እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

8. ክርስቲያናዊ ምንኩስና

8. ክርስቲያናዊ ምንኩስና

ክርስቲያናዊ የምንኩስና ሕይወት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚዘወተር ራሱን የቻለ ዓይነት የአናኗር ዘይቤ ነው። ይህን ሕይወት የሚመርጡ ክርስቲያን ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ክርስቲያኖች ሁሉ ሊኖሩት የሚገባቸውን የጥምቀት ጸጋ ራሳቸውን ለእግዚአብሔር በመለየትና በመስጠት በተለየ ሁኔታ እርሱን በማኅበራዊ ሕይወት ለመከተል የሚሹ ናቸው።

 በርግጠኝነት ገዳማዊ ሕይወት መቼና የት እንደተጀመረ መናገሩ አዳጋች ነው። ምክንያቱም ገዳማዊ ሕይወት ሌላ ሳይሆን የክርስትናን ሕይወት ለመኖር ሲባል የተጀመረ እንጂ የተሻለ ተብሎ የተመሠረተ አይደለም፤ ስለዚህም በግላዊ የጸጋ ሕይወት ውስጥ የግለሰቡና የእግዚአብሔር ግንኙነት የሚያሳድጉት ዓይነት ስለሆነ ይህንን በጊዜና በቦታ ማለትም በታሪክ ማመላከቱ አስቸጋሪ ነገር ነው። ስለ ክርስቲያናዊ ምናኔ ስናወራ በመጀመሪያው ክ.ዘ. ደናግልና መበለቶች የጀመሩት ዓይነት ሕይወት እንደነበረ አውስተናል፤ ሆኖም ግን ያ በምንም መልኩ ዛሬ እንደምንረዳው ገዳማዊ ሕይወት ነው ማለት አይደለም።

ለመጀመሪያዎቹ ሦስት ክፍለ ዘመናት ክርስቲያኖች በእምነታቸው ምክንያት እጅግ ይሰደዱና ይገደሉም ስለነበር የሰማእትነት ዘመን ነበር፤ ሆኖም ግን ከአራተኛው ክ.ዘ. ማለትም ከ313 ዓ.ም. ጀምሮ በነገሥታት ደረጃ የክርስትና እምነት ተቀባይነት እያገኘ መምጣት ሲጀምር ስደትና ሰማእትነቱም እየቀነሰ መምጣት ጀመረ። ስለዚህም የምነና ሕይወት የሰማእትነትን ዋጋ እንደሚተካ በማሰብ መዘውተር ቀጠለ። አንዳንድ ክርስቲያኖችም ስለ እምነታቸው ባይገደሉም እንኳ በሕይወታቸው ዋጋን ለመክፈል ይበልጥ እንዲመቻቸው ወደ ምድረ በዳ/በረሃ በመሄድ የጽሞናና የዓላማ ሕይወትን መኖር ጀመሩ። እዚህ ላይ ማስተዋል ያለብን ነጥብ ገዳም የሚለው ቃል በግእዝ ቋንቋ ሥርወ ትርጉሙ ምድረ በዳ ወይም በርሃ መሆኑን ነው፤ ስለዚህም ገዳም ገባ ስንል ትክክለኛ ታሪካዊ አንድምታውን ያስተላልፍልናል።

ልንገምት እንደምንችለው ይህ ሂደት በግለሰብ ደረጃ የሚጀምርና የኋላ ኋላ ግን ማኅበራዊነትን ያስከተለ መሆኑን ነው። በርግጥም በዚያ ዘመን እንደ ባሕታዊ ሆኖ ወደ ምደረ በዳ መግባቱ እየተዘወተረ መጣ። ነገር ግን ብዙም ሳይዘገይ እነዚህ ባሕታውያን ተሰባስበው በምድረ በዳ/በገዳም በአንድነት መኖር ጀመሩ። ይህ ማለት ግን የግል ጸሎት ሕይወታቸው ተቋረጠ ማለት አይደለም። ከአምላካቸው ጋር የሚገናኙበት የግል ጊዜ አላቸው፤ እንዲሁም ከወንድሞች ጋር የሚወያዩበትና የሚመገቡበት የጋራ ጊዜ ነበራቸው። በአንድ ላይ በመሆንም ይወያያሉ የሕይወት ተሞክሮቻቸውን ይካፈላሉ፣ አንዱም ሌላውን ያገልግላል። በዚህም መልኩ ያላቸውን ንብረት በመጋራት፣ በመተሳሰብና አንድ ልብ በመሆን ይህ ሕይወት በሐዋርያት ሥራ 2:42 ላይ የምናገኛትን የአዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያን ሁኔታ ማንጸባረቅና የመላይቱ ቤተ ክርስቲያን አነስተኛ አምሳል መሆን ጀመረ።


የሰው ተፈጥሮና የምንኩስና ሕይወት

የሰው ልጅ ሰው መሆኑን ማወቅ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ራሱንም ሆነ በዙሪያው ያሉ ነገሮችን ተፈጥሮ ለማወቅ ጥረትን ያደርጋል። ይህ ጥረት በውስጡ ለሚነሡ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስን ከመስጠት ይልቅ ጥያቄዎችን እያበዙበት ይሄዳሉ። ስለዚህም ቶሎ የሚረዳው ነገር ቢኖር ቁሳዊ ነገሮችም ሆኑ የራሱ ማንነት የሕይወት ጥያቄዎችን ለመመለስ አቅመ ቢስ መሆናቸውን ነው። አንዳንዴም ሰው የሕይወት ጥያቄው በሥጋዊ ምኞት፣ በእውቀት፣ በሃብት ወይም በሥልጣን እና በመስል ነገሮቻቸው መልስን የሚያገኝ መስሎት በእድሜው ይዳክራል፤ ማንነቱንም ያባክናል። ተስፋ አድርጎ መልስ ይሆኑኛል ብሎ የሚጓጓላቸው ነገሮች ጋር ሲደርስ ይበልጥ ባዶ ፍጡር መሆኑን ሲነግሩት፤ ሰው ርካታንና የማንነቱን ሙላት ጠለቅ ባለ ዓላማ ውስጥ እንደሚገኝ ያየዋል። ስለዚህ በዘመናት ሂደት ወይም በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ሰው ሕይወቱን ይሞላልኛል ብሎ ላመነበት ዓላማ ማንነቱን መስጠቱ የተለመደ ክስተት ነው። ምክንያቱም የሰው ሕይወት ቁምነገሩ ኖሮ ማለፉ ብቻ ሳይሆን በዓላማ መኖሩ ነው። ስለዚህ ከዚህ ሰዋዊ ዝንባሌ አንጻር ስናየው ሰው ብቻውን ገለል ብሎ በሆነ ዓላማ ለመኖር መወሰኑ የምንኩስና ሕይወት በተወሰነ መልኩ ተፈጥሮአችን ውስጥ አለ ለማለት ያስደፍራል።

ሰው በኖረባቸው ዘመናት ሁሉ በተለያየ ስምና ከብዙኃኑ ሕዝብ ተለይተው በአንድ ግብ የሚጓዙ የማኅበረሰብ ክፎሎች ነበሩ። በትዳር መተሳሰርን ትተው፡ ከወዳጅ ዘመዶቻቸው በመራቅ ከሃብትና ንብረት ይልቅ ለአንድ ዓላማ የሚኖሩ ጥንታውያን ግሪካውያን፡ ሮማውያን . . . ነበሩ። አንዳንዶቹ በሚያጠኑት የእውቀት ዘርፍ ፍጹም የሆነ እውቀትን /ጥበብን/ ለመገብየት፣ በያዙት ሙያ ጫፍ ላይ ለመድረስ /በስፖርት፣ በፖለቲካ/ ለብቻቸው የሚኖሩ ነበሩ። በፕሌቶ /አፍላጦን/ <<ሪፐብሊክ>> በሚለው መጽሐፉ እንደተገለጸው ለፍትሐዊና ሰላማዊ የሕዝብ አስተዳደር ራሳቸውን ከብዙኃኑ ለይተው - ወላጆቻቸውን እንዳያውቁ ተደርገው፣ ለ30 ዓመታት ያህል ልዩ ትምህርት እየተሰጣቸው፣ የግል ንብረት ሳይዙ በጋራ በመኖር ሙሉ ሕይወታቸውን ለፖለትካዊ ፍልስፍና የሚሰጡ ወንዶችና ሴቶች እንደነበሩ እናነባለን። እንዲሁም ከማኅበራዊ ሕይወትና ራስን በማግለል ሁሉን ነገር በመመነን ውስጣቸው ያገኙትን እውነት /እውቀት/ ሙሉ ለማድረግ የሚጥሩ ፈላስፎች እንደነበሩ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ4ኛው ክ.ዘ. መጀመርያ ላይ የነበረው ዲዮጋን የሚባል ግሪካዊ ፈላስፋ ምሳሌያዊ ነው። ዲዮጋን ሙሉ ምርምር ለማካሄድና በነጻነት ጥልቅ ሃሳቦችን ለማሰላሰል ያግዘው ዘንድ በማሰብ ውሃ ከሚጠጣባት ጣሳ በስተቀር ሁሉን ነገር መነነ። ይጓዝ የነበረውም ባዶ እግሩን ሲሆን ቀንም ሌሊትም የሚለብሳት አንዲት ካባ ነገር ብቻ ነበረችው። ዲዮጋን ፈላስፋው በዚህ ሁኔታ ሳለ አንድ ቀን አንድ ሕፃን ልጅ በአንድ የወንዝ ዳርቻ ሆኖ በእጁ ውሃ እየጨለፈ ሲጠጣ አየው። ይህንንም ሁኔታ ፈላስፋው በማስተዋል <<ይሄ ልጅ አዲስ ጥበብ አስተማረኝ>> በማለት ለመጠጫነት ይጠቀምባት የነበረችውንም ጣሳ እንደተዋት ይነገራል።

ይህንን እና መሰል ቅድመ ክርስትና ታሪኮችን ስናስተውል ገለል ብሎ ተፈጥሯዊ ስሜቶችን በመቆጣጠር ከነርሱ ባርነት ነፃ በመሆን የሆነ ዓላማን የመከተል ሕይወት በክርስቲያናዊ ምንኩስና ያልተጀመረና ሁሉን አቀፍ መሆኑን ያስረዳናል። በዚህም ምክንያት ከክርስቶስ ልደት በፊትና በኋላም የተነሡ ሃይማኖቶች ዓላማቸውና መልካቸው ቢለያይም የየራሳቸው የምንኩስና ሕይወት አላቸው። ስለዚህም የክርስቲያናዊ ምንኩስናን ልዩ ተፈጥሮ ለማየት እንችል ዘንድ አስቀድመን የሌሎች ዐበይት እምነታት ምንኩስናዊ ገጽታ በጣም አጠር አጠር ባለ መልኩ እንመልከት።

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት