ከእናንተ ጋር ይህን ፋሲካ ልበላ እጅግ እመኝ ነበር

Written by Super User on . Posted in የተለያዩ አስተንትኖዎችና አስተምህሮዎች


The Last Supperኢየሱስ ወደ ሰማያዊ አባቱ የሚመለስበት ጊዜ ሲደርስ ያፈቅራቸው ለነበሩ ሐዋርያቱ የፍቅርሩን የመጨረሻ ምልክት አሳያቸው፡፡ ዮሐ. 13፡1 ይሁዳ ከጻፊዎችና ከሊቃነ ካህናት ጋር ተስማምቶ በእጃቸው አሳልፎ እንደሚሰጠው ሲያውቅ ሐዋርያት የሚደርስባቸውን መከራ አሰታወቃቸው፡፡ ከእነርሱም ጋር የመጨረሻ ትልቅ ምሰጢር ያለው እራት በላ፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ ፋሲካን ከእነርሱ ጋር አከበረ፡፡

እርሱ ይፈልገው እንደነበረ ከሐዋርያቱ ጓደኞች በአንዱ ቤት ተሰበሰቡ “ከመከራዬ በፊት ከእናንተ ጋር ይህን ፋሲካ ልበላ እጅግ እመኝ ነበር” ሉቃ. 22፡2ዐ አላቸው፡፡ ሲበሉም ሳለ እንጀራውን አንስቶ የምስጋና ጸሎት ወደ አባቱ ካቀረበ በኋላ እንጀራውን ባርኮ ቆረሰው፡፡ ከዚያም ለሐዋርያቱ “እንካችሁ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው” ሉቃ. 22፡19 እያለ ሰጣቸው፡፡ ቀጥሎም ጽዋውን አንስቶ ጸሎት ካደረገ በኋላ “እንካችሁ ጠጡ ለኃጢአት ስርየት ለብዙዎች የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው” አላቸው፡፡ ሉቃ. 22፡2ዐ በዚህም ኢየሱስ ከሐዋርያቱና ከሁሉም ተከታዮቹ ጋር እስከ ዓለም መጨረሻ ድረስ በምድር የሚኖርበትን ምስጢረ ቁርባን ሠራ፡፡ ከበሉም በኋላ የልቡን ሐዘን ገለጸላቸው፡፡ “ከእናንተ አንዱ ይክደኛል” አላቸው ማር.14፡18 ሁሉም በጣም ደነገጡ እርስ በርሳቸውም ተያዩ “እኔ እሆን?” እያሉ ተጠያየቁ፡፡ ማር. 14፡19 እንደገና ኢየሱስ ጠላቶቹ ይዘውት ሁሉም በፍርሃት ጥለውት እንደሚሸሹ አስታወቃቸው፡፡

በልተውም ከጨረሱ በኋላ ኢየሱስ ወገቡን ሸብ አድርጐ ውኃ በሳህን አድርጐ እግራቸውን ማጠብ ጀመረ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ጋ ሲደርስ ግን ገርሞት መታጠብን እምቢ አለ፡፡ ኢየሱስ ግን “ ካልታጠብክ ከእኔ ጋር ህብረት የለህም” ዮሐ. 13፡ 6-9 ሲለው ፈርቶ ታጠበ፡፡ እግራቸውን ካጠበ በኋላ “ያደረግሁላችሁን አስተዋላችሁን? እናንተ መምህርና ጌታ ትሉኛላችሁ እንዲሁም ነኝና መልካም ትላላችሁ፡፡

“እንግዲህ እኔ መምህርና ጌታ ስሆን እግራችሁን ካጠብሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል” ዮሐ. 13፡ 12-14 እያለ ተናገራቸው፡፡ ቀጥሎም ደግሞ “አዲስ ትዕዛዝ እሰጣችኋለሁ እርስ በርሳችሁ ተፋቀሩ… ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚያ ያውቃሉ” ዮሐ. 13፡34 አላቸው፡፡ ከዚህም በኋላ ይዟቸው ወደ ጌተሰማኒ ሄደ፡፡ እዚያ ሲደርስ ሌሎችን ትቶ ጴጥሮስን፣ ዮሐንስና ያዕቆብን ለይቶ ወሰዳቸው ጥቂት እንደተጓዙም እነርሱን ትቷቸው ሄደ፡፡ ተንበርክኰም ጸሎት ማድረግ ጀመረ፡፡

የሕማማቱ ከባድነት ታየው ወደ ሶስቱ ተመልሶ “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች” አላቸው፡፡ ቀጥሎም ደግሞ “አባቴ ሆይ ይህችን ፅዋ ሳልጠጣት ታልፍ ዘንድ የማይቻል እንደ ሆነ እንደ ፈቃድህ ይሁን” ማቴ. 26፡ 38-39 እያለ ጸለየ፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ እያለ ይሁዳ ከጠላቶቹ ጋር መጣ፡፡ ወደ እርሱም ቀርቦ “መምህር ሆይ ሰላም ላንተ ይሁን” እያለ ሳመው፡፡ እነርሱም በፍጥነት ያዙት እጆቹንም አስረው መሰዱት፡፡

ኢየሱስ የፍቅሩ መጨረሻና ዋና ምልክት አድርጐ የተወልን በዚህ በስደት ሕይወት መንፈሳዊ ስንቃችን እንዲሆን ፈልጐ ቅዱስ ቁርባንን ሠራልን በደስታ እናመስግነው፡፡ ለዚህ የምስጢራት ራስ ለሆነው ቁርባን በልባችን ተደፍተን እንስገድለት፡፡ የልባችን ምኞትም እሱ ይሁን ዘወትር ከእርሱ ጋር መሆንን እንፈልግ፡፡

ኢየሱስ ለሐዋርያቱ እግራቸውን በማጠብ የተወልንን አብነት፣ ፍቅር፣ ትሕትና እንመልከት፡፡ እርሱ በመጨረሻ የተማፀነን የእርስ በርስ ፍቅር በማስታወስ በተግባር እናውለው፡፡ ተከታዮቹ መሆናችን የሚታወቀው በሌላ ሳይሆን ባልንጀራችንን በማፍቀር ነው፡፡