እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

የቤተሰብ አባላት ኃላፊነቶች (ልጆችና ወላጆች)

የቤተሰብ አባላት ኃላፊነቶች (ልጆችና ወላጆች)

የልጆች ግዴታዎች

መለኮታዊው አባትነት የሰብአዊው አባትነት ምንጭ ነው፤ ለወላጆች የሚገባው ክብር መሠረትም ይህ ነው፡፡ ጐልማሶችም ሆኑ ታዲጊ ልጆች ለአባቶቻቸውና ለእናቶቻቸው ያላቸው አክብሮት የሚዳብረው ከወላጆቻቸው ጋር ከሚያዋሕዳቸው ትስስር በተወለደ ባሕርአዊ ፍቅር ነው፡፡ ይህ ከበሬታ በአምላክ የታዘዘ ነው፡፡

ለወላጆች የሚኖር አክብሮት (ታዛዥነት) ምንጭ ሕይወትን፣ ፍቅርንና ሥራቸውን በስጦታነት በማቅረብ ልጆችን በመውለድ በቁመተ-ሥጋ፣ በጥበብና በጸጋ እንዲያድጉ ላደረጉት ሰዎች የሚሰጥ ምሥጋና ነው፡፡ “በፍጹም ልቦናህ አባትህን አክብረው፤ የእናትህንም መጧን አትዘንጋ፡፡ እነርሱን ለመርዳት እንደተወለድህ አስብ፤ ስላደረጉልህ ፈንታ ምን ታደርግላቸዋለህ?” ሲራክ 7፡ 27-28

የልጅነት አክብሮት በተገራ ባህርይና ታዛዥነት ይገለጻል፡፡ “ልጄ ሆይ፣ የአባትህን ትእዛዝ ጠብቅ፣ የእናትህንም ሕግ አትተው፤ ሁልጊዜ በልብህ አኑረው፣ በአንገትህም እሰረው፡፡ ስትሄድም ይመራሃል፣ ስትተኛ የጠብቅሃል፣ ስትነሳ ያነጋግርሃል፡፡” ምሳ. 6፡ 2ዐ-22 “ባለአእምሮ ልጅ የአባቱን ተግሳጽ ይሰማል፣ ፌዘኛ ግን ተግሳጽን አይሰማም፡፡” ምሳሌ 13፡1

ልጅ በወላጆቹ ቤት በሚኖርበት ዘመን ሁሉ ወላጆቹ ለእሱ ወይም ለቤተሰቡ ጥቅም የሚነግሩትን ሁሉ በታዛዥነት መንፈስ መፈጸም አለበት፡፡ “ልጆች ሆይ ይህ ለጌታ ደስ የሚያሰኝ ነውና በሁሉ ለወላጆቻችሁ ታዘዙ፡፡” ቆላ. 3፡2ዐ ልጆች ለአስተማሪዎቻቸው ተገቢ ትእዛዛት እንዲሁም እነሱን ለማሰተዳደር አደራ ለተቀበሉ (ሞግዚቶች) ሰዎች መታዘዝ አለባቸው፡፡ ነገር ግን ልጆች እንዲሠሩ የታዘዙትን አንድ ነገር ለሥነ ምግባራዊ ሕግ የሚቃረን መሆኑን ለሕሊናቸው ከተረዱ እሱን መፈጸም የለባቸውም፡፡

ልጆች ባደጉ መጠን፣ ወደጆቻቸውን ማክበራቸውን ሊገፉበት ይገባል፡፡ በሙሉ ፈቃደኝነት የወላጆቻቸውን ፍላጐት ማስቀደም፣ የእነርሱን ምክር መጠየቅና የእነርሱን ተገቢ ተግሳጾች መቀበል አለባቸው፡፡ ልጆች በዕድሜ የተወሰነ ጊዜ ከደረሱ በኋላ ከወደጆቻቸው ቁጥጥር ሥር በመውጣታቸው የታዘዥነት ጊዜ ቢያበቃም ለወላጆቻቸው የሚኖራቸው አክብሮት ግን ለሁሌም የሚዘልቅ ነው፡፡ ይህ አክብሮት የሚመነጨው ከመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች መካከል አንዱ ከሆነው እግዚአብሔር ከመፍራት ነው፡፡

አራተኛው ትእዛዝ፣ ልጆች ከአደጉም በኋላ ቢሆን ለወላጆቻቸው ያሉባቸውን ኃላፊነቶች ያስታውሳል፡፡ ልጆች ወላጆቻቸውን በዕድሜ በገፉበት ጊዜ በሕመም ወቅት እንደሁም በብቸኛነትና በችግር ላይ በሚገኙባቸው ጊዜያት ሁሉ ቁሳዊና ሥነ ምግባራዊ ድጋፍ ሊያበረክቱላቸው ይገባል፡፡ ኢየሱስ ይህን የምሰጋና ኃላፊነት ያስታውሳል፡፡

“አባትን በልጆች ላይ አክብሮአልና፤ የእናትንም አገዛዝ በልጆቿ ላይ አክብሮአልና አባቱን የሚያከብር ልጅ ኃጢአት ይሠረይለታል፤ እናቱን የሚያከብራት ልጅ ድልብ እንደሚያደልብ ሰው ነው፡፡ አባቱን የሚያከብር ልጅ በልጁ ደስ ይለዋል፤ በለመነበትም ቀን ፈጣሪ ጸሎቱን ይሰማዋል፡፡ አባቱን የሚያከበር ልጅ ዘመኑ ይበዛለታል፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል የሚሰማ ልጅ እናቱን ያሳርፋታል፡፡” ሲራክ 3፡ 2-6 “ልጄ በእርጅናው ጊዜ አባትህን እርዳው፤ በጉልበትም ሳለ አታሳዝነው፡፡ ቢያረጅ፣ አእምሮውን ሲያጣ፣ ፈቃዱን ለመፈጸም እሺ በለው ግን እንደሚቻልህ አክብረው፤ ዋጋ በመቀበል ጊዜ አባትህን መርዳትህ አይዘነጋብህምና፡፡ ባረጀ ጊዜ አባትህን አትናቀው፡፡ አባቱን የሚጠላ ሰው የተነቀፈ ነው፤ እናቱን የሚያሳዝናት ሰው በእግዚአብሔር ዘንድ የተረገመ ነው፡፡”ሲራክ 3፡ 12-13፣16

ታዛዥነት በመላው ቤተሰባዊ ሕይወት ውስጥ መግባባትን ያዳብራል፤ በወንድማማቾችና በእህትማማቾች መካከል ያለውን ግንኙነትም ይመለከታል፡፡ ለወላጆች የሚደረግ አክብሮት ቤቱን በብርሃንና በሙቀት ይመላዋል፡፡ “የሽማግሌዎች አክሊል የልጅ ልጆች ናቸው፡፡” ምሳ. 17፡6 “በትሕትና ህሊና በየዋህነት በትእግሥትም እርስ በርሳችሁ በፍቅር ታገሡ፡፡” ኤፌ. 4፡2

ክርስቲያኖች እምነትን፣ የጥምቀት ጸጋንና በቤተ ክርስቱያን ጸንተው የሚኖሩበትን መንፈስ ለሰጡአቸው ሰዎች ልዩ ምስጋና የማቅረብ ግዴታ አለባቸው፡፡ ይህ ምስጋና የሚገባቸው ወላጆች፣ አያቶች፣ ሌሎች የቤተሰብ አባላት፣ ቆሞሶች፣ የትምህርተ ክርስቶስ መምህራንና እንዲሁም ሌሎች አብነቶች ወይም ወዳጆች ናቸው፡፡

የወላጆች ግዴታዎች

የባለትዳሮች የፍቅር ዓላማ ልጆችን በማፍራት ብቻ  ሳይሆን ስነ ምግባራዊ ትምህርትና መንፈሳዊ አስተዳደጋቸውንም ያጠቃለለ መሆን አለበት፡፡ “ወላጆች የልጆቻቸውን ትምህርት በሚመለከት ጉዳይ ያላቸው ሚና በጣም ወሳኝ በመሆኑ ይህንን በተመለከተ እነርሱን መተካት እጅጉን አዳጋች ነው፡፡” ወላጆች ልጆቻቸውን ለማስተማር የላቸው መብትና ግዴታ ፍጹምና የማይገሰስ ነው፡፡

ወላጆች ልጆቻቸውን የእግዚአብሔር ልጆች እንደሆኑ አድርገው ማየትና በሰብአዊነታቸውም ሊያከብሩአቸው ይገባል፡፡ ወላጆች በሰማይ ላለው አባት ፈቃድ እራሳቸውን ታዛዥ በማድረግ ልጆቻቸው የእግዚአብሔርን ሕግ እንዲፈጽሙ ያስተምሩአቸዋል፡፡

ወላጆች ልጆቻቸውን የማስተማር ተቀዳሚ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ወላጆች ለዚህ ኃላፊነታቸውም የሚመሰክሩት ከሁሉ በፊት ገርነት፣ ይቅርታን፣ አክብሮት፣ አመኔታንትና ከራስ ወዳድነተ የነጻ አገልግሎትን መመሪያ አድርጐ የሚኖር ቤተሰብ ሲመሰርቱ ነው፡፡ ቤት መግባራትን ለማስተማር የተመቸ ስፍራ ነው፡፡ ይህ ትምህርት የእውነተኛ የነፃነት ቅድመ ሁኔታዎች የሆኑትን ራስን የመካድ፣ ቅን የሆነ ፍርድን የመስጠትና እራስን የመቆጣጠር ብቃትን ይጠይቃል፡፡ ወላጆች ልጆቻቸውን “ቁሳዊና ባሕሪያዊ ዝንባሌዎቻቸውን መንፈሳዊ ለሆኑት” ማስገዛት ይችሉ ዘንድ የሚረዱአቸውን ትምህርቶች ሊሰጧአቸው ይገባል፡፡ ወላጆች ለልጆቻቸውን መልካም አርአያ የመሆን ከባድ ኃላፊነተ አለባቸው፡፡ ወላጆች ለጆቻቸዉን በተሻለ ሁኔታ መምራትና ጉድለታቸውን ማረም የሚችሉት ራሳቸው የፈጸሙአቸውን ጥፋቶች ለልጆቹ በብልሃት ሲያሳውቁአቸው ነው፡፡

“ልጁን የሚወድ ሰው በእሱ ይለው ዘንድ ልጁን መቅጣትን ቸል አይልም፡፡” ሲራክ 3ዐ፡ 1-2 “እናትንም አባቶች ሆይ፣ ልጆቻቸውን በጌታ ምክርና ተግሣጽ አሳድጉአቸው እንጂ አታስቆጡአቸው፡፡” ኤፌ 6፡4

ቤት የሰው ልጅ አንድነትና የወል ኃላፊነቶችን የሚማርበት የመጀመሪያ ስፍራ ነው፡፡ ወላጆች ልጆቻቸውን ሰብአዊ ሕብረተሰብን የሚያውኩ አስጊና አዋራጂ ነገሮችን የሚርቁበትን መንገድ ማስተማር አለባቸው፡፡

ለላጆች በሚስጢረ ተክሊል ጸጋ አማካኝነት ለልጆቻቸው ወንጌልን የመስበክ ኃላፊነትና ልዩ መብትን ይቀበላሉ፡፡ ወላጆች ልጆቻቸውን ከህፃንነት እድሜአቸው ጀምሮ ከእምነት ሚስጢራ ጋር እንዲፈዋወቁ ያስፈልጋል፤ ወላጆቻቸውን በማስተማር “የመጀመሪያዎቹ አብሣሪዎች” ናቸውና፡፡ ወላጆች ገና በለጋ ዕድሜ ላይ እያሉ በቤተክረስቲያን ሕይወት እንዲሳተፉ ማድረግ አለባቸው፡፡ መልካም የቤተሰብ ሕይወት ግብረገብነተና ፍቅር የሰፈነበት ሕይወት ሕያው በሆነ እምነት ጸንተን እስከ እለተ ሞታችን ድረስ እምነታችንን ተከትለን ለመኖር የሚያነሳሰ እውተነኛ ዝግጅነትን በመንፈሳችን ሊያሳድር ይችላል፡፡

በወላጆች የሚሰጥ የሃይማኖት ትምህርት ልጆች ገና ህፃናት ሳሉ መጀመር አለበት፡፡ ይህ ትምህረት ተግባራዊ የሚሆነው የቤተሰቡ አባላት በእምነት ባደጉ መጠን ለወንጌል በሚስማማ መንገድ እርስ በእርሳቸው በመተጋገዝ በሚያሳዩት ክርስቲያናዊ ሕይወት አማካኝነት ነው፡፡ ከቤተሰብ የሚቀሰም ትምህርት ክርስቶስ ስለ እምነት ከሚሰጥ አስተምህሮ ቢቀድምም  ከእሱ ጋር አብሮ ይጓዛል፣ ያበለጽገዋልም፡፡ ወላጆች ልጆቻቸውን ጸሎት እንዴት እንደሚጸለይና ጥሪንም ለይቶ ማወቅ እንደሚቻል የማስተማር ተልዕኮ አላቸው፡፡ ቁምስና ቁርባናዊ ማህበርና የክርሰቲያናዊ ቤተሰቦች ግበረ አምልኮ እምብርት ናት፡፡ ቁምስና ለልጆችና ለወላጆች ትምህርት ክርስቶስ የሚሰጥባት ስፍራ ናት፡፡

የወላጅ ደግሞ በበኩላቸው የወላጆቻቸው ቅድሰና እንዲዳብር አስተዋፅኦ ያደርጋሉ፡፡ ሁሉም እያንዳንዳቸው ለፈጸሙት ጥፋት ጠብ፣ በደልና ቸልተኝነት ባለ መታከት እርስ በርሳቸው ለጋስነት በሰፈነበት መንፈስ ይቅር መባባለ አለባቸው፡፡ የእርስ በርስ መዋደድ ይህንን ይጠይቃል፡፡ የክርስቶስ ፍቅርም የሚጠይቀው ይህንን ነው፡፡

የወላጆች አክብሮትና ፍቅር ጉልህ ሆነው የሚታዩት “ወላጆች” ለልጆቻቸው አካላዊና መንፈሳዊ እድገት የሚያስፈልገውን ሁሉ በማቅረብ ረገድ በሚያደርጉላቸው እንክብካቤና ጥንቃቄ ነው፡፡ ህፃናት በእድሜ ከፍ ባሉ መጠን ወላጆቻቸው ያው በቀድሞው አክብሮትና ፍቅር በመመራት ልጆቻቸውን አእምሮአቸውንና ነፃነታቸውን በተገቢው መንገድ እንዱጠቀሙ ያስተምሯቸዋል፡፡

ወላጆች የልጆቻቸውን ትምህርት በሚመለከት ጉዳይ ከሁሉም በፊት በኃላፊነት የሚጠየቁ እነርሱ ስለሆኑ ለእምነታቸው የማስማማ ትምህርት ቤት የመምረጥ መብት አላቸው፡፡ ይህ መብት መሰረታዊ ነው፡፡ ወላጆች ክርስቲያናዊ ትምህርትን የሚያቀላጥፉ ናቸውና የሚያከናውኑት ስራ በይበልጥ የተሳካ እንዲሆን ለዚሁ ዓላማ ስኬታማነት የሚመጥኑ ትምህርት ቤቶችን የመምረጥ ግዴታ አለባቸው፡፡ የመንግስት ባለስልጣናትም ለወላጆች መብት የመስጠትና ተጨባጭ በሆነ መንገድ ተግባራዊ የሚሆኑባቸው ሁኔታዎች የማመቻቸትና የማረጋገጥ ግዴታ አለባቸው፡፡

ልጆች ለጉርምስና በደረሱ ጊዜ ስራቸውንና ሊመሩት የሚሹትን የመምረጥ መብትና ኃላፊነት አላቸው፡፡ በዚሁ ጊዜ ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት እንደተጠበቀ ይህን ኃላፊነት ይቀበላሉ፣ በሙሉ ፈቃደኝነት ወላጆቻቸውን በመጠየቀ የእነርሱን ምክርና ሃሳብ ይቀበላሉ፡፡ ወላጆች ልጆቻቸውን ሙያን ወይም ጋብቻዊ ህይወትን በሚመለከት ጊዜ የራሳቸውን ምርጫ በሚያደርጉበት ጊዜ ተጽዕኖ ከማድረግ መቆጠብ አለባቸው፡፡ በዚህ አኳያ ልጆች በተለይ ቤተሰብን ለመመስረት በሚያቅዱበት ጊዜ ለእነርሱ አመዛዛኝ የሆነ ምክርን ከመስጠት ወላጆችን ከሚያግድ ነገር የለም፡፡

አንዳንዶቹ ወላጆቻቸውን ወይም ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን ለመርዳት ሲሉ ሙሉ ጊዜአቸውን ለሙያቸው ለመስጠት አልያም ለሌላ ለላቀ ዓላማ ለማሳለፍ ሲሉ ሚስት ሳያገቡ ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ግለሰቦች ለሰብአዊ ቤተሰብ ከፍ ያለ ጥቅም ሊያበረክቱ ይችላል፡፡

ቤተሰብና መንግሥተ ሰማያት

የቤተሰብ ትስስሮች በጣም ጠቃሚ ቢሆኑም ፍፁማን አይደሉም፡፡ ልጅ እያደገ በሄደና ሰብዓዊና መንፈሳዊ ነፃነቱ እየጐመራ በመጣ ጊዜ ከእግዚአብሔር የሚመጣለት ጥሪ ጐልቶና በርትቶ የታያል፡፡ ወላጆች በበኩላቸው ይህን ጥሪ ማክበርና ልጆቻቸው ይከተሉት ዘንድ ማበረታታት አለባቸው፡፡ ወላጆች የክርስቲያን ተቀዳሚ ጥሪ ክርስቶስን መከተል እንደሆነ መገንዘብ አለባቸው፡፡ “ከእኔ ይልቅ አባቱን ወይም እናቱን የሚወድ የእኔ ሊሆን አይገባም፤ ከእኔ ይልቅም ወንድ ልጅን ወይም ሴት ልጅን የሚወድ የእኔ ሊሆን አይገባውም፡፡” ማቴ.1ዐ፡37

የኢየሱስ ደቀ መዝሙር መሆን ማለት የእግዚአብሔር ቤተሰብ አባል በመሆን እርሱ በሚፈቅደው ሕይወት ለመኖር የሚመጣን ጥሪ መቀበል ማለት ነው፡፡ “በሰማይ ያለውን የአባቴን ፍቃድ የሚፈጽም ሁሉ ወንድሜም፣ እህቴም እናቴም እርሱ ነው፡፡” ማቴ. 12፡49

ወላጆች ጌታ ስለ መንግስተ ሰማይ ብሎ በድንግልና በመኖር በተቀደሰ ዓላማ በምንኩስና ሕይወት ወይም በክህነታዊ አገልግሎት ላይ ተሰማርቶ እርሱን እንዲከተል ከልጆቻቸው አንዱን በሚጠራበት ጊዜ ይህን ጥሪ አክብሮት፣ ደስታና ምስጋና በተሞላበት መንፈስ መቀበል አለባቸው፡፡

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት