ምን ዓይነት እሳት? ትልቁ ወይስ ትንሹ?

ትልቁ ወይም ትንሹ እሳት

ትልቁ ወይም ትንሹ እሳት በሚል ርእስ በተለያየ ክፍል የምናቀርበው ይህ ጽሑፍ በአሁኑ ሰዓት በሎንዶን የዌስትሚኒስትር ሀገረ ስብከት በሆነው የፋጢማዋ እመቤታችን ቁምስና በማገልገል ላይ በሚገኙት በክቡር አባ ኤፍሬም ዓንዶም ከተዘጋጀ ጽሑፍ የተወሰደ ሆኖ በመላይቱ ቤተ ክርስቲያን የ2 ሺህን ዓ.ም. ኢዮቤላዊ ዓመት በማስመልከት ተደርጎ ለነበረው የሦስት ዓመታት ቅድመ ዝግጅት 1998 ዓ.ም. ለእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ የተሰጠ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን ይህንን ታሳቢ በማድረግ በወቅቱ የተዘጋጀ ጽሑፍ ቢሆንም ይዘቱና ፋይዳው በቀጣይነት ለእምነት ሕይወታችን የሚያግዝ ጠለቅ ባለ መልኩ በክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ያሉትን ኃይላት በእሳት በመመሰል ለጥፋትና ለዘላለማዊው እሳት የሚዳርጉንን እሳቶች ከሕይወት ሰጪው የመንፈስ ቅዱስ እሳት ጋር በማነጻጸር የተዘጋጀ ጠቃሚ ጽሑፍ ነውና ጊዜያችንን ሰጥተን ነፍሳችንን እንመግባት። ሙሉውን ጽሑፍ ማቅረብ ባንችልም እንኳ በቀጣይነት በየጊዜው እየቀጠለ የሚሄድ ጽሑፍ ነውና ዓምዱን ደጋግመን እንጎብኘው። ለክቡር አባ ኤፍሬምም ልባዊ ምስጋናችንን እያቀረብን፤ አገልግሎታቸውን እግዚአብሔር ይባርክ ዘንድ ሁላችን በጸሎታችን እንደምናስባቸው ይሁን።

 

"እነሆ፣ ትንሽ እሳት እንዴት ያለ ትልቅ ጫካ ያቃጥላል!" ያዕ. 3፡5

 

ትንሹ እሳት

ከእናንተ መካከል አንዱ፣ እሾሆች ካሉበት፣ የመንፈስ ቅዱስን እሳት በእነርሱ ላይ ይጣልባቸው፡፡ ሌላውም ጠንካራና የደነደነ ልብ ካለው፣ ይህንኑ (የመንፈስ ቅዱስን) እሳት በመጠቀም፣ ለስላሳና ልዝብ እንዲሆን ያድርገው፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ

መግቢያ

እሳት ወይስ እሳት?

(ምን ዓይነት እሳት? ትልቁ ወይስ ትንሹ?)

ዓይነቱ ይለያይ እንጂ በሁሉም ስፍራ እሳት አለ! አንድ ጸሐፊ እንዳስቀመጠው ዓለም በእሳት ተያይዛለች! በሌጣ ዓይናችን እንመልከትህ ብንለው ሁሉም እሳት በግልጽ የሚታይ አይደለም፡፡ በግዙፍ ዓይናችን የሚታየን በምድጃችን ላይ የሚንበለበለው እሳት ወይም አልፎ አልፎ ቤቶችንና ታላላቅ ደኖችን ሲያቃጥል የሚገኘው ሰደድ እሳት ብቻ ነው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ከዚህ የበረታ እሳት አለ፤ ሲነድና ሲያነድ በሌጣ ዓይን ላይታይ ይችላል፡፡ ውጤቱ ግን በግልጽ ይታያል፡፡

እስካሁን ከተባለው ልንረዳው እንደምንችለው ከግዙፋዊው እሳት ሌላ መንፈሳዊ እሳትም እንዳለ ነው፡፡ ስለ መንፈሳዊ እሳት በምናስብበት ወቅትም ቢያንስ ሁለት በጣም የተለያዩ፣ እንዲያውም ተቃራኒ የሆኑ የእሳት ዓይነቶች እንዳሉ ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ እነርሱም መለኮታዊ እሳትና ሥጋዊ ወይም ሰይጣናዊ እሳቶች ናቸው፡፡ እነዚህን እሳቶች በግዙፍ ዓይን ልናያቸው ባንችልም (አልፎ አልፎ የታዩባቸውና የሚታዩባቸው ጊዜያት እንዳሉ ባይዘነጋም) በነርሱ ምክንያት በሰዎች ሕይወት ውስጥ የሚከሰቱት ክስተቶች ምን ዓይነት እሳት በአንድ ግለሰብ ሕይወት ውስጥ በመንደድ ላይ እንዳለ ቁልጭ አድርገው ያሳያሉ፡፡ በመለኮታዊው እሳት የተያያዘ ሰው በመንፈስ ቅዱስ ሕግ ሲመራ፣ በዲያብሎሳዊ እሳት ወይም በሥጋዊ እሳት የነደደው ደግሞ በሥጋ ሕግ ሲመራ ይገኛል፡፡ ስለዚህም ነው ቅ.ጳውሎስ "እንግዲህ በመንፈስ ኑሩ፤ የሥጋንም ምኞት አትፈጽሙ እላለሁ፡፡ ምክንያቱም የሥጋ ምኞት ከመንፈስ ምኞት ጋር ተቃራኒ ነው፤ መንፈስና ሥጋ እርስ በእርሳቸው ይቃረናሉ፤ ስለዚህ እናንተ የምትፈልጉትን ማድረግ አትችሉም፤ በመንፈስ ብትመሩ ግን የሕግ ተገዢዎች አትሆኑም" በማለት የጻፈው (ገላ 5፡ 16-18)፡፡ ይህን ካለ በኋላም የሥጋ ሥራዎችን (የሥጋ እሳትን) በአንድ ወገን የመንፈስ ቅዱስ እሳት ውጤት የሆነውን የመንፈስ ቅዱስ ፍሬን ደግሞ በሌላ ወገን ይዘረዝራል፡፡ ስለነዚህ ሁለት ሕጎች በሮም 8፡1-17 ሰፋ ያለ ገለጻን ይሰጣል፡፡

በነዚህ ሁለት ዓይነት እሳቶች የተነሣ "በምድር ላይ የሰው ሕይወት ብርቱ ሰልፍ ነው" (ኢዮብ 7፡1 እይ)፡፡ ከሁለቱ እሳቶች በአንዱ መያያዝ አማራጭ የሌለው የመንፈሳዊ ሕይወት ሕግ ነው፡፡ መሃል ሰፋሪነት የሚባል ነገር እዚህ ላይ በጭራሽ አይሠራም፡፡ ምክንያቱም ለሁለት ጌቶች መገዛት ስለማይቻል ነው፡፡ ሁለት ምርጫዎች አሉ፤ ሦስተኛ ግን የለም፡፡ ወይ በመንፈስ ቅዱስ እሳት ተቀጣጥለህ መንፈሳዊ ሕይወት መኖር ወይም በሥጋዊና በሰይጣናዊ እሳቶች ተቀጣጥለህ ሥጋዊ ኑሮ መኖር፡፡ ኢዮብ የጠቀሰው ሰልፍ ብዙ ጊዜ በሰው ሕይወት ውስጥ የሚከሰተው ሰው ለሁለት ጌቶች ለመገዛት ሲሻ ነው፡፡ ትክክለኛ ምርጫን ለማድረግ የሁለቱንም እሳቶች ምንነት ማወቁ ተገቢ ስለሆነ በጥቂቱ እናያቸዋለን፡፡ አስቀድመን ስለ ትንሹ (ሥጋዊው) እሳት ጥቂት እንበል፡፡