“በአዲስ ዘመን አዲስ ነገር!” ግን እንዴት?

“በአዲስ ዘመን አዲስ ነገር!” ግን እንዴት?

2010 Addis ametበሕይወታችን አዲስ ነገር ሲባል ደስ የሚለንን ያህል ለመቀበል ግን ዝግጁ መሆን የብዙዎቻችን ላይሆን ይችላል፤ በተለይ የያዝነውን ወይም አሮጌ ነገራችንን የሚያስለቅቅ አዲስ ነገር ስጋት ቢጤ ስለሚዳበለው ለማናውቀው ስጋት ስንል የምንናፍቀው አዲስ ነገር እንዲያልፈን እንገፋፋለን እናም ጊዜው በ‘አዲስነቱ’ ሲቀጥል እኛ በድሮ ማንነታችን እንጓዛለን።

በአዲስ ዓመት ዋዜማ በባህላችን ችቦ በመለኮስ የመልካም ነገር መገለጫ የሆነውን ብርሃንን እያየን አዲሱን ዓመት በብርሃን ተምሳሌትነት በመመኘት በብርሃን የመቀብል ፍላጎታችንን እንገልጻለን። በተጫባጩ ሕይወታችን ግን ጨለማው ቢያስጠላንም ብርሃኑ ስለሚያስፈራን ጨለማው ውስጥ ለመቆየት እንመርጥ ይሆናል፤ አንድም ላለማየት አሊያም ላለመታየት!

ክርስትና ግን የብርሃንና ያለመደበቅ ሕይወት ነው፤ “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ። በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም። መብራትንም አብርተው ከዕንቅብ በታች አይደለም እንጂ በመቅረዙ ላይ ያኖሩታል በቤት ላሉት ሁሉም ያበራል። መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ” /ማቴ 514-16/። ስለዚህም በአዲስ ዘመን አዲስ ነገር ይሆን ዘንድ ከጨለማ ወደ ብርሃን፤ ከአሮጌው ነገሮቻችን ወደ አዲሱ መውጣት ያስፈልጋል።

ይህን መሰል ወደ አዲስ ነገር የመሸጋገር ፍላጎት በዘመናችን የክርስትና ስብከቶች ላይ ዋና አጀንዳ የሆነ ይመስላል። ነገሩ የሰው ልጅ ባለው ነገር መርካት ስለሚከብደው ‘ስኬት’፣ ‘ብልጽግና’፣ ‘ከፍታ’፤ ‘ሙላት’፣ ‘ግልጸት’፣ ‘አዲስ መልእክት’፣ 'በረከት'፣ ‘ትንቢት’...ወዘተ ባጠቃላይም ‘ተአምር’ የሚል ነገር ልቡን ያማልለዋል። አዬ! ክርስቶስ እነዚህን ቃላት ብቻ ቢጠቀም ኖሮ እናም "የገዛ ራስችሁን መስቀል ተሸከሙ፣ ራሳችሁን ካዱ፣ እኔን ተከተሉ፣ ያለህን ሽጠህ ለድሃ ስጥ..." የሚሉትን ንግግሮቹን ደግሞ ቢያስወግድ ምንኛ ተከታዮችን አፍርቶ ጠላት የሚሆነው ሰው እንኳ በጠፋ ነበር!

ክርስትና በጤናና በብልጽግና ስም ውጩን ሞልቶ ውስጡን ባዶ ለማድረግ የሚጥር ሳይሆን ይበልጥ የውስጥ ሙሉነትን የሚሰብክ እምነት ነው፤ እንግዲህ ለክርስትና ቅድሚያው የነገሮች መሙላት ሳይሆን የማንነት ምልአት ነው። “ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል” /ማቴ 6፥33/። እንዲሁም ቅ. ጳውሎስ “የእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቅና ሰላም በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ደስታ ናት እንጂ መብልና መጠጥ አይደለችምና” /ሮሜ 14:17/ ይላል። እነዚህና መሰል ጥቅሶች ክርስትና ከጠንቋይ ጩኸት ጋር በተመሳሰለበት ዘመን ቅድሚያ መስጠት ያለብንን ነገር እንድናስተውል የሚጋብዙን ሃሳቦች ናቸው።

በአዲስ ዓመት አዲስ ነገር መጠበቅ ካለብን በኛ ሕይወት ውስጥ እየሆነ ያለውን የእግዚአብሔር ሥራ ማስተዋል መቻል ነው፤ በሕይወታችን ያለማቋረጥ ተአምራት ይከናወናሉ። በየቀኑ እግዚአብሔር ይናገረናል! የኛ አቻ ያልሆነ አምላክ በኛ ደረጃ ዝቅ ብሎ በቃሉ ዘወትር ይመራናል፣ ያስተምረናል፣ ሳይንቅ አክብሮ ይናገረናል - ተአምር ነው! እንዲሁም በዮሐንስ ወንጌል ላይ “ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ፤ ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘላለም ይኖራል፤ እኔም ስለ ዓለም ሕይወት የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው። እንግዲህ አይሁድ። ይህ ሰው ሥጋውን ልንበላ ይሰጠን ዘንድ እንዴት ይችላል? ብለው እርስ በርሳቸው ተከራከሩ። ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም። ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ። ሥጋዬ እውነተኛ መብል ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና። ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ እኖራለሁ።” /ዮሐ 6:51-56/ በማለት ብዙዎቹን ያስደነገጠውን የሥጋ ወደሙ ተአምር በየቀኑ በየቤተ ክርስቲያናችን እውነት እያደረገ ኑ! በማለት ይጋብዘናል - ይህም ለማንም ያልሆነ ለኛ ግን በየቀኑ የሚደረግልን ተአምር ነው! እግዚአብሔር በውስጣችን የከበደውን ኃጢአት ተሸክመን አይደለም ከአንድ ዓመት ወደ ሌላ መሻገር ለአንዲትም ሰዓት እንቆይ ዘንድ አይፈቅድምና ምስጢረ ንስሐን ሠራልን - በርግጥ ክርስቶስ በካህኑ አፍ ፈትቼሃለሁ/ፈትቼሻለሁ ሲል መስማት እንዴት ያለ ተአምር ነው!።

እንግዲህ ከመንፈሳዊ ስጦታዎቹ መካከል በየቀኑ የሚሆኑንልንን ተአምራት ማስተዋል ትልቅ የምስጋና ምክንያት ሲሆን በአካላዊ ነገሮቻችን የሚከናወኑትን ማወቅም ሰው ምንኛ የተአምር ፍጡር መሆኑን እንድናስተውል ያግዙናል። እኛን በሕይወት ለማቆየት በውስጣችን የሚከናወኑትን አካላዊ ክንዋኔዎችን ብናውቅ በሆነ አጋጣሚ ስንታመም ምርር የሚለን ነገር እንዳለ ቢሆንም የሚገርመን ነገር ይሄ ሁሉ ነገር በውስጣችን እየሆነ በጤና የመኖራችን ጉዳይ ነው።

እግዚአብሔር ፈቅዶ ይህን ዘመን አዲስ ብለን ስንቀበል መልመድና መዘንጋት የሌለብን ሁልጊዜም አዲሱ ነገር የእግዚአብሔር በውስጣችንና ከኛ ጋር መሆኑን ማወቅ ነው፤ እግዚአብሔርን ዛሬም አዲስ ነገራችን ነህ፤ ሌሎች ነገሮች ብርቅ ሆነውብን አንተን ከማስተናገድ ወደ ኋላ እንዳያስቀሩን አግዘን እንበለው። በዚህም መልኩ ዓመቱን ቅድሚያ ለአምላካችን በመስጥት እናክብረው።

የተባረከ ፪፻፲ ዓ.ም. ይሁንልን!