መግቢያ


ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ተናግሮናል (ዕብ.1:1)  መላ ዓለምን በዘለዓለማዊው ቃሉ ፈጥሯልና (ዮሐ. 1:3) በፍጥረታት አስደናቂነትም ይናገረናል። እንዲሁም ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ማለትም በሕግ፣ በነቢያት፣ በወንጌልና በሐዋርያት ጽሑፋት በምናገኛቸው የአፈጣጠርና የደኅንነት ታሪክ ይናገረናል።


እነዚህ ሁሉ የተለያዩ መንገዶች ፍጹም ሆነው የሚስማሙት ሥጋ በሆነው ዘላለማዊው ቃል በኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት ነው። በኢየሱስ አማካይነት  እግዚአብሔር ራሱን ሙሉ ለሙሉ ገለጸ። ይህ ቢሆንም ግን በቃል መናገሩን አልተወም። ኢየሱስ ተናገረ፣ ሰበከ፣ መከረ፣ አስተማረ፣ በቃልም ጮኽ ብሎ ጸለየ። ጥያቄዎችን ጠየቀ፣ ታሪኮችን፣ ምሳሌዎችን ተናገረ፣ በአሸዋ ላይም ሳይቀር ቃላትን ጻፈ።


ቃላት ለሰው ልጅ መደበኛና የተለመዱ የመግባቢያ መንገድ ናቸውና እሱ ስለኛ ሲል ከቃላት ጋር ተቆራኘ። እሱ የኛን ቃላት ቢጠቀምም ቅሉ አምላክም ነውና የርሱ ቃላት እንደኛዎቹ ተራ ሆነው መቅረት አይቻላቸውም፤ የርሱ ቃላት ግልጸትን የተሞሉ ናቸው። የሰው ቃላት ሆነው ዘላለማዊውን የእግዚአብሔር ቃል ይገልጻሉ።  በወንድ በሴት፣ በትንሽና በአዋቂ የሚነገሩ ቃላት ሆነው ሳሉ የሕያው እግዚአብሔር ቃል ናቸው።


በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሕይወት የሌላቸው በድን ቃላትን ሳይሆን ራሱ ኢየሱስን እናገኛለን፦ “የእግዚአብሔር ቃል ሕያውና የሚሠራ ነው” ዕብ.4:12። ስለዚህም ይህ ቃል እኛ እንደፈለግን አጠማዘን ፍላጎታችንን ለማርካት የምንጠቀምበት ዓይነት ቃል አይደለም። ይህ ቃል በነገሮች እንዲሁም በሞትና ሕይወት ሁሉ ላይ በሚያስፈራ ግርማ ሊመጣ ያለው ኢየሱስ ነው። “ዓይኖቹም እንደ እሳት ነበልባል ናቸው፥ በራሱ ላይም ብዙ ዘውዶች አሉ… በደምም የተረጨ ልብስ ተጐናጽፎአል፥ ስሙም የእግዚአብሔር ቃል ተብሏል።” (ራእይ 19:12-13)።


ወደ እያንዳንዳችን ሕይወት ሲመጣም ይህን በመሰለ ሥልጣን፣ እንደ አስተማሪ፣ እንደ አዳኝ፣ እንደ ወንድምና እንደ አምላክ ነው። የእግዚአብሔር ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን በመቀበል ዘላለማዊውን የእግዚአብሔር ቃል ኢየሱስን እንቀበለው።