ክርስቶስ ስለኃጢአታችን ሞተ

“በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተጻፈው ክርስቶስ ስለኃጢአታችን ሞተ”

ቅዱሳት መጻሕፍት “ጻድቅ ባርያዬ” ብሎ በሚጠራው በክርስቶስ ሞት አማካይነት ይህ መለኮታዊ የድኀነት ዕቅድ፣ የዓለም መዳን ምስጢር፣ በመሆኑ ሰዎችን ከኃጢአት ባርነት ነፃ እንደሚያወጣ ተንብየውታል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ራሱ “የተቀበለውን” የእምነት መግለጫ ሲጠቅስ “በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተጻፈው፤ ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ” ይላል፡፡ በተለይ የኢየሱስ አዳኝ ሞት ኢሳይያስ መከራ ሰለሚቀበለው ባሪያ የተናገረው ትንቢት መፈጸሙን ያረጋግጣል፡፡ በርግጥም ኢየሱስ ራሱ የሕይወቱንና የሞቱን ትርጉም መከራ ተቀባይ የእግዚአብሔር ባርያ ከመሆኑ አኳያ አስረድቷል ከትንሣኤ በኋላም በኤማሁስ መንደር ለደቀመዛሙርት፣ ቀጥሎም ለሐዋረያቱ ይህን የቅዱሳት መጻሕፍት ትርጉም አብራርቷል፡፡

“እግዚአብሔር እርሱ ስለእኛ ኃጢያት አደረገው”

በመሆኑም ቅዱስ ጴጥሮስ በመለኮታዊው የድኅነት እቅድ ውስጥ ያለውን ሐዋርያዊ እምነት እንደሚከተለው ይገልጸዋል፤ “እንደምታውቁት እናንተ ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከከንቱ ኑሮዋችሁ፣ … የዋጃችሁት ነውር እንደሌለው ንጹሕ በግ በሆነው በክርስቶስ ክቡር ደሙ ነው፡፡ እርሱ የተመረጠው ዓለም ከመፈጠሩ በፊት ሲሆን፣ አሁን በመጨረሻው ዘመን ስለእናንተ ተገልጧል፡፡” ከአዳም ኃጢአት በኃላ የሰው ልጅ ኃጢአቶች በአገልጋይነት፣ በወደቀው የሰው ዘር መልክ ልኮ፣ “እኛ ከክርስቶስ ጋር በመተባበር የእግዚአብሔር ጽድቅ እንድንሆን እግዚአብሔር ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው፡፡”

 

ኢየሱስ ኃጢአትን የሰራ ይመስል፣ ኃጢአተኛ ነህ ተብሎ አልተወቀሰም፡፡ ነገር ግን ከአብ ጋር ምንጊዜም አንድ ባደረገው ከፍቅር የመነጨ ቤዛነቱ፣ በመስቀል ላይ ሆኖ በእኛ ስም “አምላኬ! አምላኬ! ለምን ተውኸኝ? እሰከ ማለት ድረስ ኃጢአታችንን ተሸክሟል፤ “በልጁ ሞት እኛ ከእግዚአብሔር ጋር እንታረቅ ዘንድ፡፡” ከእኛ ከኃጢአተኞች ጋር ኅብረት እንዲፈጠር ያደረገው እግዚአብሔር ለአንድ ልጁ ሳይራራ ስለኛ አሳልፎ ሰጥቶታል፡፡

ክርስቶስ ስለኃጢአታችን ለአባቱ ራሱን አሳልፎ ሰጠ

የክርስቶስ መላ ሕይወት ለአብ የቀረበ መስዋዕት ነው

“የራሱን ሳይሆን የላከውን ፈቃድ ለመፈጸም ከሰማይ” የወረደው የእግዚብሔር ልጅ ወደ ዓለም በመጣ ጊዜ እንዲህ አለ “አምላኬ ሆይ እነሆ ፈቃድህን ለመፈጸም መጥቻለሁ፡፡” “በዚህም ፈቃድ መሠረት ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ በማያዳግም ሁኔታ መስዋዕት ሆኖ በመቅረቡ ምክንያት ተቀድሰናል፡፡” ሥጋ ከለበሰበት ጊዜ ጀምሮ ወልድ የአብን መለኮታዊ የድኅነት እቅድ በማዳን ተልእኮው ውስጥ አካቶአል፡፡ “የእኔ ምግብ የላከኝን ፈቃድ መፈጸምና ሥራውንም ማከናወን ነው፡፡” ኢየሱስ “ለዓለም ሁሉ ኃጢአት” የከፈለው መስዋዕት ከአብ ጋር ያለው የፍቅር አንድነት ይገልጻል፡፡ ጌታ “ሕይወቴን አሳልፌ እሰጣለሁና ስለዚህ አብ ይወደኛል፡፡” “እኔ አብን እንደምወድ ዓለም ያውቅ ዘንድ አብ ያዘዘኝን ሁሉ እፈጽማለሁ” ብሏል፡፡

 

የአባቱን የማዳን እቅድ የማሟላት ጽኑ ፍላጐት የኢየሱስን መላ ሕይወት ቃኝቷል፤ ይህ የማዳን ፍላጐት ነበር ሥጋ ለመልበሱ ዋና ምክንያት የሆነው፡፡ ኢየሱስም እንዲህ አለ “አባቴ ሆይ በዚህች አድነኝ ልበል ይህን እንዳልል ግን እኔ የመጣሁት ለዚህች የመከራ ሰዓት ነው፡፡” እንደገናም “አብ የሰጠኝን የመከራ ጽዋ አልጠጣምን” ሲል እንደጠየቀ ሁሉ፤ በመስቀል ላይ እያለም፣ “ተፈጸመ” ከማለቱ በፊት “ጠማኝ” ብሏል፡፡

“የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ”

ከኃጢአተኞች ጋር ሊያጠምቀው ከተስማማ በኋላ፣ መጥምቁ ዮሐንስ ወደ ኢየሱስ እየተመለከተ “የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ እነሆ” ሲል ተናገረ፡፡ ዮሐንስ እንዲህ በማድረጉም ኢየሱስ ራሱን ለዕርድ እንደሚነዳ ጠቦት በዝምታ ራሱን የሚያቀርብ፣ መከራ የሚቀበል አገልጋይና የብዙዎችን በኃጢአት የተሸከመ፣ በመጀመሪያው ፋሲካ የእሥራኤል ድኀነት ምልክት የሆነ የፋሲካ በግ መሆኑን አሳወቀ፡፡ መላ የክርስቶስ ሕይወት ተልእኮውን ይገልጻል፤ ይኸውም “ሰዎችን ማገልገልና ሕይወቴን ለብዙዎች ቤዛ መስጠት” ነው፡፡ ማር. 1ዐ፡18