Map St Joseph Cistercians

Top Panel

የዐቢይ ጾም 24ኛ ቀን

የዐቢይ ጾም 24ኛ ቀን

Lent-main-imageየሰው ልጅ ፊት (ክፍል )

የሰው ልጅ የእግዚአብሔር መልክ ያለበት የእግዚአብሔር ቃል ሥጋ ለብሶ መገለጥ ምሥጢር ኅያው ምሥክር በመሆኑ ስለ ሰው የሚደረጉ ጥናቶች ሁሉ መሰረታዊ መረዳት ከዚህ ክብር ሊነሳ ይገባዋል።[1] ይህ እግዚአብሔር እና ሰው የተካፈሉት በሥግው ቃል መገለጥ የታየው መልክ ሰው እግዚአብሔርን፣ እግዚአብሔርም ሰውን የተቀበለበት ምሥጢር ነጸብራቅ ነው። የአሌክሳንድርያው ቅዱስ ቀለሜንጦስ በበኩሉ “እግዚአብሔር ሰውን መስሏልና እንግዲህ አሁን ሰውም እግዚአብሔርን ይመስላል”[2] እያለ በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት የተገለጠውን የሰው እና የእግዚአብሔርን የጋራ መልክ ያመለክተናል።

 

የሰው ልጅ እግዚአብሔር “በጥበብና በአእምሮ ሁሉ፥  ለማድረግ የወደደውን የአሳቡን፥ የፈቃዱን ምሥጢር ባስታወቀበት፤ በሰማይና በምድር ያለውን ሁሉ በጠቀለለበት፥ በዘመን ፍጻሜ እንዲሆን እንዳቀደው፥ እንደ ፈቃዱና እንደ ምክሩ ሁሉን በሚያከናውንበት” (ኤፌ 1፡10) “ለማይታየው አምላክ ምሳሌ፤ የፍጥረት ሁሉ በኩር በሆነው” (ቆላ 1፡16) በኢየሰስ ክርስቶስ አምላካዊ ሰውነት መልክ አምሳል ተፈጥሯል (ቆላ 1፡15፣ 1 ቆሮ 15፡47፣ ዮሐ 3፡11)። ፍጹም ሰው፤ ፍጹም አምላክ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እግዚአብሔር ሰብዓዊ የሆነውን ነገር እንደ ራሱ ያውቀዋል፤ ሰዋዊ የሆነም ማንነታችን እግዚአብሔርን በውስጡ ይገነዘበዋል፤ በዚህ አይነት በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እግዚአብሔር ሰውን እንደራሱ አብራክ ክፍይ እንዲያውቀው፤ የሰው ልጅም እግዚአብሔርን እንደ መልኩ ፍጻሜ እንዲያውቀው የአዲስ ኪዳን በር ተከፍቶልናል።[3] በዚህ በር በኩል የሰው ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ የእግዚአብሔርን ፊት መመልከት ችሏል። ጌታ ራሱ ይህንን ሲመሰክር “እኔን ያየ አብን አይቷል” (ዮሐ 14፡9) እያለ ያረጋግጥልናል።

ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር አብ ዘላለማዊ የመልኩ ምሳሌ እና ዘላለማዊ ቃሉ ነው። በመሆኑም የሰው ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ በመልኩ ምሳሌ ይገለጥ ዘንድ በቃሉ ኃይል እየጠራ እድፍ እና የፊት መጨማደድ ሳይኖርበት በራሱ በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፣ በመንፈስ ቅዱስ ሥራ በእግዚአብሔር አብ ፊት ሕያው ይሆን ዘንድ ይቀደሳል። መንፈስ ቅዱስ የሰውን ልጅ በወልደ እግዚአብሔር መልክ እየቀረጸ የኢየሱስ ክርስቶስ መልክ ነጽብራቅ በፊቱ ላይ ይሆን ዘንድ በትንሳኤው ብርኀን የአማኞችን ፊት ያትማል። በመሆኑም ቅዱሳንን የሚለያቸው ቁም ነገር የታተመባቸው መልክ ሳይሆን በታተመባቸው መልክ ላይ የሚንጸባረቀው የኢየሱስ መልክ ብርኀን ሌሎችን ወደ ጌታ የሚጠራበት የፍቅር ስበት ኃይል  ነው።  በመሆኑም ቀዳሜ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ በመጨረሻው ሰዓት ሰማያት ተከፍተው፣ ጌታ በአብ ቀኝ ቆሞ በተመለከተባት ቅጽበት በፊቱ ላይ የተንጸባረቀው የእግዚአብሔር ክብር መገለጥ ኃይል (ሐሥ 7፡56)፣ አዳም ከውድቀቱ አስቀድሞ በፊቱ ላይ ያበራው የእግዚአብሔር ብርኀን፣ ሙሴ ወደ እግዚአብሔር በቀረበ ጊዜ ፊቱን የወረሰው የእግዚአብሔር የክብር ደመና ብርኀን (ዘጸ 34, 35)፣ በመጨረሻውም ዘመን በግንባራችን ላይ ሲያንጸባርቅ የሚታየው የኢየሱስ ስም ብርኀን (ራዕ 22፡4) አሁን በሕይወታችን ተገልጦ ይታይ ዘንድ ዐቢይ ጾም የጌታ ብርኀን በፊታችን ላይ እንዲያበራ ነፍሳችን በመንፈስ ቅዱስ ምክር ለበጉ ሠርግ የምትዘጋጅበት የጸጋ ዘመን ነው።

በሉቃስ ወንጌል ስለ ዘመኑ ፍጻሜ እና ስለ ሰው ልጅ ዳግም ምጽዐት ሲነገር “ይህም መሆን ሲጀምር መዳናችሁ ቀርቦአልና ቁሙ፤ ቀናም በሉ” (ሉቃ 21፡28) እየተባለ ፊታችንን የጽድቅ ጸሐይ እና የንጋት ኮከብ ወደሆነው ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ እንድንመልስ እንጋበዛለን። እንግዲያውስ ዐቢይ ጾም የትኩረት አቅጣጫችንን የምናስተካክልበት፣ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ለዘላለሙ ፊቱን ወደ እኛ ወደ መለሰው አምላክ ፊት ፊታችንን እንድንመልስ መንፈስ ቅዱስ በእኛ ውስጥ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ወደ እግዚአብሔር አብ በማይነገር መቃተት የሚጸልይበት የጸጋ ወቅት ነው።

የሰው ልጅ ክቡርነት የመጨረሻው ዋጋ የማይታይ አምላክ ምሳሌ የሆነው የኢየሱስ ክርስቶስ መልክ የታተመበት የእግዚአብሔር መልክ ነጸብራቅ የመሆኑ ቁም ነገር ነው። በዚህም በሚታየው ፍጹም ሰውነቱ ምሥጢር የማይታየው ፍጹም አምላክነቱ ምስል ተገልጧል፤ ይህም ምስል የማይታየው አምላክ የሚታይ ማንነት ነው።[4] እግዚአብሔር በዚህ የመልኩ ምሳሌ በኩል በምድር ላይ ተገልጦ ታይቷል፤ ይህም መልክ ፍጹም ሰው እና ፍጹም አምላክ የሆነ፤ ሰው እና እግዚአብሔር በአንድ ገበታ የቀረቡበት፣ “ከእኛ ጋር እደር” (ሉቃ 24፡29) የሚለው የደቀ መዛሙርቱ ጥያቄ ዘላለማዊ ምላሽ ያገኘበት፣ ሰው እና እግዚአብሔር በወልደ እግዚአብሔር ልዩ አካል የታረቁበት መገለጥ ነው።[5]

በመሆኑም የሰው ልጅ ክብር የሚመነጨው እና ኅያው ሆኖ የሚኖረው ከዚህ በሰው እና በእግዚአብሔር መካከል መካከለኛ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ሰው፣ ፍጹም አምላክ የመሆን ምሥጢር ተካፋይ ከመሆኑ ቁም ነገር የተነሳ እንጂ የሰው ልጅ ከሌሎች እንስሣት በተለየ ባሉት ክህሎቶች ላይ የተመሰረተ አይደለም። ይልቁንም የራሱን የባሕርይ መልክ በምድር ላይ የገለጠ እግዚአብሔር በዚህ መገለጥ ከሰው ልጅ ጋር ዘመድ ስለሆነ ነው።[6] ከዚህም ዝምድናው የተነሳ “እጅግ መልካም” (ዘፍ 1፡31) አድርጎ የፈጠረውን የሰውን ልጅ በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሕማም፣ ሞት እና ትንሳኤ ምሥጢር “እጹብ ድንቅ” (መዝ 139፡14) አድርጎ አድኖታል።[7] የቤተ ክርስትያን አበው ይህንን ምሥጢር ሲያብራሩ የሰው ልጅ የመለኮታዊ ሕይወት ተካፋይነት በአዲስ ኪዳናዊ የጸጋ ሕይወት ይታደስ ዘንድ አምላክ ራሱ ሰውነትን ለበሰ። ከዚህም የተነሳ የእንዝናዙ ቅዱስ ጎርጎርዮስ “ሰው የእግዚአብሔር ሰብዓዊ መልኩ ነው” እያለ ያስተምራል።[8] በመሆኑም እግዚአብሔር በዘመን ፍጻሜ ከሚገለጥበት የሰው ልጅ መልክ ጋር አስቀድሞ የሰውን ልጅ በአርአያው እና በአምሳሉ በፈጠረበት በጎነቱ በኩል ዘላለማዊ ዝምድና አለው።[9]

እንግዲህ ዐቢይ ጾም የሰውን ልጅ የምንመለከትበትን እና የምናከብርበትን ትህትና፣ የሰውን ልጅ የምንቀበልበትን እና የምንመዝንበትን፣ ከዋጋው ጋር በሚስማማ፣ ለተፈጠረበት የእግዚአብሔር መልክ እና ለዳነበት የእግዚአብሔር ደም ተመን ፍትሐዊ በሆነ ሚዛን የክብሩን ልዕልና እንድንማር ወደ እውነውተኛው መልካችን እና ወደ ዳንንበት ደም ቀና ብለን የምንመለከትበት የአስተውሎት እና የመመልስ የጸጋ ወቅት ነው።

የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ (መዝ 8፡ 1-9)   

አቤቱ ጌታችን፥ ስምህ በምድር ሁሉ ምን ያህል ገናና ነው፥ ክብርህን በሰማዮች ላይ የምታኖር።… የጣቶችህን ሥራ ሰማዮችህን ባየሁ ጊዜ፥ ጨረቃንና ከዋክብትን አንተ የሠራሃቸውን፥ ታስበው ዘንድ ሰው ምንድነው? ትጐበኘውም ዘንድ የሰው ልጅ ምንድነው? ከመላእክት እጅግ ጥቂት አሳነስኸው፥ በክብርና በምስጋና ዘውድ ከለልኸው። በእጆችህም ሥራ ሁሉ ላይ ሾምኸው፥ ሁሉን ከእግሮቹ በታች አስገዛህለት፥ በጎችንም ላሞችንም ሁሉ ደግሞም የምድረ በዳውን እንስሶች፥ የሰማይንም ወፎች የባሕርንም ዓሦች፥ በባሕር መንገድ የሚሄደውንም ሁሉ። አቤቱ ጌታችን፥ ስምህ በምድር ሁሉ እጅግ ተመሰገነ።

ጸሎት

አቤቱ፥ በአንተ ታምኛለሁና ጠብቀኝ። አንተ ጌታዬ ነህ! ከአንተ በቀር በጎነት የለኝም። ጌታ የርስቴ እድል ፈንታና ጽዋዬ ነው፥ ዕጣ ፈንታዬንም የምታጸና አንተ ነህ፤ የመከረኝን አምላክ እባርካለሁ፥ ሁልጊዜ ጌታን በፊቴ አየዋለሁ፥ በቀኜ ነውና አልታወክም። ስለዚህ ልቤን ደስ አለው ነፍሴም ሐሴት አደረገች፥ ሥጋዬም ደግሞ በተስፋ ታድራለች። የሕይወትን መንገድ አሳየኸኝ፥ ከፊትህ ጋር ደስታን አጠገብኸኝ፥ በቀኝህም የዘለዓለም ፍሥሐ አለ።

የሰውን ሥራ አፌ እንዳይናገር ፈቃዴ ነው፥ ስለ ከንፈሮችህ ቃል ጭንቅ የሆኑ መንገዶችን ጠበቅሁ። እግሮች እንዳይናወጡ አረማመዴን በመንገድህ አጽና። አቤቱ፥ ሰምተኸኛልና ወደ አንተ ጠራሁ፥ ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል፥ ቃሌንም ስማ! ቸርነትህን ድንቅ አድርገህ ግለጠው። እንደ ዐይን ብሌን ጠብቀኝ፥ በክንፎችህ ጥላ ሰውረኝ እኔ ግን በጽድቅ ፊትህን አያለሁ፥ ክብርህን ሳይ እጠግባለሁ። አቤቱ ጉልበቴ ሆይ፥ እወድድሃለሁ። ጌታ ዓለቴ፥ አምባዬ፥ መድኃኒቴ፥ አምላኬ፥ በእርሱም የምተማመንበት ዓለቴ፥ ጋሻዬ፥ የደኅንነቴ ቀንድ መጠጊያዬም ነው። ምስጋና የሚገባውን ጌታን እጠራለሁ፥ አቤቱ ጉልበቴ ሆይ፥ እወድድሃለሁ። አሜን!

የዐቢይ ጾም አስተውሎት (Journal)

በዚህ በአብይ ጾም በየዕለቱ የጸሎት ሐሳቦችን እና አስተውሎቶችን መጻፍ ለተሻለ መንፈሳዊ ሕይወት ያግዛል። እውነተኛ የቀን ውሎ አስተውሎት እና የጸሎት ሐሳብን በነጻነት በማስፈር ለነፍስ ዕድል መስጠት በመንፈሳዊ ሕይወት መሰረታዊ ቁም ነገር ነው። ከዚህ በታች የቀረቡት ጥያቄዎችን ለራስ ውሎ በሚስማማ ሁኔታ በማስተካከል አስተውሎትን መጻፍ ይቻላል።

  1. ከሰዎች ጋር ስነጋገር ፊታቸውን አተኩሬ እመለከታለሁ?
  2. በሰዎች ፊት ስሆን ይህ መልክ የከበረ የእግዚአብሔር ክብር ነጸብራቅ በሆነበት ልክ አከብረዋለሁ?
  3. ኢየሱስ ክርስቶስ ያካፈለውን መልክ እመለከታለሁ ወይስ የወንድሜ ድካም ላይ ብቻ ያለኝ ትኩረት የጌታን መልክ ሸፍኖብኛል?
  4. የዐቢይ ጾም የጸጋ መሻቴ ምንድነው? የትኛው ጸጋ ዛሬ፣ አሁን እያለፍኩበት ባለሁት ሁኔታ ውስጥ በይበልጥ ያስፈልገኛል?

የተባረከ የጾም ጉዞ!

ሴሞ

ይቀጥላል...

 

[1] Johannes Paul II., Mulieris dignitatis. Apostolisches Schreiben am 15.8.1988. Gleiches drückt sich darin aus, daß der Ikonograph bei seiner Darstellung immer mit dem Kopf beginnt; dieser bestimmt die Stellung des Körpers und gibt das Gesamt der Komposition an.

[2] Clemens of Alexandria, Stromatum, VI (PG 9,293).

[3] ቃል ሥጋ የመሆኑ እውነት በነገረ መለኮታዊ አነጋገር የፍጥረት ሁሉ አክሊል እና ፍጻሜ ነው፤ ወልደ እግዚአብሔር በልዩ አካሉ ሰው ሆነ ስልን እግዚአብሔር ፍጹም ሰውነትን እና ፍጹም አምላክነትን በገዛ ራሱ አካል አወቀ፤ በዚሁ እውቀትም ከፍጥረት ጋር ሁሉ በኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆን አዲስ ኪዳናዊ መገለጥ ተዋወቀ ማለታችን ነው። ማለታችን ነው።   above all, allows God to be recognized both in relation to itself and to the whole of creation" (ንጽ W. Pannenberg, Systematic Theology, Vol. II, Göttingen 1991, 137 ጀምሮ)።

[4] The expression is transmitted by Pseudo-Dionysius and preserved by John of Damascus in Treatise on the Icons, XI.

[5] ንጽ J. Moltmann, In der Geschichte des dreieinigen Gottes. Beiträge zur trinitarischen Theologie, München 1991, 226 ጀምሮ)።

[6] ንጽ J. Moltmann, In der Geschichte des dreieinigen Gottes, 226.

[7] ንጽ M. Herz, Sacrum Commercium (Münchener Theologische Studien II, Bd. 15), München 1958, 71.

[8] Gregor von Nyssa, In Psalmos, IV (PG 44,446BC).

[9] Makarius, Hom. 45.

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።