የእንድርያስ ፡ ጥረት ፡ ከንቱ ፡ ልፋት ፡ ወይስ ፡ ብልህነት ?

የእንድርያስ ፡ ጥረት ፡ ከንቱ ፡ ልፋት ፡ ወይስ ፡ ብልህነት ?

በተመሳሳይ ፡ መልኩ ፡ የሐዋርያው ፡ እንድርያስ ፡ ጭንቀት ፡ ሌላው ፡ በወንጌላዊው ፡ ዮሐንስ ፡ ትኩረት ፡ የተሰጠው ፡ ትልቁ ፡ ነጥብ ፡ ነው ፡፡ በእርግጥም ፡ እንድርያስ ፡ ከሐዋርያቶች ፡ ሁሉ ፡ የመጀመርያ ፡ ሐዋርያ ፡ ብቻ ፡ ሳይሆን « መሲሁን ፡ አገኘነው ›› በማለት ፡ ትልቅ ፡ የምስክርነት ፡ ቃል ፡ ሰጥቶ ፡ የነበረ ፡ ነው ፡፡ በእብራይስጥ ፡ ቋንቋ « መሲሕ ›› ወይም ፡ በግሪክ ፡ ቋንቋ « ክርስቶስ ›› ማለት ፡ « የተቀባ ›› ማለት ፡ ነው ፡፡ ከብሉይ ፡ ኪዳን ፡ ዘመን ፡ « መቀባት ›› ለአገልገሎት ፡ መለየትንና ፡ መመደብን ፡ ያመለክታል ፤ በተለይም ፡ ንጉስ (1 ሳሙ 16 ፡ 11, 1 ሳሙ 26 ፡ 11) ወይም ፡ ካህን (ዘጸ 40 ፡ 13, ዘሌ 4፡ 3) መሆንን ፡ ያመለክታል ፡፡ ሆኖም ፡ ሰዎች ፡ ይፈልጉትና ፡ ይጠብቁት ፡ የነበረው ፡ በተለመደው ፡ ሥርዐት ፡ የተቀባ ፡ ሰው ፡ ሳይሆን ፡ ከእግዚአብሔር ፡ የተቀባውን ፡ ብቸኛ ፡ መሲህ ፡ ነበር ፡፡ ታድያ ፡ እንድርያስ ፡ ይህንን ፡ አብጠርጥሮ ፡ የተረዳና ፡ ያወቀ ፡ የመጀመርያው ፡ ሐዋርያ ፡ ሆኖ ፡ እያለ ፡ ነው ፡ ዛሬ ፡ ፈተና ፡ ሲገጥመው ፡ ሁሉን ፡ ነገር ፡ ረስቶና ፡ በሰብአዊነቱ ፡ ተረቶ ፡ ጭንቀት ፡ ውስጥ ፡ የገባው ፡፡ ለዚህም ፡ ነው ፡ የኢየሱስና ፡ የፊልጶስ ፡ ውይይት ፡ ሰምቶ ፡ መፍትሄ ፡ ፍለጋ ፡ የጀመረው ፡፡ ለእሱ ፡ አጠገቡ ፡ ቆሞ ፡ ያለውን ፡ ለጥያቄ ፡ ሁሉ ፡ መልስ ፡ ሊሰጥ ፡ የሚችለውን ፡ ኢየሱስን ፡ በመተውና ፡ ወደ ፡ ሕዝቡ ፡ ዘንድ ፡ በመሄድ ፡ እንጀራና ፡ ዓሣ ፡ መፈለግ ፡ ጀመረ ፡፡ በመጨረሻም ፡ ወደ ፡ ኢየሱስ ፡ በመምጣት « አምስት ፡ ትንንሽ ፡ የገብስ ፡ እንጀራና ፡ ሁለት ፡ ትንንሽ ፡ ዓሣ ፡ የያዘ ፡ አንድ ፡ ልጅ ፡ እዚህ ፡ አለ ፤ ይህ ፡ ግን ፡ ለዚህ ፡ ሁሉ ፡ ሕዝብ ፡ እንዴት ፡ ይዳረሳል ?›› በማለት ፡ ጭንቀቱን ፡ ሲገልጽ ፡ ይታያል ፡፡

እዚህ ፡ ላይ ፡ እንድርያስ ፡ በአንድ ፡ መልኩ ፡ ሁሉን ፡ ቻይና ፡ ሁሉን ፡ አድራጊ ፡ የመፍትሄዎች ፡ ሁሉ ፡ ቁልፍ ፡ የሆነውን ፡ ኢየሱስን ፡ ረስቶ ፡ ለመፍትሄ ፡ ወደ ፡ ሌላ ፡ ቦታ ፡ መሯሯጡ ፡ ድክመቱን ፡ ቢያሳይም ፡ በሌላ ፡ መልኩ ፡ ግን ፡ ያገኛትን ፡ ትንሿንም ፡ ነገር ፡ ቢሆን ፡ ይዞ ፡ ወደ ፡ ኢየሱስ ፡ በመምጣት ፡ « ለዚህ ፡ ሁሉ ፡ ሕዝብ ፡ እንዴት ፡ ይደርሳል ?›› በማለት ፡ መጠየቁን ፡ ከፊሊጶስ ፡ በላይ ፡ የእሱ ፡ እምነት ፡ የጠነከረና ፡ አስተዋይነቱም ፡ የላቀ ፡ መሆኑን ፡ ያሳያል ፡፡ ምክንያቱም ፡ ያለውን ፡ ትንሿንም ፡ ነገር ፡ ይዞ ፡ በመቅረብ ፡ ለኢየሱስ ፡ ጥያቄ ፡ ማቅረቡን « ያገኘሁትን ፡ ትንሽ ፡ ነገር ፡ ነው ፤ አንተ ፡ እንደሚሆን ፡ አድርገው ›› ብሎ ፡ በሱ ፡ ላይ ፡ መተማመኑን ፡ ያሳያል ፡፡ አንዳንድ ፡ ሊቃውንቶች ፡ ሲያክሉም ፡ እንድርያስ ፡ ባዶ ፡ እጁ ፡ ሳይሆን ፡ የሆነ ፡ ነገር ፡ ይዞ ፡ ወደ ፡ ኢየሱስ ፡ ቀርቦ ፡ መፍትሄ ፡ እንዲሰጠው ፡ መጠየቁ ፡ ብልህነቱን ፡ ይገልጻል ፤ ምክንያቱም ፡ የራሱ ፡ የሆነ ፡ ሰብአዊ ፡ ጥረት ፡ ካደረገ ፡ በኋላ ፡ ነው ፡ ያገኛውን ፡ ነገር ፡ ትንሽ ፡ ነው ፡ ሳይል ፡ ወደ ፡ ኢየሱስ ፡ የተጓዘው ፡፡