ክፍል 9 - የቅዱስ አውጎስጢኖስ ሥነ ጽሑፋዊ አበርክቶ

የቅዱስ አውጎስጢኖስ ሥነ ጽሑፋዊ አበርክቶ

ቅዱስ አውጎስጢኖስ በጊዜው ቤተክርስቲያንን በስብከቱና ትምህርተ ክርስቶስን በሚመለከት ጽሑፎቹ እየጠነከረች እንድትሄድ አድርጎአታል። የአጎስጢኖስ ብዕር ያልተወረወረበትና ቀለሙ ያልነጠበበት የነገረ መለኮት ክፍል ባይኖርም፤ በተለይ መለኮታዊ ጸጋን በሚመለከት ረገድ ተወዳዳሪ የለውም። 113 የሚሆኑ መጻሕፍትንና ድርሳናትን ከ200 በላይ የሚሆኑ መልእክታትን ከ500 የሚበልጡ ቃለ ስብከትና አስተምህሮችን አውርሶ አልፏል። ግላዊ ሕይወቱና ጠባዩን በጽሑፎቹ ላይ ተጽዕኖ አለው ቢባልም እንኳ ሃይማኖትንና ቅድስናን በሚመለከት የነበረው አመለካከትና ግንዛቦት ጉልህና በጽኑ መሠረት ላይ የታነጸ መሆኑን የሚያሳይ ነው።

ቅዱስ አውጎስጢኖስ በጽሑፍ ላይበዚህ ሁሉ የሥነ ጽሑፍ ባሕር ውስጥ ሊዋኝ የተገደደው የጽሕፈት ሱስ ኖሮት ወይም ለራሱ ስምና ክብር ሳይሆን በልቡ ውስጥ የነበረ የእግዚአብሔር ፍቅር ሞልቶ ተትረፍርፎ በመፍሰሱ ነው።

አንድ የቤተክርስትያን ታሪክ ማስታወሻ ይህንን ሲገልጽ “…….አውጎስጢኖስ ለራሱ ዝናን ለማትረፍ ሳይሆን ለእግዚአብሔር ፍቅርና ለሰው ፍቅር ብሎ በልቡ ውስጥ በቅሎ በብዙ ሺሕ የሚቆጠር ፍሬን ያፈራ እውነትንና ጽድቅን የሚገልጽ አዲስ ሐሳብን በማቅረብና በሐሳቡም ስፋትና ጥልቀት በጊዜው የሚተካከለው አልነበረም” ይላል።

ከመጽሓፍቶቹ በተለይ ወደ ነፍስ ወከፍ ሰው (ግለሰብ) እጅ  በመድረሳቸው በጣም የገነኑት ግን ሁለት ናቸው። እነርሱም “የእግዚአብሔር ከተማ” (The City of God) እና “ኑዛዜ” (Confession) የተባሉት ናቸው።

“ኑዛዜ”  በሚል ርእስ አውጎስጢኖስ የጻፈው መጽሐፍ ከልጅነቱ ጀምሮ ወደ ክርስትና እስከ ተመለሰበት ጊዜ ያሳለፈውን ሕይወት ይገልጻል። በተለይ የዚህ መጽሐፍ ዓላማ አውጎስጢኖስ ውጫዊ ታሪኩንና ዜና መዋዕሉን መተረክ ብቻ ሳይሆን ወደ ውስጣዊ ሁኔታውና ሐሳቡን ወደመግለጽ ያዘነበለ ነው። ስለዚህ የአውጎስጢኖስ ሥነ ልቦናዊ (Psychological)፣ ሞራላዊና አእምሮአዊ (Intellectual) ሕይወቱን ያንጸባርቃል። እግዚአብሔር በአእምሮውና በልቡ ውስጥ ያሳደረበትን ታላቅ ምኞትና ወደኋላ  ይጎትተው የነበረ የደካማነት ስሜታዊነትን በአእምሮው ብርሃኑም የተፈላሰፈውን ሁሉ ይገልጻል፤ ያምናል፤ ይናዘዘዋልም። ማንነቱን ለማግኘት ብዙ ድንጋዮችን የሚፈነቃቅል የአንድ ወጣት መንፈሳዊ ጉዞ ነው ሊባል ይቻላል።

የምታርፍበት ወደብ በመፈለግ በባህር ውስጥ በማዕበል እየተንገላታች እንደምትጓዝ መርከብ ሁሉ የሰው ነፍስ ደግሞ እውነተኛ ወደብዋ የሆነውን እግዚአብሔርን እስክታገኝ ድረስ ምን የሚመስል ፈተናና አስቸጋሪ ጉዞን እንደምታልፍ፤ እርሱን ሳታገኝ እንደማታርፍ አውጎስጢኖስ የገዛ ራሱን ሕይወትና ሁኔታ እንደማስገንዘቢያ አድርጎ በማቅረብ ሲመሰክር ስሜቱንና ሥነጽሑፋዊ ችሎታውን አቀናብሮ የሰውን መንፈስ በሚቀሰቅስ አኳኋን በዚህ “ኑዛዜ” በተባለው መጽሐፉ ማንነቱን ገልጾታል።

ምንም እንኳ በቋንቋዎቻችን የተተረጎመ ባይኖርም በሌሎች አብዛኞቹ የዘመናችን ቋንቋዎች ተተርጉሞ ስለሚገኝ የቻለ እንዲያነበው አደራ እንላለን። አውጎስጢኖስ በዕድሜ በስሎ ወደኋላ በመመለስ ያለፈ ሕይወቱን የታዘበበት መስኮት ስለ ሆነ አረጋውያን ያለፈ ሕይወታቸውን የሚመዝኑበት፤ ወጣቶች ደግሞ የሕይወት ትግላቸውና ችግራቸው፣ የጉዟቸውም ብዥታ በብዙ ቅዱሳን ዘንድ የታየና የነበረ እንጂ በእነሱ ያልተጀመረ እንዲሁም መፍትሔም ያለው መሆኑን እንዲገነዘቡና ለአካሂዳቸውም የተረጋገጠ መመሪያ ሊሆን የሚችል መጽሐፍ ነው።

“የእግዚአብሔር ከተማ” (The City of God) የተባለው መጽሐፉም ደግሞ በምድራዊ መንግሥትና በሰማያዊ መንግሥት መካከል ያለውን ንጽጽርና ልዩነት የሚገልጽ ቢሆንም አውጎስጢኖስ “ስለ ታሪክና” “ስለ ታሪክ ጉዞ” የነበረው ክርስቲያናዊ ፍልስፍናና አስተያየትን አብራርቶ የሚያንጸባርቅ ነው።

የምሥራቃዊ ቤተክርስቲያን አበውና ሊቃውንት የእግዚአብሔርን ሁናቴ የክርስቶስን ባሕርያትና የቅድስት ሥላሴን ምስጢር ለመረዳትና ለማብራራት ጥረት እንዳደረጉ ሁሉ ቅዱስ አጉስጢኖስ ደግሞ ኃጢአትን፤ የእግዚአብሔር ጸጋን፤ ደኅንነነትን ስለሚመለከት ጉዳይና እንዲሁም በምድር ላይ በመታግል ላይ የምትገኘው ቤተክርስቲያን ልታደርጋቸው የሚያስፈልጉዋትን ነገሮች ለመረዳት ብርቱ ጥረት አድርጓል።

ቅዱስ አውጎስጢኖስ ጸጋንና ኃጢአትን ስለሚመለከት ጉዳይ የነበረው ግንዛቤ የሚታየው የእነዶናቱስ፣ ማኒና ፔላጊዩስ ትምህርትን ለመግታት ባደረገው ከፍተኛ ጥልቀትና ርቀት ባለው ምርምሩ ነው። አውጎስጢኖስ ሰው በአርአያ ሥላሴ ተፈጥሮ ክፉውንና ደጉን የሚለይበት አእምሮና ፈቃድን ተሰጥቶት ነበር፤ ከአዳም ውድቀት በኋላ ግን ይህን ስጦታ አጠፋው። የአዳም ኃጢአት ለዘሩ ሁሉ ተላልፏል፤ ሕጻናትም የወረሱት ኃጢአት ስላላቸው መጠመቅ አለባቸው፤ የሰው ልጅ በኃጢአት በመውደቁ ምክንያት በራሱ ጥረትና በሥራው ብቻ ድኅነትን ሊያገኝ ወደማይችልበት ሁኔታ ተጥሎአል። ድኅነት እግዚአብሔር ራሱ በክርስቶስ ቤዛነት ላመኑት የሚሰጣቸው ጸጋ ነው። ይህንንም ሃሳቡን ቀለል ባለ አባባል ሲገልጸው “በራሱ ፈቃድ የፈጠረህ እግዚአብሔር ያላንተ ፈቃድ አያድንህም” ይለናል። የእግዚአብሔር ጸጋና ሥራችን ተባብረው ድኅንትን ያስገኛሉ። ጸጋ በጎ ምግባርን የሚያፈራ (የሚያስገኝ) እና ሠናይ ምግባር ደግሞ ጸጋን ማዳበር ይገባዋል የሚለው የዚህ የታላቁ አፍሪቃዊ ቅዱስ መንፈስና ሚዛናዊው ትምህርቱ በሰው ልጅ ግላዊ ሕይወትም ሆነ ታሪክ ለዘለቄታ የብርሃን ፋና ሆኖ ያኖራል።