የዘጠኝ ቀን ዝግጅት (ቅዱስ ዮሴፍ) ቀን 2

St Joseph Novena 2013 2

ጸሎተ ተሰዓቱ (ኖቬና) ዘቅዱስ ዮሴፍ - ቀን 2

(በየዕለቱ የሚደገም)

ቅዱስ ዮሴፍ ሆይ እኔ ደካማው ልጅህ ሰላም እልሃለሁ፡፡ አንተ የሚወዱህንና የሚያክብሩህን ትከላከላለህ፤ ታማልዳቸዋልህ፡፡ በአንተ ላይ ልዩ የሆነ መታመን እንዳለኝና ከአዳኜ ኢየሱስና ከቅድስት እናቱ በመቀጠል የደኅንነት ተስፋዬ አንተ ነህ፡፡ ምክንያቱም አንተ የእግዚአብሔር ወዳጆችን ለመርዳት ከቶ አታመነታም፡፡ ስለዚህም በትህትና ስምህን እጥራለሁ፡፡ ከምወዳቸው እና የቅድስት ቤተስብ አፍቃሪ ከሆኑት ጋር አማላጅነትህን በመተማመን ወደ አንተ እንቀርባለን፡፡ ለአዳኛችን ኢየሱስና ለወላዲተ አምላክ ባለህ ፍቅር በዚህች አለም እስካለንና በሞታችን ጊዜ እንዳትለየን እንለምንሃለን፡፡

የእመቤታችን ቅድስት ደንግል ማርያም እጮኛ ቅዱስ ዮሴፍ ሆይ ንጹሕ፣ ትሑት፣ በቸርነት የተሞላ አዕምሮና ፍጹም ለእግዚአብሔር ፈቃድ የመገዛት ጸጋ አሰጠኝ፡፡ አንተ በኢየሱስና በድንግል ማርያም እጅ እንደሞትክ እኔም ተመሳሳይ ዕድል ያጋጥመኝ ዘንድ መሪ፣ አርአያ እና አባት ሁንኝ፡፡

አፍቃሪና የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታማኝ ተከታይ ቅዱስ ዮሴፍ ሆይ ለመንፈሳዊና ለየእለቱ በጎነት በተለይ ደግሞ መልካም ሞት አገኝ ዘንድ በዚህች ሰዓት በልቤ ውስጥ ያለውን አሳብ አስፈላጊ የሆኑትን ጸጋዎች ከኢየሱስ መለኮታዊ ልብ ታሰጠኝ ዘንድ አማላጅነትህን እማጸንህለሁ፡፡

/እዚህ ላይ በልብ ያለውን አሳብ መጥቀስ/

ሥጋ የለብሰው ቃል ጠባቂ ስለእኔ የምታቀርበው ጸሎት በእግዚአበሔር ፊት እንደሚሰማ እተማመናለሁ፡ አሜን፡፡

የቅድስት ድንግል ማርያም እጮኛ፣ አፍቃሪና ጠባቂ ቅዱስ ዮሴፍ ሆይ ጥበቃህናን እርዳታህን የፈለገ፣ መጽናናትን ሳያገኘ የቀረ ማንም የለም፡፡ በቅዱስነትህ በመተማመን እነሆ ወደ ፊትህ እቀርባለሁ፡፡ የመድኃኒታችን ምድራዊ አባት ሆይ ልመናዬን በቸርነት ተቀበለኝ እንጂ ችላ አትበለኝ፡፡ አሜን፡፡

2ኛ ቀን - ቅዱስ ዮሴፍ ፡ የድንግሏ እጮኛ

ቅዱስ ዮሴፍ ሆይ እንደ ቅድስት ድንግል ማርያም ጠባቂነትህ እናከብርሃልን፤ ቅዱስ ቃሉ “ ያዕቆብ ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስ የወለደች የማርያምን እጮኛ ዮሴፍን ወለደ” ይለናል፡፡ /ማቴ 1፡16/ ከቅድስት ድንግል ማርያም ጋር የነበራችሁ ይጋብቻ ስምምነት አንዳችሁን የሌላው የሚያደርግ ቅዱስ ስምምነት ነበር፡፡ ቅድስት ድንግል ማርያም ባላትና በሆነችው ሁሉ የአንተ ነበረች፡፡ እርሷ አንተን የማፍቀርና የመታዘዝ ግዴታ ነበረባት፡፡ እንደአንተ የእርሷን አክበሮት፣ መታዘዝና ፍቅር ያሸነፈ ሰው የለም፡፡

አንተም የእርሷ ተከላካይና ኢየሱስን ከመውለዷ በፊትና ከወለደችም በኃላ ድንግል ስለመሆኗ ምስክር ነበርክ፡፡ የድንግልና ጋብቻ በየዕለቱ ሕይወት ከእግዚአብሔር ፍጥረታት ሁሉ ይብለጥ ከተወደደችው ድንግል ማርያም ይበልጥ ወደ መተዋወቅ ከማምጣቱም በላይ መንፈሳዊ ሃብታትንም አብሮ መካፈል አስችሎህ ነበር፡፡  ቅድስት ድንግል ማርያም በአንተ ሰላማዊ፣ ትህትና፣ ጥልቅ ቅድስናና ንጽሕና ሕንጸትን አግኝታ ነበር፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ እናቴ ከሚላትና የሰማይ እና ምድር ንግሥት ብሎ ከሚጥራ ት ጋር እንዲህ ያለ ቅርብ ግንኙነት ያለህ መሆኑ እንዴት ያለ ታላቅ ክብር ነው! ቅድስት ድንግል ማርያም ያላት በረከት ሁሉ ያንተም ነው፡፡ ይህም ምንም እንኳ ልጇ በለዩ ሁኔታ የእርሷ ቢሆንም የአንተን አባትነት ይጨምራል፡፡ ጋብቻችሁን ከሚስጥራት ሁሉ የላቀውንና የበጎ ነገር ሁሉ ምንጭ የሆነልንን ኢየሱሰን ወደ እዚህ ዓለም ለመላክ መንገድ እንዲሆነው መረጠ፡፡ ወልደ እግዚአብሔር እናቱን እንድትጠብቃትና እንድትንከባከባት ለአንተ አደራ ሰጠህ፡፡

የቅድስት ድንግል ማርያም ሕይወት በዚህ ዓለም ለመደሰትና ዓለማዊ ክብር ለማግኘት ሳይሆን ሥቃይና መስቀል የተሞላ ከባድ የአዳኝ እናት የመሆን ተልዕኮ ነበር፡፡ አንተ ለዚህች የሐዘን እናት ታማኝ፣ አጋር፣ ረዳትና አጽናኝ ነበርክ፡፡ አንተ ለእርሷ በድህነት፣ በሰደትና በሥቃይ ጊዜ ታማኝ ነበርክ፡፡ ለእርሷ ያለህ ፍቅር የእግዚአብሔር እናት በመሆኗ ላይ የተመሠረተ ነበር፡፡ከእግዚአብሔር አብና ከመለኮታዊው ሕጻን ቀጥሎ እንደ እርሷ ያፈቀርከው የለም፡፡ ቅድስት ድንግል ማርያም በበኩሏ ጥሪዋን በእሽታ እንደተቀበለች ሁሉ ለአንተም ታዛዥ ሆነች፡፡ የሁለታችሁን ልብ በፍጹም ፍቅር ያስተሳሰረው ራሱ መንፈስ ቅዱስ ነበር፡፡
ቅዱስ ዮሴፍ ሆይ የቅድስት ድንግል ማርያም እጮኝ ስለሆንክ እናመሰግንሃለን፡፡ ስለመመረጥህ ምልክት እንዲሆን አምላካችንና አዳኛችን ኢየሱስ ክርስቶስን አንተ እንዳደረግከው በሙል ልባችን እንድናፈቅረው፣ እንዲሁም ቅድስት ድንግል ማርያም አንተ ባፈቀርካት ዓይነት ፍቅር እናፈቅራት ዘንድ ጸጋ አሰጠን፤ አሜን።

የአምላክ እናት እጮኛ ቅዱስ ዮሴፍ ሆይ - ለምንልን፡፡

የቅዱስ ዮሴፍ መዝሙር

ቅዱስ ዮሴፍ ሆይ ጠብቀን

ወደ ገነትም አድርሰን፡፡

የማርያም እጮኛ ሆይ

ቅዱስ ዮሴፍ ሆይ

የአምላክ ልጅ

ለኛም አማላጅ::