የዐቢይ ጾም 22ኛ ቀን
- Category: የ ፵ ጾም አሰተንትኖ
- Published: Tuesday, 18 March 2025 11:01
- Written by Samson
- Hits: 127
- 18 Mar
የዐቢይ ጾም 22ኛ ቀን
ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አሁን የሰው ልጅ ፊት በፍርሃት የተዋጠበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፤ ይህ ፍርሃት በሰው ልጅ ላይ ከሌላ ነገር የመጣበት ሳይሆን ከራሱ ከሰው ልጅ የተነሳ ነው። በብዙ የሕይወት አቅጣጫዎች የሰው ልጅ በራሱ ላይ እንደ እግዚአብሔር የሚመለክ፣ ለራሱ ለሰው ልጅ ጩኸት ደንቆሮ የሆነ አምባገነን ገዢ ሾሟል። ይህ የሰው መልክ ያለው አጋንንት ምሕረት እና ርኅራሄ የማያውቅ ራሱን አምላክ ያደረገ እና በተለይዩ የሕይወት አንድምታዎች የሚገለጥ እውነታ ሆኖ ይታያል። ይህ የሰው ልጅ በራሱ ላይ የሾመው አጋንንት ራሱን የሰው ልጅን ባርያ አድርጎ የሚበዘብዘው እና የሰውን ልጅ ፊት ረግጦ የቆመው ኃይል ነው።
ይህ ክፍለ ዘመን ለፍትሕ እና ለሰላም በሚጮህ ለቅሶ፣ በጦርነት ዜማ እና በዋይታ የተሞላ ዘመን ነው። የሰው ልጅ ሰብዓዊ መብት የተከበረበት እየተባለ የሚሞካሸው ይህ ክፍለ ዘመን የሰው ልጅ በየሥፍራው እንደ ቅጠል የሚረግፍበት እና የሰው ልጅ እንደ ርካሽ ነገር በይፋ የሚሸጥበት ዘመን ነው። በቴክኖሎጂ የረቀቅንበት ይህ ዘመን በተመሳሳይ ጊዜ በርሃብ እና በምግብ እጥረት የሰው ልጅ “እሪያዎችም ከሚበሉት አሰር ሊጠግብ ይመኛል” (ሉቃ 15፡16)። ይህ እግዚአብሔር ነውር የሆነበት ዓለም በኢሰባዊነቱ ጭካኔ ተገልጦ ይታያል፤ ዓለም አንድ መንደር ሆናለች የሚለው ይህ ዘመን በተመሳሳይ ጊዜ ጉረቤታሞች አይተዋወቁበትም፤ በቤተ ሰብ መካከል በአንድ ቤት ውስጥ የማይተያዩበት ግንብ አለው። ይህ ዘመን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የስነ ልቡና ባለሙያ እጅግ የሚፈለግበት፤ ራሱን እና ልቡን ያጣ ዘመን ነው። በየስፍራው ተፈጥሮን ስለመንከባከብ በስፋት እየተነገረ በተቃራኒው የሰው ልጅ ሁነኛ ተፈጥሮው፣ የነፍሱ ጉዳይ፣ የልቡ ደኅንነት፣ የፊቱ ሰላም የማንም አጀንዳ አይደለም።
እ.ኤ.አ. በታህሳስ ወር 1975 ዓ.ም. በሮም እና በቁስጥንጥኛ መካከል ከ1054 ዓ.ም. አንስቶት የነበረው ውግዘት የተነሳበት 10ኛ ዓመት ሲከበር በሲስታይን ቤተ ጸሎት ውስጥ በተገኙት ታላቅ እንግዶች ፊት አንድ አስደናቂ ትህትና ተገልጦ ነበር።[1] ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ ፮ኛ የጸሎቱን መርሐ ግብር ካሳረጉ በኋላ በግሪክ ኦርቶዶክስ ፓትርያርኩ እግር ላይ ወድቀው የፓትርያርኩን እግሮች እየሳሙ ቤተ ክርስትያን ይህን ያህል ተከፋፍላ ስለቆየችበት ዘመን ይቅርታ ጠየቁ፤ ከታሪክ ስህተት በላይ በሚሻገር ትህትና የሮም መንበር እንደራሴ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስትያን ክብራቸውን ጥለው ተንበረከኩ። እንዲህ ያለው ተግባር ሊገለጥ የሚችለው አንዱ በሌላው ሰው ፊት በልቡ ትሑት ሆኖ መቆም እና የሌላኛውን ፊት በኢየሱስ ክርስቶስ ዐይኖች መመልከት ሲችል ብቻ ነው።[2]
ፓትርያርክ አቴናጎራስ በ1970 ዓ.ም. በሕይወታቸው ስላጋጠማቸው ታላቅ ክስተት በተጠየቁ ጊዜ የሰጡት መልስ “ለመጀመርያ ጊዜ በ1964 ዓ.ም. በጥር ወር ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ ፮ኛ ጋር በኢየሩሳሌም በደብረ ዘይት ተራራ የተገናኘንበት ነው” ሲሉ መልስ ሰጥተዋል። ከዚህ ግንኙነት በኋላ ወድያውኑ በሁለቱ አብያተ ክርስትያናት መካከል የተደረገ ምንም ስምምነት እንዴት የለም? ለሚለው ጥያቄ ፓትርያርክ አቴናጎራስ ሲመልሱ “ዋናው ቁም ነገር ፊት ለፊት መገናኘታችን እና ዐይን ለዐይን መተያየታችን ነው“ ይላሉ። ቁም ነገሩ የጋራ ውሳኔ ላይ መድረስ ሳይሆን ፊት ለፊት መቀባበል፤ ዐይን ለዐይን መተያየት መቻል ነው። ዐይን ለዐይን መተያየት ቃላት በማይደርሱበት የነፍስ ቋንቋ ጥልቀት እልፍ ነገር ይናገራል። ከእግዚአብሔር ጋር ለመገናኘት ያለን ናፍቆት ይህ ከሰው ልጆች ጋር ዐይን ለዐይን ፊት ለፊት ለመገናኘት ባለን ናፍቆት ውስጥ ተንጸባርቆ ይታያል። ወደ እግዚአብሔር መጸለይ፣ ስለ እግዚአብሔር ማንበብ ወይም ነገረ መለኮት ማጥናት ወ.ዘ.ተ. እግዚአብሔርን ፊት ለፊት ለማየት ካለን ነፍሳዊ ናፍቆት የሚመነጭ ጥልቅ ርሃብ ነው። ፊሊጶስ ከጌታ ዘንድ ስለ አብ የሰማው ነገር ነፍሱን በእጅጉ ስላናወጣት ይህንን ናፍቆቱን ሲናገር ጌታ ሆይ “አብን አሳየን” እያለ ጌታን ይማጸነዋል (ዮሐ 14፡8)።
የሰው ልጅ በእግዚአብሔር አርአያ እና አምሳል የተፈጠረ፣ የእግዚአብሔር እስትንፋስ አስቀድሞ በአዳም በኩል ኋላም ደግሞ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የተተነፈሰበት ከእግዚአብሔር ፊት ብርኀን የተነሳ ሕያው ሆኖ የሚኖር ፍጥረት ነው። በምሥጢረ ጥምቀት የሰው ልጅ ራስ እና ፊት የምስጢሩ ዋና ትኩረት ሆነው በተጠማቂው ላይ መተንፈሱ እና እጅ መጫኑ የሰው ልጅ ፊት በክርስትና ግንዛቤ ያለውን አንድምታ ያሳዩናል። ወልደ እግዚአብሔር ሥጋ ለብሶ የማይታየው አምላክ የሚታይ ፊት ሆኖ መገለጡ የሰው ልጅ ፊት ያለውን ክብር የበለጠ መለኮታዊ አንድምታ ያረጋግጥልናል።
ከዘላለማዊ ማንነቱ ሳይጎድል በጊዜ ውስጥ መገኘቱ እና የእኛን ፊት መውሰዱ የሰው ልጅ የተፈጠረበትን እውነተኛ መልክ እንዲያሰላስል በር ከፍቶለታል። ይህ የጸጋ ጊዜ (kairos καιρός)፣ ይህ የተወደደ የጌታ ዓመት፣ ይህ መለኮታዊ ጉብኝት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ በኩል በሰው ልጅ የታሪክ ሸማ ላይ የማይለቅ፣ የማይጠፋ፣ የማይደበዝዝ መለኮታዊ ጥለት ሆኖ ተሰፍቷል። ይህ የጸጋ ጊዜ (kairos καιρός) የዘመን ምልዐት፣ በእግዚአብሔር ፊት ያለው ዘላለማዊነት እና ዛሬነት በኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ ለብሶ መገለጥ የተጋጠመበት የጊዜ ቀመር፣ የዘላለማዊነት እና የውሱንነት እርቅ ነው። በመሆኑም የእግዚአብሔር መንግሥት ከዚህ መገለጥ ውጪ ባለ ጊዜ የሚመጣ እና የሚታይ ሳይሆን፤ ይልቁንም በዚህ መገለጥ በኩል የእግዚአብሔር መንግሥት “በመካከላችን ናት” (ሉቃ 17፡21)። በመሆኑም የእግዚአብሔር ልጅ በሥጋ መገለጥ የሰውን ልጅ ለዘላለማዊ ዛሬነት የተስማማ ፍጥረት እዲሆን ከአዳም በሚሻል ልጅነት አድሶታል።[3]
የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር እውነተኛ መልክ ነው። ይህ መልክ የእግዚአብሔር ምስል ብቻ ሳይሆን እውነተኛ የእግዚአብሔር መገለጥ ነው። በዚህም መገለጥ የእግዚአብሔር መልክ ታይቷል፤ የሰው ልጅ ይህንን መልክ ያሰላስለው ዘንድ ኢየሱስ ክርስቶስ “እኔን ያየ አብን አይቷል” (ዮሐ 14፡9) እያለ ትኩረታችንን እና አስተውሎታችንን በመልኩ ላይ እንድናደርግ ይጋብዛል።
የኦሪት ዘፀአት መጽሐፍ “የጌታ ክብር ለእስራኤል ልጆች እንደሚባላ እሳት” ሆኖ ታያቸው (ዘፀ 24፡17) እያለ የእግዚአብሔር መልክ ምን እንደሚመስል ይናገራል። የሰው ልጅ ይህንን “የሚባላ እሳት” ሊያስበው ቢሞክር እንኳን ለባሕርይው የሚስማማ መገለጥ ባለመሆኑ ይቸገራል። ከጌታ ሥጋ ለብሶ መገለጥ በፊት እግዚአብሔር ምን እንደሚመስል ለማሰብ የተከለከለ ነበር፤ የተቀደሰው ነገር የማይነገር፣ የተሰወረ፣ የማይታይ እና እንዲህ ነው ተብሎ ሊገለጽ የማይቻል ነበር። ነገር ግን “ያለው እና የነበረው ሁሉን የሚገዛ፣ አልፋ እና ኦሜጋ” (ራዕ 1፡8) ተብሎ የሚጠራው “የክብሩ ጸዳልና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ” (ዕብ 1፡3) እውነተኛውን የእግዚአብሔር መልክ ገለጠልን።
“የማይታይ አምላክ ምሳሌ” (ቆላ 1፡15) የሆነው ዘላለማዊው ቃል የመላእክትን የሚመስል ወይም ሌላ አዲስ መልክ አልወሰደም፤ ነገር ግን ስንፈጠር ያካፈለንን የራሱን መልክ የሚመስለውን የሰው መልክ ወሰደ፤ በመሆኑም የሰው ልጅ መልክ አስቀድሞ ከኢየሱስ ክርስቶስ የተካፈለው በመሆኑ ለእርሱ እንግዳ ነገር የሆነ አይደለም። እግዚአብሔር የሰውን ልጅ የፈጠረበት አምሳል ዘላለማዊው የልጁ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምሳል ነጽብራቅ ነው። በዚህም ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ መልበሱ ለእርሱ አስቀድሞ እንግዳ ባልነበረው በራሱ መልክ ነጸብራቅ መገለጥ ነው። የሰው ልጅ መልክ እና አምሳል የእግዚአብሔር ክብር ነጸብራቅ ነው የምንለው የሰው ልጅ መልክ እና አምሳል የዘላለማዊ የኢየሱስ ክርስቶስ መልክ እና አምሳል ቅጂ በመሆኑ ነው። በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ የሰው እና የአምላክ ምሥል ታርቀዋል፤ በመሆኑም የሰው ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የእግዚአብሔርን መልክ ይመስላል፤ እግዚአብሔርም በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የሰውን ልጅ መልክ ተካፍሏል።[4]
ይህ መለኮታዊ መልክ በሰው ልጅ ፊት ላይ ሁሉ ተንጸባርቆ ይስተዋላል፤ የክርስቶስ ፊት ውስብስብ ምናባዊ ሐሳብ አይደለም፤ ይልቁንም እውነተኛ “ሰው”ነት ነው። የቤተ ክርስትያን አባቶች እንደሚመሰክሩት እግዚአብሔር የሰውን ዘር የፈጠረው በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ዘላለማዊው መልክ (in the image of the pre-existent Christ) ነው። በመሆኑም ኢየሱስ ክርስቶስ በሰም ምሳሌ መገለጡ ለተፈጠርንበት መልክ ተስማሚ እና የእግዚአብሔርንም ክብር የሚያንጸባርቅ እውነታ ነው። ቃል ሥጋ የመልበሱ እውነታ የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ጥሪ ከመለኮታዊ ሕይወት ተካፋይ መሆን እንደሆነ ያረጋግጥልናል።
ቅዱስ ኤሬኒዮስ በጽሑፉ “የእግዚአብሔር ቃል ሰው ሆነ፤ እኛን መሰለ፤ በመሆኑም ልጁ እኛን በመምሰሉ እውነታ ሰውነት በእግዚአብሔር ዐይኖች ፊት እጅግ ውድ ሆነ” እያለ በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የእኛን መልክ መካፈል የሰው ልጅ በእግዚአብሔር አብ ፊት ያገኘውን ክብር ያስረዳል።[5] በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረው የሰው ልጅ የእግዚአብሔር እውነተኛ መልክ የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን በመሰለ ቁጥር ይበልጡን የተፈጠረበትን ዓላማ እየመሰለ ያድጋል። የእግዚአብሔር ቃል ሥጋ ለብሶ ሰው መሆን ከኃጢአት ሥርየት ባሻገር የሚዘልቅ ሁለንተናዊ ተሃድሶ ነው። በመሆኑም የሰውን ልጅ ሰብዓዊ እና መለኮታዊ ማንነት በፍጽምናው የሚያንጸባርቅ እውነታ ነው። የቤተክርስትያን አበው ቃል ሥጋ የመሆኑን ምሥጢር ሲያብራሩ እግዚአብሔር እና ሰው ፊት ለፊት የተያዩበት አንዱ በሌላው ውስጥ የተንጸባረቀበት የጋር መልክ መገለጥ እንደሆነ ይናገራሉ። ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው በእግዚአብሔር ዐይን እግዚአብሔርም በሰው ዐይን እንደ አዲስ የታየበት ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ ነው።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ (ዕብ 1፡ 1-3)
እግዚአብሔር ከጥንት ጀምሮ በብዙ እና በልዩ ልዩ መንገዶች ለአባቶቻችን በነቢያት ተናገረ፤ በእነዚህ በኋለኞቹ ዘመናት ግን፥ ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ ለእኛ ተናገረን፥ ስለ እግዚአብሔር ልጅ ታላቅነት እርሱም የክብሩ ጸዳልና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ፥ ሁሉን በሥልጣኑ ቃል እየደገፈ፥ ኀጢአታችንን ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ፤ ከመላእክት ይልቅ እጅግ የላቀ ስምን በተቀበለ መጠን፥ እንደዚሁ ከእነርሱ እጅግ ልቆ ይበልጣል።
ጸሎት
ጌታ ብርሃኔና መድኃኒቴ ነው፥ የሚያስፈራኝ ማን ነው? ጌታ የሕይወቴ ከለላዋ ነው፥ የሚያስደነግጠኝ ማን ነው? ሠራዊትም ቢከብበኝ ልቤ አይፈራም፥ ጦርነትም ቢነሣብኝ በዚህ እተማመናለሁ። ጌታን አንዲት ነገር ለመንሁት እርሷንም እሻለሁ፥ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ በጌታ ቤት እኖር ዘንድ፥ ጌታን ደስ የሚያሰኘውንም አይ ዘንድ፥ መቅደሱንም እመለከት ዘንድ። አቤቱ፥ ወደ አንተ የጮኽሁትን ቃሌን ስማኝ፥ ማረኝና አድምጠኝ። “ፊቴን እሹት” የሚለውን ቃልህን በልቤ አሰብኩኝ፦ አቤቱ፥ ፊትህን እሻለሁ። ፊትህን ከእኔ አትሰውር፥ ተቈጥተህ ከባርያህ ፈቀቅ አትበል፥ ረዳት ሁነኝ፥ አትጣለኝም፥ የመድኃኒቴም አምላክ ሆይ፥ አትተወኝ። አቤቱ፥ መንገድህን አስተምረኝ፥ የጌታን ቸርነት በሕያዋን ምድር እንደማይ አምናለሁ። በጌታ ተስፋ አደጋለሁ፥ እበረታለሁ፥ ልቤም ይጽናል፥ በጌታ ተስፋ አደርጋለሁ። አሜን!
የዐቢይ ጾም አስተውሎት (Journal)
በዚህ በአብይ ጾም በየዕለቱ የጸሎት ሐሳቦችን እና አስተውሎቶችን መጻፍ ለተሻለ መንፈሳዊ ሕይወት ያግዛል። እውነተኛ የቀን ውሎ አስተውሎት እና የጸሎት ሐሳብን በነጻነት በማስፈር ለነፍስ ዕድል መስጠት በመንፈሳዊ ሕይወት መሰረታዊ ቁም ነገር ነው። ከዚህ በታች የቀረቡት ጥያቄዎችን ለራስ ውሎ በሚስማማ ሁኔታ በማስተካከል አስተውሎትን መጻፍ ይቻላል።
- ከሰዎች ጋር ስነጋገር ፊታቸውን አተኩሬ እመለከታለሁ?
- በሰዎች ፊት ስሆን ይህ መልክ የከበረ የእግዚአብሔር ክብር ነጸብራቅ በሆነበት ልክ አከብረዋለሁ?
- ኢየሱስ ክርስቶስ ያካፈለውን መልክ እመለከታለሁ ወይስ የወንድሜ ድካም ላይ ብቻ ያለኝ ትኩረት የጌታን መልክ ሸፍኖብኛል?
- የዐቢይ ጾም የጸጋ መሻቴ ምንድነው? የትኛው ጸጋ ዛሬ፣ አሁን እያለፍኩበት ባለሁት ሁኔታ ውስጥ በይበልጥ ያስፈልገኛል?
የተባረከ የጾም ጉዞ!
ሴሞ
ይቀጥላል...
[1] Staikos, M. (2000). Resurrection: From Lived Orthodox Spirituality (pp. 136-138). Vienna: Tyrolia.
[2] Ratzinger, J. (1977). Predictions for the Future of Ecumenism. Ecumenical Forum, 1.
[3] Balthasar, H. U. von. (1990). The Whole in the Fragment: Aspects of the Theology of History. Einsiedeln: Johannes Verlag.
[4] Clemens of Alexandrien, Stromata VI,9 (PG 9,293B).
[5] Irenaeus of Lyon. (n.d.). Against Heresies (V 15,4; V 16,2).