የዐቢይ ጾም 30ኛ ቀን
- Category: የ ፵ ጾም አሰተንትኖ
- Published: Wednesday, 26 March 2025 05:45
- Written by Samson
- Hits: 120
- 26 Mar
የዐቢይ ጾም 30ኛ ቀን
የሰው “ፊት” ውበት ሳይታሰብ ይረግፋል፤ ሳይጠገብ በቶሎ ያልፋል፤ “ሥጋ ሁሉ እንደ ሣር፣ ክብሩም ሁሉ እንደ ሜዳ አበባ ነውና፤ ሣሩ ይደርቃል፤ አበባውም ይረግፋል” (1ጴጥ 1፡24)። ነገር ግን በዚያ ፊት ላይ የሚንጸባረቀው የነፍስ መልክ የሰው ልጅ ከደረሰበት መከራ እና ካሳለፈው የሕይወት ውጣ ውረድ ባሻገር ጎልቶ ይታያል። ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ “ባየነው ጊዜ መልክ እና ውበት አልነበረውም፤ እንወደውም ዘንድ ደም ግባት የለውም” (ኢሳ 53፡2) ነገር ግን በመስቀል የመጨረሻው ሰዓት እንኳን እርሱነቱ ይገለጥ ዘንድ የአምላክነቱ ጠባይ በገጹ ላይ ያበራ ነበር። ስለዚህም ከትንሣኤው አስቀድሞ “ይህ በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነው” የሚል ምሥክርነት በምድር እኩሌታ መካከል ያስተጋባ ነበር። (ማቴ 27፡54) እርሱ በውጫዊ ማንነቱ የባርያን መልክ ይዞ መገለጡ፤ ነገር ግን በውስጣዊ ማንነቱ ከዛ ፍጹም በተለየ እና ሊነገር በማይችል የአምላክነት ክብሩ መኖሩ፤ ሰው ሆኖ ከተገለጠባት ቅጽበት አንስቶ በውጫዊው እና በነፍሳዊ የሰው ልጅ ማንነት መካከል የመታረቂያ ድልድይ ሆኗልና፣ የሰው ልጅ እንዲሁ በውጪ ከሚታየው ገጽታዊ ማንነቱ ባሻገር እጅግ ጥልቅ በሆነ ነፍሳዊ ማንነት በስውር በሚያየው አምላኩ ፊት መመላለስ ይችላል።[1]
ይህ የሰው ልጅ “ፊት” ገጽታ የሰውን ልጅ ውጫዊ እና ውስጣዊ መስተጋብር ከማስነበቡም ባሻገር የመጨረሻው ዘመን ፍጻሜ የሚገለጥበት መድረክም ጭምር ነው። በመጨረሻው ሰዓት በእግዚአብሔር የፍርድ ዙፋን ፊት ሰው ከእግዚአብሔር ጋር “ፊት ለፊት” ይተያያል (1ቆሮ 13፡12)፤ ይህም የሰው ልጅ ኅላዌ ፍጽምና የሚገልጥ መተያየት ነው። ቅዱሳንም “ፊቱን ያያሉ፤ ስሙም በግንባራቸው ይሆናል” (ራዕ 22፡4)። በዚህ አይነት ሐዋርያት በኢየሱስ ፊት ላይ በታቦር ተራራ የተመለከቱት፣ ቅዱሳንም እንደ በጎ ሥጦታው ልግስና በተሰጣቸው ልክ የሚያንጸባርቁት የእግዚአብሔር ደም ግባት በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት በዳኑት በሰው ልጆች ፊት ላይ ለዘላለም ይገለጣል።
ስምኦን አዲሱ ነባቤ መለኮት (The New Theologian) እንዲህ ይላል “የብርኀኑ ተካፋይ እና የክብሩ ነጸብራቅ ወራሽ እሆናለሁ። የገዛ ራሴ ፊት ከእርሱ፣ የሕይወት ዘመን ናፍቆቴ ከሆነው ፊት ብርኀን የተነሳ ያበራል። አካሌም ሁሉ ብርኀን ይሆናል፤ በዚያን ጊዜ ከውበት የሚበልጥ ውበት፣ ከኃብትም የሚበልጥ ኃብት፣ ከኃይለኞችም የሚበልጥ ኃይለኛ፣ ከዓለም ነገሥታትም በላይ የከበረ ንጉሥ፣ በዚህም ምድር ካለው እና ከሚታየው ጋር እንደ ዐይን ቅጽበት እንኳን በማይነጻጸር መልኩ፣ በሰማያት ካሉ ነገሮች ባሻገር፣ በሚበልጥ ክብር እና ምሥጋና ሁሉ በሚገባው ለጌትነቱም ፍጻሜ በሌለው በኢየሱስ ክርስቶስ ታላቅነት እገለጣለሁ”[2]። እውነተኛው የኢየሱስ ክርስቶስ ውበት በደቀ መዛሙርቱ ፊት ላይ የእርሱ የመሆናቸው ዘላለማዊ ማኅተም ሆኖ ይገለጣል፤ ሊቁ ስምኦን መደነቁን ቀጥሎ እንዲህ ይላል፡ “የምሕረቱ ውበት በእኔ ላይ ተገልጦ ይታያል፤ እኔም በእርሱ ብርኀን እበራለሁ፤ ይህንን የማይነገር ውበት እና ጸዳል በመደነቅ አሰላስላለሁ፤ ከራሴ ውጪ ቆሜ ስለራሴ ደግሞ አሰላስላለሁኝ፤ ምን እንደነበርኩኝ እና አሁን በእርሱ ምን እንደሆንኩኝ እያየሁ እደነቃለሁ። ኦ ተዓምር! ማስተዋል ራሱ ከፊት ለፊቴ ስለቆመ ማስተዋሌ ሁሉ ንቁ ነው፤ በክብር፣ በፍርሃት፣ ከፊትህ በቆምኩባት በዚያች ቅጽበት፣ ምን ማድረግ እንዳለብኝ እንኳን አላውቅም፤ ስለዚህ ፍርሃት ወደቀብኝ፤ ወዴት መሔድ እንዳለብኝ፣ ማንን ማናገር እንዳለብኝ፣ ያንተ የሆነው አካሌ ሁሉ ምን ማድረግ እንዳለበት፣ ለየትኛው ሥራ፣ ለየትኛው ተግባር ማሰማራት እንዳለብኝ አላውቅም፤ ይህ አስደናቂ የእግዚአብሔር ተዓምር በፊቴ ሆኗልና”።[3]
የእምነት ሕይወት በኢየሱስ ፊት ላይ ተገልጦ ያየነውን እውነተኛ መልካችንን የመምሰል ጉዞ ነው፤ በመሆኑም የሰው ልጅ የራሱን እውነተኛ መልክ ከኢየሱስ ክርስቶስ ፊት ላይ እያነበበ በዚያ መጠራት ልክ ይኖር ዘንድ ይጋበዛል። የሰው ልጅ በተፈጠረበት መልክ መኖሩ የእምነት ሕይወት የዕለት ተዕለት ግብ ነው። የዚህ ግብ ፍጻሜ እኛም ደግሞ የእግዚአብሔር መልክ ምሳሌ መሆናችን ነው።
የተሰቀለውን ኢየሱስን “ፊት” መመልከት የእምነት ሕይወት ምን እንደሚመስል ማስተዋል ይቻላል። የታሪክ ፍሰት መቋጫ እስኪያገኝ ድረስ ጊዜ የሚተዳደርበት መርህ “የአንድ ነገር ሞት የሌላው ነገር ልደት ነው” የሚል ነው (destructio unius formae est generatio alterius.፤[4] ይህ ሕግ በተለይ የዕደ ጥበብ ሙያ ላይ በእጅጉ ተገልጦ ይታያል፤ ቀራጺው የእንጨቱን ወይም የድንጋዩን አካል እያፈረሰ በውጡ በመጨረሻ የሚገለጥ አዲስ ምስል ይቀርጻል፤ በዚህም ሂደት የጥሬ ዕቃው አይነተኛ መልክ ተቀይሮ አሁን ለአዲስ መገለጥ ስፍራ ለቅቋል። በተመሳሳይም በእምነት ሕይወት እውነተኛ መልካችን ከራሳችን ተግባር ብቻ የሚነሳ አይደለም፤ ይልቁንም አትክልተኛው እየገረዘ በሚያጠራው ሥራ ውስጥ ተሞርዶ የክርስቶስን መልክ የሚያንጸባርቅበት የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ነው። አናጺው የእንጨቱን፣ ቀራጺው የድንጋዩን የተወሰነ ክፍል እያስወገደ እውነተኛው ቅርጽ እንዲገለጥ እንደሚያደርግ እንዲሁ፤ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በሰው ልጅ የእምነት ጉዞ አማኙን ዕለት ዕለት እየገረዘ እውነተኛውን መልኩን እስኪያገኝ ድረስ ያጠራዋል። በዚህም አማኙ እግዚአብሔርን እያወቀ እና የማይደረስበትን ምሥጢር በሕይወቱ እያሰላሰለ ወደዚህ አምላክ ያድጋል።
ቅዱስ ቦናቬንቱራ ይህንን የክርስትያናዊ እምነት ምሥጢር ሲያስረዳ እንዲህ ይላል፡- “እግዚአብሔርን ማወቅ በውስጣችን ያለውን ለባሕርያችን የማይስማማ ነገር እያስወገደ በእጅጉ የሚስማማንን መልክ ያለብሰናል”።[5] በመሆኑም ዐቢይ ጾም እግዚአብሔርን ማወቅ እና የኢየሱስ ክርስቶስን መልክ እየመሰልን ማደግን ከመንፈስ ቅዱስ ምክር የምንማርበት የጸጋ ወቅት ነው። በመሆኑም ጊዜ ወደ ማጠቃለያው ሲቃረብ በእኛ ላይ የማያስፈልገው ነገር እየተወገደ እውነተኛ መልካችን እየተገለጠ ይሄዳል። ዐቢይ ጾም በጾማችን፣ በጸሎታችን፣ በምጽዋታችን መካከል ሁሉ የመንፈስ ቅዱስን ምክር እና ትምሕርት በመስማት እና በመቀበል እግዚአብሔርን እያወቅን የምናድግበት እና እውነተኛውን መልካችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመምሰል የምንሠራበት የጸጋ ጊዜ ነው።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
የሕይወት ወንዝና የሕይወት ዛፍ
1 ከእግዚአብሔርና ከበጉ ዙፋን የሚወጣውን እንደ ብርሌ የሚያንጸባርቀውን የሕይወትን ውሃ ወንዝ አሳየኝ። 2በከተማው አደባባይዋም መካከል፥ በወንዙም ወዲያና ወዲህ፥ በየወሩ እያፈራ ዐሥራ ሁለት ፍሬ የሚሰጥ የሕይወት ዛፍ ነበረ፤ የዛፉም ቅጠሎች ለሕዝቦች መፈወሻ ነበሩ። 3ከእንግዲህም ወዲህ መርገም ከቶ አይሆንም። የእግዚአብሔርና የበጉም ዙፋን በእርሷ ውስጥ ይሆናል፤ ባርያዎቹም ያመልኩታል፤ 4ፊቱንም ያያሉ፤ ስሙም በግምባሮቻቸው ይኖራል። 5ከእንግዲህም ወዲህ ሌሊት አይሆንም፤ ጌታ አምላክም በእነርሱ ላይ ያበራላቸዋልና የመብራት ብርሃንና የፀሐይ ብርሃን አያስፈልጋቸውም፤ ከዘለዓለምም እስከ ዘለዓለም ይነግሣሉ።
ጸሎት
ጌታ ሆይ አንተን መምሰል ምን ማለት ነው? የፊትህን ገጽታ መቼ አያለሁ? አንተ እኔን እንደምትመስል እና የመልክህ ሽራፊ የእኔም መልክ ውስጥ ለዘላለም የተቀበረ ውበት መሆኑን ማሰብ እንዴት ያጽናናል?! ጌታ ሆይ መልክህን እንዳልመስል በእኔ ላይ የማያስፈልገውን ሁሉ አንተ አስወግድልኝ፤ በመንፈስ ቅዱስ እሳታዊ የሚያነጹ እጆች ውስጥ ለፍቃድህ እንደሚስማማ አድርገኝ፤ በተፈጠርኩበት እና በዳንኩበት በአንተ በራስህ መልክ አበጀኝ! አሜን!
የዐቢይ ጾም አስተውሎት (Journal)
በዚህ በአብይ ጾም በየዕለቱ የጸሎት ሐሳቦችን እና አስተውሎቶችን መጻፍ ለተሻለ መንፈሳዊ ሕይወት ያግዛል። እውነተኛ የቀን ውሎ አስተውሎት እና የጸሎት ሐሳብን በነጻነት በማስፈር ለነፍስ ዕድል መስጠት በመንፈሳዊ ሕይወት መሰረታዊ ቁም ነገር ነው። ከዚህ በታች የቀረቡት ጥያቄዎችን ለራስ ውሎ በሚስማማ ሁኔታ በማስተካከል አስተውሎትን መጻፍ ይቻላል።
- የኢየሱስ መልክ በእኔ መልክ ላይ እንዲታይ ከጌታ ምን እጠይቃለሁ?
- የጌታ መልክ በሕይወቴ የሚንጸባረቅባቸው መልኮች የትኞቹ ናቸው? የማይንጸባረቅባቸው መልኮችስ?
- የጌታ መልክ በጸሎት አስተውሎቴ ውስጥ በምን መልኩ ይታየኛል? በጌታ መልክ ላይ አስተንትኖ አድርጌ ፊቱን በዐይነ ኅሊናዬ ለመመልከት ሞክሬ አውቃለሁ?
- የዐቢይ ጾም የጸጋ መሻቴ ምንድነው? የትኛው ጸጋ ዛሬ፣ አሁን እያለፍኩበት ባለሁት ሁኔታ ውስጥ በይበልጥ ያስፈልገኛል?
የተባረከ የዐቢይ ጾም ጉዞ!
ሴሞ
ይቀጥላል...
[1] ንጽ M. Picard, Die Grenzen der Physionomik, Zürich-Leipzig 1937, 182.
[2] ንጽ Symeon the New Theologian, XVI. Hymns.
[3] ንጽ Symeon the New Theologian. II. Hymns.
[4] ንጽ Thomas von Aquin, S.th. III, q 77, a 5 c.
[5] ንጽ Bonaventura, Hex II,33.