የዐቢይ ጾም 28ኛ ቀን
- Category: የ ፵ ጾም አሰተንትኖ
- Published: Monday, 24 March 2025 06:27
- Written by Samson
- Hits: 121
- 24 Mar
የዐቢይ ጾም 28ኛ ቀን
የእግዚአብሔር ልጅ ምስል እውነተኛውን የሰው ልጅ መልክ ገልጦልናል።[1] የሰው ልጅ መልክ በኢየሱስ ክርስቶስ ዘላለማዊ ልጅነት መልክ በእግዚአብሔር ፊት አስቀድሞ የታወቀ መልክ ነው፤ በመሆኑም ቅዱስ ጳውሎስ “አስቀድሞ ያወቃቸውን የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ወስኖአል” (ሮሜ 8,29) እያለ በእግዚአብሔር ዘንድ ስለታወቅንበት የኢየሱስ ክርስቶስ መልክ ይመሰክራል። ቃል ሥጋ በመልበሱ ምሥጢር ውስጥ የተገለጠው ምድራዊው እውነታ የሰማያዊው እውነታ የሚታይ መገለጫ በመሆኑ፤ በተመሳሳይ መልኩ የሰው ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ “ሰው” የመሆን ምሥጢር በኩል መለኮታዊ መልኩ ተመልሶለት፣ አስቀድሞ በተፈጠረበት እውነተኛ መልክ ታድሶ፣ በአዲስ ኪዳናዊ ማንነት ይገለጣል። የሰው ልጅ የበለጠ ሰው በመሆኑ ምልዓት የሚገለጠው የተፈጠረበትን መልክ ይኸውም “ፊቱ” ኢየሱስ ክርስቶስን ባንጸባረቀበት ጸዳል ልክ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንጦስ ክርስትያኖች የሚሰብከው የአዲስ ኪዳን ወንጌል ይህ ነው “ እኛም ሁላችን፥ በመጋረጃ በማይሸፈን ፊት፥ የጌታን ክብር እንደ መስተዋት እያብለጨለጭን፥ የእርሱን መልክ እንድንመስል ከክብር ወደ ክብር እንለወጣለን፥ ይህም መንፈስ ከሚሆን ጌታ የመጣ ነው” (2ቆሮ 3፡18) በመሆኑም “አንታክትም፤ ውጫዊው ሰውነታችን እየመነመነ ቢሄድ እንኳን፥ ውስጣዊው ሰውነታችን በየዕለቱ ይታደሳል” (2ቆሮ 4፡16)።
ነገር ግን የድኅረ አብርሖት ዘመን መሰረታዊ መፈክር “ራስህን ሁን!” የሚል ነው፤ ይሁን እንጂ የክርስትያን ጥሪ ራስን መሆን ብቻ ሳይሆን ከዛም ባሻገር በክርስቶስ ልብ በማሰብ እና በአእምሮአችን መታደስ በመለወጥ ዕለት በዕለት እግዚአብሔርን እየመሰልን ወደ መልካችን ፍጻሜ እና ወደ ክብር ተስፋችን መዳረሻ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ማደግ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጅ ሆኖ በመገለጡ ምሥጢር ውስጥ እያንዳንዱ ሰው የዚህ ምሥጢር ማኅተም አለበት፤ ይህም ማኅተም በኢያንዳንዱ የሰው ልጅ “ፊት” ላይ የተጻፈ እና በእምነት አይኖች የሚነበብ እግዚአብሔር ከእያንዳንዷ ነፍስ ጋር ያለው የፍቅር ታሪክ ነው። ይህ የሰው ልጅ “ፊት” ያለው ነገረ መለኮታዊ አንድምታ በያዕቆብ እና በዔሳው ታሪክ ውስጥ በጉልህ ይስተዋላል። እነዚህ ሁለት ወንድማማቾች በመካከላቸው ዕርቅ ለማውረድ ሲነሱ ያዕቆብ የወንድሙን ፊት ያየበትን ሁኔታ ሲናገር “የእግዚአብሔርን ፊት እንደሚያይ ፊትህን አይቼአለሁና” (ዘፍ 33፡10) በማለት በዕርቅ ጉዞ የዔሳው ፊት ለወንድሙ ለያዕቆብ የዕርቅ ደብረ ታቦር እንደሆነለት እንመለከታለን። ያዕቆብ ከዚያች ቀን በፊት አንድ በሌሊት ሲታገለው የቆየውን ሰው ማንነት ሲናገር እንዲሁ “ፊቱ” ላይ ትኩረት በማድረግ “እግዚአብሔርን ፊት ለፊት አየሁ ሆኖም ሕይወቴ ተርፋለች” (ዘፍ 32፡ 23-33) እያለ ይመሰክራል። ከዚህ ግንኙነት በመነሳት ያዕቆብ 400 ሰዎችን ይዞ በፊቱ የቆመውን እና ጠላት የነበረውን ወንድሙን ዔሳውን ተመልክቶ “ ዔሳውን ባገኛችሁት ጊዜ ይህንኑ ነገር ንገሩት፤ በፊቴ በሚሄደው እጅ መንሻ እታረቀዋለሁ፤ ከዚያም በኋላ ምናልባት ይራራልኛል ፊቱንም አያለሁ ብሎአልና“ (ዘፍ 32፡21)። በዚህ የወንድሙን ፊት የማየት ጽኑ ፍላጎት ውስጥ ብሉይ ኪዳን ስለ ሰው ልጅ “ፊት” ያለው መሰረታዊ መረዳት ግልጽ ሆኖ ይታያል፤ ይኸውም የእያንዳንዱ ሰው “ፊት” በሰማይም በምድርም የማይደገም፤ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ እግዚአብሔር በዚያ መልክ የተገለጠበት የእግዚአብሔር መለኮታዊ ነጸብራቅ መሆኑ ነው።
በዘመናዊው ዓለም አንዱ ልክ ሌላኛውን መስሎ እስከሚታይ ድረስ በውጫዊ ጥበብ መመሳሰል ይቻላል፤ ነገር ግን በዚያ እውነተኛ ፊት ላይ ያለው የእግዚአብሔር ነጸብራቅ በምንም ሊመሳሰል የማይችል፣ በዚያ ፊት ላይ ብቻ በተገለጠበት መለኮታዊ ጸዳል በሰማይም በምድርም በዚያ አይነት ብቻ የተገለጠ የኢየሱስ ክርስቶስ መልክ ነጸብራቅ ነው። በመሆኑም እያንዳንዱ የሰው ልጅ “ፊት” ቅጂ የለውም፤ ኦሪጅናል ነው! በዚህም አንድ እና ብቸኛ “ፊት” ላይ የማንነቱ አንድ እና ብቸኛ ኅላዌ ተገልጦ ይታያል። ያ ሰው በሚያልፍበት የሕይወት መልኮች ውስጥ ሁሉ ይህ ኅላዌ ሳይለወጥ በተለያዩ ገጽታዎች በዘመናት መካከል ተንጸባርቆ ያ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር፣ እግዚአብሔርም ከዚያ ሰው ጋር ያለውን ታሪክ ያስነብበናል። በመሆኑም አንድ ሰው ራሱን ሊጎዳ የሚችልበት የመጨረሻው ከባዱ ኃጢአት ይህንን አንድ እና ብቸኛ “ፊቱን” የሚያበላሽ እና ገጽታውን የሚለውጥ ኃጢአት ውስጥ መኖር ነው። ዐቢይ ጾም ይህንን “ፊት” በተፈጠረበት፣ ከዘላለም ጀምሮ ካለመኖር ወደ መኖር በተጠራበት፣ በታወቀበት እና በመንፈስ ቅዱስ ሥራ የልጁን መልክ ይመስል ዘንድ በእግዚአብሔር አብ አስቀድሞ የተወሰነበትን መልክ የሸፈኑትን ነገሮች ከላዩ ላይ ለማስወገድ ራሳችንን በንስሐ፣ በእምነት እና በጸጋ መስታዎት የምንመለከትበት የጸጋ ወቅት ነው።
የሰው ልጅ “ፊት” በውጫዊ ገጽታው ከሚታየው እውነታ ባሻገር የእግዚአብሔር ክብር ነጽብራቅ ነው። ይህም የእግዚአብሔር ክብር በእያንዳንዳችን “ፊት” ላይ ልዩ እና የማይደገም በሆነ መገለጥ የሚንጸባረቅ በመሆኑ እያንዳንዳችን የእግዚአብሔር ከዋክብት ሆነን አንዱ ኮከብ በሁለንተናው ነገሩ ከሌላው ኮከብ የተለየ ነገር ግን በእርሱነቱ ከሌላው ኮከብ የማይበልጥ ወይም የማያንስ ሆኖ በመንፈስ ቅዱስ የጸጋ ሕይወት የእግዚአብሔርን ክብር፣ የልጁን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን መልክ ያንጸባርቃል። በመሆኑም በሰው ልጅ “ፊት” ላይ የሚነበበው ትልቁ ምሥጢር ሊገለጥ የሚቻለው በእግዚአብሔር በራሱ ብቻ ነው፤ ምንም እንኳን የሰው ልጅ “ፊት” በሚታየው ውጫዊ ገጽታው የሚገልጠው የተወሰነ ነገር ቢኖርም፤ በእግዚአብሔር አርአያ እና አምሳል ከመፈጠሩ ቁም ነገር የተነሳ ከሚታየው ገጽታ ባሻገር የተሸከመው የእግዚአብሔር መልክ የሚገኝበት የማንነቱ ጥልቅ ምሥጢር አለ። በመሆኑም እያንዳንዱ “ፊት” ትኩረት የሚፈልግ የእግዚአብሔር መገለጥ አይነተኛ ምሳሌ ነው።
ዛሬ በደረስንበት የቴክኖሎጂ እመርታ ትናንት ድንቅ የነበሩት የዚህ ዓለም ምሥጢሮች ዛሬ ላይ ተራ መረጃዎች ሆነዋል፤ ይሁን እንጂ ከእያንዳንዱ የሰው ልጅ “ፊት” ጋር የምናደርገው ግንኙነት ዛሬም በምልዓት ሊመለስ የማይቻለው ጥልቅ ጥያቄን የሚፈጥር እንቆቅልሽ ነው። የዚህን “ፊት” ውጫዊ ገጽታ በምናስተውልበት ተመስጦ በእምነት ዐይኖች ወደ ውስጥ ዘልቀን የክርስቶስን “ፊት” ውበት እስከምናስተውል ድረስ ይህ “ፊት” የማይደረስበት ምሥጢር ነው። የሰው ልጅ “ፊት” የሰው ልጅ ማንነት፣ ቃል፣ ድርጊት እና ታሪክ በአንድ ወረቀ ዘቦ ጥለት የተከተቡበት ግምጃ ነው። በመሆኑም የሰው “ፊት” በመላ ማንነቱ እና በታሪኩ ዐውድ ውስጥ የሚነበብ እና ከነጻነቱ ምሥጢር ጋር የተያያዘ የእግዚአብሔር ጥበብ ያለበት መለኮታዊ ትረካ ነው።
በፊቱ ላይ የሚንጸባረቀው የሰው ልጅ ነጻነት የዚያን ሰው ታሪክ እና የሕይወት ምርጫዎች የሚያሳይ መስታወት ነው። የሰው ልጅ በዕለት ተዕለት የሕይወት ምርጫዎቹ የራሱን ታሪክ ለመጻፍ ነጻነት አለው። ይህ ነጻነቱ የፊቱን ገጽታ የሚወስን እና የሄደባቸውን የሕይወት መንገዶች የሚተርክ “ፊቱ” ላይ የተጻፈ የማንነቱ ፍሰት ነው። ስቃይ እና መከራ የዚህን ሰው “ፊት” በእጅጉ ሊለውጡት ይችላሉ፤ በመሆኑም ከላይ ከሚታየው ውጫዊ ገጽታው ባሻገር የሰው ልጅ ታሪክ በፊቱ መልክዓ ምድር የተቀበረ የብዙ ታሪኮች ስብስብ ነው። የሰው ልጅ በውስጡ የተሞላው፣ የሚያስበው፣ ልቡን እና አእምሮውን የገዛው ቁም ነገር በፊቱ ብራና ላይ ተዘርግቶ በዘመን ፋኖስ ብርኀን ይነበባል፤ ይሁን እንጂ የሰው ልጅ በፊቱ ገጽታ ላይ ከተገለጠው ታሪኩ እና ማንነቱ ባሻገር ጥልቅ የሆነ የእግዚአብሔር ሐሳብ ያለበት ምሥጢር ነው።
ደስታ እና ኀዘን በፊቱ ላይ የተጻፉበት ይህ የሰው ልጅ በእምነት ጉዞው እየበሰለ፣ በአእምሮው መታደስ እየተለወጠ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ የአዲስ ኪዳን ልብ እያሰበ ባደገበት ነገር ሁሉ የፊቱ ገጽታ ይበልጥ የተፈጠረበትን መልክ፤ ኢየሱስ ክርስቶስን እየመሰለ ከክብር ወደ ክብር ይገለጣል። ነገር ግን ይህ ከክብር ወደ ክብር የሚገለጠው “ፊት” በዚህ ዓለም በክርስቶስ ኢየሱስ “ፊት” ላይ የደረሰው ነገር ሁሉ ተካፋይ ነው፤ በመሆኑም በዚህ ዓለም ለኢየሱስ ክርስቶስ “ፊት” ከእሾህ አክሊል ይልቅ የከበረ ዘውድ፣ ከመስቀል ይልቅ የከበረ ዙፋን አልተገኘለትም፤ ስለዚህ በትንሳኤው የክብር ፊት በኢየሱስ ክርስቶስ መልክ በእግዚአብሔር ፊት መቆም የሚወድ ማንም ቢኖር የጌታን “ፊት” በሕማሙ እና በሞቱ ሊመስለው ይገባዋል።[2] ዐቢይ ጾም ይህንን “የጌታን ፊት” ዕለት ዕለት ከራሳችን “ፊት” ጋር የምናመሳክርበት የጸጋ መስታዎት ነው። Formularende
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ (መዝ 8፡ 1-9)
አቤቱ ጌታችን፥ ስምህ በምድር ሁሉ ምን ያህል ገናና ነው፥ ክብርህን በሰማዮች ላይ የምታኖር።… የጣቶችህን ሥራ ሰማዮችህን ባየሁ ጊዜ፥ ጨረቃንና ከዋክብትን አንተ የሠራሃቸውን፥ ታስበው ዘንድ ሰው ምንድነው? ትጐበኘውም ዘንድ የሰው ልጅ ምንድነው? ከመላእክት እጅግ ጥቂት አሳነስኸው፥ በክብርና በምስጋና ዘውድ ከለልኸው። በእጆችህም ሥራ ሁሉ ላይ ሾምኸው፥ ሁሉን ከእግሮቹ በታች አስገዛህለት፥ በጎችንም ላሞችንም ሁሉ ደግሞም የምድረ በዳውን እንስሶች፥ የሰማይንም ወፎች የባሕርንም ዓሦች፥ በባሕር መንገድ የሚሄደውንም ሁሉ። አቤቱ ጌታችን፥ ስምህ በምድር ሁሉ እጅግ ተመሰገነ።
ጸሎት
አቤቱ፥ በአንተ ታምኛለሁና ጠብቀኝ። አንተ ጌታዬ ነህ! ከአንተ በቀር በጎነት የለኝም። ጌታ የርስቴ እድል ፈንታና ጽዋዬ ነው፥ ዕጣ ፈንታዬንም የምታጸና አንተ ነህ፤ የመከረኝን አምላክ እባርካለሁ፥ ሁልጊዜ ጌታን በፊቴ አየዋለሁ፥ በቀኜ ነውና አልታወክም። ስለዚህ ልቤን ደስ አለው ነፍሴም ሐሴት አደረገች፥ ሥጋዬም ደግሞ በተስፋ ታድራለች። የሕይወትን መንገድ አሳየኸኝ፥ ከፊትህ ጋር ደስታን አጠገብኸኝ፥ በቀኝህም የዘለዓለም ፍሥሐ አለ።
የሰውን ሥራ አፌ እንዳይናገር ፈቃዴ ነው፥ ስለ ከንፈሮችህ ቃል ጭንቅ የሆኑ መንገዶችን ጠበቅሁ። እግሮች እንዳይናወጡ አረማመዴን በመንገድህ አጽና። አቤቱ፥ ሰምተኸኛልና ወደ አንተ ጠራሁ፥ ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል፥ ቃሌንም ስማ! ቸርነትህን ድንቅ አድርገህ ግለጠው። እንደ ዐይን ብሌን ጠብቀኝ፥ በክንፎችህ ጥላ ሰውረኝ እኔ ግን በጽድቅ ፊትህን አያለሁ፥ ክብርህን ሳይ እጠግባለሁ። አቤቱ ጉልበቴ ሆይ፥ እወድድሃለሁ። ጌታ ዓለቴ፥ አምባዬ፥ መድኃኒቴ፥ አምላኬ፥ በእርሱም የምተማመንበት ዓለቴ፥ ጋሻዬ፥ የደኅንነቴ ቀንድ መጠጊያዬም ነው። ምስጋና የሚገባውን ጌታን እጠራለሁ፥ አቤቱ ጉልበቴ ሆይ፥ እወድድሃለሁ። አሜን!
የዐቢይ ጾም አስተውሎት (Journal)
በዚህ በአብይ ጾም በየዕለቱ የጸሎት ሐሳቦችን እና አስተውሎቶችን መጻፍ ለተሻለ መንፈሳዊ ሕይወት ያግዛል። እውነተኛ የቀን ውሎ አስተውሎት እና የጸሎት ሐሳብን በነጻነት በማስፈር ለነፍስ ዕድል መስጠት በመንፈሳዊ ሕይወት መሰረታዊ ቁም ነገር ነው። ከዚህ በታች የቀረቡት ጥያቄዎችን ለራስ ውሎ በሚስማማ ሁኔታ በማስተካከል አስተውሎትን መጻፍ ይቻላል።
- ከሰዎች ጋር ስነጋገር ፊታቸውን አተኩሬ እመለከታለሁ?
- በሰዎች ፊት ስሆን ይህ መልክ የከበረ የእግዚአብሔር ክብር ነጸብራቅ በሆነበት ልክ አከብረዋለሁ?
- ኢየሱስ ክርስቶስ ያካፈለውን መልክ እመለከታለሁ ወይስ የወንድሜ ድካም ላይ ብቻ ያለኝ ትኩረት የጌታን መልክ ሸፍኖብኛል?
- የዐቢይ ጾም የጸጋ መሻቴ ምንድነው? የትኛው ጸጋ ዛሬ፣ አሁን እያለፍኩበት ባለሁት ሁኔታ ውስጥ በይበልጥ ያስፈልገኛል?
የተባረከ የጾም ጉዞ!
ሴሞ
ይቀጥላል...
[1] Thus, iconoclasm is not merely a heresy that affects only one aspect of the Christian faith; rather, according to the declaration of the Seventh Council, it is the sum of all heresies, as it undermines the entire economy of salvation. Unconsciously docetic (cf. PG 98,173B), it combats the reality of the Incarnation and the divinity of the Word made flesh. On the other hand, in a nominalistic manner, it includes the human aspect of the Incarnation while denying the realism of holiness, which transfigures nature (PG 94,1249). Therefore, Pope Gregory III convened a council in Rome against the iconoclasts and instituted the Feast of All Saints. Gregory IV set its date on November 1.
[2] K. Pfleger, Gott im Antlitz?, in: M. Picard, Briefe an den Freund Karl Pfleger, Zürich-Stuttgart 1958, 107.