Apostolica Sedes Vacans
- Category: ዜናዎች
- Published: Tuesday, 22 April 2025 17:37
- Written by Samson
- Hits: 1053
- 22 Apr
ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቺስኮስ ዕረፍት በኋላ መንበረ ጴጥሮስ ባዶ ነው!
የክርስቶስ እንደራሴ የሆኑት ር.ሊ.ጳ. ከዚህ ዓለም ድካም ካረፉ በኋላ አዲስ የመንበረ ጴጥሮስ ጠባቂ እስኪመረጥ ድረስ ባሉት ጊዜያት ምን ይፈጠራል?
ር.ሊ.ጳ. ፍራንቺስኮስ ሕልፈት በኋላ 1.4 ቢሊዮን ካቶሊካውያን ያለ ር.ሊ.ጳ. የጴጥሮስን መንበር ለመመልከት ይገደዳሉ። ቀጣዩ በመንበረ ጴጥሮስ የክርስቶስ እንደራሴ የቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ የሆኑት ር.ሊ.ጳ. ምርጫ ጊዜ የሚፈልግ ሂደት ነው። የዚህ ምርጫ መሪ መንፈስ ቅዱስ እንደመሆኑ መጠን የምርጫው ውጤት በዚህ ቀን ይፋ ይሆናል ብሎ መተንበይ የሚቻል አይደለም። ነገር ግን ሂደቱ ምን እንደሚመስል ከዚህ በታች እንደሚከተለው እንመለከታለን።
በካቶሊካዊት ቤተ ክርስትያን ሕገ ቀኖና መሠረት የር.ሊ.ጳ. መንበር በተወካይ የሚመራ አይደለም፤ የመንበረ ጴጥሮስ አገልግሎት በእንደራሴ አይመራም፤ ይህም ማለት የር.ሊ.ጳ. መንበር አዲስ ር.ሊ.ጳ. እስከሚመረጥ ድረስ ባዶ ሆኖ ይቆያል (Apostolica Sedes Vacans) ማለት ነው። የኢየሱስ ክርስቶስ እንደራሴ እና የቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ እስከሚመረጥ ደረስ ቤተ ክርስትያን በጸሎት እና በጽሞና የመንፈስ ቅዱስን ውሳኔ ትጠባበቃለች።
ጳጳስ የሚለው ቃል πάπας ከሚለው ከግሪኩ አቻው የተወሰደ ሲሆን ትርጓሜውም አባት የሚል ነው። ር.ሊ.ጳ. የመንበረ ሮሜ ጳጳስ እና የቫቲካን የበላይ ጠባቂ ናቸው። በተመሳሳይም Pontifex እየተባሉም ይጠራሉ ትርጓሜውም ድልድይ የሚገነባ ማለት ነው።
ባዶ መንበር (Apostolica Sedes Vacans) ማለት ምን ማለት ነው?
አዲስ ር.ሊ.ጳ. እስኪመረጥ ድረስ ያለው ጊዜ ሴዴቫካንስ ተብሎ ይጠራል፤ የዚህ ጊዜ ርዝመት እና ቆይታ ይህን ያህል ነው ተብሎ ሊገመት አይችልም። ሴዴ ቫካንስ የሚለው መግለጫ ከላቲን ቋንቋ የተገኘ ሲሆን ትርጓሜውም ባዶ መንበር ማለት ነው። ከር.ሊ.ጳ. ሕልፈት በኋላ የር.ሊ.ጳ. ሐዋርያዊ ግምጃ ጠባቂ በኩል ከሕክምና ባለሚያዎች ጋር በጋራ በመሆን ር.ሊ.ጳ. በእርግጥም ስለመሞታቸው ሦስት ጊዜ ያህል ያረጋገጣል። ር.ሊ.ጳ. መሞታቸው እውን ሆኖ ከተረጋገጠ በኋላ መንበረ ጵጵስናቸው በይፋ መገባደዱን ለማሳየት የጣት ቀለበታቸው እና ማኅተማቸው በብረት መዶሻ ተቀጥቅጦ ከጥቅም ውጪ እንዲሆኑ ይደረጋል። ከዚህ በኋላ ቢሮአቸው እና መኖርያ ቤታቸው አዲስ ር.ሊ.ጳ. እስኪመረጥ ድረስ ታሽጎ ይቆያል። በመቀጠል የር.ሊ.ጳ. ሕልፈት ለመላው ዓለም በይፋ ከታወጀ በኋላ ቤተ ክርስትያን በይፋ የዘጠኝ ቀን የኀዘን እና የጸሎት ጊዜ ትወስዳለች፤ በዚህም መካከል የር.ሊ.ጳ. ግብዓተ መሬት ይፈጸማል። ከዚህ በኋላ ዕድሜያቸው ከ 80 ዓመት በታች የሆኑ ካርዲናሎች ወደ ቅድስት መንበር በመምጣት ለኮንክሌቭ (Conclave) ይዘጋጃሉ። በዚህ የጸሎት፣ የኀዘን እና የዝግጅት ወቅት አዲስ ር.ሊ.ጳ. እስከሚመረጥ ድረስ ከመደበኛ የቤተ ክርስትያን የዕለት ተዕለት ሕይወት ባሻገር ምንም አይነት ታላላቅ ውሳኔዎች አይደረጉም። እነዚህ የቤተ ክርስትያን የዕለት ተዕለት ሕይወት እና አገልግሎቶች በካርዲናል መማክርት ጉባዔ ብጹአን ጳጳሳት የሚመሩ ይሆናል። እነዚህ ካርዲናሎች የር.ሊ.ጳ. ግብዓተ መሬት እና አዲስ ር.ሊ.ጳ. ለመምረጥ የሚደረገውን ዝግጅት በበላይነት ያስተባብራሉ።
የግብዓተ መሬት ሥርዐቱ ምን ይመስላል?
የካርዲናሎች መማክርት ጉባዔ የር.ሊ.ጳ. አስክሬን መቼ እና እንዴት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ይፋ እንደሚሆን ይወስናሉ። በዚህም የር.ሊ.ጳ. አስክሬን ለምዕመናን ይፋዊ ስንብት እና ጸሎት ክፍት ሆኖ ይቆያል። ምዕመናን መንፈሳዊ አባታቸውን በጸሎት እና በምሥጋና ይሰናበታሉ። በተለምዶ የር.ሊ.ጳ. ቀብር ከዕረፍታቸው ከአራት እስከ ዘጠኝ ቀን ባለው ጊዜ ውስጥ ይፈጸማል። ምንም እንኳን ር.ሊ.ጳ. ሲያርፉ ግብዓተ መሬታቸው በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ የሚፈጸም ቢሆንም ር.ሊ.ጳ. ፍራንቺስኮስ ግን ከዕረፍታቸው አስቀድመው በቅድስት ማርያም ታላቁ ካቴድራል ማረፍ እንደሚፈልጉ በገለጹት መሠረት ግብዓተ መሬቱ በ5ኛው ክፍለ ዘመን ከአርዮስ ክሕደት እና ከኤፌሶን ጉባዔ ውሳኔ በኋላ ለእመቤታችን ክብር በተሰራው ታላቁ የቅድስት ማርያም ካቴድራል Santa Maria Maggiore እ.ኤ.አ. በኤፕሪል 26 ቀን 2025 ዓ.ም. የሚፈጸም ይሆናል። ለዚሁ ግብዓተ መሬት የተለያዩ የሀገራት መሪዎች እና የሐይማኖት አባቶች ብሎም ሌሎች ትልልቅ እንግዶች ከዓለም ዙርያ ወደ ቅድስት መንበር እንደሚመጡ ይጠበቃል።
የር.ሊጳ. ፍራንቺስኮስ ተተኪ እንዴት ነው የሚመረጠው?
ከር.ሊ.ጳ. ዕረፍት በኋላ እስከ 20 ቀን ድረስ ዕድሜያቸው ከ80 ዓመት በታች የሆኑ ካርዲናሎች ወደ ቅድስት መንበር ይሰበሰባሉ። ከዚህ በኋላ ኮንክሌቭ ይጀመራል፤ ኮን ክሌቭ (Conclave) የሚለው ቃል ከላቲን የመጣ ሲሆን ትርጓሜውም “ከቁልፉ ጋር” ማለት ነው። በዚህም በሰስታይን ቤተ ጸሎት ካርዲናሎች ከተቀረው ዓለም ተቆራርጠው በቀን ለሁለት ጊዜ እየተገናኙ ከጸሎት እና ከአስተንትኖ ጎን ለጎን ምርጫ ያደርጋሉ። በዚህ ግዜ ሁሉ ከተቀረው ዓለም ጋር ምንም አይነት ግንኙነት አይኖራቸውም፤ ለመጀመርያ ጊዜ ከተቀረው ዓለም ጋር የሚኖራቸው ይፋዊ ግንኙነት አዲሱ ር.ሊ.ጳ. ከተመረጡ በኋላ እርሳቸውን በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለዓለም ለማቅረብ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ሰገነት በኩል በሚወጡበት ጊዜ ነው። እስከዚያው ድረስ የምርጫ ወረቀቶቹን ከልዩ ኬሚካል ጋር በማቀላቀል በሚፈጠረው ጭስ የምርጫውን ሂደት ለዓለም ያሳውቃሉ። ጥቁር ጭስ በሰስታይን ቤተ ጸሎት በኩል ከታየ ር.ሊ.ጳ. እንዳልተመረጠ የሚያሳይ ሲሆን፣ በተቃራኒው ደግሞ ነጭ ጭስ የታየ እንደሆነ አዲስ ር.ሊ.ጳ. መመረጣቸውን ለዓለም ያበስራል። ከዚህ ውጪ ከተቀረው ዓለም ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የለም፤ ይህ ጊዜ ሰዓታት፣ ቀናት፣ ሳምንታት፣ ወራት ብሎም ዓመታት ሊቆይ ይችላል። ለምሳሌ እ.ኤ.አ. በ1268 ዓ.ም. የነበረው ኮንክሌቭ ሁለት ዓመት ከዘጠኝ ወር ከሁለት ቀናት የቆየ ሲሆን ከዚህ በኋላ ር.ሊ.ጳ. ጎርጎሪዮስ 10ኛ ተመርጠዋል። ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ ር.ሊ.ጳ. ፍራንቺስኮስ በ2013 ዓ.ም. በ26 ሰዓታት በአምስት የምርጫ ዙር ነበር የተመረጡጥት። ከእርሳቸው በፊት የነበሩት ነፍሰ ኄር ር.ሊ.ጳ ቤኔዲክቶስ 16ኛ ደግሞ ከአራት ዙር በኋላ መመረጣቸውን እናስታውሳለን። ወቅታዊ በሆነው መረጃ መሰረት 138 ካርዲናሎች ቀጣዩን ር.ሊ.ጳ. ለመምረጥ በመጪዎቹ ሳምንታት በቅድስት መንበር ይሰበሰባሉ። ከምርጫው አስቀድመው የምርጫውን ነጻነት እና ምሥጢራዊነት ለመጠበቅ ካርዲናሎች ቃለ መሃላ ይፈጽማሉ። ከዚህ ቃለ መሃላ ውጪ የትኛውንም የምርጫውን ሂደት ምሥጢራዊነት አሳልፎ የሚሰጥ ካርዲናል ከቤተ ክርስትያን ተወግዞ ይለያል።
በኮንክሌቭ (Conclave) ውስጥ ምን ይከናወናል?
የር.ሊ.ጳ. ምርጫ የሚወሰነው ከካርዲናሎች ጉባዔ ሁለት ሶስተኛ አብላጫ ድምጽ ሲገኝ ነው። የመጀመርያው ዙር ምርጫ የሚከናወነው በጉባዔው የመጀመርያ ቀን ውሎ ከሰዓት በኋላ ነው። በቀጣዮቹ ቀናት ደግሞ ጠዋቱ ክፍለ ጊዜ ቅድሳሴ እና ከመንፈስ ቅዱስ ጸሎት በኋላ ሁለት ዙር ምርጫ እንዲሁም ደግሞ ከሰዓት በኋላ ሁለት ዙር ምርጫ ይከናወናል።
በእያንዳንዱ የምርጫ ወረቀት ላይ እያንዳንዱ ካርዲናል “Eligo in Summum Pontificem” እያለ ይጽፋል፤ ይህም በትርጓሜው “እኔ ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳስ መንበር ብጹዕ አቡነ... እመርጣለሁ” ማለት ነው። በዚህ አይነት የዕጩውን ስም በመጻፍ ለዚሁ ተግባር በተዘጋጀው ሳጥን ውስጥ ይጨምራል። ምርጫውን የሚያስተባብሩ ሦስት ከርዲናሎች እነዚህን ወረቀቶች አንድ በአንድ እያነበቡ የዕጩዎችን ስም በመጥራት እና ትክክለኛ መሆኑን በማረጋገጥ ር.ሊ.ጳ. ለመምረጥ አስፈላጊ የሆነው ድምጽ መገኘቱን ያረጋግጣሉ። ከዚህ በኋላ የምርጫ ወረቀቶቹ ተሰብስበው ይቃጠላሉ። ለዚሁ ተግባር ሲባል እ.ኤ.አ. ከ1939 ዓ.ም. ጀምሮ በሰስታይን ቤተ ጸሎት ውስጥ ሁለት ጭስ ማውጫዎች እና ምድጃዎች የተገጠሙ ሲሆን ር.ሊ.ጳ. ለመምረጥ የተሰበሰበው ጉባዔ አዲስ ር.ሊ.ጳ. ስለመመረጡ በዚህ መልኩ ለተቀረው ዓለም መረጃ ያጋራሉ። በሰስታይን ቤተ ጸሎት ጭስ ማውጫ በኩል የሚታየው ጭስ ጥቁር ከሆነ ር.ሊ.ጳ. ለመምረጥ የሚፈለገው ሁለት ሦስተኛ ድምጽ ገና አልተገኘም ማለት ሲሆን። ጭሱ ነጭ ከሆነ ግን አዲስ ር.ሊ.ጳ. ተመርጧል ማለት ነው። ኮንክሌቩ ረዘም ያለ ጊዜ የሚወስድ ከሆነ በመኃል ለጸሎት፣ ለአስተንትኖ እና ለምክክር ጊዜ ይወሰዳል።
ከምርጫው በኋላ እንዴት ይቀጥላል?
ምርጫው በሁለት ሶስተኛ አብላጫ ድምጽ ከተጠናቀቀ በኋላ አዲስ የተመረጡት አባት የጴጥሮስን መንበር ለመምራት ይህንን ኃላፊነት ይቀበሉ እንደሆን በይፋ ይጠየቃሉ። ኃላፊነቱን ለመበል እሺታቸውን ከገለጹ በኋላ የኢየሱስ ክርስቶስ እንደራሴ እና የቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ ሆነው በመበረ ጴጥሮስ ይሾማሉ። ቤተ ክርስትያንም በዓለም ዙርያ የበዓል ደወል በመደወል ይህንን ታላቅ የጌታ ሥጦታ በማክበር ምሥጋናዋን ታቀብርባለች። ከዚህ በኋላ ሕይወታቸው እስኪያልፍ ይህንን ሐዋርያዊ አገልግሎት ይፈጽማሉ።
አዲስ የተመረጡት ር.ሊ.ጳ. ማንነት ከቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ሰገነት በካርዲላል ዲያቆኑ በኩል ለዓለም “Habemus papam” (“አባት አግኝተናል”) ተብሎ ይታወጃል። በዚሁ አዋጅ አዲሱ ር.ሊ.ጳ. መንበረ ጵጵስናቸውን የሚመሩበት መጠርያ ስማቸው ይፋ ይሆናል። ይህ መጠርያ ስም ከመጠርያነቱ ባሻገር የር.ሊ.ጳ. መንፈሳዊነት እና ሐዋርያዊ ትኩረት ጠቋሚ ቁም ነገር ጭምር ነው። ከዚህ በኋላ አዲሱ ር.ሊ.ጳ. ከቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ሰገነት ለምድር እና ሞላዋ ሁሉ “Urbi et Orbi” ሐዋርያዊ ቡራኬያቸውን እና ሰላምታቸውን ይሰጣሉ።
ጌታ የር.ሊ.ጳ ነፍሰ ኄር ፍራንቺስኮስን ነፍስ በዘላለም ደስታ ይቀበልልን፤ በረከታቸው ትደርብን!
ሴሞ