11- ሌላው ደቀ መዝሙር፤ ‹‹ኢየሱስ የሚወደው ደቀ መዝሙር››

11

ሌላው ደቀ መዝሙር፤ ‹‹ኢየሱስ የሚወደው ደቀ መዝሙር››

በዮሐንስ ወንጌል በብዙ ቦታ አንድ ደቀ መዝሙር ያለ ስም፣ ‹‹ኢየሱስ የሚወደው ደቀ መዝሙር›› የሚል ሐረግ እናገኛለን፤ (ንጽ. ዮሐ 1፡ 35-40፤ 13፡ 23-26፤ 18፡ 15-16፤ 19፡ 26-27፤ 20፡ 2-8፤ 21፡ 2፣7፣20-24)፡፡

-    እርሱ እውነትን እየፈለገ ያለ ደቀ መዝሙር ነው፡፡ እርሱ አጥማቂው ዮሐንስን መከተል ጀምሮ ነበር፡፡ አጥማቂው ዮሐንስ ‹‹እነሆ የእግዚአብሔር በግ›› ሲል በሰማ ጊዜ ክርስቶስን ተከተለ፡፡ እርሱ ሄዶ አየና ከእርሱ ጋር ቆየ፡፡ (ንጽ. ዮሐ 1፡ 35-40)

-    እርሱ በመጨረሻ እራት በኢየሱስ ጎን የተቀመጠና ራሱን ወደ ኢየሱስ ልብ አስጠግቶ የነበረ ደቀ መዝሙር ነው፡፡ እርሱ ኢየሱስን አሳልፎ የሰጠው የይሁዳ ተቃራኒ ነበር፡፡ እርሱ የኢየሱስ ልብ ያውቅ ነበር፡፡ በኢየሱስና በእርሱ መሐል ትልቅ ቅርበት፣ እምነት፣ ፍቅር፣ መረዳዳትና ስምምነት ነበራቸው፡፡ (ንጽ. ዮሐ 13፡ 23-26)፡፡

-    እርሱ ኢየሱስን በሕማማቱ ጊዜ እንደ ጴጥሮስና እንደ ሌሎች ደቀ መዛሙርት ሳይክዳው በጀግንነት ይከተለው የነበረ ደቀ መዝሙር ነው (ንጽ. ዮሐ 18፡ 15-16)፡፡

-    ለእርሱ ኢየሱስ ‹‹ይህችውልህ እናትህ›› አለ (ዮሐ 19፡ 27)

-    እርሱ ማርያምን ወደ ቤቱ ወሰዳት፡፡ (ዮሐ 19፡ 27)

-    እርሱ ስለ ኢየሱስ ሞት ምስክር ነበር፡፡ (ዮሐ 19፡ 30)

-    እርሱ ፋጥኖ የሮጠና ቀድሞ ወደ መቃብሩ ደርሶ ጴጥሮስን የጠበቀ ደቀ መዝሙር ነው፡፡ ጴጥሮስ ወደ መቃብር ገብቶ ካየ በኋላ እርሱም ገብቶ አየና አመነ፡፡ (ዮሐ 20፡ 2-8)

-    እርሱ ከሞት የተሳውን ኢየሱስን ያወቀ፣ ኢየሱስ እስኪመጣ የጠበቀና ስለ ክርስቶስ የመሰከረ ደቀ መዝሙር ነው (ንጽ. ዮሐ 21፡ 2፣7፣20-24)

ኢየሱስ ይወደው የነበረው ደቀ መዝሙር የእወነተኛ ተምሳሌትና ኢየሱስን የተቀበለና በስሙ ያመነ አርአያ የሚሆን ደቀ መዝሙር ሲሆን (ንጽ. ዮሐ 1፡ 12-13) ሁል ጊዜ ለኢየሱስ ታማኝ ሆኖ እስከ መጨረሻ የተከተለና ለእርሱ ምስክርነት የሰጠ ነው፣ ለዚህ ደቀ መዝሙር (ለእያንዳንዱ ክርስቲያን) ኢየሱስ እናቱን ሰጠ እና እውነተኛ ደቀ መዝሙር ስለሆነ እርሷን ወደ ቤቱና ወደ ልቡ ወሰደ፡፡ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እዚህ ጋ የደቀ መዝሙር (የክርስቶስ አካል)፣ የቤተ ክርስቲያን እናት ትሆናለች፡፡

ዮሐንስ በወንጌሉ ‘lambanin’ (‹‹ላምባነይን›› መቀበል) የሚለውን የግሪክ ቃል ሦስት ጊዜ ይጠቀማል፡፡

እውነተኛ ደቀ መዝሙር፤

  1. ኢየሱስን (ቃል ሥጋ የሆነውን) ይቀበላል (ዮሐ 1፡ 12)
  2. እናታችን ማርያምን ይቀበላል (ዮሐ 19፡ 27)
  3. እናም መንፈስ ቅዱስን ይቀበላል (ዮሐ 20፡ 22)፡፡

እውነተኛ ደቀ መዛሙር ኢየሱስን ይቀበላል፣ እስከ መስቀሉ ይከተለዋል፣ ስለ እርሱም ይመሰክራል፣ መንፈስ ቅዱስን ይቀበላል፣ እመቤታችን ቅድስተ ድንግል ማርያምንም እንደ እናት ይቀበላል፡፡

ኢየሱስ የሚወደውን ደቀ መዝሙር መምሰል እንድንችል እናታችን ማርያም እንድትረዳን እንለምናት፡፡

እንጸልይ፡-

አባት ሆይ ድንግል ማርያም የክርስቶስና የቤተ ክርስቲያን እናት እንደሆነች እንደምናውጅ ሁሉ ከልጅህ ጋር ያለን አንድነት ደኅንነት እንዲያመጣልን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት እንለምንሃለን፡፡ አሜን፡፡