የዐቢይ ጾም 32ኛ ቀን
- Category: የ ፵ ጾም አሰተንትኖ
- Published: Friday, 28 March 2025 07:18
- Written by Samson
- Hits: 127
- 28 Mar
የዐቢይ ጾም 32ኛ ቀን
የደጉ ሳምራዊ ምሳሌ እግዚአብሔር የልቡን እውነተኛ መልክ የገለጠበት፣ ምሕረት ሥጋ ለብሶ በሰው ልጆች መካከል የተመላለሰበት፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ትረካ ሁሉ ማሰርያ ውል ነው። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ በሰራ አካላቱ የሚናገረው ይህ የእግዚአብሔር ምሕረት እንዴት ያለ ምሕረት ነው? መዝሙረኛው ዳዊት እንደዚያ የሚቀኝለት ይህ የእግዚአብሔር ምሕረት ምን አይነት ምሕረት ነው? ምሕረት የመጽሐፍ ቅዱስ ገዢ መዝሙር እና የእግዚአብሔር ቃል የወርቅ ደወል ሆኖ በትውልድ መካከል በመለኮታዊ ዜማ ፈውስን፣ ነጻነትን፣ መፈታትን፣ ሰላምን፣ እርጋታን፣ መጽናትን፣ መጽናናትን ይዘምራል።
ሔሴድ የሚለው የዕብራይስጡ ቃል ምንም እንኳን ምሕረት ተብሎ ይተርጎም እንጂ በአማርኛ ከሚያሰማው ትርጓሜ የሚገዝፍ የእግዚአብሔርን ሐቅ የተሸከመ ቃል ነው። ሔሴድ ምሕረት ብቻ ሳይሆን መታመንም ጭምር ነው። ሔሴድ ብርታት ነው፣ ሔሴድ ለእግዚአብሔር ነገር መጨከን፣ መቁረጥ ነው፤ ሔሴድ በእግዚአብሔር ጸጋ ከስብርባሪነት ተነስቶ ራስን ችሎ በእግር መቆም ነው፣ ሔሴድ የኃጢአትን እድፍ አስወግዶ “አብ” በሚደርብልን “የወልድ” የጸጋ ካባ “በመንፈስ ቅዱስ” አብሪነት በአዲስ ውበት መገለጥ ነው። ሔሴድ በሁሉ ነገር በእኛ ላይ ተስፋ የማይቆርጠው “የአብ” ልብ እያንዳንዳችንን ከሞት ወደ ሕይወት የጠራበት “ቃል” እና እያንዳንዳችንን በአዲስ ኪዳን ማንነት ከኃጢአት ሞት ያነቃበትን “እስትንፋስ” እፍ ያለበት “ሕይወት” ነው።
ሔሴድ እግዚአብሔር በእኛ ተስፋ ያለመቁረጡ ማኅተም እና እኛም በራሳችን ላይ ተስፋ እንዳንቆርጥ ከገባንበት ሰርጥ ይልቅ የሚጠልቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ከእኛ ጋር የመሆኑ ምስክር ነው። ትልቁ ኃጢአት በእግዚአብሔር ምሕረት ተስፋ መቁረጥ ነው! እግዚአብሔር በእኔ ተስፋ ካልቆረጠ፣ በሞት እና በሕይወት መካከል በቆምኩበት ነገር እንኳን እኔ በራሴ ላይ ተስፋ ለመቁረጥ ምክኒያት የለኝም። የሞተልኝ ተስፋ የማይቆርጥብኝ ሠርክ አዲስ ወዳጄ ከሆነ እኔ ለምን እሞትበታለሁ? እርሱ በእኔ ተስፋ እያደረገ እኔ እንዴት በእርሱ ተስፋ እቆርጣለሁ? መዝሙረኛው ዳዊት ይህንን የሕይወት መንታ መንገድ በራሱ ዘመን እየታዘበ “በእሳት እና በውኃ መካከል አሳለፍከን” በማለት የሕይወትን መንታ ገጽታ ከተናገረ በኋላ፣ በሆነውም ባልሆነውም ነገር ውስጥ ጌታ ከእርሱ ጋር እንደነበር ከመሰከረ በኋላ ምን እንደመጣ ሲናገር “ወደ በረከትም አወጣኸን” (መዝ 66፡12) ይላል። በእሳትም፣ በውኃም መካከል ከእርሱ ጋር ያለፍንባቸው የሕይወታችን ገጠመኞች እርሱ በእኛ ተስፋ እንደማይቆርጥ የሚመሰክሩልን እና “እግዚአብሔር አይጥልም” የሚል ወንጌል የሚሰብኩን የገዛ ራሳችን የሕይወት ተመክሮዎች ናቸው።
እግዚአብሔር የምሕረት አምላክ ነው፤ በዚህ ማንነቱ አይጸጸትም፤ የትኛውም ኃጢአት የእግዚአብሔርን ምሕረት የሚገዳደር ኃይል የለውም፤ የእግዚአብሔር ምሕረት የልጁ ደም ፍትሕ ነው፤ የእግዚአብሔር ምሕረት ልጁ የተዋረደበት ደመወዝ ነው። ስለዚህም “ኃጢአታችሁ እንደ ዐለላ ቢቀላ እንደ በረዶ ይነጣል፤ እንደ ደም ቢቀላ እንደ ባዘቶ ነጭ ይሆናል” (ኢሳ 1፡18)። ከእግዚአብሔር ምሕረት የሚጠልቅ የምንወድቅበት ነገር የለም፤ በኃጢአት ከምንወድቅበት ውርደት ይልቅ በእግዚአብሔር ምሕረት የምንታደስበት ክብር ልክ የለውም። እግዚአብሔር ሲሰጥ አይሰፍርም፤ እግዚአብሔር ሲምር አይቆጥርም፤ እግዚአብሔር ይቅር ሲል ገደብ የለውም።
ዐቢይ ጾም ይህንን የእግዚአብሔርን ምሕረት መቀበል የምንለማመድበት የጸጋ ወቅት ነው። ዐቢይ ጾም ለእግዚአብሔር ምሕረት ልባችንን ያለገደብ የምንከፍትበት፣ በቁስላችን ሳናፍር በጌታ እቅፍ ውስጥ ራሳችንን ለመጣል የምንዘጋጅበት፣ የፈውስ፣ የነጻነት፣ የመፈታት፣ የእረፍት፣ የሰላም፣ የእውነተኛ ሳቅ ዘመን ነው። ወዳጄ ራስህን መጣል ካለብህ እግዚአብሔር ላይ ጣል። መውደቅ ካለብህ እግዚአብሔር ላይ ውደቅ፣ ተስፋ መቁረጥ ካለብህ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርገህ ሁኔታው ላይ ተስፋ ቁረጥ። ዐቢይ ጾም ይህንን የመንፈሳዊ ሕይወት ኑሮ በዘዴ የምንማርበት የጸጋ ጊዜ ነው።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ (ሉቃስ 10፡ 30-38)
“ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ፦ “አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ወረደ፤ በወንበዴዎችም እጅ ወደቀ፤ እነርሱም ደግሞ ገፈፉት፤ ደበደቡትም፤ በሕይወትና በሞት መካከልም ትተውት ሄዱ። እንደ አጋጣሚም አንድ ካህን በዚያ መንገድ ወረደ፤ አይቶትም ገለል ብሎ አለፈ። እንዲሁም ደግሞ አንድ ሌዋዊ ወደዚያ ስፍራ መጣና አይቶት ገለል ብሎ አለፈ። አንድ ሳምራዊ ግን በጉዞ ላይ ሳለ እርሱ ወደ ነበረበት መጣ አይቶትም አዘነለት፤ ቀርቦም ዘይትና የወይን ጠጅ በቁስሎቹ ላይ አፍስሶ አሰራቸው፤ በራሱ አህያም ላይ አስቀምጦት ወደ እንግዶች ማደሪያ ወሰደው፤ ተንከባከበውም። በማግሥቱም ሁለት ዲናር አውጥቶ ለእንግዳ ማደሪያው ባለቤት ሰጠና፦ ‘ተንከባከበው፤ ከዚህም በላይ የምታወጣውን ወጪ ሁሉ እኔ ስመለስ እከፍልሃለሁ፤’ አለው። እንግዲህ ከነዚህ ከሦስቱ በወንበዴዎች እጅ ለወደቀው ሰው ባልንጀራ የሆነው ማንኛው ይመስልሃል?” እርሱም፦ “ምሕረት ያደረገለት፤” አለ። ኢየሱስም፦ “ሂድ አንተም እንዲሁ አድርግ!” አለው”።
ጸሎት
ጌታ ሆይ እንደምወደድ ከማወቄ አስቀድመህ ወደድከኝ! ብዙ ምሕረት ባደረጉልኝ ሰዎች ይቅር የማለት ኃይል የፈወስከኝ ዘላለማዊ ይቅርታዬ ሆይ አመሰግንሃለሁ! ኢየሱስ የእኔ ዘላለማዊ ይቅርታ! በብዙ ሰዎች በኩል አፈቀርከኝ፣ መከርከኝ፣ አጽናናኸኝ፣ መራኸኝ፣ አሳደግኸኝ፣ አስተማርከኝ። ዛሬ ስለ እያንዳንዳቸው አንተን አመሰግንሃለሁ! በአንተም ፊት እያንዳንዳቸውን እያመሰገንኩኝ በፊትህ የተቀደሰ መሥዋዕት አድርጌ አቀርባቸዋለሁ። ጌታ ሆይ ባርካቸው፣ ቀድሳቸው፣ የፊትህን ጸዳል፣ የመገኘትህን ብርኀን ሙላቸው አሜን!
የዐቢይ ጾም አስተውሎት (Journal)
በዚህ በአብይ ጾም በየዕለቱ የጸሎት ሐሳቦችን እና አስተውሎቶችን መጻፍ ለተሻለ መንፈሳዊ ሕይወት ያግዛል። እውነተኛ የቀን ውሎ አስተውሎት እና የጸሎት ሐሳብን በነጻነት በማስፈር ለነፍስ ዕድል መስጠት በመንፈሳዊ ሕይወት መሰረታዊ ቁም ነገር ነው። ከዚህ በታች የቀረቡት ጥያቄዎችን ለራስ ውሎ በሚስማማ ሁኔታ በማስተካከል አስተውሎትን መጻፍ ይቻላል።
በሕይወቴ ታማኝ የሆነልኝ ማነው?
በሕይወቴ ሁሌ ያመነብኝ፣ በእኔ ተስፋ ያልቆረጠብኝ፣ ተሰብሬ እንኳን አይዞህ ደርሰሃል ብሎ ያበረታኝ ማነው?
በሕይወቴ ሳይገባኝ ይቅርታ ያደረገልኝ፣ በደሌን ይቅር ብሎ ነውሬን የሸፈነልኝ ማነው?
ያንን ሰው አመስግኜው ይሆን? ነግሬው ይሆን? ጌታንስ ስለነዚህ ሰዎች ሥጦታ አመስግኜው ይሆን?
የዐቢይ ጾም የጸጋ መሻቴ ምንድነው? የትኛው ጸጋ ዛሬ፣ አሁን እያለፍኩበት ባለሁት ሁኔታ ውስጥ በይበልጥ ያስፈልገኛል?
የተባረከ የዐቢይ ጾም ጉዞ!
ሴሞ