Map St Joseph Cistercians

Top Panel

የዐቢይ ጾም 27ኛ ቀን

የዐቢይ ጾም 27ኛ ቀን

mount-of-olivesደብረ ዘይት

ጌታ በደብረዘይት ተራራ ያስተማረው ትምህርት በአንድ በኩል ሊሆን ያለው ነገር የሚፈጸምበትን ጊዜ እና ቦታ እየተመለከተ በሌላ በኩል ደግሞ የዘመን ፍጻሜ ምልክቶችን ለሚሰሙት እየተናገረ የዋለበት ዘለግ ያለ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ነው። ይህ የዐብይ ጾም አምስተኛ ሳምንት በአንድ በኩል ይህ የጌታ ትምህርት የሚታሰብበት ሰንበት በመሆኑ ደብረዘይት ተብሎ ይጠራል፤ በሌላ በኩል ደግሞ የጾም እኩሌታ በመሆኑ እኩለ ጾም እየተባለ ይጠራል።

ይህ ሰንበት ክርስቶስ በደብረዘይት ተራራ ሳለ ለሐዋርያቱ ስለዳግም ምፃቱ በግልጽ የተናገረበት እና ስለ ጊዜው ምልክቶች የሰበከበት ሰንበት ነው። ጌታችን በዚህ ወቅት የሁሉ ነገር ፍፃሜ እንደቀረበ ለሐዋርያቱና ለደቀመዛሙርቱ ይነግራቸዋል። የእግዚአብሔር መንግስት በኃይል እና በክብር እንደሚገለጥ ሲያስተምራቸው ከእርሱ በፊት መከራ እና ጭንቅ እንደሚመጣ፤ አሳሳቾች እንደሚነሱ፤ታላላቅ ተዓምራቶች እንደሚደረጉ ወ.ዘ.ተ. እያስጠነቀቀን ከዚህ ሁሉ ተጠበቁ ይለናል። ይህ የደብረ ዘይት ሰንበት ጽኑ የሆኑት የእግዚአብሔር ልጆች ከብዙ መከራና ስቃይ በኋላ የእግዚአብሔር ልጅ በክብሩ ሲገለጥ እንደሚመለከቱት የሚያረጋግጠውን የኢየሱስን ስብከት የምናሰላስልበት ሰንበት ነው።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ስብከቱ በእርሱ ስም አማካኝነት በዓለም ሁሉ ፊት የተጠላችሁ ትሆናላችሁ ይላል። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ስም ሲጠራ “አሜን” የሚል ስደትና ሞትን ለመቀበል የደፈረ ጽኑ ሰው መሆን አለበት። “አሜን” ማለት ዋጋ የሚያስከፍልበት ዘመን እንደሚመጣ ኢየሱስ ይናገራል። “አሜን” ማለት ዛሬ አይደለም፤ነገር ግን የኢየሱስ ስም የጠላት ስም፣ የጥፋት ስም፤፣ የሞት ቅጣት ስም የሚሆንበት ዘመን ላይ “አሜን” ማለት ይቻል ይሆን? ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእነዚያ ጊዜያት “ከዐመጽ ብዛት የተነሳ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች” እያለ ያስጠነቅቃል። በፍቅር የሚጸና፤ ለመዳን ብሎ ሁሉን ታግሶ የሚጸና ብዙ ሰው እንደማይኖር ያስተምራል። ስለዚህ በዚህ በደብረዘይት ሰንበት ጌታችን “እነሆ አስቀድሜ ነገርኳችሁ” (ማቴ 24፡25) ይላል። የክርስትና ሕይወት የሚያስከትለውን ውጊያ አይተናል፤ ክርስቲያን መሆን የሚያስከፍለውን ዋጋ አውቀናል፤ የምንሸከመውን መስቀል ሽራፊ ተመልክተናል፤ የምናገኘውንም ድል አውቀናል ስለዚህ መወሰን አለብን! ክርስቲያን ነኝ ወይም ክርስቲያን አይደለሁም! መኃል ሰፋሪ መሆን የለም።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስላደረገው የሕይወት ምርጫ ሲናገር “ከክርስቶስ ጋር ተሰቅያለሁ” (ገላ 2፡20) እያለ ለገላትያ ክርስቲያኖች ምሥክርነቱን ይሰጣል። የመስቀሉ ኑሮ ምን እንደሚመስል ሲናገር“እኔም አሁን ህያው ሆኜ አልኖርም፣ ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፤ አሁንም በስጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው” (ገላ 2፡20) ይላል። ክርስትያን መሆን በክርስቶስ፣ ለክርስቶስ ከክርስቶስ ጋር መኖር ማለት ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ክርስትና የኑሮ ዘይቤ ሲናገር “እኔ ባለሁበት አገልጋዬም በዚያ ይኖራል” (ዮሐ 12፡26) ይላል። ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ በአብ ቀኝ አለ። እሱ ባለድል ሆኖ ከነሙሉ ክብሩ በአባቱ ዘንድ አለ። የእያንዳንዱ ክርስትያን ድል ይህ ነው። በዚህ ድል በክርስቶስ ኢየሱስ ተመርጠናል። ነገር ግን ይህ ድል ምን አይነት ድል ነው?

ይህ የክብር ድል የመስቀል መንገድ ድል ነው። ኢየሱስ በመስቀል መንገድ ሔዶ የከፈተው የድል በር ነው። ማንም በዚህ የድል በር መግባት እና የእግዚአብሔርን መንግስት ወርሶ ከክርስቶስ ጋር መንገስ ቢፈልግ ኢየሱስ በግልጽ መመርያውን ይሰጣል።”መስቀሉን ተሸክሞ ይከተለኝ” (ማቴ 16፡24)። ወዴት? ኢየሱስ መስቀሉን ተሸክሞ ወደሚሰቀልበት ሥፍራ ወጣ። የመስቀሉን ሥራ ፈጸመ። ሞተ፣ ተቀበረ፣ በሦስተኛው ቀን ሞትን ድል አድርጎ ተነሳ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን የመስቀል ጉዞ ሲያብራራልን “ሞቱን በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን፤ ትንሳኤውን በሚመስል ትንሳኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን” (ሮም 6፡5) ይላል። ስለዚህ ያለ ስቃይ ክብር፣ ያለ መስቀል አክሊል፣ ያለ ውጊያ ድል የለም።

የደብረዘይት ሰንበት ቀደም ሲል እንደተመለከትነው የጾም እኩሌታ በመሆኑ እኩለ ጾም ተብሎ ይጠራል። ጾማችንን ማጋመሳችን ፤ ወደ ትንሳኤው መቅረባችንን የሚያሳስበን ሰንበት ነው። ስለዚህ ያለፉት አራት ሰንበቶች እንዴት አለፉ? ብለን የምናሰላስልበት አጋጣሚ ነው። አንድ ወር ያህል የዐብይ ጾም ውስጥ ስንቆይ ምን አተረፍን? ከውጊያው አፈግፍገን ከሆነ የተዳከምንባቸው ምክናያቶች ምንድናቸው? የሚሉትን እነዚህን ጥያቄዎች አበክረን በመጠየቅ እንደ ጥንቁቅና ብልህ ነጋዴ ከእግዚአብሔር ጋር የምንተሳሰብበት ሳምንት ነው። እንዲሁም ደግሞ በቀጣዮቹ የዐብይ ጾም ሳምንታት የበለጠ ተጋድሎ በማድረግ የምንበረታበት ይሆን ዘንድ ታጥቀን የምንነሳበት ሳምንት ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለዚህ እያዘጋጀን መንገዱን ይጠቁመናል፤ “በቀረውስ በጌታና በኃይሉ ችሎት የበረታችሁ ሁኑ። የዲያቢሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን የጦር ዕቃ ሁሉ ልበሱ” (ኤፌ 6፡10-11)።

የሉቃስ ወንጌል በ15ኛው ምዕራፍ ጠፍተው ስለተገኙ ሦስት ነገሮች በምሳሌ እያስተማረ እኛም ከጠፋንበት ሥፍራ እንመለስ ዘንድ ይጋብዘናል። እነዚህ ምሳሌዎች የሚያሳስቡን ዐብይ ቁምነገር አንድ ውድ የሆነ ነገር ከጠፋን ባለን ኃይል ሁሉ ተጠቅምን እስከምናገኘው ድረስ እንደምንፈልገው የሚገልጽ ነው። ሰው የሚወደውን ነገር ሲያጣ የሚሰማው ስቃይ ከባድ ነው። በሞት ከምንወደው ሰው ስንለያይ፤ በሕይወት አጋጣሚ ከወዳጆቻችን ስንራራቅ ወ.ዘ.ተ. ከባድ ኃዘን ይሰማናል እግዚአብሔር አባታችን ልጆቹ በማወቅም ባለማወቅም ከእርሱ ሲርቁ ልቡ ያዝናል። ወደ እርሱ እንድንመለስ ይናፍቃል። ፀጋውን በመስጠት ወደ እርሱ እንቀርብ ዘንድ ዘወትር የልባችንን በር ያንኳኳል። ምንም ያህል ከእግዚአብሔር ርቀን የተጓዝን ብንሆንም ወደ እርሱ ለመመለስ የሚያስፈልገው አንድ እርምጃ ብቻ ነው! ይህ የዐብይ ጾም ጊዜ በእግዚአብሔር ምሕረት በመተማመን ወደ እርሱ ለመመለስ አንድ እርምጃ ወደእርሱ ለመቅረብ የምንወስንበትና የምንራመድበት ወቅት ነው። ስለዚህ “አንተ የምታንቀላፋ ንቃ፤ ከሙታንም ተነስ፤ክርስቶስ ያበራልሃል” (ኤፌ 5፡14) እንደተባለ የመንቃት ጊዜ አሁን ነው።

የሉቃስ ወንጌል ስለጠፋው ልጅ የሚያደርገው ትረካ ሁለት መልኮችን የያዘ ነው። የመጀመሪያው በልጁ መመለስ የተደሰተው አባት ያደረገው ነገር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በወንድሙ መመለስ የተበሳጨው ታላቁ ልጅ የፈጸመው ተግባር ነው። ይህንን ሐሳብ በጥልቀት ስናስተነትን እኛ ከፈጣሪያችን ጋር ሊኖረን ስለሚገባው ጤናማ ግንኙነት እንደሚናገር ማየት ይቻላል። በተለይ በዚህ በዐብይ ጾም ልናከናውነው የሚገባንን ነገር ያሳስበናል። ይህ ታላቁ ልጅ ዘወትር የሚኖርበትን የአባቱን ቤት ጣዕም አጣጥሞ አያውቅም። የአባቱን ቤት ጣዕም፤ በአባቱ ቤት ያለውን ክብር ለማስተዋል ልቦናው ተዘግቶ ነበር። በቤትህ ያለውን የፍቅር ጣዕም ማጣጣም ካልቻልክ በአካል በቤት ውስጥ ብትገኝም በልብህ ግን የከፋ ስደት ላይ ነህ። ሰው በቤቱ፣ በትዳሩ፣ በሥራው፣ በመንፈሳዊ ሕይወቱ የእግዚአብሔርን ጣዕም መቅመስ ካልቻለ፣ የእግዚአብሔርን ለዛ ማጣጣም ካልቻለ፣ በመንፈሱ ሙት ነው። ሕይወቱም የስደት ሕይወት ነው። ስለዚህ በዐቢይ ጾም በእግዚአብሔር ቤት ባለን ሕይወት የእግዚአብሔርን ለዛ እያጣጣምን ነውን? በአባታችን ቤት ያለውን ፍቅር፣ ሰላም፣ ደስታ፣ ተስፋ፣በትዳራችን፣ በልጆቻችን መካከል፣ በሥራ ገበታችን፣ በመንፈሳዊ ሕይወታችን ምን ያህል ተጠቅመንበታል? ብለን ራሳችንን እንድንመረምር ይጋብዘናል።

በዚሁ የሉቃስ ወንጌል ትረካ የታናሹን ልጅ ሕይወት እና ምርጫ እንመለከታለን። ታናሹ ልጅ ወደ ሩቅ ሀገር ተሰደደ። በዚያም ያለውን ነገር ሁሉ አባከነ። ሥራውም በሙሉ ትርፍ አልነበረውም። ገንዘቡን አጥፍቶ እስከሚጨርስ ድረስ ብዙ ወዳጆች በዙርያው ነበሩ፤ነገር ግን ገንዘቡ ባለቀበት ጊዜ ማንም አብሮት አልቆየም። የዕለት ቁራሽ እንጀራ የሚሰጠው ሰው ስላጣ ወደ አሳማዎች ዘንድ እንደሄደ ወንጌል ይናገራል። በመጽሐፍ ቅዱስ አነጋገር አሳማ የተዋረደ ሕይወት ምሳሌ ነው። ልጁ ከአባቱ ቤት ከወጣ ጀምሮ ምን ያህል የአባቱ ክብር እንዳጎደለውና ሕይወቱ ዋጋ እንዳጣ ያስገነዝበናል። በእኛም ሕይወት ዛሬ የእግዚአብሔር ክብር ጎድሎ ይሆን? በብዙ ቦታ ወጣቶች በሱስ፣ በአጸያፊ ፊልሞች፣ በኢ-ግብረገባዊ ባሕርያት ምርኮኛ ሆነው ለእግዚአብሔር ልጆች በማይገባ የተዋረደ ሕይወት ይኖራሉ። ኢየሱስ ግን እነዚህን ወጣቶች ነፃ ሊያወጣቸው ይፈልጋል። ከባርነት ቀንበር አላቅቆ የእግዚአብሔርን ክብር ሊያለብሳቸው ይፈልጋል። ታናሹ ልጅ ወደ አባቱ ቤት ለመመለስ ቁርጥ ፈቃድ አድርጎ ጉዞ እንደጀመረ ሁሉ እኛም በዚህ በዐብይ ጾም ቁርጥ ፍቃድ ልናደርግባቸው የሚገቡንን የሕይወት ዘርፎች በመመርመር መመለስ ያስፈልጋል። የተማረክንባቸውን ውጊያዎች እንደገና ተዋግተን ድል በመንሳት የእግዚአብሔርን ልጆች ክብር እንድንወርስ ቁርጥ ፈቃድ አድርገን እንነሳ።

በዚህ በደብረዘይት ሳምንት ኢየሱስ በተራራ ላይ ለደቀ መዛሙርቱ ምሥጢሩን እንደገለጠላቸው ወንጌል ይናገራል። እነዚህ ደቀ መዛሙርት ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው የትምህርቱን ትርጉም እንደጠየቁት አንብበናል (ማቴ 24፡3)። ለብቻቸው ወደ ኢየሱስ መምጣታቸው ላይ አተኩረተን ስንመለከት ወደ ራሳችን ሕይወት ይመልሰናል። በግል የጸሎት ሕይወታችን ከኢየሱስ ጋር የልብ ለልብ ውይይት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ያሳየናል። ይህ የልብ ለልብ ልውውጥ የሕይወታችንን ምሥጢራዎ ነገሮች በግልጽ የምናስተውልበት መልካም አጋጣሚ ነው። በዚህ የዐብይ ጾም ጊዜ ቅዱስ ቁርባን የመጎብኘትና በጽሙና ከኢየሱስ ጋር የመወያየት መንፈሳዊነት በመለማመድ የጸሎት ሕይወታችን የበለጠ ፍሬአማ እንዲሆን ማድረግ አለብን። በቅዱስ ቊርባን ፊት በጽሞና ከኢየሱስ ጋር የሚደረገው ውይይት ብዙ በረከት የሚያስገኝ በመሆኑ ይህንን መንፈሳዊ ኃብት በሚገባ ልንጠቀምበት ያስፈልጋል። ኢየሱስ በቅዱስ ቊርባን ሆኖ የእኛን መምጣት በመጠባበቅ እንዲህ ይላል” ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ” (ዮሐ 7፡37)።

የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ (ማቴ 24፡1-15)

በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ደቀመዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው “እስቲ ንገረን፤ ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድነው?” አሉት። 4ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ። ብዙዎች ‘መሢሑ እኔ ነኝ’ እያሉ በስሜ ይመጣሉና ብዙዎችንም ያስታሉ። ጦርነትንና የጦርነትን ወሬ ትሰማላችሁ፤ አስተውሉ፥ አትደንግጡ፥ ይህ ሊሆን ግድ ነውና፤ ነገር ግን መጨረሻው ገና ነው። ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና፤ ራብና የምድር መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል፤ እነዚህ ሁሉ የምጥ መጀመሪያ ናቸው። “በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፤ ይገድሉአችኋልም፤ ስለ ስሜም በሕዝቦች ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ። በዚያን ጊዜ ብዙዎች ይሰናከላሉ፤ እርስ በርሳቸውም አሳልፈው ይሰጣጣሉ፤ እርስ በርሳቸውም ይጠላላሉ፤ ብዙ ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉ፤ ብዙዎችንም ያስታሉ፤ ከሕገ ወጥነት ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች። እስከ መጨረሻው የሚጸና ግን እርሱ ይድናል። ለሕዝቦች ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥቱ ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፤ በዚያን ጊዜ መጨረሻው ይመጣል።

ጸሎት

ጌታ ሆይ በዐቢይ ጾም ጉዞዬ አጋማሽ ላይ ካንተ ጋር ሁሉን በድጋሚ እመለከት ዘንድ ጸግህን ስጠኝ። በዚህ ጉዞ በደከምኩባቸው ነገሮች ሁሉ ምህረትህን አድለኝ። ወደ ትንሳኤህ ምሥጢር በማደርገው በዚህ ጉዞ ይበልጥ በብዙ ተጋድሎ ሕማምህን እካፈል ዘንድ አበርታኝ። የላሉትን መንፈሳዊ ነገሮቼን እና ቁርጥ ፈቃድ የማድረግ ፈቃዴን አበርታ። ነፍሴ ሆይ፥ ጌታን ባርኪ፥ አጥንቶቼም ሁሉ፥ የተቀደሰ ስሙን። ነፍሴ ሆይ፥ ጌታን ባርኪ፥ ውለታውንም ከቶ አትርሺ፥ ጥፋትሽንም ሁሉ ይቅር የሚል፥ ደዌሽንም ሁሉ የሚፈውስ፥ ሕይወትሽን ከጥፋት የሚያድናት፥ በፍቅርና በርኅራኄ የሚከልልሽ፥ ምኞትሽን ከበረከቱ የሚያጠግባት፥ ጎልማሳነትሽን እንደ ንስር ያድሳል። የቃሉንም ድምፅ የምትሰሙ ሁሉ፥ ጌታን ባርኩ።ሠራዊቱ ሁሉ፥ ፈቃዱን የምታደርጉ አገልጋዮቹ፥ ጌታን ባርኩ። ፍጥረቶቹ ሁሉ በግዛቱ ስፍራ ሁሉ፥ ጌታን ባርኩ። ነፍሴ ሆይ፥ ጌታን ባርኪ። አሜን!

የዐቢይ ጾም አስተውሎት (Journal)

በዚህ በአብይ ጾም በየዕለቱ የጸሎት ሐሳቦችን እና አስተውሎቶችን መጻፍ ለተሻለ መንፈሳዊ ሕይወት ያግዛል። እውነተኛ የቀን ውሎ አስተውሎት እና የጸሎት ሐሳብን በነጻነት በማስፈር ለነፍስ ዕድል መስጠት በመንፈሳዊ ሕይወት መሰረታዊ ቁም ነገር ነው። ከዚህ በታች የቀረቡት ጥያቄዎችን ለራስ ውሎ በሚስማማ ሁኔታ በማስተካከል አስተውሎትን መጻፍ ይቻላል።

  1. ስለዚህ ያለፉት አራት ሰንበቶች እንዴት አለፉ?
  2. አንድ ወር ያህል የዐብይ ጾም ውስጥ ስንቆይ ምን አተረፍን?
  3. ከውጊያው አፈግፍገን ከሆነ የተዳከምንባቸው ምክናያቶች ምንድናቸው?
  4. የጸሎት ሕይወታችን ምን ይመስላል?
  5. የዐቢይ ጾም የጸጋ መሻቴ ምንድነው? የትኛው ጸጋ ዛሬ፣ አሁን እያለፍኩበት ባለሁት ሁኔታ ውስጥ በይበልጥ ያስፈልገኛል?

የተባረከ የጾም ጉዞ!

ሴሞ

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።