ሰሙነ ሕማማት
- Category: የ ፵ ጾም አሰተንትኖ
- Published: Tuesday, 15 April 2025 07:12
- Written by Samson
- Hits: 91
- 15 Apr
ሰሙነ ሕማማት
ፈጣሪ ቃል! ሕያው እግዚአብሔር በታሪካችን ማዕከል የማንነታችን የልብ ምት ሆኖ ኃይሉን ባልተለመደ መልኩ በኃይል አልባነት በመግለጥ ወደ ራሱ ይስበን ዘንድ በኢየሩሳሌም መካከል ይመላለሳል። ይህ ወሰን የሌለው ፍቅር እና በማንም ኃጢአት የማይዝል ምሕረት የክብር ተስፋ ወዳለው፣ ከፍጥረት ሁሉ ጋር፣ ሁሉን ወደሚያቅፍ ትንሳኤያዊ ነገ እንጓዝ ዘንድ ይጋብዘናል። ከዚህ ከማያልቀው መለኮታዊ ምንጭ የሚፈልቀው የስበት ኃይል ከተራበው፣ ከሚያለቅሰው፣ ከተናቀው እና ደም ግባት የለውም ተብሎ ከተጠላው ከኢየሱስ ልብ ውስጥ የሚነሳ የፍቅር ኃይል ነው። ይህ የፍቅር ኃይል በምድራዊ እውነታ ውስጥ ከጎደለው ነገር ይልቅ በመለኮታዊ መጋቢነት ውስጥ ባለው ሙላት የሚጽናና ሕያው እምነት ነው።
ኢየሱስ የተገለጠበት ማንነት መንግሥት ለመመስረት የሚያስቡ ኃይሎች ሁሉ በታሪክ ውስጥ ከተገለጡበት ማንነት እና መልክ የተለየ አዲስ መለኮታዊ መገለጥ ነው። ኃይል የማያሳይ ኃይለኛነት፤ በርግጥ ኃይሉን መቆጣጠር እና በትህትናው ጥልቀት የኃያልነቱን ኃይለኝነት መግለጥ የሚችል እርሱ በርግጥም ኃይል ያለው ብቻ ሳይሆን እርሱ ራሱ ሰማይ እና ምድር በቃሉ ጉልበት የጸኑበት ዘላለማዊ ኃይል ነው። ይህ ኃይል አዲስ አብሮነትን የሚያስተምር በዘር፣ በቋንቋ፣ በቀለም፣ በጾታ ወ.ዘ.ተ. ላይ ማንነቱን የሚፈልግ ሳይሆን በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ አካል ሆኖ እርስ በእርሱ በተገጠጠመ የእምነት ማኅበር የሚገለጥ፣ ሁሉን የሚያቅፍ እና ሁሉን የሚወድ አብሮነት ነው። በመሆኑም ከተቃውሞ ይልቅ ከኢየሱስ መንግሥት ጋር በመተባበር ለአዲሱ መንግሥት አእምሮን ሁሉ በመማረክ የክፋትን ኃይል እናሸንፍ ዘንድ ጌታ “ከእኔ ተማሩ፤ እኔ በልብ የዋሕ እና ትሑት ነኝ” ይላል።
ሴሞ