Map St Joseph Cistercians

Top Panel

የዐቢይ ጾም 23ኛ ቀን

የዐቢይ ጾም 23 ቀን

Lent-main-imageየሰው ልጅ ፊት (ክፍል ፪)

ዘላለማዊው የአብ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር እውነተኛ መልክ ነው፤ የእርሱ መልክ መታየት ለሰው ልጆች የሆነ የእግዚአብሔር ቃል ማንነት የመጨረሻው የጸጋ መገለጥ ነው።  የሰው ልጅ መልክ የሥጋ እና ደም መገለጥ ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሔር ሕያው አምሳል (living icon)፣ የእግዚአብሔር ክብር ማኅተም ያለበት መዝገብ ነው። ር.ሊ.ጳ. ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር አርአያ እና አምሳል የመፈጠሩ እውነታ “የክርስትያን ስነ ሰብ ጥናት የማይለወጥ መሰረት ነው” በማለት ስለ ሰው ልጅ ክቡር ማንነት ያብራራሉ። ይህ በእግዚአብሔር አርአያ እና አምሳል የመፈጠሩ ቁም ነገር ለሰው ልጅ በአንድ በኩል የጸጋ ሥጦታ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የጸጋ የቤት ሥራ ነው፤ ይህም የቤት ሥራ ይህ የሰው ልጅ መልክ ወደ እውነተኛው እና ፍጹም ወደሆነው የእግዚአብሔር መልክ ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሙላት ለማደግ የሚያደርገው ተጋድሎ ነው።  

እያንዳንዱ የሰው ልጅ ፊት የሚናገረው ታሪክ አለው። የወንድሙን ፊት የሚያስተውል ካለ በእያንዳንዱ ፊት ላይ ደስታ፣ ኀዘን፣ ተስፋ፣ ስቃይ ተገልጠው ይነበባሉ። በእምነት ዐይኖች ሲታይ ደግሞ ከዚህ ሰብዓዊ የሕይወት መልክ ባሻገር ዘልቆ የሚሄድ ሌላ መልክ አለ። ይህም በሰው ልጅ ፊት ላይ የሚያንጸባርቀው የእግዚአብሔር ክብር ነው። በዘመን መጨረሻ ይህ የእግዚአብሔር ክብር ልክ በቀዳሚ ሰማዕት በቅዱስ እስጢፋኖስ ላይ እንደነበረ እንዲሁ (ሐሥ 7፡56) በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በእያዳንዳችን ላይ ተገልጦ ይታያል።

በዓለም ፍጻሜ (ἔσχατον) የሰው ልጅ የመጨረሻው መዳረሻ የእግዚአብሔር ክብር ሕያው ነጽብራቅ መሆን ነው። ቃል ሥጋ ለብሶ በመገለጡ ምሥጢር በኢየሱስ ክርስቶስ ለሆኑት ይህ የእግዚአብሔር ክብር ሕያው ነጸብራቅ የመሆን ጉዞ በምሥጢረ ጥምቀት ተጀምሯል፤ በኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽአት ይህ የክብር መልክ ጉዞ “የእግዚአብሔር ክብር በሚያበራበት፥ መብራትዋም በጉ ስለ ሆነ፥ ፀሐይ ወይም ጨረቃ እንዲያበሩላት በማያስፈልጋት” (ራዕ 21፡23) ከተማ  ፍጻሜውን ያገኛል። በዚህም የሰው ልጅ ፊት በመለኮታዊ የጸጋ ብርኀን ሕያው እና የሚያበራ የእግዚአብሔር ክብር ሆኖ እውነትም በእግዚአብሔር አርአያ እና አምሳል መፈጠሩን በኅልውናው ሁሉ ይመሰክራል።

እግዚአብሔር በዔደን ገነት መካከል ድምጹን ተከትሎ አዳምን ፈልጎ እንዳነጋገረው እንዲሁ በዘመን መጨረሻ የራሱን ድምጽ የሚመስል ድምጽ ያለውን የሰውን ልጅ ዳግም ወደ ተፈጠረበት ለመመለስ ኢየሱስ ክርስቶስ እያንዳንዳችንን ፍለጋ መጥቷል።[1] ቃል ሥጋ ከሆነበት በዚህ ምሥጢር የሰው ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ከሆነው ጸጋ የተነሳ የእግዚአብሔር ክብር ኅያው ነጽብራቅ ሆኖ የእግዚአብሔር ሰብዓዊ ፊት ለመሆን ተጠርቷል። በዚህ መረዳት ቃል ሥጋ የለበሰው የሰው ልጅ በኃጢአት ስለወደቀ ብቻ ሳይሆን ይልቁንም የሰው ልጅ በተፈጠረበት መልክ እና ምሳሌ ምልዓት ከመለኮት ባሕርይ እየተካፈለ ፍጹም እውነተኛ መልኩን ኢየሱስ ክርስቶስን እስኪመስለው ድረስ ይለወጥ እና እግዚአብሔርን ይመስል ዘንድ ነው። በዚህም እግዚአብሔር በሰው ውስጥ ተገለጦ እንደሚታየው እንዲሁ በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የሰው ልጅ በፍጽምናው መልክ እና ምሳሌ በእግዚአብሔር ፊት ተገልጦ ይታያል። በመሆኑም ይህ እግዚአብሔር እና ሰው የተመሳሰሉበት መልክ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘወትር ፊቱ ወደ ሰው ልጆች ፊት የተመለሰ ነው። ስለዚህ በቅዳሴያችን “ፍቅር ኃያሉን ወልድ ከሰማያት ስቦ እስከ ሞት አደረሰው፤ በማይነገር አርምሞ ውስጥ የነበረው እግዚአብሔር ከዚህ ፍቅር የተነሳ በሰው ቋንቋ ተናገረ” እያልን የተሰግዎተ ቃል ምሥጢር እናከብራለን።[2]

በኢየሰስ ክርስቶስ ሥጋ ለብሶ መገለጥ የእግዚአብሔር እና የሰው የጋራ ናፍቆት ምላሽ አግኝቷል። በመሆኑም የሰው ልጅ ፊቱን ወደ እግዚአብሔር የሚመልሰው ሕግ እና ሥርዐትን በመፈጸም ሳይሆን ይልቁንም የእግዚአብሔር መልክ ያለበት ስለሆነ እና ወደዚህ እውነተኛ መልኩ የሚናፍቅ ማንነት ስላለው ነው። የሰው ልጅ በነፍሱ ውስጥ የታተመ እግዚአብሔርን የሚያሰላስል፣ እግዚአብሔርን የሚጠማ እና እግዚአብሔርን የሚናፍቅ የእግዚአብሔር ጥበብ አለው።[3] የሰው ልጅ በእግዚአብሔር አርአያ እና አምሳል (kat'eikona) በመፈጠሩ ቀድሞውንም ከእግዚአብሔር ጋር አንድ ለመሆን እና ለመለኮታዊ ሕይወት የታሰበ ፍጡር ነው። ታላቁ የነገረ መለኮት ሊቅ ኒኮላስ ካባሲላስ ይህንን በሚመለከት ሲናገር “ክርስቶስ ኢየሱስ ራሱን በእኛ ውስጥ ያፈሰሰበትን እና ከእኛ ጋር የተዋሃደበትን፣ ይልቁንም እኛን በራሱ መልክ የለወጠበትን እና ያነጸበትን ጥበብ መመልከት እንችላለን፤ ይህም በከርቤ ባሕር ውስጥ እንደፈሰሰ የውኃ ጠብታ ያለ ነው፤ የፈሰስንበት የከርቤ ባሕር ኃይል ጠረኑን ብቻ ይዘን የምንወጣበት ወይንም መዓዛውን ብቻ የምንተነፍስበት ሳይሆን፣ ይልቁንም ሁለንተናችንን ስለ እኛ በፈሰሰው በዚህ ከርቤ መዓዛ በአዲስ ማንነት የሚለውጠን ኃይል ነው፤ ከዚህም የተነሳ ለእግዚአብሔር የክርስቶስ መዓዛ (2ቆሮ 2፡15) ተብለን እንጠራለን”።[4]

የሰው ልጅ የክብሩ ማማ የመጨረሻው ሰገነት በእግዚአብሔር አርአያ እና አምሳል የመፈጠሩ እና የእግዚአብሔር መልክ ያለበት ፍጥረት የመሆኑ ቁም ነገር ነው። በዚህም ያልተፈጠረው ነገር ግን የ-“ልጅ”-ነት መልኩን ለሰው ልጆች ያካፈለው ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ የጸጋ መልክ ሥጦታ የሰው ልጅ ከመለኮታዊ ሕይወት ይካፈል ዘንድ በር ሆኖለታል። በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የእግዚአብሔር ወዳጅ የሆነው የሰው ልጅ መለኮታዊ ሕይወት በሚጠይቀው ማንነት ለመኖር በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል “በጸጋ ላይ ጸጋ” ተቀብሏል። የሰው ልጅ በዚህ የጸጋ ሕይወት በታደሰው በአዲሱ ማንነት ሲኖር የራሱን ማንነት ምሥጢር እና የተፈጠረበትን ዓላማ የበለጠ እየተገነዘበ ወደ ቅድስናው ፍጻሜ ያድጋል። የእግዚአብሔር የባሕርዩ ምሳሌ እና የክብሩ ነጸብራቅ የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን በመመልከት እና እርሱን በመምሰል የእምነት ተጋድሎ የሰው ልጅ “ለእግዚአብሔር እንድኖር በሕግ በኩል ለሕግ ሞቼአለሁ፤ ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ። ክርስቶስ በእኔ ይኖራል እንጂ ከእንግዲህ ወዲያ እኔ አልኖርም፤ አሁን በሥጋ የምኖረው በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ በማመን የምኖረው ነው” (ገላ 2፡18-20) በሚል የሕይወት ትርጉም በእግዚአብሔር ፊት በኢየሱስ ክርስቶስ ይገለጣል።

የሰው ልጅ የራሱን እውነተኛ መልክ አስቀድሞ ከእግዚአብሔር መልክ አግኝቷል፤ ይህ መልክ ፍጹም የሆነ መልክ ሳይሆን ለፍጽምና የተፈጠረ፣ ወደ ፍጽምና የሚያድግ  መልክ ነው።[5] በዚህ አይነት የሰው ልጅ “የኢየሱስ ክርስቶስ ፊት” ሆኖ መገለጡ ክርስትያናዊ ተልዕኮው ነው፤ በእምነት በኩል ባገኘው የልጅነት ጸጋ በኢየሱስ መልክ የሚገለጠው የሰው ልጅ በእያንዳንዱ የሰው ፊት ላይ ክርስቶስ ኢየሱስን የሚያነብበት የእምነት ዐይኖች ያስፈልጉታል። በእነዚህ የእምነት ዐይኖች በኩል ሁሉን በክርስቶስ ፊት እያወቅን “እኛም ሁላችን፥ በመጋረጃ በማይሸፈን ፊት፥ የጌታን ክብር እንደ መስተዋት እያብለጨለጭን፥ የእርሱን መልክ እንድንመስል ከክብር ወደ ክብር እንለወጣለን” (2 ቆሮ 3፡18)።

በመሆኑም የሰው ልጅ ፊት የራሱን የሕይወት ታሪክ ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር በእርሱ ሕይወት ያለውን ታሪክ የሚመሰክር መስተዋት ነው። ሰው በሥጋ እና በደም የቆመ ፍጥረት ብቻ ሳይሆን ይልቁንም የእግዚአብሔር የክብር መልክ ያለበት ፍጥረት ነው። በመሆኑም ሰው የእግዚአብሔር መልክ ምሳሌ እና የክብሩ ነጸብራቅ ነው። ስለዚህ በእያንዳንዱ ሰው ፊት ላይ የእግዚአብሔር ጉዞ ታሪክ በግልጽ ይነበባል። በምሥጢረ ጥምቀት ባገኘነው ጸጋ የልጁ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መልክ በእያንዳንዱ ሰው ላይ በእግዚአብሔር ፊት የተገለጠ፣ የማይጠፋ ዘላለማዊ ውበት ሆኖ ታትሟል።

ዐቢይ ጾም በእያንዳንዱ ሰው ፊት ላይ ክርስቶስ ኢየሱስን መመልከት እና ከእያንዳንዱ ሰው ፊት ላይ የእግዚአብሔርን ታሪክ ማንበብ የምንለማመድበት፣ በማንም ላይ ፊታችንን የማናዞርበትን እና ማንንም ፊት የማንነሳበትን ማንነት ለመላበስ የምንሰራበት የጸጋ ወቅት ነው።

የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ (መዝ 51፡ 11፣13)

ከኃጢአቴ ፊትህን መልስ... ከኃጢአቴ ፊትህን መልስ

ጸሎት

አቤቱ ፊቴን የነሳኋቸው እና አንተን የከለከልኳቸው ሰዎች ስንት ናቸው? አቤቱ አንተ ፊትህን ሳታዞርብኝ እኔ በባልንጀራዬ ላይ ፊቴን አዞር ዘንድ እኔ ማን ነኝ? ጌታ ሆይ ይቅር በለኝ! የራሴን ፊት የማልደብቅበት፣ የባልጀራዬንም ፊት በእምነት አይኖች የምመለከትበት ጸጋ ስጠኝ። አቤቱ እንዳንተ እያንዳንዱን የሰው ፊት ትኩር ብዬ እንደመለከት እና በባልንጀራዬ ነፍስ ውስጥ ያለውን መስቀል ማስተዋል እንድችል አበርታኝ። የራሴ መልክ የባልንጀራዬን ፊት ውበት እንዳይጋርድብኝ እና በዚያ ያለን የአንተን መገለጥ ከማስተዋል እንዳያጎድለኝ ጠብቀኝ። መልክህን ያካፈልከኝ ዘላለማዊ ውበት ሆይ ተመስገን!

የዐቢይ ጾም አስተውሎት (Journal)

በዚህ በአብይ ጾም በየዕለቱ የጸሎት ሐሳቦችን እና አስተውሎቶችን መጻፍ ለተሻለ መንፈሳዊ ሕይወት ያግዛል። እውነተኛ የቀን ውሎ አስተውሎት እና የጸሎት ሐሳብን በነጻነት በማስፈር ለነፍስ ዕድል መስጠት በመንፈሳዊ ሕይወት መሰረታዊ ቁም ነገር ነው። ከዚህ በታች የቀረቡት ጥያቄዎችን ለራስ ውሎ በሚስማማ ሁኔታ በማስተካከል አስተውሎትን መጻፍ ይቻላል።

  1. ከሰዎች ጋር ስነጋገር ፊታቸውን አተኩሬ እመለከታለሁ?
  2. በሰዎች ፊት ስሆን ይህ መልክ የከበረ የእግዚአብሔር ክብር ነጸብራቅ በሆነበት ልክ አከብረዋለሁ?
  3. ኢየሱስ ክርስቶስ ያካፈለውን መልክ እመለከታለሁ ወይስ የወንድሜ ድካም ላይ ብቻ ያለኝ ትኩረት የጌታን መልክ ሸፍኖብኛል?
  4. የዐቢይ ጾም የጸጋ መሻቴ ምንድነው? የትኛው ጸጋ ዛሬ፣ አሁን እያለፍኩበት ባለሁት ሁኔታ ውስጥ በይበልጥ ያስፈልገኛል?

የተባረከ የጾም ጉዞ!

ሴሞ

ይቀጥላል...

[1] Irenaeus of Lyon. (n.d.). Adversus Haereses (V 15,4; V 16,2).

[2] Macarius. (n.d.). Homilia (XXVI,1).

[3] Basil the Great. (n.d.). Homily on "Give Heed to Yourself". In Patrologia Graeca (Vol. 31, pp. 213D-214A).

[4] Kabasilas, N. (1958). The Sacramental Mysticism of the Eastern Church: The Book of Life in Christ (Ivanka, Ed.). Klosterneuburg: Mayer.

[5] Guardini, R. (1943). School of Prayer. Einsiedeln-Zürich: Benziger Verlag.

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።