ት/ርት ፴፭ - ነቢያት በአዲስ ኪዳን ውስጥ ቁ. ፩

ክፍል ሦስት (ትምህርት ሠላሳ አምስት) Prophets in the NTነቢያት በአዲስ ኪዳን ውስጥ
ነቢይነት በብሉይ ኪዳን ውስጥ በመጨረሻው ነቢይ ማለትም በነቢዩ ሚልክያስ የተደመደመና የተዘጋ የአልግሎት ተግባር አይደለም፡፡ በአዲስ ኪዳን ዘመንም የነቢይነት አገልግሎት የቀጠለና እግዚአብሔር ለራሱ ሥራ በመረጣቸውና በጎ ፈቃድ ባላቸው ሰዎች የተከናወነና እየተከናወነ የሚገኝ የተቀደሰ የአገልግሎት ተግባር ነው፡፡ ከብሉይ ኪዳን ወደ አዲስ ኪዳን በተደረገው ሽግግር በእርግጥ ነቢይነት በተመለከተ የአመለካከት ለውጦች አሉ፡፡ ከብሉይ ወደ አዲስ ኪዳን በተደረገው ጉዞ የነቢይነት አገልግሎት ተግባራት በሂደት መልካቸው በተወሰነ መልኩ መቀየሩ ግልጽ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የነቢይነት ዋና መሠረቱና ተልእኮው ግን አንድ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ እንደ ነቢይ መቈጠሩ ብቻ ሳይሆን የነቢይነትም ተግባር አከናውኗል፡፡ እንደ ነቢይ ካከናወናቸው ተግባራት ውስጥ ነቢይ ሆኖ መልእክቶችን ከአብ ማቅረቡ(ዮሐ 8፡26-28)፣ ወደፊት የሚሆነውን መግለጡን(ሉቃ 19፡41-44)፣ የእግዚአብሔር ሕግ መተርጐሙን(ማቴ5፡21-48)፣ ሰዎችን ስለ ኃጢአታቸው መውቀሱን(ሉቃ11፡42-46)፣ ስለ እምነታቸው ማበረታታቱን(ማቴ 8፡10-13) ከብዙዎቹ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
ሐዋርያው ጳውሎስ የነቢይነት አገልግሎት ጠቃሚነትና አስፈላጊነት በመተንተን ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ያስገነዝባል፡፡ ነቢይነት ከጠቀሜታው አኳያ በቤተክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ ከሐዋርያነት ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ተመድቦ ይገኛል፡፡ ይህንንም ሲያስገነዝብ እግዚአብሔር እያንዳንዱ ሰው በቤተ ክርስቲያን የተለያየ አገልግሎት እንዲኖረው አድርጎአል፤ በዚህም መሠረት በመጀመሪያ ሐዋርያትን፣ ሁለተኛ ነቢያትን፣ ሦስተኛ መምህራንን ሾሞአል ይላል(1 ቆሮ 12፡28-29)፡፡ በዚህም ነቢይነት ከማስተማር፣ ከመፈወስ፣ ከማስተዳደር፣ ሰዎችን ከመርዳትና በአዲስ ቋንቋ ከመናገር ስጦታዎች ሁሉ የበለጠ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ትንቢት መናገር ከመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች አንዱ ሲሆን ትንቢት የሚነገረውም ሌላውን ለማነጽ፣ ለማበረታታትና ለማጽናናት እንደሆነ ሐዋርያው ያስገነዝባል(1ቆሮ 14፡3)፡፡ ስለዚህ የትንቢት ስጦታ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ስለሆነ በብርቱ መፈለግ አለበት እንጂ መናቅ የለበትም(1ተሰ 5፡19-20)፡፡
በአጠቃላይ አማኞች ትንቢት ለመናገር በብርቱ መፈለግ እንዳለባቸውና ትንቢት መናገራቸውም ለሌሎች አገልግሎት ጠቀሜታው ከፍተኛ እንደሆነና ክርስቲያኖች የሚታነጹበት የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ እንደሆነ ሐዋርያው ጳውሎስ ያስገነዝባል(1 ቆሮ 14፡12 እና 39)፡፡ ነገር ግን ትንቢት የሚናገር ሰው ሁሉንም ነገር ያውቃል ወይም ይገለጥለታል ማለት አይደለም፤ እንዲያውም የምናውቀውም ሆነ ትንቢት የምንናገረው በከፊል ነው ካለ በኋላ ትንቢት የመናገር ስጦታ ጊዜያዊ ስለሆነ ሊጠፋም እንደሚችል ሐዋርያው ያስጠነቅቃል(1 ቆሮ 13፡8-9)፡፡
በአዲስ ኪዳን ውስጥ ነቢያቶችና የነቢያቶች አስተምህሮ ወይም የነቢያቶች ትንቢታዊ ቃል ብሉይ ኪዳን ውስጥ ከሚገኝው የተለየ ነው፡፡ በመጀመሪያ በአዲስ ኪዳን ውስጥ እንደ ብሉይ ኪዳኖቹ “ነቢያቶች ነን” ወይም “እኔ ነቢይ ነኝ” ብሎ ራሱን ግልጽ በሆነ ሁኔታ እንደ ነቢይ የሚያቀርብ የዮሐንስ ራእይ ከጻፈው ከዮሐንስ ውጪ ማንም የለም(ራእ 1፡3፤ 10፡11፤ 22፡7፡10 እና 18)፡፡ እንደ ብሉይ ኪዳን በነቢያት የተሰየሙ መጻሕፍትም የሉም፡፡ በአዲስ ኪዳን ውስጥ እንደ ብሉይ ኪዳን ነቢያቶች “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል” የሚል የንግግር ዘይቤም አይገኝም፡፡ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ነቢያቶች ስለ ማንነታቸው ግላዊም ሆነ ቤተሰባዊ ሕይወት ወይም ከየትኛው ወገንና ከወዴት መምጣታቸው የሚናገሩትም ነገር የለም፡፡ የብሉይ ኪዳን ነቢያቶች ልዩ ትኩረት ሰጥተውት ይናገሩለት የነበረው ስለ እስራኤልና ይሁዳ ሕዝብ፣ ስለ ሕዝቡ የንስሓ ጥሪ እንዲሁም ስለ ወቅታዊ የፖለቲካ መሪዎቻቸው ጉዳይ ነበር፤ አዲስ ኪዳን ግን አብዛኛውና ዋና ትኩረቱ የሆነው ስለ እያንዳንዱ ሰው ደኅንነት ነው፡፡
ነገር ግን የትንቢት ቃልና የትንቢት ሁሉ ዋና መሠረቱ ወይም ምንጩ እንዲሁም አላማው አንድ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን እንደነበረው በአዲስ ኪዳንም ነቢያቶች አሉ፤ የተነገሩም የትንቢት ቃሎች አሉ፤ የሁለቱም የትንቢቶቻቸው ዋናው መነሻው እግዚአብሔር ነው፡፡ ነገር ግን ከላይ እንደተጠቀሰው በብሉይና በአዲስ ኪዳን ነቢያቶች መካከል ግልጽ የሆኑ ልዩነቶች አሉ፡፡ በአቀራረባቸው፣ በአነጋገራቸውና በአጻጻፋቸው ሰፋ ያሉ ልዩነቶች ይዘው ይገኛሉ፡፡ ይህንን የበለጠ ለመረዳት እንድንችል በአዲስ ኪዳን ውስጥ ነቢያቶች ተብለው በነቢያት ስም የተጠሩትንና ከትምህርታቸው ወይም ካከናወኑት ተግባራቸው በመነሣት ነቢያት ነበሩ የተባሉትን መመልከት አስፈላጊ ነው፡፡
መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ 
በተለምዶ መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ የብሉይ ኪዳን የመጨረሻውና የአዲስ ኪዳን የመጀመሪያው ነቢይ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በእርግጥ ዮሐንስ ነቢይ ብቻ ሳይሆን ከነቢያትም የሚበልጥ ትልቁ ነቢይ እንደሆነ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስክሮለታል(ማቴ11፡ 9)፡፡ የመጥምቁ ዮሐንስ መወለድ አስቀድሞ መላኩ ገብርኤል አብስሮ ነበር፡፡ ይኸውም በተራራማው በይሁዳ አገር ከሚስቱ ከኤልሳቤጥ ጋር ይኖር የነበረው ካህኑ ዘካርያስ የክህነት አገልግሎት ተግባሩን በቤተ መቅደስ ውስጥ በመወጣት ላይ እያለ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከው መላኩ ገብርኤል ተገልጦለት በዕድሜ ገፍታ የነበረችው ሚስቱ ኤልሳቤጥ ወንድ ልጅ እንደምትወልድለት አበሰረው፡፡ ዕጣን በማጠን ተግባር ላይ የነበረው ዘካርያስም በዕድሜ ገፍቶ ስለነበር እጅግ በጣም ተገረመ፡፡ መላኩ ግን ስለሚወለደው ሕፃን ማንነትና የወደፊት ተግባሩ ማብራራቱን ቀጠለ፡፡ እንደ መላኩ አገላለጽ ሕፃኑ ዮሐንስ ተብሎ ይጠራል፤ በእግዚአብሔር ፊት ታላቅ ይሆናል፤ የወይን ጠጅና ሌላም የሚያሰክር መጠጥ አይጠጣም፤ ገና በእናቱ ማሕፀን ሳለ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ይሆናል(ሉቃ1፡13-15)፡፡ መላኩ ገብርኤል በተጨማሪም ስለ ዮሐንስ የወደፊት ተግባር ሲናገር ከእስራኤል ሕዝብ ብዙዎችን ወደ እግዚአብሔር ወደ አምላካቸው ይመልሳቸዋል፤ በመንፈስና በኃይል እንደ ነቢዩ ኤልያስ ሆኖ ሕዝቡን ለጌታ ያዘጋጃል፤ እርሱ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆቻቸው፣ የማይታዘዙትንም ሰዎች ልብ ወደ ጻድቃን ጥበብ ይመልሳል በማለት ስለ ነቢይነት አገልግሎቱ ይገልጻል(ሉቃ 1፡16-17)፡፡
ስለዚህ ዮሐንስ ገና ከመወለዱ ቀድሞ የብሉይ ኪዳን ነቢያቶች ይወጡት የነበረው የነቢይነት ተግባር ማለትም ሕዝብን ከተሳሳተ መንገድ ወደ እግዚአብሔር የመመለስና ዐመፀኞችን ወደ ታዛዥነት ሕይወት የመምራት ሥራ ያከናውን ነበር፡፡ በተጨማሪም የጌታ መንገድ ያዘጋጃል እንደተባለው እንደ ነቢዩ ኤልያስ ሆኖ ሕዝቡን ለጌታ እንደሚያዘጋጅም ተነገሮለታል፡፡ እነዚህን በመላኩ የተብራሩት የአንድ ነቢይ ዋና ዋና ተግባራት በማየት ብቻ ዮሐንስ ለነቢይነት በእግዚአብሔር በራሱ የታጨና የተዘጋጀ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ በተጨማሪም ተወልዶ እንደ አይሁዳዊነቱ በስምንተኛው ቀን በተገረዘ ጊዜ ሰዎች በሕጻኑ እጅግ በጣም ተገርመው ይህ ሕፃን ምን ሊሆን ይሆን? እያሉ ይጠያየቁ ነበር፡፡ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ረድኤት በእርግጥ ከእርሱ ጋር ስለነበር ነው በማለት ወንጌላዊው ያስገነዝባል(ሉቃ 1፡66)፡፡
የብሉይ ኪዳን ነቢያት በኖሩበት ወቅት አገራትን ይመሩ የነበሩትን ነገሥታቶች የሚያከናውኑት ክፉ ተግባራት በመቃወም ይናገርዋቸው እንደነበረ ሁሉ መጥምቁ ዮሐንስም በጊዜው የነበረውን የገሊላውን ገዥ ሄሮድስ የወንድሙን የፊልጶስ ሚስት ሄሮድያዳን በግፍ ቀምቶ በማግባቱና ሌላም ብዙ ክፉ ነገር በማድረጉ ገሠጸው፡፡ ሄሮድስ ግን ይህ ሁሉ አልበቃ ብሎት በክፋት ላይ ክፋት በመጨመር ዮሐንስን ወደ ወህኒ ቤት አስገባው በማለት ወንጌላዊው የሄሮድስን ክፋትንና የዮሐንስን ወኔ የተሞላበት የነቢይነት ተግባር አበክሮ ይገልጻል(ሉቃ 3፡19-20)፡፡ ይህንኑ እውነት ተናጋሪነቱ ወህኒ ቤት እንዲጣል ከማድረጉም በላይ አንገቱን በወህኒ ቤት ውስጥ በንጉሥ ሄሮድስ ትእዛዝ ተቈርጦ በመሥዋዕትነት እንዲያልፍ እንዳደረገው ወንጌላዊው ይገልጣል(ማቴ 14፡1-12)፡፡ በሕይወት ዘመኑ ያከናወናቸው የነቢይነት ተግባራት በማየት በቅርብ ይከተሉት የነበሩት አይሁዳውያንም እንደ ነቢይ ያዩት እንደነበር ወንጌላት አበክረው ይገልጣሉ(ማቴ 14፡5)፡፡
በአጠቃላይ መጥምቁ ዮሐንስ ገና ከመወለዱ በፊት በእግዚአብሔር ምርጫ ለነቢይነት የተዘጋጀ የእግዚአብሔር ሰው ነበር፡፡ ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መንገድ ጠራጊ ሆኖ በመምጣት የነቢይነት ተግባሩም ጀመረ፡፡ በውሃ እያጠመቀ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው እንዲመለሱ የንስሓ ጥሪ ሲያሰማ ኖረ፡፡ ይመጣል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው መሲሕ ታላቅነት እየተናገረ መንገድ ጠራጊ ሆኖ ሕዝቡን የማዘጋጀት ተግባሩን ተወጣ፡፡ በኋላም ከነቢይም ነቢይ ተብሎ ታላቅነቱ በጌ.ኢ.ክ ተመሰከረለት፤ ራሱን ዝቅ አድርጎ በትኅትና ኖረ፤ ነገሥታትን ሳይፈራ ፍትሕ በተጓደለበት ስለ ድኾች መብት ተናገረ፤ በወህኒ ቤት በግፍ የተጣለና በመጨረሻም ሕይወቱ በምስክርነቱ መሥዋዕት ሆኖ ያለፈ ታላቅ ነቢይ ነው፡፡ ነቢይነቱ ከተረጋገጠባቸው መንገዶች ውስጥ ሌላው አብዛኛው የተናገራቸው የትንቢት ቃላት ወዲያውኑ ፍጻሜ ማግኘታቸው ነው፡፡
በእርግጥ መጥምቁ ዮሐንስ የተናገራቸው አብዛኞቹ የትንቢት ቃላት ጌ.ኢ.ክን የሚመለከቱ ነበሩ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ለመጥቀስ ያህል መንፈስ ቅዱስ እንደ ርግብ ከሰማይ ሲወርድና ሲያርፍበት አየሁ፤ እኔ እራሴ አላውቀውም ነበር፤ ነገር ግን በውሃ እንዳጠምቅ የላከኝ "መንፈስ ቅዱስ ሲወርድና ሲያርፍበት የምታየው በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቅ እርሱ ነው" ሲል ነግሮኛል፡፡ እኔም ይህን አይቻለሁ፤ ስለዚህ እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን እመሰክራለሁ ብሎ የተናገረው የትንቢት ቃል ይገኝበታል(ዮሐ 1፡32-34)፡፡ በእርግጥ ይህ ቃል ከትንቢት ቃልነቱ ይልቅ ምስክርነትን የሚገልጥ ነው፡፡ ነገር ግን ከዚህ ቃል በፊት ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ ይበልጣል፤ ምክንያቱም ከእኔ በፊት ነበር እያለ የጌ.ኢ.ክ መምጣት ሲያበስር ነበር፡፡
ባለ ራእዩ ዮሐንስ
በአዲስ ኪዳን ውስጥ በነቢይነት ከተጠሩት መካከል የዮሐንስ ራእይ የጻፈው ዮሐንስ ይገኝበታል፡፡ ይህ ጸሐፊ እንደ ነቢይ የተቈጠረበት ሁለት ምክንያቶች አሉ፡፡ የመጀመሪያው ጸሐፊው ራሱ ስለ ብዙ ወገኖች፣ ልዩ ልዩ ቋንቋ ስለሚናገሩ ሰዎችና ስለ ነገሥታት እንደ ገና ትንቢት መናገር አለብህ ተብሎ ተነገረኝ በማለት ራሱ እንደ ነቢይ ስለሚቆጥር ነው፡፡ ሌላው ደግሞ የጻፈው መልእክት እንደ ትንቢት መጽሐፍ በመቁጠር ይህን የትንቢት መጽሐፍ የሚያነብ የተባረከ ነው በማለት የመጽሐፉ ቃል እንደ ትንቢት ቃል ስለሚገልጸው ነው(ራእ 1፡3፤ 10፡11)፡፡ በተጨማሪም ጸሐፊው እንደ ነቢዩ ሕዝቅኤል፣ ነቢዩ ዳንኤልና ነቢዩ ዘካርያስ ያያቸውን ራእዮች ይተርካል፤ ከመላእክቶች ጋር ይነጋገራል፤ ሰማያዊ ክንውኖችን በሰብአዊ ቋንቋ ለመግለጽ ይሞክራል፡፡ እንደ ነቢዩ ሕዝቅኤል እኔም ትንሽቱን መጽሐፍ ከመላኩ እጅ ወስጄ በላኋት፤ በአፌ እንደ ማር ጣፈጠች፤ ከበላኋት በኋላ ግን ሆዴ መራራ ሆነ እያለ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ያለውን ቀረቤታና ወዳጅነት ይገልጻል(ራእ 10፡10፤ ሕዝ 3፡2)፡፡
በመጨረሻም ጸሐፊው እንደ ብሉይ ኪዳን ነቢያቶች በተለይም እንደ ትንቢተ ዳንኤል ምስጢራዊ የሆኑ ማለትም በመጀመርያው ዕይታ ለመረዳት የሚያስቸግሩና በተወሰኑ ሰዎች ብቻ እንደ መግባቢያ ቋንቋ ሆነው የሚያገለግሉ ንግግሮች ይጠቀማል፡፡ በእርግጥ እነዚህ ከበስተጀርባቸው ሌላ ትርጓሜ የሚኖራቸው ድብቅ የሆኑ የንግግር ዘይቤዎች ክርስቲያኖች የሚያሳድዱ ተቃዋሚዎች በበዙበት ወቅት መልእክቶቻቸው ከአሳዳጆቻቸው በተደበቀ ሁኔታ ለመግባባት ይጠቀሙበት የነበረ ነው፡፡ በአጠቃላይ የዮሐንስ ራእይ እግዚአብሔር በጌ.ኢ.ክ አማካኝነት የዚህ ምድር ጠላቶች ሁሉ ድል ነሥቶ ለታመኑትና ፈተናን ተቋቁመው እስከ መጨረሻ ለሚጸኑት ሁሉ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር ወደ ፊት እንደሚያወርሳቸው ተስፋ በሚሰጥ መልኩ የተጠናቀረ በመሆኑ ጸሐፊው የነቢይነት ቃሉም የትንቢት መሆኑን ከይዘቱ መረዳት ይቻላል፡፡
ዘካርያስና ነቢይት ሐና
በአዲስ ኪዳን ከተጠቀሱት ነቢያቶች ውስጥ ዘካርያስና ሐና ስለ ነቢይነት አገልግሎታቸው ብዙም የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ ካህኑ ዘካርያስ በልጁ በመጥምቁ ዮሐንስ መወለድ ተደስቶ ዘካርያስ ትንቢት ተናገረ ይበል እንጂ ዘካርያስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ያሰማው የምስጋና ቃል ነው(ሉቃ 1፡67-79)፡፡ የፋኑኤል ልጅ ሐናም ነቢይት አንደነበረችና ከባልዋ ሞት በኋላ ሰማኒያ አራት ዓመት እስኪሆናት ድረስ ከቤተ መቅደስ ሳትለይ በጾምና በጸሎት ቀንና ሌሊት እግዚአብሔርን በማገልገል መኖርዋን ከመጠቀሱ ውጪ እንደ ነቢይት ምን እንዳከናወነች ወይም የአገልግሎት ተግባርዋ ምን እንደነበር ምንም የተጠቀሰ ነገር የለም (ሉቃ 2፡36-37)፡፡
ሊቀ ካህኑ ቀያፋ
ሊቀ ካህናት የነበረው ቀያፋ ግን ከእነዚህ ለየት ባለ መልኩ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ የትንቢት ቃል እንደተናገረ ወንጌላዊው ዮሐንስ ይነግረናል፡፡ በእርግጥ ቀያፋ ለሕዝቡ እናንተ ምንም አታውቁም፤ ሕዝብ ሁሉ ከሚጠፋ አንድ ሰው ስለ ሕዝብ ቢሞት ለእናንተ የሚሻል መሆኑን ከቶ አልተገነዘባችሁምን? በማለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሕዝቡ መሞት እንደሚገባው ተናግሮ ነበር(ዮሐ 11፡49-51)፡፡ ቀያፋ ይህንን የተናገረው ከራሱ አመንጭቶ እንዳልነበረና በሊቀ ካህንነቱ መንፈስ ቅዱስ የገለጸለት የትንቢት ቃል እንደነበር ወንጌላዊው አበክሮ ይገልጻል፡፡ በዚህም ምክንያት ከአዲስ ኪዳን ነቢያት እንደ አንዱ ሆኖ በብዙዎች ሲገለጽ ይታያል፡፡
ነቢዩ አጋቦስ
ከአዲስ ኪዳን ነቢያት ውስጥ ትንቢት በመናገሩና የተለያዩ የነቢይነት አገልግሎት በመወጣቱ እንደ ነቢይ የተቈጠረው ሌላው የአዲስ ኪዳን ነቢይ አጋቦስ ነው፡፡ አጋቦስ በይሁዳ አገር በኢየሩሳሌም ከተማ ውስጥ ይኖር እንደነበረና የነቢይነት ተግባሩም ወደ ተለያዩ የአገልግሎት ቦታዎች በመሄድ ይወጣ እንደነበር ተገልጿል(ሐዋ 11፡27-28፤21፡10-11)፡፡ በመጀመሪያ ከይሁዳ ወደ አንጾኪያ በመሄድ በዓለም ሁሉ ታላቅ ረሀብ እንደሚሆን በመንፈስ ቅዱስ አነሣሽነት ትንቢት ተናገረ(ሐዋ 11፡28)፡፡ ይህንን የትንቢት ቃል የሰሙ አማኞች ሁሉ እያንዳንዳቸው የችሎታቸውን ያህል ገንዘብ አዋጥተው በይሁዳ አገር ለነበሩት ክርስቲያን ወንድሞቻቸው በበርናባስና በሳውል አማካኝነት መላካቸውን ተጠቅሷል(ሐዋ11፡29)፡፡ በተመሳሳይ መልኩ አጋቦስ ከይሁዳ ወደ ቂሳርያ በመሄድ በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ ስለ ሐዋርያው ጳውሎስ የትንቢት ቃል ተናገረ(ሐዋ 21፡11)፡፡ በጊዜው ቂሳርያ የነበረው ጸሐፊው ስለ አጋቦስ ትንቢት እንዲህ ይላል አጋቦስ የሚባል ነቢይ ከይሁዳ አገር መጣ፡፡ ይህ ነቢይ ወደ እኛ ቀረበ፤ የጳውሎስን መታጠቂያ ወስዶ የገዛ እግሮቹን አሰረና “መንፈስ ቅዱስ የዚህን መታጠቂያ ባለቤት በኢየሩሳሌም ያሉ አይሁዳውያን እንደዚህ አስረው ለአረማውያን አሳልፈው ይሰጡታል ይላል” አለ (ሐዋ 21፡11)፡፡ የትንቢቱንም ቃል የሰሙት አማኞች ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይሄድ እያለቀሱ ለመኑት፡፡ ይህም የሚያሳየው የአጋቦስ የትንቢት ቃል በአማኞች ዘንድ ታማኝነት የነበረውና እሱም እንደ እውነተኛ ነቢይ ይቈጠር ስለነበር ነው፡፡ በእርግጥ የተናገረው የትንቢት ቃል ብዙም ሳይቆይ ተፈጻሚነት እንዳገኘ ተገልጿል(ሐዋ 21፡33)፡፡
ይሁዳ፣ ሲላስና የወንጌላዊው ፊልጶስ ሴት ልጆች
አዲስ ኪዳን ውስጥ እንደ ነቢያት ከተጠቀሱት ውስጥ ቀጥለን የምናገኛቸው ይሁዳና ሲላስ ናቸው፡፡ ይሁዳና ሲላስ እንደ ነቢያት የተናገሩት ትንቢትም ይሁን ያዩት ራእይ ባይጠቀስም ጸሐፊው ይሁዳና ሲላስ ነቢያት ስለነበሩ ወንድሞችን በብዙ ቃል መክረው አጽናኑአቸው፤ አበረታቱአቸውም በማለት የማጽናናትና የማበረታታት ተግባር በአማኞች ዘንድ እንዳከናወኑ ይገልጻል(ሐዋ 15፡32)፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በሐዋርያት ሥራ ውስጥ የተጠቀሱት ሌሎች የአዲስ ኪዳን ነቢቶች የወንጌላዊው ፊልጶስ አራት ሴት ልጆች ናቸው፡፡ እነዚህ ልጆች ትንቢት የመናገር ስጦታ እንደነበራቸው ከመጠቀሱ ውጪ የተናገሩት ትንቢትም ሆነ የተወጡት የነቢይነት አገልግሎት አልተጠቀሰም(ሐዋ 21፡9)፡፡ በአጠቃላይ እነዚህ በአዲስ ኪዳን ውስጥ እንደ ነቢያት የተጠቀሱትንና ያከናወኑትን ተግባር በምናይበት ጊዜ ብሉይ ኪዳን ውስጥ ከነበረው ነቢይነትና የነቢይነት ተግባር ለየት ያለ አመለካከት ወይም ነቢይነት ቀድሞ ከነበረው ትርጓሜው ይልቅ ሰፋ ባለ መልኩ እንደቀረበ እንረዳለን፡፡ ይህንን አመለካከት የበለጠ መገንዘብ እንድንችል ነቢይነት በአዲስ ኪዳን ውስጥ ምን ዓይነት ተጨማሪ ወሰነ ትርጉም እንዳገኝ መመልከቱ አስፈላጊ ነው፡፡

የትምህርቱ አዘጋጅ፦ አባ ምሥራቅ ጥዩ

      የትምህርቱ አስተባባሪ፦ ተስፋዬ ባዴዢ