የዐቢይ ጾም 21ኛ ቀን
- Category: የ ፵ ጾም አሰተንትኖ
- Published: Sunday, 16 March 2025 07:47
- Written by Samson
- Hits: 75
- 16 Mar
የዐቢይ ጾም 21ኛ ቀን
የዐብይ ጾም ወቅት ክርስቲያኖች በጥምቀት የገቡትን ቃልኪዳን የሚያድሱበት እና ጠለቅ ባለ መንፈሳዊነት በመኖር ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የሕይወት ምስክርነት የሚሰጡበት ወቅት ነው፡፡ ይህ ወቅት እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ ጾም እና ሕማማት ለሰው ልጆች ሁሉ የከፈተውን ምሕረት የምናከብርበት እና የምናካፍልበት ጊዜ መሆን ይገባዋል፡፡ በዐብይ ጾም ወቅት የእግዚአብሔር አብ ምሕረት፣ የእግዚአብሔር ወልድ ፍቅር እና የመንፈስ ቅዱስ ማጽናናት ምን ያህል ጥልቅ መሆኑን እንድናሰላስል እንጋበዛለን። የነብዩ ሚኪያስን ትንቢት ለዚህ አስተንትኖ አይነተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋልናል እኛም ከእርሱ ጋር በአንድ ድምጽ ምሕረቱን እንመሰክራለን፡-
“በደልን ይቅር የሚል …ምሕረትን ይወዳልና ቁጣውን ለዘላለም አይጠብቅም፡፡ ተመልሶ ይምረናል…ኃጢአታችንንም በባሕሩ ጥልቅ ይጥለዋል” (ሚኪ 7፡18-19)።
የዐብይ ጾም አራተኛ ሳምንት ዘመፃጉዕ ተብሎ ይጠራል። ይህ ሰንበት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሽተኞችን የፈወሰበትን እና ወደ ሕሙማን ቀርቦ ከእነርሱ ጋር የተወያየበትን የፈውስ ተግባር የምናስብበት ሰንበት ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰላሳ ስምንት ዓመት በሕመም ይሰቃይ ወደ ነበረው ሰው ቀርቦ ጠየቀው። በዚያ ሁሉ ዓመታት ይህንን ሰው ወደ ፈውስ ውኃ የሚያስገባው ዘመድ አልነበረውም፤ አሁን ግን የፈውስ ባለቤት የሆነው አምላክ መጥቶ “መዳንን ትወዳለህን?” ብሎ ይጠይቀዋል። ሰውየው ወደ ውኃው የሚያስገባው አለመኖሩን ይናገራል። የእርሱ ፈውስ በውኃው ዘንድ ብቻ መሆኑን አምኗል። ኢየሱስ ግን “አልጋህን ተሸክመህ ሒድ” አለው። ሰላሳ ስምንት ዓመት በሕማም ሲሰቃይ የነበረው ሰው በቤተ መቅደስ ከወንድሞቹ ጋር ለመቆም በቃ። አልጋውን ተሸክሞ ኢየሱስ እንዳዳነው እየመሰከረ ሔደ።
ይህ ሰንበት ዘመፃጉዕ ተብሎ ሲጠራ ሁላችንም ወደ ውስጣችን ቁስል በጥልቀት ተመልክን ኢየሱስን እንድንጠራው ያሳስበናል። ሥጋዊና መንፈሳዊ ቁስሎቻችንን ለእርሱ በማቅረብ እንድንፈወስ “እናንተ ሸክም የከበደባችሁ ወደ እኔ ኑ እኔም አሳርፋችኋለሁ” (ማቴ 11፡28) ያለውን ጌታ በማመን ወደ እርሱ እንጩህ። እያንዳንዳችን ለማንም የማናካፍለው ቁስል፤ እንዲህ ሆንኩ ብለን ለመናገር የማያስደፍረን ሕማም፣ ማንነት፣ በሱስ ባርያ የሆንበት ነገር፣ ከሰው ተደብቀን የምንገዛለት እስራት ወ.ዘ.ተ ይኖረናል። ኢየሱስ ይህንን አይጠየፍም፤ ታሪካችንን ሰምቶ ከጀርባችን አያወራም፤ ነገር ግን የእርሱ አመለካከት የተለየ ነው። ያ በውኃ አጠገብ ተኝቶ የነበረውን ታማሚ ባየው ጊዜ “እስከ አሁን ለብዙ ዘመን እንዲህ እንደነበረ ዐውቆ ልትድን ትወዳለህን” (ዮሐ 5፡6) አለው። ታሪኩን ያውቅ ነበር ማለት ነው።
ለእያንዳንዳችን ሕማም፣ ቁስል፣ ባርነት፣ እሥራት ወ.ዘ.ተ የኢየሱስን ጥያቄ ይህ ነው “ልትድን ትወዳለህን”? “ልትድኚ ትወጃለሽን”? የእኛ ፋንታ እሺ ብሎ መዳን ነው። እሺ ብሎ መዳን! ስለዚህ ወደ ኢየሱስ ቀርበን ከእርሱ ዘንድ ለመፈወስ ጊዜው አሁን ነው፤ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በበለጠ እንዲህ እያለ ያበረታታናል “በተወደደ ሰዓት ሰማሁህ፤ በመዳንም ቀን ረዳሁህ ይላልና፤ እነሆ የተወደደው ሰዓት አሁን ነው፤ እነሆ የመዳን ቀን አሁን ነው” (2ኛ ቆሮ 6፡2)። የመፃጉዕ ሰንበት እንግዲህ በሥጋዊ ዐይን ስለምናያቸው ሕሙማን የምናስብበት እኛን የማያጠቃልል ሳይሆን የራሳችንን ሥጋዊና መንፈሳዊ ቁስሎችና ሕማም ይዘን በኢየሱስ ፊት በትህትና በመቆም ፈውስ የምንለምንበት ጊዜ ነው።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ (መዝ 41፡2-13)
ለችግረኛና ለምስኪን የሚያስብ ምስጉን ነው፥ ጌታ በክፉ ቀን ያድነዋል። ጌታ ይጠብቀዋል፥ ሕያውም ያደርገዋል፥ በምድር ላይም ብፁዕ ያደርጋቸዋል፥ ለጠላቶቹም አሳልፈህ አትሰጠውም። ጌታ በደዌው አልጋ ሳለ ይረዳዋል፥ መኝታውን ሁሉ በበሽታው ጊዜ ያነጥፍለታል። እኔስ፦ “አቤቱ፥ ማረኝ፥ አንተን በድያለሁና ነፍሴን ፈውሳት” አልሁ። ጠላቶቼም በላዬ ክፋትን ይናገራሉ፦ መቼ ይሞታል ስሙስ መቼ ይሻራል? ይላሉ። እኔን ለመጠየቅ የሚገባ ከንቱን ይናገራል፥ ልቡ ኃጢአትን ሰበሰበለት፥ ወደ ውጭ ይወጣል ይናገራልም። በላዬ በመተባበር ጠላቶቼ ሁሉ ያንሾካሽካሉ፥ በእኔ ላይም ክፋትን ያስባሉ። ክፉ ነገር መጣበት፥ ከተኛበት ከእንግዲህ ወዲህ አይነሣም ይላሉ። ደግሞ የሰላሜ ሰው፥ የታመንሁበት እንጀራዬን የበላ በእኔ ላይ ተረከዙን አነሣ። አንተ ግን አቤቱ፥ ማረኝ፥ እመልስላቸውም ዘንድ አቁመኝ። ጠላቴ እልል አይልብኝምና በዚህም በእኔ እንደ ተደሰትክ አወቅሁ። እኔንም ስለ ቅንነቴ ደገፍከኝ፥ በፊትህም ለዘለዓለም አጸናኸኝ። ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም የእስራኤል አምላክ ጌታ ይባረክ። አሜን አሜን።
ጸሎት
አቤቱ! ማረኝ! አቤቱ! ፈውሰኝ እኔም እፈወሳለሁ፤ አድነኝ እኔም እድናለሁ፤ አንተ ምስጋናዬ ነህና።
የዐቢይ ጾም አስተውሎት (Journal)
በዚህ በአብይ ጾም በየዕለቱ የጸሎት ሐሳቦችን እና አስተውሎቶችን መጻፍ ለተሻለ መንፈሳዊ ሕይወት ያግዛል። እውነተኛ የቀን ውሎ አስተውሎት እና የጸሎት ሐሳብን በነጻነት በማስፈር ለነፍስ ዕድል መስጠት በመንፈሳዊ ሕይወት መሰረታዊ ቁም ነገር ነው። ከዚህ በታች የቀረቡት ጥያቄዎችን ለራስ ውሎ በሚስማማ ሁኔታ በማስተካከል አስተውሎትን መጻፍ ይቻላል።
- ዛሬ ከጌታ የምጠይቀው ፈውስ ምንድን ነው?
- ፈውስ የሚያስፈልገው የሕይወቴ ክፍል የትኛው ነው?
- ጌታ “ሰው” የሆነው “ሰው የለኝም” እንዳልል ነው፤ በመሆኑም የጌታን መምጣት የሚጣበበቅ “ሰው የለኝም” ያልኩበት የሕይወቴ ጉዳይ የቱ ነው?
- የዐቢይ ጾም የጸጋ መሻቴ ምንድነው? የትኛው ጸጋ ዛሬ፣ አሁን እያለፍኩበት ባለሁት ሁኔታ ውስጥ በይበልጥ ያስፈልገኛል?
የተባረከ የጾም ጉዞ!
ሴሞ