Map St Joseph Cistercians

Top Panel

የዐቢይ ጾም 33ኛ ቀን

የዐቢይ ጾም 33ኛ ቀን

Lent-main-imageበጊዜ - መዳን

በኢየሱስ ክርስቶስ ሕማም ሞት እና ትንሳኤ መዳናችን ሰርክ አዲስ ኅያው የሆነ፣ ሁለንተናችንን ዘልቆ የሚያረሰርስ፣ ከእምነት በሚሆን የጸጋ ሥጦታ የሚገለጥ እውነታ ነው። መዳን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ነው! መዳን አሁን ክርስቶስ በእኔ ይኖራል እንጂ ከእንግዲህ ወዲያ እኔ አልኖርም፤ አሁን በሥጋ የምኖረው በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ በማመን የምኖረው ሕይወት ነው ማለት ነው። መዳን ኢየሱስ ክርስቶስ በእኔ ሕይወት ያለው ሕያውነት መገለጥ ነው። መዳን “ከእግዚአብሔር ዘንድ ጥበባችን፣ ጽድቃችንና ቅድስናችንም፣ ቤዛችንም በተደረገልን በክርስቶስ ኢየሱስ መሆን ነው። መዳን እርሱ በእኛ፣ እኛም ደግሞ በእርሱ መለኮታዊ ሕይወትን መኖር እና ከሌሎች ጋር ይህንኑ ሕይወት መካፈል ማለት ነው። መዳን ማለት በእግዚአብሔር ፊት ከኃጢአት ኩነኔ ነጻ ሆኖ መገኘት ማለት ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም በክርስቶስ ኢየሱስ ሕያው ሆኖ መኖር፣ ከውኃ እና ከመንፈስ ቅዱስ እንደገና መወለድ፣ በክርስቶስ አዲስ ፍጥረት ሆኖ በመንፈስ ቅዱስ ሕይወት መኖር ማለት ነው።

መዳናችን ሰርክ አዲስ ኅያው የሆነ ቁም ነገር ነው ማለት ኢየሱስ ጊዜን ገንዘቡ አድርጎ ቀድሶታል ማለት ነው። ስለዚህ ጊዜ ሁሉ የተቀደሰ እና ክርስቶስ የመዳናችንን ምሥጢር እንድንፈጽምበት የሰጠን የኅልውና ሥጦታ ነው። በመሆኑም ጊዜ መዳን ለሰው ልጆች ሁሉ አሁን እና ዛሬ የሚሆንበት የጸጋ ሥጦታ ነው። በዚህ በዐቢይ ጾም ጉዟችን የጊዜ አጠቃቀማችን ላይ ትኩረት በማድረግ ኢየሱስ ጊዜን እና ዘመንን ሁሉ እንደቀደሰ በማወቅ ጊዜን ሁሉ ለማዳን ሥራ እንድንጠቀምበት እንጋበዛለን። እነሆ የመዳን ቀን ዛሬ ነው፤ ሰዓቱም አሁን ነው።

የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ (መዝ 19)

ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፥ ጠፈርም የእጁን ሥራ ያወራል። ቀን ለቀን ንግግርን ታወጣለች፥ ሌሊትም ለሌሊት እውቀትን ትናገራለች። ንግግር የለም መናገርም የለም፥ ድምፃቸውም አይሰማም። ድምፃቸው ወደ ምድር ሁሉ፥ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ወጣ። በእነርሱም ውስጥ የፀሐይን ድንኳን አደረገ፥ እርሱም እንደ ሙሽራ ከእልፍኙ ይወጣል፥ እንደ አርበኛ በመንገዱ መሮጥ ደስ ይለዋል። አወጣጡ ከሰማያት ዳርቻ ነው፥ ዙሪቱም እስከ ዳርቻቸው ነው፥ ከትኩሳቱም የሚሰወር የለም። የጌታ ሕግ ፍጹም ነው፥ ነፍስን ይመልሳል፥ የጌታ ምስክር የታመነ ነው፥ የዋሆችን ጠቢባን ያደርጋል። የጌታ ሥርዓት ቅን ነው፥ ልብንም ደስ ያሰኛል፥ የጌታ ትእዛዝ ብሩህ ነው፥ ዓይንንም ያበራል። ጌታን መፍራት ንጹሕ ነው፥ ለዘለዓለም ይኖራል፥ የጌታ ፍርድ እውነትና ቅንነት በአንድነት ናቸው። ከወርቅና ከክቡር ዕንቁ ይልቅ ይወደዳል፥ ከማርና ከማር ወለላም ይጣፍጣል። አገልጋይህ ደግሞ ይጠብቀዋል፥ በመጠበቁም እጅግ ይጠቀማል። ስሕተትን ማን ያስተውላታል? ከተሰወረ ኃጢአት አንጻኝ። የድፍረት ኃጢአት እንዳይገዛኝ አገልጋይህን ጠብቅ፥ የዚያን ጊዜ ፍጹም እሆናለሁ፥ ከታላቁም ኃጢአት እነጻለሁ። አቤቱ፥ ዓለቴና ቤዛዬ የአፌ ቃልና የልቤ አሳብ በፊትህ ያማረ ይሁን።

ጸሎት

መንፈስ ቅዱስ ሆይ ና! የእኔን የምስኪኑን ልብ ሙላ፣ የፍቅርህንም እሳት በውስጤ አንድድ፣ የእውነተኛነት መንፈስ ሆይ በቀናች እምነት ደስ እንዳሰኝህ ብርኀንህን አድለኝ። አንተ ለእኔ ምን እንደሆንክ አሳየኝ፤ ለነፍሴም እኔ ቤዛሽ፣ መድኃኒትሽ ነኝ በላት፤ እኔ እና ነፍሴ እናደምጥህ ዘንድ ተናገር፤ ልቤ በፊትህ ነው፤ ጆሮዎቼን ወደ አንተ ድምጽ አቅጣጫ አቅናቸው፤ ፊትህን ከእኔ አትሰውር፤ አንተ ትሆንበት ዘንድ ልቤን ክፈት፤ ትኖርበት ዘንድ በውስጤ የፈረሰውን የአንተን ቅጥር አድስ አሜን!

የዐቢይ ጾም አስተውሎት (Journal)

በዚህ በአብይ ጾም በየዕለቱ የጸሎት ሐሳቦችን እና አስተውሎቶችን መጻፍ ለተሻለ መንፈሳዊ ሕይወት ያግዛል። እውነተኛ የቀን ውሎ አስተውሎት እና የጸሎት ሐሳብን በነጻነት በማስፈር ለነፍስ ዕድል መስጠት በመንፈሳዊ ሕይወት መሰረታዊ ቁም ነገር ነው። ከዚህ በታች የቀረቡት ጥያቄዎችን ለራስ ውሎ በሚስማማ ሁኔታ በማስተካከል አስተውሎትን መጻፍ ይቻላል።

  1. አብዛኛውን ጊዜዬን የሚወስድብኝ ነገር ምንድነው?
  2. አብዛኛውን ጊዜዬን ከማን ጋር ነው የማሳልፈው?
  3. አብዛኛውን ጊዜዬን በምንድን ነው የማሳልፈው?
  4. በቂ ጊዜ ያልሰጠሁት ነገር ግን ጊዜ የሚገባው ነገር ምንድን ነው?
  5. የዐቢይ ጾም የጸጋ መሻቴ ምንድነው? የትኛው ጸጋ ዛሬ፣ አሁን እያለፍኩበት ባለሁት ሁኔታ ውስጥ በይበልጥ ያስፈልገኛል?

የተባረከ የዐቢይ ጾም ጉዞ!

ሴሞ

 

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።