3.1 - በእግዚአብሔር መንፈስ አነሣሽነትና መሪነት

4 - በእግዚአብሔር መንፈስ አነሣሽነትና መሪነት

 

“ቅዱሳት መጻሕፍት በሙሉ በእግዚአብሔር መንፈስ መሪነት የተጻፈ ነው፤ እርሱ እውነትን ለማስተማር፣ የተሳሳቱትን ለመገሠጽ፣ ስሕተትን ለማረም ለትክክለኛ ኑሮ የሚበጀውን መመሪያ ለመስጠት ይጠቅማል።” (2ጢሞ. 3:16)በዚህ ጥቅስ መጀመሪያ ላይ “በእግዚአብሔር መንፈስ መሪነት” ስንል ምን ማለታችን ነው?

 

በግሪክ ቋንቋ የዚህ 2ጢሞ. “በእግዚአብሔር መንፈስ መሪነት” የሚለው አባባል “በእግዚአብሔር ተንፋሽነት” ይላል።   ስለዚህ በእግዚአብሔር መንፈስ መሪነት የሚለው አባባል በእግዚአብሔር ርዳታ፣ ተቆጣጣሪነት ወይም በእርሱ ስምምነት ከማለት በላይ በጽሑፎቹ ላይ የእሱን ሥልጣንና ድራሲነት ያመለክታል።

 

እግዚአብሔርን “ዋነኛ ደራሲ” ሰውን ደግሞ “መሣሪያዊ ደራሲ” በማድረግ ካቶሊካዊ ትውፊት የመጽሐፍ ቅዱስን “ሁለትዮሽ ደራሲነት” ይናገራል። የእግዚአብሔር የደራሲነት ሥልጣን የጸሐፊው (የሰው) ቃላት የመምረጥ ችሎታ ድረስ ይዘረጋል። ጸሐፊዎቹ እግዚአብሔር የፈለገውን ነገር ሁሉና ብቻ በነጻነት ጽፈዋል።

 

ይህ ጥምር ደራሲነት ታላቅ ምስጢር ነው፤  ይህን ያህልም ታላቅ ምስጢር ከመሆኑ የተነሣ ቤተ ክርስቲያናችን ይህን የእግዚአብሔር ቃል በሰው ቃላት የመገለጥ ሁኔታ ከክርስቶስ ሥጋ የመልበስ (ትሥግውት) እውነታ ጋር ታነጻጽረዋለች። በሁለቱም ሁኔታዎች እግዚአብሔር አብ እንደ እውነተኛ አባት ከልጆቹ ጋር ለመገናኘት ራሱን ዝቅ ማድረጉ ይታያል።

 

ሥጋ የለበሰው “ቃል” (ክርስቶስ) እና በእግዚአብሔር ዋነኛ ደራሲነት የተጻፈው “ቃል” ሁለቱም ፍጹም አምላክና ፍጹም ሰብአዊ ባሕርይ አላቸው። በሁለቱም ውስጥ ሰብአዊውና መለኮታዊው አይለያዩም፤ በሁለቱም ውስጥ ሰዋዊው ባሕርይ መለኮታዊውን ለማስተላለፍ ይጠቅማል።

 

የመጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ደራሲነትም ሆነ የወልደ እግዚአብሔር ሥጋ መልበስ መለኮታዊ ግልጸት እንደመሆናቸው መጠን ሊታወቁ የሚችሉት በእምነት ብቻ ነው፤ ከእምነት ውጭ በሆነ ሰዋዊ ነገር ሊታወቁ አይችሉም። ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛው “ከኃጢአት በቀር የእግዚአብሔር ቃል (ክርስቶስ) በሁለ ነገሩ ሰው እንደሆነ ሁሉ በሰው ቋንቋ የተገለጸው የእግዚአብሔርም ቃል (በመጽሐፍ ቅዱስ) ከስህተት በስተቀር በሁለንተናው የሰው ልጅ ንግግርን ሆነ” ይላሉ።

 

በርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ ስህተት የለሽ ነው፤ ር.ሊ.ጳ. ሌዮ 13ኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ ውስጣዊ ይዘት ስህተት የለሽ መሆኑ ከእግዚአብሔር ደራሲነት የተነሣ ነው በማለት ይገልጻሉ (እግዚአብሔር የመጽሐፍ ቅዱስ ዋነኛ ደራሲ ከሆነ ስህተት መጠበቁ መሳሳት ነው)። እንዲሁም “በእግዚአብሔር መንፈስ መሪነት ተጻፈ የሚለው ሀሳብና ስህተት አብረው ሊሄዱ የማይችሉ ነገር ናቸው” ይላሉ።

 

ሆኖም ግን ይህ “ስህተት የለሽ” የሚለው አባባል ገና ሙሉ ለሙሉ በበቂ ሁኔታ የመጽሐፍ ቅዱስን ባሕርይ አይገልጸውም። ምክንያቱም ሌሎች መጻሕፍትም ስህተት ላይኖራቸው ይችላል፤ ለምሳሌ በጥንቃቄ እርማትና አርትዖ የተደረገለት የሂሳብ መማሪያ መጽሐፍ በይዘቱ ስህተት ላናገኝለት እንችላለን። ትልቁ የመጽሐፍ ቅዱስ መለያ እግዚአብሔር ዋነኛ ደራሲው መሆኑ ነው፤ ሌላ ማንኛውም መጽሐፍ እግዚአብሔር ደራሲው የሆነለትና የእሱን የማዳን ኃይል በምልአት የሚያስተላልፍ የለም። ኢየሱስ ራሱ ሲመሰክር “ሕይወትን የሚሰጥ የእግዚአብሔር መንፈስ ነው፤ የሰው ኀይል ግን ለምንም አይጠቅምም። እኔ ለእናንተ የተናገርሁት ቃል ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ነው” (ዮሐ.6:63) ይላል። መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ቃል ለሰው ልጆች ደኅንነት በማስተላለፉ ረገድ ልክ እንደ ቤተ ክርስቲያናችን ምስጢራት ልንመስለው እንችላለን።