የብፁዕ ገብረ ሚካኤል አጭር ሰማዕታዊ ገድል

ብጹዕ ገብረሚካኤል ሰማዕትየብፁዕ ገብረ ሚካኤል አጭር ሰማዕታዊ ገድል

ብጹዕ ገ/ሚካኤል በ 1788 በጎጃም ልዩ ስሙ ዲቦ በተባለ አውራጃ ተወለዱ። ከልጅነታቸው ጀምረው የአገራችንን ትምህርት ማለትም ዜማ፡ ቅዱሳት መጻሕፍትንና ቅኔ ወዘተ. . . ለመማር ተሰማሩ። በትምህርት ትጋታቸውና በውጤታቸው መምህሮቻቸው በጣም አደነቁዋቸው። ይህን ሁሉ መንፈሳዊ እውቀት ካካበቱ በኋላ ራሳቸውን ለእግዚአብሔር በሙሉ ልባቸው ሊሰጡ ፍላጎት ዕቅድ ስለነበራቸው በ25 ዓመታቸው በመርጡለ ማርያም ገዳም ገቡ። በጣም ጎበዝና ከፍተኛ የዕውቀትና የእውነት ጥማት ስለነበራቸው ከገዳም ወደ ገዳም ይዘዋወሩ ነበር። እንደዚህም እያሉ ሲታገሉ ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ሕሊናቸውን ያስጨንቅ የነበረው የሃይማኖት ልዩነትና ጭቅጭቅ ገጠማቸው።

በዚህም ዕረፍት አጥተው ተጨንቀው "ጌታዬና መድኃኒቴ፡ ጽድቅ የት እንደምትገኝ ግለጥልኝ፡ አንተ ጻድቅ እንደሆንክ አምናለሁ። ጻድቅ ነኝ፤ ትክክለኛው የኔ ነው ወዘተ . . . የሚሉኝ ብዙዎች ናቸው፤ እኔ ግን ጽድቅን ሳትበላሽ ከምንጭዋ ላገኛት እፈለጋለሁ" እያሉ ጸለዩ። እግዚአብሔርምጸሎታቸውንና የልባቸውን ምኞት ሰምቶ ከቅዱስ ኣቡነ ያዕቆብ ጋር አገናኛቸው። ብጹዕ ገ/ሚካኤል በቅዱስ አቡነ ያዕቆብ ሕይወት ዘመን በብዙ የሃይማኖት ትምህርት ታነጹ።

በ 1851? በሀገሪቱ ፓትርያርክ ስላልነበር በደጃች ውቤ ተመርጠው ወደ እስክንድርያ ፓትርያርክ እንዲሰጣቸው ሊጠይቁ መልእክተኛ ሆነው ወደ አሌክሳንድርያ ተላኩ :: ከመልእክተኞቹ አንዱ ደግሞ በዛን ግዜ ጥሩ ዝናና ተቀባይነት የነበራቸው ካቶሊካዊው አባ ያዕቆብ (አሁን ቅዱስ አቡነ ያዕቆብ ) አንዱ ነበሩ :: በዚህ አጋጣሚ ስለሃይማኖታቸው ለመወያየት ጥሩ አጋጣሚ አገኙ :: አባ ያዕቆብ ለሚያቀርቡላቸው ለነበረው <ክርስቶስን > በሚመለከት በደንብ ያውቁ ስለነበረ፤ እነሱን ለማስረዳት የሰጡት መልስ <ስለ ሥላሴ በምታስተምሩት ትምህርት ላይ: አንድ አምላክ ሦስት አካላት ትላላችሁ:: ታዲያ የኢየሱስ አንድ አካል ሁለት ባሕሪ እንዴት ሊከብዳችሁ ቻለ?> እንደዚህ እየተጠያየቁ: አንዱ ከአንዱ እየተማረ ከእስክንድርያ ወደ ቤተልሔም: ቅ .ጴጥሮስ ንግደት በአንድ ላይ ፈጸሙ ::

ከ1846-1854 ካቶሊክ ስለሆኑና በፓትርያርክ አቡነ ሰላማ ትእዛዝ በተለያየ ጊዜ ወደ እስር ቤት ወረዱ:: በእስር ቤት ውስጥ በጣም በሚያሰቅቅ ሁኔታ በዱላ ተደበደቡ:: ምንም ለውጥ ስላላሰዩና በእምነታቸው ጸንተው ስለተገኙ እንደገና ለማረጋገጥ ብለው አቡነ ሰላማ: አባ ገ/ሚካኤልን ከእስር ቤት አስጠርተው ስለእምነታቸው ጠየቁዋቸው:: ምንም ለውጥ ስላላገኙባቸው ወደ ንጉሡ (አጼ ቴዎድሮስ) አሳልፈው ሰጡዋቸው:: ንጉሡም በግርፋት እንዲቀጡ አዘዙ:: አሁንም ከእምነታቸው ነቅነቅ ስላላሉ ንጉሡ ወታደሮቹን ሁላችሁም በአንድ ጊዜ ግረፉዋቸው ሲሉ አዘዙ:: 150 ጅራፍ ፊታቸው ላይ ተገረፉ (ያቺ የቀረችውን አንድ ዓይናቸውን ሊያጠፉ):: በዛ የነበሩ ስቃያቸውን የሚመለከቱ የነበሩ ሲመሰክሩ <የገራፊዎቹን ብዛት : የግርፊያውን ቁጥር : ይህን ያህል ተብሎ መናገር አይቻልም > በማለት የግርፊያውን አሰቃቂነት ይገልጻሉ:: በዛ የነበሩ ሰዎች በቃ <ሞተዋል >: እያሉ እየተነጋገሩ እያሉ : ሰማዕቱ (አባ ገ/ሚካኤል ) ከዛ ሁሉ ድብደባና ግርፊያ በኋላ : ምንም እንዳልሆኑ፡ ፊታቸው ላይ ቁስል የምትባል ሳትታይባቸው : አይናቸው ከበፊቱ የበለጠ ብሩሕና ደስተኛ ሆነው ወደ እስር ቤት ሲያመሩ አይዋቸው። ከሁለት ቀን በኋላ በንጉሡ ትእዛዝ መሠረት በሰንሰለት ታስረው ከወታደሮች ጋር በእግር እንዲጓዙ ተደረገ :; በዚህን ጊዜ ዕድሜያቸው ከ 60 በላይ ነበር:: ይህንን ስቃያቸውን የተመለከቱ ወታደሮች በጣም ከመገረምና ከመደነቅ የተነሳ አባ ገ/ሚካኤልን <ቅዱስ ጊዮርጊስ > በሚል ቅጽል ስም ይጠሯቸው ጀመር:: ምክንያቱም ቅ .ጊዮርጊስ 7 ጊዜ ሞቶ ተነሳ የሚባል ታሪክ ስላለ:: እንደገና ንጉሡ አጼ ቴዎድሮስ እና አቡነ ሰላማ በተገኙበት እንደገና አባ ገ/ሚካኤልን ስለእምነታቸው ጠየቁዋቸው:: አባ ገ/ሚካኤልም "አምባገነኑና እውነተኛው የክርስቶስ ጠላት ሆይ ስማ! ዛሬ በር.ሊ.ጳ. ፒዮ 9ኛ በምትመራውና በምታስተምረው ካቶሊክ ቤ/ያንና: እኔ የእምነት ልጁ - እስከመጨረሻው የሕይወት እስትንፋሴ ድረስ - ፍጹም አምላክና ፍጹም ሰው በሆነው ክርስቶስ አምናለሁ - ደግሞም መሞት የምፈልገው በዚህ እምነት ነው " ሲሉ መሰከሩ :: በዚህ ምስክርነታቸው ደግሞ ሞት ተፈረደባቸው: :: ነሐሴ 23 ደግሞ ስለ ካቶሊካዊ እምነታቸው ብለው በሰማዕትነት ሕይወታቸውን ኣሳልፈው ሰጡ::

ጥቅምት 3/1926 እ.ኤ.አ. በቅዱስ ጴጥሮስ ቤ/ያን በተደረገው መስዋዕተ ቅዳሴ ብጽዕነታቸው ታወጀ:: የኢትዮጵያ ካቶሊካውያን ካህናት አርአያና ባልደረባ (patron) ይባላሉ።

ሰላም ለሞትከ ዕረፍተ ጻድቃን ዘኮነ :

ወኅሉቀ ንርከብ ዘነፍስነ ድኂነ ::

አምሳሊሁ ለኢየሱስ ዘሞተ በእንቲአነ :

ለነኒ ሀበነ ገብረሚካኤል አቡነ

ለነፍስነ ሞገስ ወለልብነ ዛህነ

የጻድቃን እረፍት ለሚመስለው ሞትህ ሰላም ይሁን፡አባታችን ገ/ሚካኤል ሆይ ! ሞትህ ስለ እኛ የሞተውን የክርስቶስን ይመስላል፡አባታችን ሆይ ለነፍሳችን ድኅነት እንድናገኝ ለልባችን ጸጋና እረፍት ስጠን።

የሀገራችን ቅዱስ : ስለ ሀይማኖታቸው ብለው በመስዋዕትነት የሞቱት የብጹዕ ገብረሚካኤል በዓል ነሐሴ 23 ይከበራል ::

ዋዜማው <ተሰአሎ ንጉሥ ለብጹዕ ገብረሚካኤል : ወይቤሎ ንግር ሃይማኖተከ : አውሥኦ ብጹዕ አአምን በኢየሱስ አምላክ ወሰብእ : ወበአሐቲ መንበረ ጴጥሮስ : ሰማዕተ ኮነ በሃይማኖት ወወረሰ መንግሥተ ሰማያት > እየተባለ ይከበራል ;;

ትርጉሙ : <ንጉሡ (አጼ ቴዎድሮስ) ብጹዕ ገብረሚካኤልን ሀይማኖትህን (እምነትህን) ተናገር ብለው ጠየቁት : ብጹዑም አምላክና ሰው በሆነው ኢየሱስና በአንዲት መንበረ ጴጥሮስ አምናለሁ ብሎ ተናገረ : በሰማዕትነት ሞተ : በእምነታቸው ደግሞ መንግሥተሰማይን ወረሱ >

አባ ጸሊ በእንቲአነ : እስመ ጸሎተ ጻድቅ ይሰምዕ እግዚአብሔር