ሦስተኛይቱ ትዕዛዝ
- Category: ፲ቱ ትእዛዛት
- Published: Sunday, 06 March 2011 00:10
- Written by Super User
- Hits: 4235
- 06 Mar
ሦስተኛይቱ ትዕዛዝ
የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ፡፡ ስድስት ቀን ሥራ ተግባርህንም ሁሉ አድርግ፤ ሰባተኛው ቀን ግን ለእግዚአብሔር ለአምላክህ ሰንበት ነው፡፡ በዚያን ቀን ምንም መሥራት የለብህም፡፡
1. ሰንበት /ቀዳሚት ሰንበት/
የአሠርቱ ቃላት ሦስተኛው ትእዛዝ የሰንበትን ቅድስና ያስታውሰናል፡፡ “ሰባተኛው ቀን ግን ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ሰንበት ነው” ዘጸ. 31፡15
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሰንበት ቀን ሲጠቅስ ፍጥረትን ያስታውሳል፡፡ “እግዚአብሔር በስድስት ቀን ሰማይንና ምድርን፣ ባሕርንም፣ ያለባቸውንም ሁሉ ፈጥሮ በሰባተኛው ቀን አርፏልና፣ ስለዚህ እግዚአብሔር የሰንበትን ቀን ባርኮታል፤ ቀድሶታልም፡፡” ዘጸ. 2ዐ፡11
ቅድስ መጽሐፍ በጌታ ቀን ሕዝበ እስራኤል ከግብፅ ባርነት ነፃ ስለወጣበት ቀን መታሰሲያ እንደህ ሲል ይገልጻል፤ “አንተም በግብፅ ባርያ እንደነበረህ አስብ፤ እግዚብሔር አምላክህ በጸናች እጅና በተዘረጋ ክንድ ከዚያ አወጣህ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክህ የሰንበትን ቀን ትጠብቅ ዘንድ አዘዘህ፡፡” ዘዳ. 5፡15
እግዚአብሔር ሰንበትን የማይሻር የቃል ኪዳን ምልክት ሆኖ እንዲጠበቅ በአደራ ለእስራኤል ሰጠ፡፡ ሰንበት የተቀደሰ ለእግዚአብሔር ክብር፣ ለፍጥረት ሥራውና፣ ስለእሥራኤል ስላደረገው የአዳኝነት ሥራው የተለየ ነው፡፡
የእግዚአብሔር ሥራ ለሰው አርአያ ነው፡፡ ይህም ማለት፣ እግዚአብሔር “በሰባተኛው ቀን ካረፈና ከተነፈሰ “ ሰውም “ማረፍ” አለበት፡፡ ሰንበት የሰባቱን ቀን እንቅስቃሴ እንዲቆም ስለሚያደርግ ፋታን ይሰጣል፡፡ ሰንበት የሥራ ባርነትንና ፍቅረ ንዋይን የሚቃወሙበት ዕለት ነው፡፡
ወንጌል ኢየሱስ የሰንበትን ሕግ ጥሶአል በሚል የተወነጀለባቸውን ብዙ ሁኔታዎች ይጠቅሳል፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ የዚህን ቀን ቅድስናን ከማክበር ወደ ኋላ ያለበት ጊዜ የለም፡፡ ኢየሱስ የዚህን ሕግ እውነተኛና ትክክለኛ ትርጉም የሚሰጠው እንዲህ ሲል ነው” ሰንበት ስለሰው ተፈጥሯል እንጂ ሰው ስለሰንበት አልተፈጠረም፡፡” ማር. 2፡27 ሰንበት የተሠራው ክፉ ከማድረግ ይልቅ መልካም ለማድረግ፣ ነፍስን ከመግደል ይልቅ ለማዳን ነው ሲል ኢየሱስ በርኅራኄ አውጇል፡፡ ሰንበት የምሕረቶች ጌታ ዕለት እንዲሁም አምላክ የሚከበርበት ዕለት ነው፡፡ “የሰው ልጅ ለሰንበት እንኳ ጌታዋ ነው”፡፡ማር. 2፡28
የጌታ ቀን
እግዚአብሔር የሠራት ቀን ይህች ናት፤ ሐሴትን እናድርግ፣ በእርስዋም ደሰ ይበለን፡፡ መዝ. 118፡24
የትንሣኤ ቀን፤ አዲሱ ፍጥረት
ኢየሱስ “ከሳምንቱ በመጀመሪያ ቀን” ከሙታን ተነሳ፡፡ “የመጀመሪያ ቀን” በመሆኑ ክርስቶስ ከሙታን የተነሳበት ዕለት የመጀመሪያውን ቀን ፍጥረት ያስታውሳል፡፡ ዕለቱ ከሰንበት (ቅዳሜ) ማግስት የሚመጣ ስምንተኛው ቀን በመሆኑ በክርስቶስ ትንሣኤ የተገኘው የአዲስ ፍጥረት ተምሳሌት ነው፡፡ ይህን ቀን ለክርስቲያኖች የቀኖች ሁሉ መጀመሪያ፣ የበዓላት ሁሉ መጀመሪያ፣ የጌታ ቀን “ዕለተ እግዝእነ” ሲሆን እሁድ በሚል ስያሜ ይጠራል፡፡
እኛ ሁላችን በዚሁ የፀሐይ ቀን (ሰንዴይ) እንሰባሰባለን (ከአይሁድ ሰንበት በኋላ የሚመጣ ግና ደግሞ የመጀመሪያው ቀን) ግዙፋን ነገር ከጨለማ በመለየት ዓለምን የፈጠረበት የመጀመሪያው ዕለት ነውና አዳኛችን ኢየሱስ ክርሰቶስ ከሙታን ተለይቶ የተነሳውም በዚህ ዕለት ነው፡፡
ዕለተ እሑድ፡ የቀዳሚት ሰንበት ፍፃሜ
ዕለተ እሑድ በየሳምንቱ በጊዜ ኡደት ቀድሞት ከሚመጣው ሰንበት በግልጽ ይለያል፤ በክርስቲያኖች ዘንድ የሰንበት (ቅዳሜ) ክብረ በዓል የሚተካው በዕለተ እሑድ ነው፡፡ እሑድ በክርስቶስ ፋሲካ አማካይነት የአይሁድን ሰንበት መንፈሳዊ እውነት ከፍፃሜ ከማድረስ ጋር ሰው ለወደፊቱ በእግዚአብሔር ዘንድ ስለሚያገኘው ዘለዓለማዊ እረፍት ያውጃል፡፡ በህግ ስር ሲፈፀም የነበረው አምልኮ ለክርስቶስ ሚስጢር ፈር ቀዳጅ ሲሆን በዚህ የተፈጸመውም የክርስቶስን አንዳንድ ገጽታዎች አስቀድሞ የጠቆመ ነበር፡፡
በቀድሞው ሥርዓተ-ነገር ይመሩ የነበሩ ሰዎች አዲስ ተስፋን አገኙ፤ ከእንግዲህ የሚያከብሩት ቀዳሚት ሰንበትን ሳይሆን ህይወታችን በእርሱና በሞቱ የተቀደሰችበትን የጌታን ቀን ነው፡፡
በባሕርዩ በሰው ልብ ውሰጥ የተቀረጸው ስነ-ምግባራዊ ሕግ “እግዚአብሔር ለሁሉ ላደረገው ጠቅላላ መልካም ነገር ሁሉ ምልክት” ይሆን ዘንድ፣ ውጪአዊ ግልጽና ይፋ የሆነ ደንብን ተከትሎ የሚከናወነውን አምልኮ ተግባራዊ የሚያደርገው በእሁድ ክብረ በዓል ነው፡፡ በእሑድ የሚከናወነው አምልኮ አካሄዱና መንፈሱ የወሰደው በህዝቡ ፈጣሪና መድኃኒት የሆነው ጌታን ለማመስገን በየሳምንቱ ይደረግ ከነበረው ክብረ በዓል ስለሆነ የብሉይ ኪዳን ስነ-ምግባራዊ ሕግን ከፍፃሜ ያደርሳል፡፡
የእሑድ መሥዋዕተ ቅዳሴ
በጌታ ቀን የሚከናወነው የእሑድ ክብረ በዓል እና መስዋዕተ ቅዳሴ የቤተ ክርስቲያን ሕይወት እምብርት ነው፡፡ ሐዋሪያዊው ባህል ባቆየልን መሰረት የፋሲካዊ ሚስጢር ክብረ በዓል የሚከናወንበት እሑድ የኩላዊት ቤተክርስቲያን የላቀ ቅዱስ እለት ሆኖ መከበር አለበት፡፡ እንደዚሁም
“የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት፣ ጥምቀት፣ ዕርገት፣ የክርስቶስ ሥጋና ደም በዓል፣ የእመ አምላክ ማርያም፣ ፍጹም ንፁህ የሆነው የፅንሰቷ በዓል፣ በፍልሰቷ በዓል፣ የቅዱስ ዮሴፍ በዓል፣ የቅዱሳን ሐዋርያት የጴጥሮስና ጳውሎስ በዓል እንዲሁም የሁሉም ቅዱሳን በዓላት መከበር አለባቸው፡፡”
ክርስትያኖች በአንድነት መሰባሰብን ተግባራዊ ማድረግ የጀመሩት በሐዋርያት ዘመን ነው፡፡ ወደ ዕብራውያን የተላከው መልዕክት “ዘወትር እየተገናኘን እርስ በእርሳችን እንበረታታ እንጅ አንዳንዶች ማድረግ እንደለመዱት መሰብሰባችንን አንተው፡፡” ሲል ያሳስባል፡፡
ትውፊት ሁልጊዜ ወቅታዊ የሆነ ማሳሰቢያን (ትምህርትን) ያቀርብልናል፤ እሱም ከዚህ ቀጥሎ የተመለከተው ነው፡፡ “ማልዳችሁ ወደ ቤተክርስቲያን ኑ፣ ወደ ጌታ ቅረቡ፣ ኃጢያታችሁን ተናዘዙ፣ በጸሎት ጊዜ ተጸጸቱ፣ በቅዱስ ስርዓተ አምልኮ ተሳተፋ፣ ጸሎት እስኪፈጸም ጠብቁ፤ እስኪያልቅ አትውጡ …” ከዚህ በፊት ብዙ ጊዜ እንዳልነው “ይህ ቀን ለጸሎትና ለእረፍት ይሆን ዘንድ ለእናንተ ተሰጥቷል፤ ይህ እግዚአብሔር የሰራው ቀን፣ በእርሱ ደስ ይበለን፣ ሐሴትም እናድርግ”
“በሀረገ ስብከት ሰበካዊ ክልል ውስጥ የተቋቋመው የክርስቲያን ማህበረሰብ የሚኖርባት የተወሰነች ስፍራ ቁምስና ትባላለች፡፡ ቁምስና በሀረገ ስብከቱ ጳጳሳዊ ስልጣን ስር ሆኖ እንዲያስተዳድር የነፍሳት እረኛነት ኃላፊነትን የተቀበለ ቆሞስ አላት፡፡” ቁምስና በምእመናን ሁሉ ሰንሰት ሰንበት የሚደረገው የመስዋዕተ ቅዳሴ አከባበር ለመሳተፍ የሚሰባሰቡባት ስፍራ ናት፡፡ ቁምስና ሕዝበ ክርስቲያኑ መደበኛ ስርዓተ አምልኮ ወደሚገለጽባት ሕይወት ታስገባዋለች፤ ይህ ስርዓተ አምልኮ በሚከናወንበት ክብረ በዓልም ትሰበስበዋለች፤ የክርስቶስ አዳኝ ትምህርት ታስተምራለች መልካም ስራንና ወንድማዊ ፍቅርን በመተግበር የክርስቶስን ቸርነት ታንጸባርቃለች፡፡
በቤተክርስቲያን እንደሚጸለይ አድርገህ በቤትህ መጸለይ አትችልም፤ ምክንያቱም በቤተክርስቲያን ሕዝበ እግዚአብሔር በአንድነት ተሰብስቦ በአንድ ልብ ድምጹን ወደ እግዚአብሔር ያሳርጋል፡፡ በቤተክርስቲያን ከዚህ የበለጡ ሌሎችም ነገሮች አሉ፤ እነሱም የመንፈስ ውህደት፣ የነፍሳት ስምረት፣ የፍቅር ትስስር፣ የካህናት ጸሎቶችና ምልጃዎች ናቸው፡፡
የሰንበት ግዴታ
የቤተክርስቲያን ትእዛዝ የጌታን ሕግ በትክክል ይገልጻል፡፡ “ምእመናን በእሑዶችና በቤተክርስቲያን በተወሰኑ በሌሎች የበዓላት ቀናት በቅዳሴ የመሳተፍ ግዴታ አለባቸው” “በቅዳሴ የመሳተፍ ግዴታ ተግባራዊ የሚሆነው በበዓል ቀን ወይም በበዓል ዋዜማ በየትም ስፍራ በካቶሊክ ስርዓት የሚከናወነውን ቅዳሴ ላይ በመገኘት ነው፡፡”
የሰንበቱ መስዋዕተ ቅዳሴ ለክርስቲያናዊ ተግባር መሰረታቸውና ማረጋገጫቸው ነው፡፡ ስለዚህ ምእመናን ከባድ ምክንያት ካላጋጠማቸው በስተቀር (ለምሳሌ ህመም የህፃናት እንክብካቤ) ወይም የቆሞሳቸውን ብያኔ ያገኙ ካልሆኑ በስተቀር የቤተክርስቲያን በታዘዙ ቀኖች በቅዳሴ የመሳተፍ ግዴታ አለባቸው፡፡ ሆን ብለው ይህንን ግዴታ ቸል የሚሉ ሰዎች ከባድ ኃጢአት ይፈጽማሉ፡፡
በሰንበቱ የመስዋዕተ ቅዳሴ አከባበር ጉባኤ ላይ መሳተፍ የክርስቶስና የቤተክርስቲያን ወገን የመሆን ማረጋገጫ እንዲሁም ለእነርሱ የመታመን ተጨባጭ ምስክር ነው፡፡ ይህን በመፈጸም ምእመናን በእምነትና በፍቅር ለሚሆን ሱታፌአቸው ምስክርነት ይሰጣሉ፡፡ ምእመናን በአንድነት ለእግዚአብሔር ቅድስናና ስለ ድኀነት ላላቸው ተስፋ ይመሰክራሉ፡፡ በመንፈስ ቅዱሰ መሪነት እርስ በእርሳቸው ይደጋገፋሉ፡፡
“ካህናት ባለመኖራቸው ወይም በሌላ ከባድ ምክንያት በመስዋዕተ ቅዳሴ አከባበር ላይ ለመሳተፍ የማይቻል ሲሆን ምእመናን፣ በቁምስና ቤተ ክርስቲያን ወይም በሀገረ ስብከቱ ጳጳስ በተወሰነ ቅዱስ መካን ተሰብስበው እንዲጸልዩ፣ የቅዱሳን መጻሕፍት ምንባባትንና ሌሎች መንፈሳዊ ስብከቶችን እንዲሰሙ፤ ወይም ደግሞ ተገቢ ለሆነ ጊዜ በግል ወይም ከቤተሰባቸው አባላት ጋር በመሆን ወይም ሁኔታዎች የማይፈቅዱ ከሆነ በርከት ያሉ ቤተሰቦች በአንድነት ተሰብስበው እንዲጸልዩ አደራ ይባላሉ”
የጸጋና የዕረፍት ቀን
እግዚአብሔር “ሥራውን ሁሉ ከፈጸመ በኋላ በሰባተኛው ቀን እንዳረፈ” እንዲሁም የሰው ሕይወት የሥራና የዕረፍተ ጊዜ አለው፡፡ የጌታ ቀን መደንገግ፤ “ሰዎች እንደደደሰቱግ በሚገባ እንደዝናኑ፣ እንዲሁም ቤተሰባዊ ባህላዊ፣ ማሕበራዊና መንፈሳዊ ሕይወታቸውን እንዲያዳብሩ ይረዳል፡፡”
ምእመናን በዕለተ እሑድና በቤተ ክርስቲያን እንዲከበሩ በታዘዙ ቅዱሳን ቀኖች ለእግዚአብሔር የሚገባ አምልኮን ከማቅረብ በጌታ ቀን ከሚገኝ ደስታ፣ የምሕረት ሥራዎችን ከማከናወን፣ የአእምሮና የአካል መዝናናት ከማግኘት በሚያግዱ ሥራዎች ወይም እንቀስቃሴዎች መጠመድ የለባቸውም፡፡ የቤተሰብን ችግር ለማቃለል ወይም በጣም አስፈላጊ የሆነ ማሕበራዊ አገልግሎትን ለማበርከት በሰንበት የሚፈጸም ማናቸውም ተገቢ ሥራ የእሑድን ዕረፍት በመሻር አያስጠይቅም፡፡ ሆኖም ምእመናን ችግርን ለማቃለል ተብለው የሚፈጸሙት ተግባራት ሃይማኖትን፣ የቤተሰባዊ ሕይወትንና ጤናን ወደሚጐዱ ልማዶች የሚመሩ እንዳይሆኑ መጠንቀቀ አለባቸው፡፡
የእውነት ፍቅር የተቀደሰ የመዝናናት ጊዜን ይሻል፤ የፍቅር ጥያቄ ተገቢ ሥራን ይቀበላል፡፡
ነፃ የመዝናናት ጊዜ ያላቸው ክርስቲያኖች እንደ እነሱ ፈላጐቶችና መብቶች ያሏቸውም ቢሆን ድሆችና መከረኞች ስለሆኑ በሥራ ተጠምደው የዕረፈት ጊዜ የማያገኙትን ወንድሞቻቸውን ማስታወስ አለባቸው፡፡ በክርስቲያኖች መንፈሳዊ ባህል መሠረት እሑድ መልካም ሥራን ለማከናወን፣ እንዲሁም ሕሙማንን፣ አቅመ ደካማዎችንና አረጋውያን ለማገልገል የተወሰነ ዕለት ነው፡፡ እንደዚሁም ክርስቲያኖች ዕለት እሑድን ቤተሰቦቻቸውንና ዘመዶቻቸውን በመርዳትና በመንከባከብ ይቀድሱታል፤ በሣምንቱ ቀናት ውስጥ ይህን መሰሉን ሥራ ለመሥራት አይቻላቸውምና፡፡ ዕለተ እሑድ በጥሞና የሚታሰብበት የፀጥታ ቀን ነው፤ እሑድ አእምሮ የሚጐለብትበትና ክርስቲያናዊው ውስጣዊ ሕይወት የሚዳብርበትና አስተንተኖ የሚደረግበት ቀን ነው፡፡
ሰንበታችንና በዓላትን ለመቀደስ ጠንከር የለ የጋራ ጥረትን ይጠይቃል፡ እያንዳንዱ ክርስቲያን የጌታች ቀን ከማክበር የሚያግድ አስፈላጊ የልሆነ ማንኛውም ሥራ ወይም ትእዛዝ ለሌሎች ሰዎች ከስጠት መቆጠብ አለበት፡፡ ባህላዊ እንቅስቃሴ (ለምሳሌ ስፖርት፣ ምግብ ቤቶች …) እና ለሕብረተብ ተፈላጊነት የላቸው ጉዳዮች (ሕዝባዊ አገልግሎቶች…) አንዳንድ ሰዎች እሑድ እንዲሠሩ የግድ ይላሉ፡፡ ነገር ግን እየንዳንዱ ሰው በጢ የሆነ የዕረፍት ጊዜ ይኖረው ዘንድ ማቀድ አለበት፡፡ ምእመናን አንዳንድ ጊዜ በርካታ ሰዎች በሚሳተፋባቸው መዝናኛዎች የሚከሰቱ ብጥብጦችን ለማስወገድ ትእግሥትና ፍቅር በሰፈነበት መንፈስ ከፍ ያለ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው፡፡ ኤኮኖሚን ከፍ ለማድረግ ከባድ ግፊት ቢኖርም የመንግሥት ባለሥልጣናት ለዕረፍትና ለአምልኮ የተወሰነ ጊዜ መኖሩን ለዜጐቻቸው ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ አሠሪዎችም ቢሆኑ በዚሁ ጉዳይ ላይ ለሠራተኞቻቸው ተመሳሳይ ግዴታ አለባቸው፡፡
የሃይማኖት ነፃነትንና የሁሉ የሆነ የጋራ ጥቅምን በሚመለከት ጉዳይ እሑዶችና የቤተክርስቲያን የተቀደሱ ቀኖች በሕግ ፊት በዓላት ሆነው እንዲታወቁ ጥረት ማድረግ የክርስቲያኖች ተግባር ነው፡፡ ክርስቲያኖች ጸሎትን፣ አክብሮትንና ደስታን በሚመለከት ጉዳይ በሰዎች ፊት ጉልህ ሆኖ የሚታይ አርአያነት ማሳየት አለባቸው፤ እንደሁም ትውፊቶቻቸው ለሕብረተሰቡ መንፈሳዊ ሕይወት የላቀ አስተዋጽኦ እንደሚሰጡ በመገንዘብ እነሱን በሚገባ መጠበቅ አለባቸው፡፡ የአንድ ሀገር ሕግ ወይም ሌሎች ምክንያቶች በሰንበት መሥራትን የግድ የሚሉ ቢሆን ዕለቱ እንዲያም ሆኖ እኛን “በደስታ ከተሰባሰቡት” እንድንቀላቀል የሚያደርገን “በሰማያት ወደተጻፉት የበኩራት ማኅበር” የሚያስገባን የነፃነታችን ቀን ሆኖ ሊያልፍ ይገባል፡፡
ምንጭ፡ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ
አንቀጽ 3 ከቁጥር 2168-2188