እምነት ክፍል ፮

532200posterl

የማስተዋል እና የዕውቀት መንፈስ

የማስተዋል መንፈስ ከልቡና ጋር የተሳሰረ የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታ ነው፤ ይህም ሥጦታ ለመለኮታዊ ተግባቦት ክፍት የሚያደርገን የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ስለሆነ ለእግዚአብሔር መገለጥ እና ለእግዚአብሔር ቃል የተዘጋጀን፣ ይህንን መለኮታዊ ምሥጢር የምንቀበል እና በልባችን እየጠበቅን በቀጣይነት የምናሰላስል አማኞች የምንሆንበት ኃይል ነው። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዚህ የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታ ተሞልታ ስለነበር “ነገሩን ሁሉ በልብዋ እያሰበች ትጠብቀው ነበር” (ሉቃ 2፡19)።

የማስተዋል መንፈስ የእግዚአብሔርን ምሥጢር በልብ መያዝ እና ከልብ በሚነሳው ገዢ ሐሳብ ሕይወትን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መኖር የምንማርበት መንፈስ ነው። ይህ መንፈስ “ መዝገባችሁ ባለበት ልባችሁ ደግሞ በዚያ ይሆናልና” (ሉቃ 12፡34) ተብሎ እንደተጻፈ የእግዚአብሔርን ነገር የልባችን ውድ መዝገብ አድርገን መያዝ እንድንችል የሚያበረታን መንፈስ ነው። ጌታ በወንጌል በተደጋጋሚ የሚያሳስበን ቁም ነገር ልባችንን እንድንጠብቅ ነው! ልብ የሰው ልጅ ሰው ሆኖ የመኖሩ ሕልውና ማዕከል በመሆኑ ልባችንን የሚገዛን ሐሳብ ማንነታችንን ደግሞ ይገዛልና መጽሐፍ ቅዱስ “አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ፥ የሕይወት መውጫ ከእርሱ ነውና” (ምሳ 4፡23) እያለ መንፈሳዊ ሕይወት በልብ ባለ ውድ መዝገብ የሚተረጎም እና የሚኖር የዕለት ተዕለት የአስተውሎት ጉዞ መሆኑን ያመላክተናል።

 በዚህ የስተውሎት ጉዞ የእግዚአብሔርን ምሥጢር እያሰላሰልን ነፍሳችን ዘወትር  በማያቋርጥ  የንስሐ፣ የምሥጋና እና የምልጃ ጸሎት በእግዚአብሔር ፊት ሕያው ሆና ትኖራለች። በዚህም አይነት “የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ” (ሮሜ 12፡2) የሚለው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለሮም ክርስትያኖች የሰጠው የመንፈሳዊ ሕይወት መመርያ በማስተዋል መንፈስ ጸጋ በእያንዳንዳችን ሕይወት እየተገለጠ ይበልጡን ክርስቶስን ወደ መምሰል እናድጋለን።

የማስተዋል መንፈስ መልዕልተ ባሕርያዊ ለሆነ መለኮታዊ ፍቅር ክፍት ያደርገናል። እምነት ዘወትር ለፍቅር ክፍት የሆነ ለእግዚአብሔር መገለጥ የሚሰጥ ምላሽ ነው። ስለዚህ በእግዚአብሔር አምናለሁ! እታመንማለሁ! የሚል እምነት ለእግዚአብሔር ፍቅር የተሰጠ ተግባራዊ ምላሽ ነው እንጂ ነገሮችን በማወቅ እና በመረዳት የምንወስነው አእምሮአዊ ቁም ነገር አይደለም። በእምነት በኩል ባገኘነው ጸጋ እግዚአብሔር አሁን እና ዛሬ በሕይወታችን ሕያው ሆኖ ይኖራል፤ እግዚአብሔር አስቀድሞ በአርአያ እና በአምሳሉ በመፍጠሩ፣ በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ሥጋ ለብሶ በመገለጡ ምሥጢር እና በኋላም በምሥጢረ ጥምቀት በእያንዳንዳችን ውስጥ ሕያው ሆኖ ይኖራል። ስለዚህ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህን “መለኮታዊ አሁናዊነት” ለቆሮንጦስ ክርስትያኖች ሲጽፍላቸው “እነሆ፥ የተወደደው ሰዓት አሁን ነው፤ እነሆ፥ የመዳን ቀን አሁን ነው” (2ቆሮ 6፡2) እያለ ያበረታታል።

የማስተዋል መንፈስ በባሕርይዩ ከሌላ የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታ ጋር የተያያዘ ሲሆን ይህም የዕውቀት መንፈስ ነው። የማስተዋል መንፈስ ለእግዚአብሔር መለኮታዊ ሐሳብ እና ቃል ክፍት ስለሚያደርገን ነፍስን የሚያበራ የመለኮታዊ ዕውቀት ብርኀን ወደ ማንነታችን አስኳል ዘልቆ ይደርሳል። በዚህም በማስተዋል በሚገራ ዕውቀት ነገርን ሁሉ እየመረመርን እና መልካም የሆነውን እየያዝን በኢየሱስ ክርስቶስ ባለን እምነት እናድጋለን። መጽሐፈ ምሳሌ ይህንን የብስለት ጉዞ በሚመለከት እጅግ ውብ በሆነ አገላለጽ እንዲህ ይላል “የጻድቃን መንገድ ግን እንደ ንጋት ብርሃን ነው፥ ሙሉ ቀን እስኪሆንም ድረስ እየተጨመረ ይበራል” (ምሳ 4፡18)። በዚህም የዕለት ተዕለት ሕይወታችንን በቀኑ ገጠመኝ በተቃኘ የኑሮ ዘይቤ ሳይሆን ይልቁንም በመለኮታዊ ጥበብ በተቃኘ የሕይወት መንገድ የዕለት ተዕለት ኑሮአችንን በማስተዋል እና በዕውቀት እንድንኖር ያስችለናል።

የማስተዋል እና የዕውቀት መንፈስ በሕይወታችን ትክክለኛ ምርጫ እንድናደርግ ግልጽ የሆነ የሕይወት ራዕይ ይሰጡናል። መጽሐፈ ምሳሌ “ለሰው ቅን የምትመስል መንገድ አለች ፍጻሜዋ ግን የሞት መንገድ ነው” (ምሳ 14፡12) እያለ የምንመርጠውን የሕይወት መንገድ በማስተዋል እና በዕውቀት እንድንመርጥ ይመክረናል።  ማስተዋል ነፍስ በእግዚአብሔር ሰላም ከምትሞላበት እርጋታ የሚመነጭ መለኮታዊ ጥበብ ነው፤ ይኸውም በእግዚአብሔር ሰላም ውስጥ ማረፍን የሚጠይቅ፣ ራስን ለእግዚአብሔር መለኮታዊ ምሕረት አሳልፎ መስጠትን የሚሻ የሕይወት ውሳኔ ነው። ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ የእሥራኤል ሕዝብ በመካከሉ ያለውን የእግዚአብሔርን ሕላዌ ያስተውል ዘንድ፣ በማስተዋሉም ከድካሙ አርፎ እግዚአብሔርን ይታመን ዘንድ “ዕረፉ፥ እኔም አምላክ እንደ ሆንሁ እወቁ” (መዝ 46፡10) እያለ ጥሪውን ያቀርባል። ማስተዋል በእግዚአብሔር መጋቢነት ተማምኖ ማረፍ ነው፤ ማስተዋል እና ዕውቀት ማለት ሕይወትን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የመታዘዝ አብነት፣ በእግዚአብሔር አብ እጆች ውስጥ ለመንፈስ ቅዱስ ሥራ መተው ማለት ነው። ስለዚህም መጽሐፈ ምሳሌ ይህንን ቁም ነገር ሲያስረዳን “የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው” (ምሳ 1፡7) ይላል።

የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታዎች የእግዚአብሔርን ምሥጢር በአእምሮአችን ለመረዳት፣ በልባችን ጠብቀን ለማሰላሰል፣ ሕይወታችንን በዚሁ ምሥጢር ለመቃኘት እንዲሁም  እግዚአብሔር በሕይወታችን ላለው በጎ ዓላማ ክፍት እንድንሆን ያደርጉናል። በዚህም ባልተከፋፈለ ልብ በተትረፈረፈ ሕይወት ለመኖር እና “ወደ ፈተና አታግባን” ለሚለው የዘወትር ጸሎታችን የተገባን እንሆናለን። የዕውቀት መንፈስ በሕይወታችን ከእግዚአብሔር በጎ ዓላማ እና ፈቃድ ጋር የተጣጣመ ውሳኔ ለማድረግ የሚያግዘን መንፈስ ነው። ቅዱስ ዮሐንስ በመልእክቱ “ወዳጆች ሆይ፥ መንፈስን ሁሉ አትመኑ፥ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር ሆነው እንደ ሆነ መርምሩ” (1ዮሐ 4፡1) እያለ የሚያቀርብልን ምክር ሕይወትን እና የሕይወትን መንገድ በማስተዋል እና በእውቀት መንፈስ እንመራ ዘንድ የሚያሳስበን ነው።

ይህን መሰል የሕይወት ውሳኔ ለማድረግ ከሁሉ አስቀድመን እውነትን ማወቅ እና እውነትን መከተል ይጠበቅብናል። እውነትን ወደማወቅ የሚያደርሰን የእግዚአብሔር መንፈስ በውስጣችን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ይንቀሳቀስ ዘንድ በምሥጢረ ጥምቀት ለመንፈስ ቅዱስ ሥራ ክፍት ሆነናል። በዚህ የጥምቀት ምሥጢር አማካይነት በተቀበልነው የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታ ነፍስ ዘወትር እውነትን በመፈለግ ትቃትታለች፤ ለዚህ የነፍስ መቃተት ደረጃ በደረጃ ራሱን እየገለጠ የበለጠ ወደራሱ የሚያቀርባት እና የሚያጽናናት አምላክ በእውቀት እና በማስተዋል መንፈስ መለኮታዊ ምሥጢርን ትረዳ ዘንድ ፈቃዱ ሆኗል። የእሥራኤል ሕዝብ ሕያው ሆኖ የሚኖረው እግዚአብሔር በመካከሉ ያደረገውን የማዳን ሥራ በሚዘክር ሕይወት በየዕለቱ በእግዚአብሔር ፊት በመመላለሱ ነበር፤ ስለዚህ ዳዊት በመዝሙሩ “በመኝታዬ አስብሃለሁ በማለዳም እናገርልሃለሁ” (መዝ 63፡6) እያለ ቀን እና ሌሊት የእግዚአብሔርን ነገር ማሰላሰል ሕይወት ያለው ቁም ነገር መሆኑን ይዘምራል።

የማስተዋል እና የዕውቀት መንፈስ ልብን በእግዚአብሔር ጥበቃ ውስጥ አሳርፎ የልብን ቅጥር ለመንፈስ ቅዱስ ጥበቃ አሳልፎ መስጠትን የሚያስችሉን የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታዎች ናቸው። ራስን ለመንፈስ ቅዱስ አሳልፎ የሚሰጥ የእምነት ጉዞ መንፈስ ቅዱስ በነፍስ ውስጥ ለሚያደርገው እንቅስቃሴ ልብን አሳልፎ የሚሰጥ፣ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን በሚገጥሙን ክስተቶች መካከል የሚናገረውን የመንፈስ ቅዱስን ድምጽ የሚያደምጥ እና ለቤተ ክርስትያን ሕይወት የሚታዘዝ ጉዞ ነው! በመሆኑም “ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁም በምድር ትሁን” ብለን የምንጸልየውን ጸሎት በተግባር ደግሞ እንደንቀበለው እንችላለን።

ሴሞ