የዐቢይ ጾም 35ኛ ቀን
- Category: የ ፵ ጾም አሰተንትኖ
- Published: Monday, 31 March 2025 06:22
- Written by Samson
- Hits: 140
- 31 Mar
የዐቢይ ጾም 35ኛ ቀን
ይቅርታ በጥልቅ ስብራት መካከል የሚያብብ የእግዚአብሔር ፍቅር መገለጥ ነው። ጌታ “አባታችን ሆይ” የሚለውን ጸሎት ለደቀ መዛሙርቱ ሲያስተምር “እኛ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በልልን” እያለ የእኛን እና የእግዚአብሔርን ይቅርታ ትይዩ መስመር ላይ ያስቀምጠዋል። በመሰረቱ ይህንን ጸሎት በልማድ፣ በቃል ስለምናውቀው እና ስለምንጸልየው እንጂ ቆም ብለን ብናስተውል የእኛ ይቅርታ ከእግዚአብሔር ይቅርታ ጋር ትይዩ ሆኖ ተቀምጧል። በማቴዎስ ወንጌል የተከተበው ይህ የጌታ ጸሎት መደምደሚያ “የሰዎችን በደል ይቅር ብትሉ፥ የሰማዩ አባታችሁ ይቅር ይላችኋል፤ ሰዎችን ይቅር ባትሉ ግን፥ አባታችሁም በደላችሁን ይቅር አይላችሁም” (ማቴ 6፡15) የሚል ነው። ጌታ ጸሎት እንዲያስተምራቸው ለጠየቁት ደቀ መዛሙርት ጸሎት ካስተማረ በኋላ በቀጥታ ይቅርታ እና ምሕረት ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት የምናደርግበት ክርስትያናዊ ማንነት መሆኑን ያመላክታል። ይቅርታ ማድረግ የእግዚአብሔር የመሆናችን መታወቂያ ነው።
በመሰረቱ እግዚአብሔር ልጁን የከፈለበትን ምሕረት እኔ በምን ዋጋ ነው ደረሰኙን አጭበርብሬ ለወንደሜ እና ለእኅቴ ይቅርታ አላደርግም የምለው? እርሱ በከፈለው ደረሰኝ እኔ በምን ሥልጣን ነው ፈቃጅ እና ከልካይ የምሆነው? እግዚአብሔር ይቅር ያለውን የምትኮንን አንተ ማን ነህ? እግዚአብሔር “ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን የሚወድ አምላክ ነው”! በምሕረት ውስጥ በሰው ልጆች መካከል የእግዚአብሔር ልብ ሲመታ ይሰማል። የእግዚአብሔር ልብ በእያንዳንዱ ምቱ የሚረጨው ደም ምሕረት ነው። ቅዱስ ጳውሎስ “እኛ የክርስቶስ ልብ አለን” (1ቆሮ 2፡16) እያለ የማንነታችንን ጥግ ያሳየናል። ክርስትና ምሕረት ነው ወይም ክርስትና አይደለም!
አማኞች በአንዱ በክርስቶስ ኢየሱስ ላይ ባላቸው እምነት እና በእርሱም አካል ውስጥ ባላቸው አንድነት እግዚአብሔር በምድር ላይ ተገልጦ የሚታይባት የአማኞች ኅብረት የሆነችው ቤተ ክርስትያን የምትገለጥ ከሆነ፤ ቤተ ክርስትያን መለኮታዊ እና ሰብዓዊ መልክ አላት ማለት ነው። በሰብዓዊ መልኳ ቤተ ክርስትያን የአማኞች ኅብረት እንደመሆኗ መጠን በአማኞች መካከል ሰው እንደመሆናቸው መጠን አለመግባባቶች፣ ቅራኔዎች፣ ጠብ እና ክርክር መኖሩ የማይካድ ሐቅ ነው። በመሆኑም ቤተ ክርስትያን የእግዚአብሔር በሕዝቡ መካከል መገለጥ መሆኗን በሚገባ ለመመስከር ከምንም በላይ በአማኞች መካከል ያለው የዕርቅ፣ የይቅርታ እና የምሕረት ዝግጁነት እጅግ ወሳኝ ቁም ነገር ነው። ነገር ግን ይህ ቁም ነገር እያንዳንዱ አማኝ በግሉ እና በውስጡ ከጌታ ጋር የሚጨርሰው ግለሰባዊ ቁም ነገር ሳይሆን ይልቁንም በቤተ ክርስትያን መካከል ሊኖር የሚያስፈልገው ይቅርታ፣ ምሕረት እና ዕርቅ ክርስቶስ ኢየሱስ እኛን ከአባቱ ጋር ያስታረቀበት አይነት ነው፤ ይህም በግልጽ እና በይፋ ያለምንም ከልካይ ወደ ላይ እና ወደ ታች፣ ወደ ግራ እና ወደ ቀኝ ዕርቃኑን ተዘርግቶ የሚታይ ነው። ስለዚህ የክርስትያን ይቅርታው እና ምሕረቱ ይፋዊ ማንነቱ እንጂ በጓዳ ብቻውን የሚጨርሰው ነገር አይደለም፤ ይልቁንም በዳይ እና ተበዳይ በእግዚአብሔር ምሕረት ጸጋ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ መካከለኛነት፣ በእግዚአብሔር አብ ፊት የሚቆሙበት የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ነው።
ክርስትያኖች እርስ በእርሳቸው እንዲሁም ከሌሎች ሰዎች ጋር የሰላም አምባሳደሮች መሆናቸውን ባልገለጡበት መጠን በዓለም ውስጥ የክርስቶስ መልክ ደብዝዞ ይታያል። ጌታ ይህንን ቁም ነገር በወንጌል ስብከቱ ሲያሳስበን “እርስ በእርሳችሁ ብትዋደዱ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ” (ዮሐ 13፡35) ይላል። ነገር ግን እርስ በእርሳችን መዋደድ ሁልጊዜ ቀላል አይደለም፤ አንድነትን መጠበቅ ሁልጊዜ ቀላል አይደለም። ይሁን እንጂ የእግዚአብሔርን ምሕረት የቀመሰን፣ ይቅር የተባልን ሰዎች ስለሆንን ይቅርታ እና ምሕረት ያለውን ኃይል እናውቃለን። ስለዚህ ሰብዓዊ ድክመቶቻችን በሚያጎሉት ስፍራ በይቅርታ እና በምሕረት እርስ በእርሳችን በመቀባበል እያንዳንዱን ደግሞ በዚህ አይነት ወንድም አድርገን ከክርስቶስ ጋር በአንድነት እንቤዠዋለን።
ዐቢይ ጾም የተደረገልንን ይቅርታ እና ምሕረት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የምናስብበት፣ እግዚአብሔር ሲጠራን የነበርንበትን ስፍራ ዘወር ብለን የምናስታውስበት፣ የምሕረቱ ጸጋ እኛን የጠገነበትን የመንፈስ ቅዱስ ፈዋሽ ማጽናናት የምናሰላስልበት፣ ከእግዚአብሔር ጸጋ እና ምሕረት በስተቀር የለየልን ኃጢአተኞች መሆናችንን በእግዚአብሔር ፊት የምንታመንበት፣ ከእግዚአብሔር ጸጋ እና ሰርክ አዲስ ምሕረት በስተቀር “ቀራጮች እና ዘማውያን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በመግባት የሚቀድሙን” (ማቴ 21፡31) ምስኪኖች መሆናችንን የምንቀበልበትን ትህትና የምንማርበት እና የምንለማመድበት የጸጋ ወቅት ነው።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ (ማቴ 6፡9-15)
ስለዚህ እንዲህ ብላችሁ ጸልዩ፦ ‘በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ! ስምህ ይቀደስ፤
መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነ እንዲሁም በምድር ይሁን፤
የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን፤
እኛ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን፤ 1
ከክፉ አድነን እንጂ ወደ ፈተና አታግባን።’
የሰዎችን በደል ይቅር ብትሉ፥ የሰማዩ አባታችሁ ይቅር ይላችኋል፤
ሰዎችን ይቅር ባትሉ ግን፥ አባታችሁም በደላችሁን ይቅር አይላችሁም።
ጸሎት
‘በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ! ስምህ ይቀደስ፤
መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነ እንዲሁም በምድር ይሁን፤
የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን፤
እኛ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን፤ 1
ከክፉ አድነን እንጂ ወደ ፈተና አታግባን።’
መንግሥት፣ ኃይል እና ምሥጋና ለዘላለሙ የአንተ ነውና አሜን!
የዐቢይ ጾም አስተውሎት (Journal)
በዚህ በአብይ ጾም በየዕለቱ የጸሎት ሐሳቦችን እና አስተውሎቶችን መጻፍ ለተሻለ መንፈሳዊ ሕይወት ያግዛል። እውነተኛ የቀን ውሎ አስተውሎት እና የጸሎት ሐሳብን በነጻነት በማስፈር ለነፍስ ዕድል መስጠት በመንፈሳዊ ሕይወት መሰረታዊ ቁም ነገር ነው። ከዚህ በታች የቀረቡት ጥያቄዎችን ለራስ ውሎ በሚስማማ ሁኔታ በማስተካከል አስተውሎትን መጻፍ ይቻላል።
- ዐቢይ ጾም ይቅርታ የመጠየቅ፣ የንስሐ እና ይቅርታ የመቀበል ጥሪ ነው። ለዚህ ጥሪ በምን መልኩ ምላሽ እሰጣለሁ?
- ለራሴም ሆነ ለሌሎች ይቅርታ ማድረግ ምን ያህል ከባድ ነው? ይህንን ለማድረግ ከጌታ ምን እጠይቃለሁ?
- በዚህ ዐቢይ ጾም በይቅርታ ዘግቼው ወደ ሕይወቴ ቀጣይ ምዕራፍ መሻገር ያለብኝ ነገር የቱ ነው?
- ይቅርታ ያላደረኩለት፣ በደሉን የያዝኩበት ሰው ማን ነው? ጌታ ስለዚያ ሰው ምን ያስባል?
- የዐቢይ ጾም የጸጋ መሻቴ ምንድነው? የትኛው ጸጋ ዛሬ፣ አሁን እያለፍኩበት ባለሁት ሁኔታ ውስጥ በይበልጥ ያስፈልገኛል?
የተባረከ የዐቢይ ጾም ጉዞ!
ሴሞ