ራስን መስጠትና 3 ዓይነት ንጽሐ ድንግልና
- Category: ፲ቱ ትእዛዛት
- Published: Monday, 09 May 2011 22:05
- Written by Super User
- Hits: 7369
- 09 May
ራስን የመስጠት አስፈላጊነት
ፍቅር የምግባራት ሁሉ ራስ ነው፡፡ በፍቅር ጥላ ስር ንጽሐ ድንግልና ሰው በስጦታነት እንደሚቀርብበት ትምህርት ቤት ይቆጠራል፡፡ የገዛ ራስን መግዛት ራስን ከመስጠት ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ ንጽሐ ድንግልና እሱን ተግባራዊ ለሚያደርገው ሰው በባልንጀራው ፊት ስለ እግዚአብሔር ታማኝነትና ርኀራኄ ምስክር ይሆን ዘንድ ያስችለዋል፡፡
ንጽሐ ድንግልና በወዳጅነት ይበልጥ ያብባል፡፡ ንጽሐ ድንግልና፣ ወዳጆቹ እንድንሆን የመረጠን ዋና በመለኮታዊ ሕይወቱ ተሳታፊዎች ያደርገን ዘንድ ፈጽሞ ራሱን አሳልፎ የሰጠ ኢየሱስን የምንከተልበትንና እሱን የምንመስልበትን መንገድ ያሳያል፡፡ ንጽሐ ድንግልና የሕያውነት ቃለ መሃላ ነው፡፡ ንጽሐ ድንግልና ከባልንጀራ ጋር በሚሆን ወዳጅነት በጐላ ሁኔታ ይገልጻል፡፡ ፆታቸው ተመሳሳይ ወይም ተቃራኒ በሆኑ ሰዎች መካከል የማዳብር ወዳጅነት ለሁሉም የላቀ ጥቅምን ያስገኛል፤ ወደመንፈሳዊ ሱታፌም ይመራል፡፡
የንጽሐ ድንግልና መልኮች
የተጠመቁ ሰዎች ሁሉ ንጽሐ ድንግልናን እንዲጠብቁ ተጠርተዋል፡፡ ክርስቲያን ሁሉ የንጽሐ ድንግልና ሁሉ አርአያ የሆነውን “ክርስቶስን ለብሷል” ገላትያ 3፡27 በክርስቶስ የሚያምኑ ሁሉ የሕይወታቸው ሁኔታ በሚፈቅደው መሠረት ንጽሕና በሰፈነበት ሕይወት እንደኖሩ ተጠርተዋል፡፡ ክርስቲያን በተጠመቀበት ዕለት ሕይወቱን በንጽሕና እንደመራ ቃል ገብቶአል፡፡
“ሰዎች ለሕይወታቸው አመቺ በሆነ መንገድ ድንግልናን ማዳበር አለባቸው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ፍጹም በሆነ መንፈስና ባልተከፋፈለ ልብ ራሳቸውን ለእግዚአብሔር ብቻ ለማስገዛት ሲሉ በድንግልና ወይም በተቀደሰ ብሕትውና ይኖራሉ፤ እንዲሁም የሥነ ምግባር ሕግ ለሰው ሁሉ የሚያዝዘውን የንጽሐ ድንግልናን ደንብ ተከትለው የሚኖሩ ያገቡ ወይም ያላገቡ ሌሎች ሰዎችም አሉ፡፡” ባለትዳሮች ጋብቻዊ ንጽሕናን ማክበር ይጠበቅባቸዋል፤ ሌሎች ደግሞ ከሩካቤ ተቆጥበው ንጽሕናን ተግባራዊ ያደርጋሉ፡፡
ንጽሐ ድንግልና ሦስት ዓይነት ነው፤
1ኛ የባልና ሚስት /የባለትዳሮች/ ንጽሕና
2ኛ ባሎቻቸው ወይም ሚስቶቻቸው የሞቱባቸው ሰዎች ንጽሕና
3ኛ የደናግል ንጽሕና ናቸው፡፡ እነኚህን እርስ በእርስ አናበላልጥም የቤተ ክርስቲያን ሥነ ሥርዓት ብልፅግና ምንጭም ይህ ነው፡፡
እጮኛሞች ከሩካቤ በመቆጠብ ንጽሐ ድንግልና እንዲጠብቁ ተጠርተዋል፡፡ እነዚህ እጮኛሞች ባለው የሙከራ ወቅት እርስ በርሳቸው ምን ያህል እንደሚከባበሩ ይገነዘባሉ፡፡ እንደሁም አንዱ ሌላውን ከእግዚአብሔር ዘንድ የመቀበል ተስፋንና የመታመንን ሥልጠና ያገኛል፡፡ እጮኛሞች የጋብቻ ፍቅር መገለጫዎችን በጋብቻቸው ወቅት ማቆየት አለባቸው፡፡ እንደዚህ በማድረጋቸውም በንጽሐ ድንግልና ለማደግ እርስ በርሳቸው ይደጋገፋሉ፡፡