ስቅለት!
- Category: የ ፵ ጾም አሰተንትኖ
- Published: Friday, 18 April 2025 07:04
- Written by Samson
- Hits: 94
- 18 Apr
ስቅለት!
የቤተ መቅደሱ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች መቀደዱ የስቅለተ ዓርብ አንዱ ቀለም ነው፤ ቅዱስ ማርቆስ በወንጌሉ ይህ ክስተት የአሮጌዎቹ ሥርዐቶች መሻር ምልክት መሆኑን ያስረዳል፤ ማቴዎስ በበኩሉ የቤተ መቅደሱ መጋረጃ የዘመናት መቁጠርያ ቀመሮችን ከዋክብት የያዘ በመሆኑ የቀደመው ዘመን፣ የቀደመው ዓለም፣ ዓመተ ፍዳ መሻሩን የሚያሳይ ምልክት እንደሆነ ያስነብባል፤ ሦስቱም ወንጌላት በጌታ ስቅለት ጊዜ ምድር በሙሉ እንደጨለመች ይናገራሉ፤ ዓለምን ሁሉ የሚያበራው የጽድቅ ጸሐይ በትንሳኤው ሞትን ድል አድርጎ እስከሚነሳ ምድር በጨለማ ውስጥ ነበረች። ይህ ጨለማ በትንቢተ አሞጽ 8፡9 እግዚአብሔር ራሱ “በዚያ ቀን ጸሐይ በቀትር እንድትገባ አደርጋለሁ፤ ቀኑም በብርኀን ሳለ ምድሩን አጨልማለሁ” ሲል የተናገረው ትንቢት ፍጻሜ ነው። ይህ ጨለማ እግዚአብሔር ስለ ልጁ ሞት ያዘነበት መለኮታዊ ጸጥታ ነው። ይህ የእግዚአብሔር ኀዘን በትንቢተ ዘካርያስ 12፡10 ላይ የሚያስተጋባው ስለ በኩር ልጅ የሚሆን ኀዘን ነው።
የመሬት መንቀጥቀጥ፣ የዓለቶች መሰንጠቅ፣ የመቃብራት መከፈት ሁሉ ፍጥረት በራሱ መቆም የማይችል፤ እርስ በእርሱ የተያያዘበት፣ የተፈጠረበት እና የጸናበት ቃል በሌለበት ከመሠረቱ እንደሚናጋ የሚያሳይ ምልክት ነው። ፍጥረት ከማንነቱ ፈጽሞ እንደተናጋ፤ የእግዚአብሔር ልጅ ስቅለት ፍጥረትን ሁሉ ከመሰረቱ እንዳናወጠው መመልከት እንችላለን። አንዱ ውል ሲለቅ ሌላው እርሱን ተከትሎ ሲፈርስ እንመለከተዋለን፤ በመጀመርያ የመሬት መንቀጥቀጥ፤ በመንቀጥቀጡ ንዝረት የዓለቶች መሰንጠቅ፣ በዓለቶች መሰንጠቅ ደግሞ የመቃብራት መከፈት፣ በመቃብራት መከፈት ደግሞ በሲኦል የነበሩ ነፍሳት በኢየሱስ ሞት በኩል መንቃት እንደሆነላቸው በኋላም በትንሳኤው ከሙታን በመነሳት በኩር ሆኖ ከእርሱ ጋር ደግሞ በመቃብር የነበሩት ቅዱሳን ሁሉ ወደ ቅድስቲቱ ከተማ ወደ ኢየሩሳለም ገብተው እንደታዩ እናነባለን።
በሕማሙ፣ በሞቱ እና በትንሳኤው ከእርሱ ጋር፣ በእርሱ ስም እና በእርሱ በኩል በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ወደ አብ የምንገባበት የፋሲካችን ምሥጢር ዓለም እና ሞላዋን በሚጠቀልል ክንዱ እና ለሁሉም ግልጥ ሆኖ በሚታይ ሥጋው በመስቀል ላይ ወደ ግራ እና ወደ ቀኝ፣ ወደ ላይ እና ወደ ታች ተዘርግቷል። እነሆ ሰውየው!
መልካም የስቅለተ ዓርብ በዓል!
ሴሞ