ፈረንሳይ ውስጥ አንድ ካህን በቅዳሴ ላይ ሳሉ በአይኤስ ተገደሉ

Martyr Catholic Priest86 ዓመት እድሜያቸውም ቢሆን አገልግሎታቸው ቀጥሏል፤ መሆን ያለበትን ነገር ሁሉ በትክክል ማከናወናቸውንና የክህነት አገልግሎታቸውን ማለትም ሕፃናትን ማጥመቅ፤ መስዋዕተ ቅዳሴ ማሳረግ የቁምስና ምእመናንን በሌሎች ምስጢራት ማገልገል ብዙ የሕይወት ጊዜያቸውን ባሳለፉባት ኖርማንዲ ከተማ እየቀጠሉ ነበር። “75ዓመት በሞላቸው ጊዜ ከቆሞስነት አገልግሎት መገለል ይችሉ ነበር ግን የካህናት እጥረት መኖሩን ስላወቁ በዚህ ሁኔታ ምድራዊው ሕይወታቸው በአሳዛኝ ሁኔታ እስከተደመደመባት እለት ምእመናንን ማገልገል መረጡ” ይላሉ አባ ሐሜል እንደ ረዳት ቆሞስ ያገለገሉባት ቁምስና ዋና ቆሞስ ካህን። ቆሞሱ አክለው ሲናገሩ “አባ ሐሜል ሁላችንም የምንወዳቸውና የአያትነትን አብሮነት የሚያሳድሩ ነበሩ፤ እርሳቸው አብረውን ሲሆኑ ደስ ይለን እንዲሁም በሆነ ነገር ከኛ ጋር ከሌሉ ደግሞ ይሰማን ነበር” ብለዋል።

አባ ጃክ ሐሜል ትላንት ማክሰኞ ሐምሌ 19 ቀን 2008 ዓ.ም. ጠዋት በቅዳሴ ላይ ሳሉ ነበር ሁለት ግለሰቦች ጩቤ ይዘው በመግባት የአባን ጉሮሮ የቆረጡት፡ ይህም ዜና ለፈረንሳይንና ለመላው ዓለም ዘግናኝ ሆነ። እስላማዊ መንግሥት ብሎ ራሱን የሚጠራው ቡድን /አይኤስ/ ይህን ጭካኔ የተሞላ ዜና ተከትሎ እነዚህ ሁለት ወንጀለኛ ግለሰቦች የእርሱ ወታደሮች መሆናቸውን ገልጧል። ይህን ድርጊት ሲያድርጉ ከአባ ጃክ ሐሜል ጋር አራት ሌሎች ሰዎችን አግተው እንደነበርና ከነርሱም አንዳቸው ከበድ ያለ ጉዳት እንደደረሰባችው ተዘግቧል። የፈረንሳይ ፖሊሶች በቦታው ተገኝተው በከፈቱት ተኩስ ይህን ወንጀል የፈጸሙት ግለሰቦች መገደላቸው ታውቋል።

ር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ ይህን ድርጊት ሲያወግዙ፤ የተለያዩ የፈረንሳይ ባለሥልጣናት የድርጊቱን አሳዛኝነትና የተሰማቸውን ኀዘን ገልጸዋል። የቦታው ሊቀ ጳጳስም ይህ ድርጊት የተፈጸመበት ቁምስና ምእመናንን ለማጽናናት በፖላንድ ክራኮቭ የሚካሄደው ዓለም አቀፍ የካቶሊካውያን ወጣቶች ትልቅ ስብሰባን በማቋረጥ ወደ ካቴድራላቸው ተመልሰዋል።  

አባ ጃክ ሐሜል መስዋዕተ ቅዳሴ እያሳረጉ ሳሉ የተገደሉበት ሁኔታ በ1980 ዓ.ም. እኤአ ብዙዎች በጊዜው እሳቸው የሚያስተምሩትን የወንጌል ትምህርት ይቃወሙ የነበሩ ታጣቂዎች በተመሳሳይ ሁኔታ በቅዳሴ ጊዜ ተኩሰው የገደሏቸውነ የኤልሳቫዶር ሊቀ ጳጳስ የነበሩትን ኦስካር ሮሜሮን አስታውሰዋል። በየማሕበራዊ ገጾችም “እኔም ካህን ነኝ”፤ “እኔም ካቶሊክ ነኝ”፤ እንዲሁም “እኔም ክርስቲያን ነኝ” የሚሉ አጫጭር መፈክሮች እንደ ማንነት መገለጫ በመጠቀም ላይ ይገኛሉ። አንዳንድ ክርስቲያኖችም “አባ ሐሜል ከምድራዊው የቅ. ቁርባን ማዕድ ወደ ሰማያዊው የጌታ ማዕድ ተሸጋገሩ” በማለት የክርስቲያን ሞት ፍጻሜ ሳይሆን ወደ ክብር መሻገር መሆኑን ጽፈዋል። የክርስትናን እምነት ከሚያንጸባርቁ ብዙ የግለሰቦች አስተያየት አንዱ “የገዳዮቹ ጩቤ የአባ ጉሮሮ ላይ እንጂ ነፍሳቸው ላይ አይደርስም” ሲል ተነቧል።