እውነት መቀበል ብቻ ሳይሆን እምነት እንደ እመቤታችን ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስነት “እሺ” ብሎ እግዚአብሔርን ራሱን በማንነታችን መቀበል ነው። የተገለጠውን እውነት የምንቀበለው ስለተገለጠው እውነት ተዓማኒነት ብቻ ሳይሆን ይልቁንም ያ እውነት ስለገለጠው እና ያንንም እውነት በምልዐት ስለሚገልጠው ስለ እርሱ ስለ እግዚአብሔር ስንል ነው። የተገለጠው እውነት ገዢ ትርጉም የሚፈጸመው እግዚአብሔር ራሱ በእውነት በእኛ ውስጥ ሕያው ሆኖ ሲኖር ነው።

አብዛኛውን ጊዜ ስለ እምነት ያለን መረዳት ስለ እግዚአብሔር ከተነገረው ነገር የተነሳ የተገነባ ነው፤ ነገር ግን እምነት ከራሱ ከእግዚአብሔር ብርኀን እና እውነት ጋር ያለን ኅብረት ነው። ስለ እግዚአብሔር የተባለው እና የተገለጠ እውነት ሁሉ ወደዚህ መዳረሻ የሚያመጣን መንገድ እንጂ በራሱ ፍጻሜ አይደለም፤ ፍጻሜው አልፋ እና ኦሜጋ ተብሎ የሚጠራው፣ እግዚአብሔር ራሱ ነው። የእምነት ፍጻሜ ስለ እግዚአብሔር የተነገረ ነገር ወይም ስለ እግዚአብሔር ያለን ትምሕርት ሳይሆን እግዚአብሔር ራሱ ነው። የእምነት ፍጻሜ እግዚአብሔር ሳይሆን ስለ እግዚአብሔር የተነገሩ ሐሳቦች በሆኑበት ሥፍራ ሁሉ እምነት በየቀኑ በማያቋርጥ ጸጉር ስንጠቃ እና ክርክር የተሞላ የአእምሮ ጦርነት፣ ጥላቻ እና መከፋፈል ወደ መሆን ይወርዳል። 

የእምነት እውነት ከእግዚአብሔር መገለጥ አንጻር የሚታይ እና የሚጠና ቁም ነገር በመሆኑ ሳይንሳዊ የነገረ መለኮት ስልታዊ ጥናት ያስፈልገዋል፤ ነገር ግን የነገረ መለኮት ጥናት ሁሉንም አስተሳስሮ አንድ የሚያደርግ የእምነት ፍጻሜ አይደለም፤ እምነት ስለ እግዚአብሔር ከምናውቀው በላይ እግዚአብሔር ራሱን ለነፍስ የሚያስተዋውቅበት መገለጥ ነው። የነገረ መለኮት ቀኖናዊ ዶግማዎች እና አስተምሕሮዎች እግዚአብሔር ስለ እርሱ ማወቅ የምንችለውን ያህል ስለራሱ የተናገረባቸው መንገዶች ናቸው፤ በመሆኑም በዚህ መረዳት ወደ እግዚአብሔር የሚያመለክቱ መስታዎቶች እንጂ በራሳቸው ፍጻሜዎች አለመሆናቸውን፤ እምነትም ከስልታዊ ቀመር ባሻገር ያለውን እግዚአብሔርን ራሱን የሚፈልግ ቁም ነገር መሆኑን በግልጽ መገንዘብ ያስፈልጋል።

እምነት የነፍስ ዐይኖች መከፈት ነው፤ እምነት የነፍስ ዐይኖች በመለኮታዊ ብርኀን መሞላት ነው። እምነት እግዚአብሔርን መመልከት ይችሉ ዘንድ እነዚህ የነፍስ ዐይኖች በመንፈስ ቅዱስ የሚኳሉበት ጥበብ ነው። እምነት ፍጥረት ሁሉ የሚከፈትበት ቁልፍ፣ የሰው ልጅ ሕልወና ምሥጢር የሚገለጥበት ኃይል፣ የሕይወት ጥያቄዎች ሁሉ መልስ ያለበት መዝገብ ነው።

የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ማር 9፡17-24

ከሕዝቡ መካከል አንድ ሰው እንዲህ አለው፤ “መምህር ሆይ፤ ርኩስ መንፈስ አድሮበት ዲዳ የሆነውን ልጄን ወደ አንተ አምጥቼዋለሁ፤ በተነሣበት ጊዜ ሁሉ ይጥለዋል፤ አረፋ ይደፍቃል፤ ጥርሱንም ያፏጫል፤ ሰውነቱም ይደርቃል፤ ርኩስ መንፈሱን እንዲያስወጡት ደቀ መዛሙርትህን ጠየቅኋቸው፤ እነርሱ ግን አልቻሉም።” ኢየሱስም መልሶ፥ “የማታምን ትውልድ ሆይ፤ እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? ልጁን ወደ እኔ አምጡት” አላቸው። ሰዎቹም ወደ እርሱ አመጡት፤ ርኩስ መንፈሱም ኢየሱስን ባየው ጊዜ ልጁን ወዲያውኑ አንዘፈዘፈው፤ እርሱም መሬት ላይ ወድቆ በመንፈራገጥም አረፋ ይደፍቅ ጀመር። ኢየሱስም የልጁን አባት፥ “ከያዘው ስንት ጊዜው ነው?” ብሎ ጠየቀው። እርሱም እንዲህ አለው፤ “ከሕፃንነቱ ጀምሮ ነው፤ ሊገድለው ፈልጎ ብዙ ጊዜ እሳትም ውስጥ ውሃም ውስጥ፥ ይጥለዋል፤ የሚቻልህ ከሆነ ራራልን፤ ርዳንም።” ኢየሱስም፥ “የሚቻልህ ከሆነ አልህ? ለሚያምን ሰው ሁሉም ነገር ይቻላል” አለው። ወዲያውኑ የልጁ አባት፥ “አምናለሁ፤ አለማመኔን አይተህ እርዳኝ” በማለት ጮኸ።

ጸሎት

ጌታዬ ሆይ በእኔ ኑር እንዳልከኝ እንዲሁ አንተም በእኔ ኑር፤ ካንተ ጋር መቆየት ብቻ ሳይሆን ይልቁንም ካንተ ጋር ልኑር። ኢየሱስ ሆይ ካንተ ጋር ልጸልይ፣ ካንተ ጋር ልመን፣ ካንተ ጋር ልስራ፣ ካንተ ጋር ላፍቅር፣ ካንተ ጋር ልሰቃይ፣ በአንተ ኃይል ላምልክ። ከእኔ ጋር ሁን፤ በነፍሴም ጥልቅ ማንንነት ውስጥ በስውር አነጋግረኝ፤ ራሷን በአንተ ውስጥ ታገኝ ዘንድ ነፍሴን ሁሉ ውረስ። ቀላይ ቀላይን እየጠራች እስከ ነፍሴ ወለል ድረስ የአንተ ስም ያስተጋባ! ምንምነቴ ካንተ ምሕረት ጋር ፊት ለፊት ይገናኝ፤ ከምሕረትህ ጥልቀት ነፍሴን በአዲስ ማንነት በእምነት ወደምኖረው ሕይወት ጥራት። አሜን!

የዐቢይ ጾም አስተውሎት (Journal)

በዚህ በአብይ ጾም በየዕለቱ የጸሎት ሐሳቦችን እና አስተውሎቶችን መጻፍ ለተሻለ መንፈሳዊ ሕይወት ያግዛል። እውነተኛ የቀን ውሎ አስተውሎት እና የጸሎት ሐሳብን በነጻነት በማስፈር ለነፍስ ዕድል መስጠት በመንፈሳዊ ሕይወት መሰረታዊ ቁም ነገር ነው። ከዚህ በታች የቀረቡት ጥያቄዎችን ለራስ ውሎ በሚስማማ ሁኔታ በማስተካከል አስተውሎትን መጻፍ ይቻላል።

  1. ወደ እግዚአብሔር የቀረብኩበትን ጊዜ፣ ቦታ እና ሁኔታ አስታውሳለሁ? እግዚአብሔር በነፍሴ ውስጥ ያነጋገረኝ ጊዜ ትዝ ይለኛል? ምን ይመስል ነበር?
  2. ጸሎቴ፣ እምነቴ እና ኑሮዬ እርስ በእርሳቸው ይተዋወቃሉ?
  3. በቀን ውስጥ ለትንሽ ደቂቃ በእግዚአብሔር ሕላዌ ፊት ጊዜ ወስጄ ሕይወቴን እመለከታለሁ?
  4. የዐቢይ ጾም የጸጋ መሻቴ ምንድነው? የትኛው ጸጋ ዛሬ፣ አሁን እያለፍኩበት ባለሁት ሁኔታ ውስጥ በይበልጥ ያስፈልገኛል?

የተባረከ የጾም ጉዞ!

ሴሞ

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።