እግዚአብሔር ዘወትር ያስደምመናል!

ር.ሊ.ጳ. ቤኔዲክቶስ 16ኛው የጌታችንን ልደት በዓል ምክንያት በማድረግ በቢቢሲ ሬድዮ ለመጀመሪያ ጊዜ መልእክት ማስተላለፋቸው ተገለጠ። በመልእክታቸውም ለሕሙማን፣ ለአረጋውያንና በማንኛውም ዓይነት ችግር ውስጥ ለሚገኙ ሁሉ እንደሚጸልዩ አሳውቀው፤ በቅርቡ በእንግሊዝ አገር አድርገውት የነበረውን ጉብኝት በታላቅ ፍቅር እንደሚያስታውሱትና ይህን የገና መልእክታቸውን ለሚያዳምጡ ሁሉ ዳግም መልካም ምኞት ለመግለጽ በመቻላቸውም ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል።

"በስኮትላንድ፣ ኢንግላንድና ዌይልስ የምትገኙና የእንግሊዘኛ ተናጋሪ አገር ወዳጆቼ ሆይ!

በዚህ በተቀደሰ የገና ወቅት በልዩ ሁኔታ በጸሎቴ እንደማስታውሳችሁ ለማሳወቅ እወዳለሁ። ስለ ጌታችን ልደት ስናስብ እስራኤላውያን ነጻነታቸውን ዳግም የሚመልስላቸውን መሪና መሲሕ ይጠባበቁ እንደነበር እናስታውሳለን፤ በቤተልሔም የተወለደው ሕፃን በርግጥም ነጻነትን አምጥቷል፤ ሆኖም ግን ያመጣው ነጻነት በዚያን ጊዜና ቦታ ብቻ የተገደበ ሳይሆን ለመላው ዓለምና ታሪክ ሁሉ አዳኝ ይሆን ዘንድ ነው። ይህም ነጻነት አንድም በፖለቲካ አሊያም በወታደራዊ ኃይል ያይደል በክርስቶስ የመስቀል ላይ አሳፋሪ ሞት አማካይነት ሞትን ለአንዴና ለመጨረሻ በመደምሰስ የተገኘ ነው።" ብለዋል።

ር.ሊ.ጳ. ለአዳማጮቻቸው ማንኛውንም ዓይነት የሕይወት ጨለማ ለማስወገ ወደ ኢየሱስ እንዲያቀኑ አሳስበው "አምላካችንን ለመልካምነቱ እናመስግነው፤ ከማንኛውንም ዓይነት ሸክም ነጻ እንደሚያደርገን በደስታ በአካባቢያችን መልካሙን ዜና እናብስር፣ እርሱ ተስፋና ሕይወትን ይሰጠናል።" በማለት አበረታትተዋል።

"እግዚአብሔር ለተስፋ ቃሉ ታማኝ ነው፤ ሆኖም ግን የሰጠንን ተስፋ የሚፈጽምባቸው ሁኔታዎች ሁሌም ያስደምመናል፤ ያስደንቀናል" በማለት ኢየሱስ ሕፃን ሆኖ ተወልዶ ሰው በመሆን ያዳነንን ሁኔታ የገለጹበት የአጭር ደቂቃውች የሬድዮ መልእክታቸውን ደምድመዋል።

 

ምንጭ - http://www.bbc.co.uk/news