ቅዱስ አባታችን ቡሩክ (ቤኔዲክቶስ) ማን ናቸው?
- Category: የምንኩስና ሕይወት
- Published: Saturday, 20 March 2021 11:25
- Written by Super User
- Hits: 1535
- 20 Mar
ቅዱስ አባታችን ቡሩክ (ቤኔዲክቶስ) ማን ናቸው?
ቅዱስ አባታችን ቡሩክ እ.ኤ.አ. በ480 በጣልያን ሀገር ኑርሺያ በምትባል መንደር ከክርስቲያን ቤተሰብ ተወልዱ። ቡሩክ (ቤኔዲክቶስ) በቀለም ትምህርትና በመንፈሣዊ ሕይወት ከልጅነታቸው ጀምረው ትጉህና ታታሪ ነበሩ። በተወለዱበት አከባቢ የነበረውን የትምህርት ደረጃ ካጠናቅቁ በኋላ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ሮም ከተማ ተላኩ። በወቅቱ በዩኒቨርስቲና በሮም ከተማ ወጣቶች ዘንድ ይታይ የነበረውን የሞራል ውድቀትና የተበላሸ ሥነ–ምግባር ስለተመለከቱ “ ሰው ዓለምን ሁሉ አግኝቶ ነፍሱን ግን ቢያጣ ምን ይጠቅመዋል? ” (ማር. 8፡36) የሚለውን የክርስቶስ ቃል በማስታወስ ትምህርታቸውን ትተው በምንኵስና ሕይወት በብህትውና ለመኖር ሱቢያኮ ወደሚባል ቦታ ሂደው በጾምና በጸሎት በዋሻ ማሳለፍ ጀመሩ።
ቤኔዲክቶስ በዋሻ ውስጥ ቅጠላ ቅጠል፣ ስራ ስርና የጫካ ፍራፍሬ እየተመገቡ ከእግዚአብሔር ጋር እንደሚያሳልፉ በአከባቢው የሚኖሩ ሰዎች ስለተመለከቱ በመንፈሣዊ ሕይወታቸው እጅግ ተማረኩ። ነገር ግን ከአከባቢው የሃይማኖት መሪዎች አንዳንዶቹ በቅናት መንፈስ ተነሳስተው ለመግደል እንደሚያሴሩ ስለተረዱ ሞንቴ ካሲኖ ወደሚባል ተራራ ወጥተው ገዳም በመመስረት መኖር ጀመሩ። በሌላ በኩል ደግሞ በርሳቸው መንፈሣዊነት የተማረኩ የአከባቢው ወጣቶች በምንኵስና ሕይወት ከርሳቸው ጋር ለመኖር በቀጣይነት ስለጠየቋቸው በዚሁ ገዳም አብረው እንዲኖሩ ተቀበሉአቸው። የምንኵስናን ሕይወት ለመኖር የወሰኑ ወጣቶች እየተበራከቱ በመምጣቱና ቁጥሩም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ስለሄደ ለመነኵሴዎቹ መተዳደሪያ ደንብና መምሪያ አዘጋጁ።
በዘመናችንም ይህ የምንኵስና መተዳደሪያ ደንብ ለአቡነ ቡሩክ ማህበርና ለሲታውያን ማህበር ብቻ ሳይሆን በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ውስጥ ለተመሠረቱት ለሴቶችና ለወንዶች ገዳማት በሙሉ እንደ ዋና ምንጭ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።
ቅዱስ ቤኔዲክቶስ ለዓለም ምን አስተዋጽኦ አበርክቷል? በመካከለኛው ዘመን በጣም ብዙ የአውሮፓ አገራት በስብከተ ወንጌል እና በስልጣኔ የቤኔዲክቶስን ሕግ ተከትለው እንዲሁም የመነኮሳትን ሥራ በማየት ማለትም በግብርና፣ በእንስሳት እርባታ፣ በሥነ–ጽሑፍ እንዲሁም በብረታ ብረት ሥራ ለማህበራዊ ዕድገት ታላቅ አስተዋጽዖ አበርክተዋል። በአጠቃላይ የአውሮፓ ስልጣኔ ምንጩ የአቡነ ቡሩክ ገዳማት ስለመሆናቸው ታሪክ የሚዘክረው እውነታ ነው።
እኛ ሲታውያን ማነን?
የሲታውያን ማህበር የተጀመረው በፈረንሣይ ሀገር ሲቶ በሚባል ቦታ ሲሆን የአቡነ ቡሩክን ደንብ በይበልጥ በተግባር ለመኖር ሲሉ ከአቡነ ቡሩክ ማህበር በወጡት መነኮሳን ማለትም በቅዱስ ሮቨርቶስ፣ ቅዱስ አልቨርኮስ እና ቅዱስ እስጢፋኖስ የተጀመረ በመሆኑ ተመሳሳይ መመሪያ እየተጠቀምን እንገኛለን። በዚህ መሠረት በፈረንሣይ ሀገር የተጀመረው የሲታውያን ማህበር በኤርትራ (1932 ዓ/ም) የተመሠረት ሲሆን ከዚያም ቀጥሎ ወደ ኢትዮጵያ ሊስፋፋ ችሏል።
በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የሚገኙ የሲታውያን ገዳማት ማለትም በመንዲዳ (1948 ዓ/ም)፣ በአዲስ አበባ (1967 ዓ/ም)፣ በሆሣዕናና (1971 ዓ/ም) በጎንደር (1972 ዓ/ም) ተመሠረቱ። በአሁኑ ጊዜ በነዚህ በአራቱ ገዳማት 29 መነኮሳን በማገልገል ላይ ይገኛሉ።
በተጨማሪም የፍልስፍናና የነገረ መለኮት ተማሪዎች 5 ፤ ተመካሪያን 4 ፤ ሰዓሊያን 1፣ የዘርዓ ምንኵስና ተማሪዎች በአዲስ አበባ 20፣ በመንዲዳ 9 በመከታተልና ጥሪያቸውን በመፈልግ ላይ ይገኛሉ። የገዳመ ሲታውያን ማህበር ዓላማም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው። ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።
ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።
ቅዱሱ አባታችን ቡሩክ እ.ኤ.አ. በ547 ገደማ ሞንቴ ካሲኖ በተባለው ገዳም በቅድስና አረፉ፡፡ ከሞታቸውም በኋላ ጀምሮ በመነኮሳኑ ዘንድ በየዓመቱ መጋቢት 12 ቀን ክብረ በዓላቸው ሲከበር ቆይቷል።
በመጨረሻም የቅዱስ አባታችን የምንኵስና ፈለግ በመከተል በጸሎትና በሥራ በመጠመድ ለምንኵስና ሕይወት ጥሪ ያላቸውና ጥሪያቸውንም ለምፈልጉ ወጣቶች ከአራቱም አቅጣጫ ቢመጡ ለመቀበል በራችን ክፍት ነውና ይጠይቁን፤ የእግዚአብሔርን ድምፅ ዘወትር ይስሙ፤ ወደ ቅዱስ አቡነ ቡሩክም ይጸልዩ።
እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን። (ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!) 1ጴጥ.4:11
ጸሎት ወደ ቅዱስ አቡነ ቡሩክ
ቅዱስ አቡነ ቡሩክ ሆይ! በእውነት ስምህ እንደሚያመለክተው “በረከት” ነህ፡፡ የሰበከውን በመኖርና በመተግበር የምዕራባውያንን ገዳማዊ ሕግ መሠረትክ - የምንኵስና ሕግ ሁሉ አባትና ጀማሪ ነህ፤ የጉልበት ሥራን ከጸሎት ጋር በማዋሃድና በመቀላቀል፤ ሥርዓተ- አምልኮንም ከግል ጸሎት ጋር ለእግዚአብሔር ማቅረብን አስተማርክ፡፡
ቅዱስ አቡነ ቡሩክ ሆይ! ማህበራት ሁሉ ደንባቸውን እንዲከተሉና ለጥሪያቸው ታማኞች እንዲሆኑ እርዳቸው፤ በዘወትር አማላጅነትህም እስከ መጨረሻው አጽናቸው።
እግዚአብሔር አባታችን ሆይ! በፍቅርህና በአገልግሎትህ የሚኖሩትን ወደ ታላቁ ክብርህ ለመምራት ተዋቂውን ቅዱስ አቡነ ቡሩክን ስለፈጠርክ እናመሰግንሃለን፤ ካንተ ፍቅር ምንም ሳናስቀድም፤ ትዕዛዛትህን በመጠበቅና በትዕዛዛትህም መመላለስ እንድንችል ጸጋህን ስጠን። ለቤተክርስቲያንና ለዓለም በሙሉ የምጸልዩትን መነኮሳትን ሁል ጊዜ ጠብቅልን፤ አንተ በቸርነትህ የምንኵስናን ጥሪ አብዝተህ ስጥልን ብለን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንለምንሃለን፡፡ አሜን።
በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ... 1X
ጸጋ የሞላሽ ማርያም ሆይ... 1X
ለአብና ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስም... 1X
ቅዱስ አቡነ ቡሩክ ሆይ! ለምንልን።
ድንቅ ተአምራት አድራጊ ቡሩክ ሆይ! ለምንልን።
እውነተኛ የእግዚአብሔር አገልጋይ ሆይ! ለምንልን።
ለቅዱስ አቡነ ቡሩክ ክብረ በዓል
ገዳመ ሲታውያን ዘቅድስት ሥላሴ ሆሣዕና
መጋቢት 12/2013 ዓ.ም - ሆሣዕና