እዝነ ኅሊና

እዝነ ኅሊና፣ እዝነ ሥጋ የሚባል ነገር አለ፤ ልክ ዓይነ ሥጋና ዓይነ ኅሊና እንደሚባለው ማለት ነው፤ ሥጋ ግዙፍ ነገርን ስለሚያመለክት የሚታይና የሚዳሰሰውን ይወክላል፡፡ እዝነ ማለት ደግሞ በግእዝኛ ጆሮ ሰለሆነ እዝነ ኅሊና በግዙፉ ሥጋዊ ጆሮ ጠለቅ ብሎ በማይታይ ሁኔታ በውስጣችን ከነገሮች መርገብገብ ያልሆነውን አይነት ድምጽ ወይም የዝምታ ድምጽ የምናዳምጥበትን ተፈጥሮ ይወክላል፡፡

ይህን መሰል ድምጽ ጊዜ ሰጥተነውና ሁኔታዎችን አመቻችተን ማዳመጥ ወይንም መታዘዝ ከቻልን የእረፍትና እፎይታ ምንጭ ሊሆንልን የሚለንን ተቃራኒ ስንታዘዝ እረፍተ ቢስነትና ቁጭት ሊፈጥርብን ይችላል፡፡ እነዚህን ሁለት አይነት ጆሮዎችና ድምጾች ጐላ አድርገው የሚያሳዩንን አንዳንድ የወንጌል ክፍሎችን እንውሰድ፡፡ 

በመጀመሪያ የአመንዝራይቱን ሴት ታሪክ እናስታውሰ ዮሐ. 8፡1-11  እነዚህ ሰዎች ይህችን ሴት ወደ ኢየሱስ ሲያወጧት ብዙ መክረዋል ዶልተዋልም፤ ሤራቸው ሴቲቱን ለመውገር ብቻ ሳይሆን አየሱስንም አጣብቂኝ ውስጥ ለማስገባት ጭምር የታለመ ነበር፡፡ ምክንያቱም እሱ አትውገሯት ካለ የሙሴን ሕግ አፍራሽ  ትወገር ካለም ከእነርሱ እንደ አንዱ ሊሆንና ለሕዝቡ ሊያሳጡት የሚችሉት ነገር ያገኙ ዘንድ አስበው ነበር፡፡ ወደ እርሱ ሴቲቱን ይዘው ከመምጣታቸው በፊት እንዲህ ካለን እንዲህ እንለዋለን ብለው ለእዝነ ሥጋቸው ብዙ አውርተዋል፡፡ ሆነው ግን ጠብቀው የነበሩትን የዝም ብለው እሺታ ወይም የበላ ልበልሃ አይነት ንግግር አልጠበቃቸውም፡፡ በዝምታ በጣቱ መሬት ላይ ከሞነጫጨረ በኋላ አንዲት ነገር ብቻ ተናገራቸው፡፡ “ከእናንተ ኃጢአት የሌለበት አስቀድሞ በድንጋይ ይውገራት አላቸው።” ዮሐ 8፡7

ይህ ንግግሩ ለእዝነ ሥጋቸው ሲሆን እዝነ ኅሊናቸው ውስጥ ግን ሊሞግቱት የማይችሉትን ጩኸት ለቀቀባቸው፤ በርግጥም ሴቲቱን ለመውገሪያ ካመጡት ድንጋይም በላይ የበዛና የከበደ ውስጣዊ ድምጽ ነበርና በውጭ ትንሽ በውስጥ ግን ብዙ በሚናገረውና በጸጥታ ከሚያያቸው “ሰው” ከትልቅ እስከ ትንሽ መሸሽ ጀመሩ፤ ወዴት? ምንአልባት መጠጊያ ይሆናል ብለው ወዳመኑበት ውጫዊ ጫጫታ፡፡ ሌላኛው ወንጌላዊ ምሳሌያቸው ይበልጡት በእለተ ሆሳእና እና በሰሙነ ሕማማት የምናስታውሳቸው ክንዋኔዎች ናቸው፡፡ በእለተ ሆሳዕና ሕዝቡ በየጐዳናው የዘንባባ ዝንጣፊ በመያዝና ልብሳቸውን  በማንጠፍ “ሆሳእና! ለዳዊት ልጅ ምሰጋና …” በማለት እነርሱን ከሮማውያን አገዛዝ ብቻ ነጻ እንደሚያወጣቸው አንድ መሲሕ አድርገው ያስቡት ነበር፡፡ ኢየሱስ ግን በአንዲት የአህያ ውርንጭላ ላይ ተቀምጦ በዝምታ ወደ ኢየሩሳሌም እንደገባ እናነባለን፡፡ ምናልባት ኢየሱስ ሕዝቡ ስለርሱ ያለውን ስእል ቢስማማበት ኖሮ “አዎን ታያላችሁ ከዚህ የባዕድ አገዛዝ ቀንበር በቅርቡ ነጻ አወጣችኋለሁ ወዘተ” እያለ ወደ ከተማይቱ በገባ ነበር፤ ነገር ግን ሕዝቡ የእርሱን ማንነት እንዳልተረዳው ስላወቀ ሊቀበል ያለውን የመስቀል መራራ የመስቀል ጽዋ በማሰብ ድላዊ ለሆነው ለአባቱ ፍቃድ በመታዘዝ ተጓዘ፡፡ ይህን የመሰለ የዝምታ አገባብ በራሱ ለሕዝቡ ግራ የሚያጋባ ነበር፤ ይበልጡንም ደግሞ ቀጥለው ባሉት ቀናት ያለምንም ተቃውሞ ኢየሱስ በካህናት አለቆች መያዝና መታሰር ሲጀምር ይህን ዓይነት ዝምታ የሚፈልጉት ነገር አልነበረምና ከካህናት አለቆችና ጸሐፍትና ጋር በመሆን ዘግናኝ የሆነውን “ስቀለው” ለሚለው ጩኸታቸው ራሳቸውን አዘጋጁ፡፡

ጲላጦስ ሊቀካህናት ኢየሱስን የከሰሱት በቅናት መሆኑን ቢያውቅምና የኢየሱስ የዋህነት ቢረዳውም ለፍርዱ የሚያግዘውን ንግግሮች ከኢየሱስ አፍ ለመስማት ፈልጐ “በርግጥ አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን?” በማለት ሲጠይቀው ኢየሱስ ለጲላጦስ እዝነ ሥጋ ብዙ አስረጂ ነገሮችን መዘርዘር አልፈለገም፡፡ “አንተ ራስህ እያልከው ነው” ከማለት ሌላ ተጨማሪ ንግግር አላበዛም። ይህ መልስ ጲላጦስን ለብዙ ጥያቄ ገፋፋው ኢየሱስ ግን መልሱ ዝምታ ሆነ፡፡ በዝምታው ጲላጦስ ራሱ በጣም ተገረመ፡፡ ይህ ዓይነት የኢየሱስ ውጫዊ ዝምታ ለጲላጦስ እዝነ ኅሊና ከባድ መልእክት ነበረው፤ ስለዚህም ጲላጦስ ለዚህ ውስጣዊ ጩኸት ማብረጃ ይሆነው ዘንድ ውሃ አስመጥቶ “ከደሙ ነጻ ነኝ” በማለት ታጠበ፡፡ ይህ የኢየሱስ አስደናቂ ጸጥታ እዚያ ተሰብስቦ ለነበረው ሕዝብ ሸክም ሆኖ ስለተሰማቸው ወንጌሉ እንደሚለው ከበፊቱ በበረታ ድምጽ “ስቀለው” እያሉ መጮኻቸውን ቀጠሉ፡፡ በዚህ መልኩ እነሱ ለእዝነ ሥጋ ሲጨኹ ኢየሱስም ለእዝነ ኅሊና በዝምታ ሲጮኽ የመስቀሉ ፍርድ ተፈጸመ፡፡ ይህ የክርስቶስ መስቀል የክርስቶስ ታሪክ ፍጻሜ እንዳልሆነ ወንጌልና እምነታችን ይነግረናል፡፡ ኢየሱስ ከሙታን በመነሣት የበኹር ሆኖ ለሕዝቡ ከመናገር ያቋረጠበት ጊዜ የለም፡፡ ዛሬም በተለያየ መልክ የሚናገረን ቢሆንም ኀያልና የበረታው ድምጹ በውስጣችን ለእዝነ ኅሊናችን የሚናገረን ነውና ልባችንን ለዚህ ድምጽ እናስገዛው፡፡ ብዙ ድምጾች ለሥጋዊው ጆሮአችን ይጮኻሉ በነሱ ሳንገደብ ስለእኛ ሲል የተሰቀለውን የሞተውንና የተነሳውን ዛሬም እንዲሁ እጅግ የሚያፈቅረንን የኢየሱስ ድምጽ እንታዘዘው፡፡