የዐቢይ ጾም 31ኛ ቀን
- Category: የ ፵ ጾም አሰተንትኖ
- Published: Thursday, 27 March 2025 06:35
- Written by Samson
- Hits: 117
- 27 Mar
የዐቢይ ጾም 31ኛ ቀን
ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ዋጋ ሊከፍል ይችላል? የሚለው የጌታ ጥያቄ ቆም ብለን እንድናስብ ግድ ይለናል። ይህ ጥያቄ ስለ ሕይወታችን ዕጣ ፈንታ፣ ስለ ኑሯችን ትርጉም እና ስለ መንገዳችን ዓላማ የሚጠይቀን ጠንካራ ድምጽ ነው። ነፍሳችን በሰማይም ይሁን በምድር በምንም ሊተካ የማይችል የእግዚአብሔር ሥጦታ ነው፤ ነገር ግን ክርስቶስ በነፍሳችን መካከል ድምጹ ሲያስተጋባ እስኪሰማን ድረስ፣ በቤተ ክርስትያን ማኅጸን ውስጥ ጥሪውን ተቀብለን እንደገና እስክንወለድ ድረስ፣ ምሥጢራዊ እና ልዩ የሆነውን፣ ማንም በእኛ ፈንታ ሊሰጥ የማይቻለውን የነፍስ እሺታ በነጻ ፈቃድ ተዐዝዞ ለእርሱ እስከምንሰጥ ድረስ፣ ራሳችንን በእርሱ ውስጥ እስከምናገኝ ድረስ “ሰው” መሆን ማለት ምን ማለት እንደሆነ ገና አላወቅንም።
ማንነትን በክርስቶስ ማወቅ ማለት የግለሰቡን ነፍሳዊ ማንነት እና ጥልቅ ምሥጢራዊ “ሰው”ነት መድረክ ላይ አውጥተን ለመንፈሳዊ የቁንጅና ውድድር ማሰለፍ ማለት አይደለም፤ ይልቁንም ማንነትን በክርስቶስ ማወቅ ሕይወታችን ይበልጡን ከክርስቶስ ጋር የሚሰወርበት፣ መለኮታዊ ክብራችንን እና ነጻነታችንን በመገንዘብ እና በማክበር፣ የሌሎች ሰዎችን መለኮታዊ ክብር እና ነጻነት በትክክለኛ ሚዛን መመዘን መቻል ነው። ይህም ሥጋችን እና ነፍሳችን በተቀደሰበት በኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት በኩል እውነተኛውን ማንነታችንን በመመልከት ይህንን እውነተኛ ማንነት ከወንድሞቻችን እና ከእኅቶታችን ጋር በፍቅር ምሥጢር መካፈል ነው። ይህ በክርስቶስ ኢየሱስ ባለው እውነተኛ ማንነት ራስን ከሌሎች ጋር መካፈል የራስን ማንነት ክብር እና ምሥጢራዊነት ከማክበር የሚጀምር፣ የሌሎችንም ማንነት በዚሁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ባላቸው ክብር እና ነጻነት ልክ በመቀበል የሚጎለብት ክርስትያናዊ ግብረገብ ነው። በመሆኑም ክርስትያናዊ ሕይወት የራስን እውነተኛ ነፍሳዊ ማንነት እና ምሥጢራዊነት፣ እንዲሁም የባልንጀራዬን እውነተኛ ነፍሳዊ ማንነት እና ምሥጢራዊነት በአንዱ በኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት ውስጥ መመልከት፣ ማድነቅ፣ ማክበር፣ ማግኘት እና መቀበል ነው።
ይህ ክርስትያናዊ ሕይወት በእግዚአብሔር ልብ ውስጥ ለዘላለሙ የተሸሸገውን የቅድስት ሥላሴ ጥልቅ አስተንትኖ፣ የዚህ ጥልቅ አስተንትኖ የሚታይ መገለጥ የሆነውን የእያንዳንዱን ሰው ሥውር ምሥጢራዊነት፣ ግለሰባዊነት፣ “እኔ”ነት ማክበር፣ በተሰወረበት ምሥጢራዊነት ጥልቀት ልክ፣ እንዲሁም በተገለጠበት መልክ ወሰን ማወቅ ማለት ነው። ከዚህ በላይ የማይጨምር፣ ከዚህ በታች ዝቅ የማይል፣ መለኮታዊ ጨዋነት ወሰን ያበጀለት የፍጥረት ውኃ ልክ በተገለጠበት ፍጥረታዊ ክብሩ ልክ መመልከት፣ ማክበር፣ መንከባከብ እና ፈጣሪውን ማመስገን መሰረታዊ ካቶሊካዊ መንፈሳዊነት ነው።
ዐቢይ ጾም ሁሉን በልክ፣ በመጠን፣ በወሰን፣ በአግባብ፤ ማየት፣ ማድነቅ፣ ማግኘት እና መቀበል የምንለማመድበት የጸጋ ልጓም ትምሕርት ቤት ነው። ዐቢይ ጾም የፍጥረትን ተዋረድ፣ ፍጥረት ሁሉ በልኬት፣ በቁጥር፣ በወሰን፣ በመጠን፣ በክብደት የተገለጠበትን የቅድስት ሥላሴን ጥበብ የምናሰላስልበትን የነፍስ ጽሞና ገንዘባችን የምናደርግበት የምዕመናን ሁሉ ገዳማዊ ማንነታቸው ዘመን ነው። በዚህም ዐቢይ ጾም ወደ ጥንተ ተፈጥሮአችን በመመለስ ነፍሳችንን ከነክብሯ በእግዚአብሔር ፊት ዕድፍ እና ነቀፋ የሌለባት አድርጎ በሚያቀርባት በኢየሱስ ክርስቶስ እያወቅን፣ የእግዚአብሔርን ፍጥረት ሁሉ ለተፈጠረበት ዓላማ ለእግዚአብሔር እየቀደስን፣ በጥምቀት ጸጋ ትሩፋት ለእግዚአብሔር ልጆች በተሰጠ ክህነት፣ ንግሥና እና ነብይነት የምንገለጥበት የጸጋ ወቅት ነው። ዐቢይ ጾም በክርስቶስ ነፍስ ማወቅ፣ በክርስቶስ ምራቅ መዋጥ፣ በክርስቶስ ማደግ ነው። ስለዚህ አሁን ክርስቶስ በእኔ ይኖራል እንጂ ከእንግዲህ ወዲያ እኔ አልኖርም፤ አሁን በሥጋ የምኖረው በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ በማመን የምኖረው ሕይወት ነው ለማለት በመንፈስ ቅዱስ የምሰራበትን ይህንን የጸጋ ዘመን ዕለት ዕለት በቁም ነገር ልጠቀምበት ይገባኛል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ (ሚክ 7፡18-20)
18 በደልን ይቅር የሚል፥ የርስቱን ትሩፍ ዓመጽ የሚያሳልፍ እንደ አንተ ያለ አምላክ ማን ነው? ርኅራኄ ይወድዳልና ቁጣውን ለዘለዓለም አያቆይም። 19 እንደገና ይራራልናል፤ በደሎቻችንን ይረጋግጣል፥ ኃጢአታቸውን ሁሉ በባሕሩ ጥልቅ ትጥላለህ።20 ከቀድሞ ዘመን ጀምረህ ለአባቶቻችን እንደማልህላቸው እውነትን ለያዕቆብ፥ ርኅራኄን ለአብርሃም ታደርጋለህ።
ጸሎት
ጌታ ሆይ ከአንተ ውጪ ማንነት የለኝም፤ ከአንተ ውጪ ራሴንም አላውቅም! ወንጌልህ ከሚታወጅበት እና ቊርባንህ ከሚፈተትበት ማኅበር ውጪ በግሌ ምንም አይደለሁም፤ ሁለንተናዬ ባንተ መታወቅ ነው! እሥራኤል በምድረ በዳ ማረፊያ ፍለጋ ይንከራተት እንደነበር የኔም ነፍስ አንተን ትፈልጋለች፤ ክርስቶስ ሆይ አንተ የሕይወት ውኃ የምታፈልቅ ዐለታችን፣ በቊርባን ሥጋህን የምትመግበን የሕይወት ዛፍ ነህ፤ በአንተ፣ ከአንተ እና ለአንተ ብቻ የታወቅን፣ ባልንጀራችንንም በአንተ፣ ከአንተ እና ላንተ እንድናውቀው ጸጋህን ስጠን። አሜን!
የዐቢይ ጾም አስተውሎት (Journal)
በዚህ በአብይ ጾም በየዕለቱ የጸሎት ሐሳቦችን እና አስተውሎቶችን መጻፍ ለተሻለ መንፈሳዊ ሕይወት ያግዛል። እውነተኛ የቀን ውሎ አስተውሎት እና የጸሎት ሐሳብን በነጻነት በማስፈር ለነፍስ ዕድል መስጠት በመንፈሳዊ ሕይወት መሰረታዊ ቁም ነገር ነው። ከዚህ በታች የቀረቡት ጥያቄዎችን ለራስ ውሎ በሚስማማ ሁኔታ በማስተካከል አስተውሎትን መጻፍ ይቻላል።
- ስለ ነፍሴ ቤዛ ምን ያህል ዋጋ ከፍላለሁ? የሕይወቴ ክብር ዋጋው ምን ያህል ነው?
- ነፍሴን በተቤዠችበት ዋጋ ክብር እንከባከባለሁ? ሕይወቴ የተከፈለልኝን የጌታን ደም ዋጋ ያንጸባርቃል?
- የዐቢይ ጾም የጸጋ መሻቴ ምንድነው? የትኛው ጸጋ ዛሬ፣ አሁን እያለፍኩበት ባለሁት ሁኔታ ውስጥ በይበልጥ ያስፈልገኛል?
የተባረከ የዐቢይ ጾም ጉዞ!
ሴሞ