ዘገብር ኄር

ዘገብር ኄር                         የጸጋ "አትራፊ ነጋዴዎች"

ምስባክ - ከመ እግበር ፈቃድከ መከርኩ አምላኪየ፤ ወሕግከኒ በማእከለ ከርስየ፤ ዜኖኩ ጽድቅከ በማኅበር ዐቢይ።

አምላኬ ሆይ ፈቅድህን ለማድረግ ወደድኩ፤ ሕግህም በልቤ ውስጥ ነው፤ በታልቁ ጉባኤም ጽድቅህን ተናገርኩ። መዝ. 40:8

ንባባት፦- 2ጢሞ.2:1-15 - 1ጴጥ.5:1-11- ሐዋ.1:6-8 - ማቴ.25:14-30

three servants

የዚህ ሰንበት ሥያሜ በግእዝ ገብር ኄር ሲሆን ትርጉሙም ታማኝ፣ ቸር አገልጋይ ማለት ነው። በዛሬው ወንጌል ውስጥ በአገልጋይ መልክ የተንጸባረቁት ሦስት ግለሰቦች በተለያየ ዓይነት ደረጃ ክርስቲያኖችን ይወክላሉ። በጥምቀት ጸጋ ክርስቲያን ከሆንን በኋላ እንደ የአናኗራችንና ለተቀበልነው ወይም ለተሰጠን ጸጋ እንደምንሰጠው ምላሽ ሁኔታችን ይለያያል።

እምነታችን ማለትም ክርስትናችን አንዴ ተቀብለነው ምንም መሥራት ወይም መተባበር የማያስፈልገው ነገር ቢሆን ኖሮ ቀላል ነበር። እውነቱ ግን ይህ አይደለም፤ እምነት ጸጋ ነው ስለዚህም በነጻ የተሰጠን ማለት ሲሆን እንደየትብብራችንና ጥረታችን ደግሞ የተቀበልነው ወይም እንዳልተቀበለ ልንሆንበት የምንችለው ነገር ማለት ነው። ስለዚህም የእምነት ጸጋን ከተቀበልን በኋላ ትብብራችንና ጥረታችን እጅጉን እንደሚያስፈልግ ክርስቶስ በዛሬው ወንጌሉ በተናገረው የአገልጋዮች ምሳሌ በግልጽ ይታያል።

አንዴ ክርስቲያን ሆኛለሁና ድኛለሁ ስለዚህም ከአሁን በኋላ እጆቼ ለጭብጨባና ለአምልኮ ብቻ እንጂ ለበጎ ሥራ አይንቀሳቀስም፣ ጌታ እምነትን ሲሰጠኝ ከሥራ ገላገለኝ እንዳንል እምነትን መቀበል ሌላ፤ አማኝ መሆን ደግሞ ሌላ ጉዳይ መሆኑን ያሳየናል። በጾማችን ወቅት የምናደርጋቸው የተለያዩ የ"እምነት ሥራዎች" ዋጋ እንዳላቸው አንጠራጠርም። ይብዛ ይነሥ ግን በአቅማችን መጠን ያተረፍነውን ክርስቶስ ይጠይቀናል። የግድ እንደ እገሌ ባይሆንም እንደ ራሳችን በእምነታችን እንድናተርፍ ጥሪው ይስተጋባል። ወንጌሉ "ወደ ሌላ አገር የሚሄድ አንድ ሰው አገልጋዮቹን ጠርቶ ንብረቱን አስረከባቸው፤ ለእያንዳንዱ እንደ ችሎታው በማካፈል...ሄደ።" ስለዚህ ከችሎታችን በላይ አልተቀበልንምና ከዚያ በላይ አንጠየቅም። ይህ የሕይወት እንጂ የሙያ ጥያቄ አይደለም፤ እያንዳንዳችን ክርስትናችንን የምንተገብርበትን አቅም እግዚአብሔር አልነሳንም።

ታማኝ፣ ሰላማዊ፣ የፍቅር ሰው፣ ታጋሽ፣ ትሑት...መሆን ማለት የክርስትናችን ጸጋ ወይም ስጦታዎች ቢሆኑም ተባብረን ካላሳደግናቸው ግን ምንም ትርጉም የላቸውም። አንድ ሰው ታማኝነቱ፣ አፍቃሪነቱ ወይም ታጋሽነቱ እስኪነካ ድረስ ከሆነ ያው የተሰጠውን ሀብት ቀብሮ ጌታውን የጠበቀው አገልጋይ ቢጤ መሆኑ ነው። ስለዚህ በተሰጠን ጸጋ መኖር ካለብን በዚያ ላይ ሠርተን ማትረፍ ስንችል ነው። አንድ ነጋዴ እውነተኛ ነጋዴ ከሆነ የሚያተርፍበትን ሁኔታዎች ከማውጣትና ማውረድ አእምሮው አያርፍም። ለማትረፍም በእጁ ያለውን ሀብት መጀመሪያ ማውጣት ይኖርበታል፤ ከዚያ ነው ትርፍ የሚከተለው። ይህ ካልሆነ ግን ማለትም ምንም ሳያወጣ ገንዘቡን እንደያዘ ማትረፍ ቢያስብ ነጋዴነቱ ትርጉም የለውም። እኛም ክርስትናችን የሰጠንን ጸጋ አስቀድመን በማድረግ ካልሆነ በሌላ መንገድ ወይም ስለእምነታችን በማውራትና በመመስከር ብቻ ማትረፍ አንችልም። ስለፍቅር፣ ትሕትና፣ ትእግሥት እያወራን በጥላቻና ነቀፌታ የተሞላን፣ ትእቢተኞች፣ አትንኩኝ ባይ... ከሆንን ጸጋችንን በመቅበር የጌታችንን መመለስ እየጠበቅን ሊሆን ይችላልና እግዚአብሔር የሰጠንን ይህንን የጾም ጊዜ ከቃሉና ከቅዱስ ማዕዱ ራሳችንን በመመገብ በሕይወታችን አድራጊዎችና አትራፊዎች መሆንን እንጀምርበት፤ እናሳድግበት።