የወንጌሉ ፡ መልእክት ፡ ማን ፡ ላይ ፡ ያተኩራል

የወንጌሉ ፡ መልእክት ፡ ማን ፡ ላይ ፡ ያተኩራል

በዮሐ 6 ፡ 1-15 የተካተቱት ፡ ዋና ፡ ዋና ፡ ገጸ ፡ ባሕርያት ፡ ሦስት ፡ ሲሆኑ ፡ ሌላ ፡ ተጨማሪ ፡ የሆነ ፡ አራተኛ ፡ ገጸ ፡ ባሕርይም ፡ ይገኛል ፡፡ እነዚህም ፡ ኢየሱስ ፣ ሐዋርያቶች ፣ ሕዝቡ ፡ እና ፡ እንጀራና ፡ ዓሣ ፡ የያዘ ፡ አንድ ፡ ትንሽ ፡ ልጅ ፡ ናቸው ፡፡ በተለምዶ ፡ ሕዝቡ ፡ ኢየሱስ ፡ ወደሚገኝበት ፡ ስፍራ ፡ ይሄድ ፡ የነበረው ፡ በሽተኞችን ፡ በመያዝ ፡ ፈውስ ፡ ለማግኘትና ፡ ትምህርቱን ፡ ለማድመጥ ፡ ነበር ፤ በዚህ ፡ ታሪክ ፡ ውስጥ ፡ ግን ፡ ሕዝቡ ፡ ወደ ፡ ኢየሱስ ፡ ለመሄድ ፡ ያነሳሳው ፡ የራሱ ፡ የሆነ ፡ ውስጣዊ ፡ ፍላጎት (ልባዊ ፡ መሻት) ፡ ነው ፡፡ በዚህም ፡ ውስጣዊ ፡ ፍላጎት ፡ ተገፋፍቶ ፡ ነው ፡ የኢየሱስን ፡ ትምህርት ፡ ለማድመጥ ፡ ቀዬውን ፡ ጥሎ ፡ ራቅ ፡ ወዳለ ፡ ቦታ ፡ እንደሄደ ፡ የተገለጸው ፡፡ እንግዲህ ፡ ኢየሱስ ፡ ያስተምራል ፡ ሕዝቡ ፡ ደግሞ ፡ መንፈስንና ፡ ሥጋን ፡ የሚያረካውን ፡ አጥንትና ፡ ጅማትን ፡ የሚቆራርጠውን ፡ ቃሉን ፡ እያደመጠና ፡ መንፈሱን ፡ እየመገበ ፡ ቆይታውን ፡ አስረዝሟል ፡፡ በጌ.ኢ.ክ ፡ ፊት ፡ ተገኝቶ ፡ ቃሉን ፡ መስማትና ፡ ነፍስን ፡ ማደስ ፡ ሁሉንም ፡ ነገር ፡ ያስረሳል ፡ ከሁሉም ፡ ነገር ፡ ይበልጣልና ፡ ጊዜው ፡ ሳይታወቅ ፡ እጅግ ፡ በጣም ፡ ሄደ ፡፡ ኢየሱስ ፡ ስለምን ፡ እንዳስተማራቸው ፡ ግን ፡ ምንም ፡ አልተገለጸም ፡፡ እዚያ ፡ ቦታ ፡ ላይ ፡ ግን ፡ ለረጅም ፡ ጊዜ ፡ አብረው ፡ እንደቆዩ ፡ ተገልጿል ፡፡ ቀጥሎም ፡ የሕዝቡን ፡ ረሃብ (የምግብ ፡ ጥያቄ) ታሪኩ ፡ እንደቀየረውና ፡ ውይይቱም ፡ ወደ ፡ ጌ.ኢ.ክ ፡ እና ፡ ወደ ፡ ሐዋርያቶች ፡ እንደዞረ ፡ እናያለን ፡፡ በአጠቃላይ ፡ የወንጌሉ ፡ ተኩረት ፡ በጌ.ኢ.ክ ፡ በሕዝቡና ፡ በሕዝቡ ፡ ረሃብ ፡ ላይ ፡ መሆኑን ፡ በደንብ ፡ ይንጸባረቃል ፡፡ ታድያ ፡ ረሃቡ ፡ ምንን ፡ ያመለክታል ፡፡ የሥጋ ፡ ወይስ ፡ የመንፈስ ፡ ረሃብ ፡ ነበር ? ረሃቡ ፡ ለማስታገስስ ፡ ታምራት ፡ ማከናወን ፡ ያስፈልግ ፡ ነበርን ? ተሰብስበው ፡ የሚገኙበትስ ፡ ቦታ (ተራራ ፡ ላይ) ፡ ከረሃቡና ፡ ከጥማቱ ፡ ጋር ፡ በተያያዘ ፡ መልኩ ፡ ለየት ፡ ያለና ፡ ማስተላለፍ ፡ የፈለገው ፡ መልእክት ፡ ይኖር ፡ ይሆን ?