Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ዐቢይ ጾም 39ኛ ቀን 

ዐቢይ ጾም 39ኛ ቀን 

Lent-main-imageኃጢአት፣ ንስሐ፣ ተጋድሎ (ክፍል 1) 

ዛሬ የምንኖርበት ዓለም ኃጢአት ለሚባለው ነገር ጆሮ የለውም፤ የሕይወት ዑደት እና የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ሁሉ ኃጢአት የሚባል ነገር አያውቅም፤ ሁሉም ነገር የግል ጉዳይ እና የምርጫ ጉዳይ ነው። ጊዜው ኃጢአት የሚባል ጽንሰ ሐሳብ ምን እንደሆነ ለመግለጽ ቋንቋ ያጣ፣ ኃጢአት የሚወገድበት ስፍራ በመካከሉ የሌለው ከመሆኑ ባሻገር ኃጢአትን የሚገልጽበት ቋንቋም ሆነ ኃጢአት የሚወገድበት ስፍራ እንዲኖረው የማይናፍቅ ዘመን ነው።1 ኃጢአት፣ ንስሐ፣ ተጋድሎ የሚሉት ነገሮች ትርጉም ማጣት በተለይ በዘመኑ ወጣቶች ዘንድ በጉልህ ይስተዋላል። “ንስሐ ገብቼ ምንድን ነው የምለው?” የሚለው ጥያቄ በወጣቶች ዘንድ የተለመደ ነው። በምሥጢረ ንስሐ ዙርያ የሚነሱ ጥያቄዎች በአብዛኛው የምሥጢሩን ፍሬ በሕይወታችን ካለመለማመዳችን የሚነሱ ናቸው። አንዳንድ ጊዜ ከንስሐ በኋላ ቀለል አለኝ የሚሉ ንግግሮች ምናልባትም ቀለል ያለኝ ከመንበረ ኑዛዜው ቶሎ መውጣቴ ሊሆን ይችላል። ለብዙኀን ንስሐ የፈውስ ከመሆኑ ይልቅ “የፍርሃት ምሥጢር” ነው፤ ፍርሃት ጥልቅ የሆኑ መሻቶቻችን እና የሕይወት እውነታዎች ወደ ብርኀን እንዳይመጡ እና እንዳይገለጡ የሚያደርግ ኃይል ነው።  

በምዕራቡ ዓለም ባዶ የሆኑት መንበረ ኑዛዜዎች ምዕራቡ ዓለም ከአባቱ እቅፍ መውጣቱን የሚያሳብቁ ምስክሮች ናቸው። ቅዱስ ቦናቬንቱራ “ምሥጢረ ተክሊል እና ምሥጢረ ንስሐ” ከሰው ልጅ የመጀመርያ የሕይወት ቁም ነገር ጋር አብረው የተገመዱ ምሥጢራት ስለመሆናቸው ይናገራል።2 ነገር ግን ዘመናዊው ዓለም ይህንን የምሥጢራት ሁሉ ሥር ነቅሎ ሊጥል ጫፍ ደርሷል። ቤተሰብ “ፍቅር ፍቅር ነው!” የሚል አዲስ ትርጓሜ አግኝቷል፤ ንስሐ፣ ኃጢአት፣ በደል የሚሉት ቁም ነገሮች ደግሞ በተቃራኒው ለዘመናዊው ዓለም ጆሮ እንግዳ ድምጾች ሆነዋል። የሰው ልጅ ኃጢአት በእውነት ያን ያህል የሚካበድ ነው? የሰው ልጅ የታወቀ ደካማነትስ ቢሆን ይህን ያህል መጋነን ይገባዋል? የሚሉት ጥያቄዎች ዛሬ ዛሬ ያልተለመዱ ጥያቄዎች አይደሉም፤ ነገር ግን የሰው ልጅ ቤዛ የሚያስፈልገው ኃጢአተኛ መሆኑ በተካደበት በማንኛውም ጊዜ፣ ቦታ እና ሁኔታ ውስጥ የክርስትና መሰረታዊ ወንጌል ጥያቄ ውስጥ ይወድቃል።3  

በዘመናዊው ዓለም ግንዛቤ ትኩረት እና ዋጋ የሚሰጠው ጉዳይ የግለሰብ ኃጢአት ሳይሆን ይልቁንም በማሕበራዊ እና መዋቅራዊ እውነታዎች ውስጥ የሚስተዋለው ብልሹ አሰራር ነው። በመሆኑም ከወንጌል እሴቶች ወይም ከቅድስና ተጋድሎ ይልቅ ሰብዓዊነት በዘመናዊው ዓለም ውስጥ እንደ መርሕ ተደርጎ ይነገራል። በሰው ልጆች መካከል ያለው ያልተገባ ግንኙነት የብስለት እና ያለመማር ችግር እንጂ ኃጢአት ተደርጎ መወሰድ ካቆመ ሰንበትበት ብሏል። በመሆኑም ኃጢአት የሞራል ጥያቄ ከመሆኑ ይልቅ እንደ ተራ ስህተት፣ እንደ ብስለት ችግር ብቻ ተደርጎ እየተቆጠረ ኃጢአት ባለቤት አልባ፣ ከሰው ልጅ ውጪ ያለ እና ከሰው ልጅ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የሊለው ተራ አሉታዊ ተጽዕኖ ሆኖ ይነገራል።  

በዛሬው ዓለም ያለው ማኅበራዊ ሕይወት የጋራ የሚባል ቁም ነገር የሌለው፣ ገዢ ሐሳብ፣ ገዢ ግብረግብ የማይታይበት፣ የኅሊና ጥያቄን በሚመለከት እያንዳንዱ ሰው ለራሱ እንዲወስን እንጂ እንደ ማኅበረሰብ ምንም የጋራ የኅሊና ጥያቄ እና ኃላፊነት የማይወስድበት ጊዜ ላይ እንገኛለን። በቤተ ክርስትያን ሕይወት ውስጥም እንዲሁ የተለያዩ ርዕዮተ ዓለማት ጎን ለጎን የተቀመጡበት እና አንድ ወጥ የሆነ የሞራል ሕይወት የማይስተዋልበት፣ የምንሰማቸው ስብከቶች ሁሉ የሰውን ልጅ የኅሊና ጥያቄ የማይመለከቱ ይልቁንም የሰባኪውን አዝናኝ ንግግር የምንታዘብበት መድረክ ከሆነ ዋል አደር ብሏል። መልዕልተ ባሕርያዊ የሆነው የማንነታችን እውነታ እየቀጨጨ በመጣበት የሕይወት መድረክ ሁሉ ሰው የመሆናችን እውነተኛ መልክ እየከሰመ ይመጣል። ነገር ግን የቅዱስ ጳውሎስ ሕይወት ከዚህ በተቃራኒው የሰው ልጅ መልዕተ ባሕርያዊ ከሆነው መለኮታዊ ልምምድ ጋር በተገናኘበት ጊዜ “ከፈረሱ ላይ መውደቁ” የአዲስ ሕይወት፣ የአዲስ መንገድ፣ የአዲስ ታሪክ የመጀመርያ ምዕራፍ እንደሆነ ይመሰክራል።  

የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ (ሉቃ 7፡ 36-40)

ከፈሪሳውያንም አንዱ ኢየሱስን ከእርሱ ጋር እንዲበላ ለመነው፤ በፈሪሳዊው ቤትም ገብቶ በማዕድ ተቀመጠ። እነሆም፥ በዚያች ከተማ ኀጢአተኛ የነበረች አንዲት ሴት፥ በፈሪሳዊው ቤት በማዕድ እንደተቀመጠ ባወቀች ጊዜ፥ ሽቶ የሞላበት የአልባስጥሮስ ብልቃጥ አምጥታ ነበር። በስተ ኋላውም በእግሩ አጠገብ ቆማ፥ እያለቀሰች በእንባዋ እግሩን ታርስ ጀመረች፤ በራስ ጠጉርዋም ታብሰው፥ እግሩንም ትስመው፥ ሽቶም ትቀባው ነበረች። የጠራው ፈሪሳዊም አይቶ፦ “ይህ ሰው ነቢይ ቢሆን ኖሮ፥ ይህች የምትዳስሰው ሴት ማን እንደ ሆነች፥ እንዴትስ እንደ ነበረች ባወቀ ነበር፤ ኀጢአተኛ ናትና፤” ሲል በልቡ አሰበ። ኢየሱስም መልሶ፦ “ስምዖን ሆይ! አንድ የምነግርህ ነገር አለኝ፤” አለው። እርሱም፦ “መምህር ሆይ! ተናገር፤” አለ። “አንድ አበዳሪ ሁለት ተበዳሪዎች ነበሩት፤ አንዱ አምስት መቶ ዲናር ነበረበት፤ ሌላው ደግሞ አምሳ። የሚከፍሉትም ቢያጡ ለሁለቱም ዕዳቸውን ተወላቸው። እንግዲህ ከእነርሱ አብልጦ የሚወደው ማንኛው ነው?” ስምዖንም ሲመልስ፦ “ብዙ የተወለትን ይመስለኛል፤” አለ። እርሱም፦ “በትክክል ፈረድህ፤” አለው። ወደ ሴቲቱም ዘወር ብሎ ስምዖንን እንዲህ አለው፦ “ይህችን ሴት ታያለህን? እኔ ወደ ቤትህ ገባሁ፤ ውሃ እንኳ ለእግሬ አላቀረብህልኝም፤ እርሷ ግን በእንባዋ እግሬን አራሰች፤ በጠጉርዋም አበሰች። አንተ አልሳምኸኝም፤ እርሷ ግን ከገባሁ ጊዜ ጀምሮ እግሬን ከመሳም አላቋረጠችም። አንተ ራሴን ዘይት አልቀባኸኝም፤ እርሷ ግን እግሬን ሽቶ ቀባች። ስለዚህም እጅግ ወዳለችና ብዙ ኃጢአትዋ ተሰርዮላታል እልሃለሁ፤ ጥቂት ግን የሚሰረይለት ጥቂት ይወዳል።” እርሷንም፦ “ኃጢአትሽ ተሰርዮልሻል፤” አላት። ከእርሱም ጋር በማዕድ ተቀምጠው የነበሩት በልባቸው፦ “ኃጢአትን እንኳ የሚያስተሰርይ ይህ ማን ነው?” ይሉ ጀመር። ሴቲቱንም፦ “እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ፤” አላት። 

ጸሎት 

አቤቱ ኃጢአቴ በልቤ እንዳይቀልብኝ፣ በደሌንም በፊትህ እንዳላሳንስ የልቤን ትህትና ጠብቅልኝ! የበደልኩትን እንድክስ፣ ያፈረስኩትን እንዳድስ፣ ማስተዋልህን ስጠኝ። አቤቱ ለኅሊናዬ እውነተኛ ምስክር ነህና አመሰግንሃለሁ! ኅሊናዬን ለማዳመጥ የልቤን እና የአእምሮዬን መታዘዝ መንፈስ ቅዱስ ይመራ ዘንድ ራሴን ለአንተ አስገዛለሁ። አቤቱ እንደ ቸርነትህ መጠን ማረኝ፣ የቀናውንም መንፈስ በውጤ አድስ፤ አሜን!  

የዐቢይ ጾም አስተውሎት (Journal) 

በዚህ በአብይ ጾም በየዕለቱ የጸሎት ሐሳቦችን እና አስተውሎቶችን መጻፍ ለተሻለ መንፈሳዊ ሕይወት ያግዛል። እውነተኛ የቀን ውሎ አስተውሎት እና የጸሎት ሐሳብን በነጻነት በማስፈር ለነፍስ ዕድል መስጠት በመንፈሳዊ ሕይወት መሰረታዊ ቁም ነገር ነው። ከዚህ በታች የቀረቡት ጥያቄዎችን ለራስ ውሎ በሚስማማ ሁኔታ በማስተካከል አስተውሎትን መጻፍ ይቻላል። 

  1. የቀን ውሎዬ ምን እንደሚመስል የኅሊና ምርመራ አደርጋለሁ? 
  1. በማሰብ፣ በመናገር፣ በማድረግ፣ ተግባሬን ባለመፈጸም የሰራሁትን ኃጢአት በእግዚአብሔር ፊት አሰላስላለሁ? 
  1. አሥርቱን ትዕዛዛት ከፊቴ አስቀምጬ ራሴን በእነርሱ መነጽር ስመለከት እንዴት ነኝ? 
  1. የዐቢይ ጾም የጸጋ መሻቴ ምንድነው? የትኛው ጸጋ ዛሬ፣ አሁን እያለፍኩበት ባለሁት ሁኔታ ውስጥ በይበልጥ ያስፈልገኛል? 

ይቀጥላል...

የተባረከ የዐቢይ ጾም ጉዞ! 

ሴሞ 

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።