የፊልጶስ ፡ ፈተና ፡ እና ፡ የእንድርያስ ፡ ጭንቀት (ዮሐ 6 ፡ 1-15)

የፊልጶስ ፡ ፈተና ፡ እና ፡ የእንድርያስ ፡ ጭንቀት (ዮሐ 6 ፡ 1-15)

በዚህኛው ፡ የጥናታችን ፡ ክፍል ፡ የምናየው ፡ በወንጌሉ ፡ ሐተታ ፡ ሂደት ፡ ውስጥ ፡ ኢየሱስ ፡ ከሁለቱ ፡ ደቀ ፡ መዛሙርት ፡ ከፊልጶስና ፡ ከእንድርያስ ፡ ጋር ፡ በሚያደርገው ፡ ውይይት ፡ ዙርያ ፡ ይሆናል ፡፡ ኢየሱስ ፡ ከአምስት ፡ ሺህ ፡ ሕዝብ ፡ በላይ ፡ በአምስት ፡ ትንንሽ ፡ የገብስ ፡ እንጀራና ፡ በሁለት ፡ ዓሣ ፡ ተመግበው ፡ እንዲረኩ ፡ ካረገ ፡ በኋላ ፡ ዐሥራ ፡ ሁለት ፡ መሶብ ፡ ሙሉ ፡ ቁርስራሽ ፡ መሰብሰቡን ፡ የሚገልጸውን ፡ ታሪክ ፡ በአራቱም ፡ ወንጌላውያን ፡ ተደጋግሞ ፡ ተጽፎአል (ማቴ 14 ፡ 12 ማር 6 ፡ 32 ሉቃ 9 ፡ 10) ፡፡ ነገር ፡ ግን ፡ ወንጌላዊው ፡ ዮሐንስ ፡ በዚህ ፡ ታሪክ ፡ ውስጥ ፡ በተለየ ፡ መልኩ ፡ የተለያዩ ፡ ተጨማሪ ፡ መልእክቶች ፡ ለማስተላለፍ ፡ በማለት ፡ የሚያክላቸው ፡ ተጨማሪ ፡ ነገሮች ፡ አሉ ፡፡ ከእነዚህም ፡ ውስጥ ፡ አንዱ ፡ እዚያ ፡ ቦታ ፡ ላይ ፡ ከነበሩት ፡ ሐዋርያቶች ፡ ውስጥ ፡ የተወሰኑትን ፡ ለይቶ ፡ በሥማቸው ፡ መጥራትና ፡ ከኢየሱስ ፡ ጋር ፡ ውይይት ፡ ማድረጋቸውን ፡ አንዱ ፡ ነው ፡፡ በዚህ ፡ ታሪክ ፡ ውስጥ ፡ በመጀመርያ ፡ ሥሙ ፡ የተጠራው ፡ ሐዋርያው ፡ ፊልጶስ ፡ ሲሆን ፡ ቀጥሎም ፡ እንድርያስ ፡ ነው ፡፡ ወንጌላዊው ፡ ዮሐንስ ፡ ለምን ፡ እነሱን ፡ ብቻ ፡ ለይቶ ፡ በሥማቸው ፡ በመጥራት ፡ ከኢየሱስ ፡ ጋር ፡ እንዲወያዩ ፡ አደረጋቸው ? እነዚህ ፡ ሁለት ፡ ሐዋርያቶች ፡ ከሌሎች ፡ ሐዋርያቶች ፡ ለየት ፡ የሚያደርጋቸው ፡ ነገር ፡ ነበርን ?

እንድርያስ

እንደ ፡ ወንጌላዊው ፡ ቅ. ዮሐንስ ፡ አገላለጽ ፡ እንድርያስ ፡ ግንባር ፡ ቀደም ፡ ከሁሉም ፡ ሐዋርያቶች ፡ የመጀመርያው ፡ የጌ.ኢ.ክ ፡ ደቀ ፡ መዝሙር ፡ ነው (ዮሐ 1 ፡ 40) ፡፡ መጥምቁ ፡ ቅ.ዮሐንስ ፡ ኢየሱስ ፡ ባጠገቡ ፡ ሲያልፍ ፡ አይቶ ፡ « እነሆ ! የእግዚአብሔር ፡ በግ ›› ብሎ ፡ ሲመሰክር ፡ በመስማቱ ፡ እንድርያስ ፡ ሁሉንም ፡ ነገር ፡ በመተው ፡ ኢየሱስን ፡ መከተል ፡ ጀመረ ፡፡ ኢየሱስም ፡ ዞር ፡ ብሎ ፡ « ምን ፡ ትፈልጋላችሁ ›› ብሎ ፡ ሲጠይቃቸው ፡ « ረቢ ፡ የት ፡ ትኖራለህ ›› አሉት ፤ ኢየሱስም ፡ ኑና ፡ እዩ ፡ አላቸው (ዮሐ 1 ፡ 35 – 39) ፡፡ እንድርያስም ፡ ሁሉን ፡ ነገር ፡ እርግፍ ፡ አርጎ ፡ በመተውና ፡ የመጀመርያው ፡ ሐዋርያ ፡ በመሆን ፡ ኢየሱስን ፡ ከመከተሉም ፡ አልፎ ፡ በፍጥነት ፡ ወደ ፡ ወንድሙ ፡ ስምዖን ፡ ጴጥሮስ ፡ በመሄድ « መሲሑን ፡ አገኘነው ›› በማለት ፡ ስምዖን ፡ ጴጥሮስን ፡ ወደ ፡ ኢየሱስ ፡ ያመጣ ፡ ቀደምት ፡ ሐዋርያ ፡ ነው (ዮሐ 1 ፡ 42) ፡፡ እዚህ ፡ ላይ ፡ ማስተዋል ፡ ያለብን ፡ አንደ ፡ ዮሐንስ ፡ ወንጌል ፡ አገላለጽ ፡ እንድርያስ ፡ ከመጀመርያዎቹም ፡ የመጀመርያ ፡ ሐዋርያ ፡ ከመሆኑም ፡ በላይ ፡ ኢየሱስን « ከእግዚአብሔር ፡ የተቀባው ፡ ብቸኛ ፡ መሲሕ ›› እንደሆነ ፡ ለይቶ ፡ ያወቀና ፡ ለመጀመርያ ፡ ጊዜ ፡ ለምስክርነት ፡ ወደ ፡ ሌሎች ፡ ዘንድ ፡ በመሄድ ፡ መልካሙን ፡ ዜና ፡ በማብሰርና ፡ ወደ ፡ ኢየሱስ ፡ ዘንድ ፡ እንዲመጡ ፡ በመጋበዝ ፡ ታጥቆ ፡ የተነሳ ፡ ሐዋርያ ፡ ነበር ፡፡ ይህም ፡ ማለት ፡ ኢየሱስ ፡ ሁሉን ፡ አድራጊና ፡ በሁሉም ፡ ነገር ፡ ላይ ፡ ሀይልና ፡ ሥልጣን ፡ ያለው ፡ ሁሉንም ፡ ማከናወን ፡ የሚችል ፡ መሆኑን ፡ ከማንም ፡ በፊት ፡ በመረዳቱ ፡ አየሱስን ፡ መከተል ፡ የጀመረና ፡ ለሌሎችም ፡ መንገድ ፡ ጠራጊ ፡ ሆኖ ፡ የሚታይ ፡ ሐዋርያ ፡ ነው ፡፡ ታድያ ፡ በዚህ ፡ ታሪክ ፡ ውስጥ ፡ ከሌሎች ፡ በተለየ ፡ መልኩ ፡ ሥሙን ፡ መጠቀሱ ፡ ለምንድን ፡ ነው ? ከፊልጶስስ ፡ ጋር ፡ የሚያመሳስለው ፡ ነገር ፡ ምንድን ፡ ነው ? ቀድመን ፡ የፊልጶስን ፡ ማንነትና ፡ የጥሪው ፡ ጉዞ ፡ እንመልከትና ፡ ወደ ፡ ጥያቄው ፡ መልስ ፡ እናመራለን ፡፡

ፊልጶስ

ፊልጶስ ፣ እንድርያስና ፡ ስምዖን ፡ ጴጥሮስ ፡ የአንድ ፡ መንደር (የቤተ ፡ ሳይዳ) ፡ ሰዎች ፡ ናቸው ፡፡ ፊልጶስ ፡ ከእንድርያስና ፡ ከጴጥሮስ ፡ በኋላ ፡ ለሐዋርያነት ፡ አገልግሎት ፡ ለመጀመርያ ፡ ጊዜ ፡ በቀጥታ ፡ በኢየሱስ ፡ የተጠራ ፡ ሐዋርያ ፡ ነው (ዮሐ 1 ፡ 43) ፡፡ እንደ ፡ ወንጌላዊው ፡ ቅ.ዮሐንስ ፡ አገላለጽ ፡ ለመጀመርያ ፡ ጊዜ ፡ በኢየሱስ ፡ እይታ ፡ ውስጥ ፡ ገብቶ ፡ የተመረጠ ፣ ለአገልግሎት ፡ የታጨና ፡ እሱ ፡ ምንም ፡ አይነት ፡ ጥያቄ ፡ ሳያቀርብ ፡ ወይም ፡ አንድም ፡ ቃል ፡ ሳይናገር ፡ በኢየሱስ ፡ ተፈልጎ ፡ የተገኘና ፡ « ና ፡ ተከተለኝ ›› የተባለ ፡ የመጀመርያውና ፡ ብቸኛው ፡ ሐዋርያ ፡ ነው (ዮሐ 1 ፡ 43) ፡፡ በሌላ ፡ አገላለጽ ፡ እንደ ፡ ወንጌላዊው ፡ ቅ.ዮሐንስ ፡ አገላለጽ ፡ ትንተና ፡ ፊሊጶስ ፡ በኢየሱስ ፡ በቀጥታ « ተከተለኝ ›› ተብሎ ፡ የተጠራ ፡ ብቸኛው ፡ ሐዋርያ ፡ ነው ፡፡ በሌላ ፡ በኩል ፡ በዮሐንስ ፡ ወንጌል ፡ ውስጥ ፡ ሌሎቹ ፡ ሐዋርያቶች ፡ እንዴት ፡ እንደተጠሩና ፡ እንዴት ፡ ኢየሱስን ፡ መከተል ፡ እንደጀመሩ ፡ በግልጽ ፡ አይታወቅም ፡፡

ፊሊጶስም ፡ ልክ ፡ እንደ ፡ እንድርያስ ፡ ኢየሱስን ፡ ካገኘው ፡ በኋላ ፡ ሳይዘገይ ፡ ወድያውኑ ፡ ሲመሰከርና ፡ ናትናኤልን ፡ ወደ ፡ ኢየሱስ ፡ እንዲመጣ ፡ ሲጋብዝ ፡ ይገኛል (ዮሐ 1 ፡ 45) ፡፡ ልክ ፡ እንድርያስ « መሲሑን ፡ አገኘነው ›› ብሎ ፡ ለወንድሙ ፡ ለጴጥሮስ ፡ መስክሮለት ፡ እንደነበር ፡ ሁሉ ፡ ፊልጶስም ፡ ለናትናኤል « ሙሴ ፡ በሕግ ፡ መጻሕፍት ፣ ነቢያትም ፡ ስለ ፡ እርሱ ፡ የጻፉለትን ፡ የዮሴፍ ፡ ልጅ ፡ የናዝሬቱ ፡ ኢየሱስን ፡ አገኝተነዋል ››  በማለት ፡ ነበር ፡ የመሰከረውና ፡ ወደ ፡ ኢየሱስ ፡ እንዲመጣ « መጥተህ ፡ እይ ›› በማለት ፡ የጋበዘው ፡፡ ስለዚህ ፡ እንደ ፡ ወንጌላዊው ፡ አገላለጽ ፡ እንድርያስና ፡ ፊልጶስ ፡ ከመጥምቁ ፡ ቅ. ዮሐንስ ፡ በኋላ ፡ ከየትኞቹም ፡ ሐዋርያቶች ፡ በፊት ፡ ስለ ፡ ኢየሱስ ፡ ማንነት ፡ ጠንቅቀው ፡ የተረዱና ፡ ወድያውኑ ፡ መመስከር ፡ የጀመሩ ፡ ሐዋርያቶች ፡ በፊት ፡ ስለ ፡ ኢየሱስ ፡ ማንነት ፡ ጠንቅቀው ፡ የተረዱና ፡ ወድያውኑ ፡ መመስከር ፡ የጀመሩ ፡ ሐዋርያቶች ፡ ናቸው ፡፡ ይህም ፡ ማለት ፡ ኢየሱስ ፡ የእግዚአብሔር ፡ ልጅ ፡ መሆኑን ፣ በምድር ፡ ላይ ፡ የሥልጣን ፡ ሁሉ ፡ ባለቤት ፡ ሁሉንም ፡ ማዘዝና ፡ ማከናወን ፡ የሚችል ፡ ፍጹም ፡ አምላክ ፡ ፍጹም ፡ ሰው ፡ መሆኑን ፡ የተረዱ ፡ የመጀመርያዎቹ ፡ ሐዋርያቶች ፡ ናቸው ፡፡ ይህንን ፡ ተረድተው ፡ ጉዞ ፡ የጀመሩት ፡ ዛሬ ፡ በዮሐ 6 ፡ 1-15 ፡ ላይ ፡ ፈተና ፡ ውስጥ ፡ ሲገኙ ፡ አስተሳሰባቸውና ፡ የመፍትሄ ፡ አፈላለጋቸው ፡ ወይም ፡ ደግሞ ፡ ያንን ፡ ከማንም ፡ በፊት ፡ አምነው ፡ የተከተሉትን ፡ ኢየሱስ ፡ ላይ ፡ ያላቸው ፡ እምነት ፡ ምን ፡ ይመስላል ፡ የሚለው ፡ ሀሳብ ፡ ሳይሆን ፡ አይቀርም ፡ ወንጌላዊው ፡ ሊያተኩርበት ፡ የፈለገው ፡፡ ለዚህም ፡ ይመስላል ፡ ወንጌላዊው ፡ የእነሱን ፡ ሥም ፡ ብቻ ፡ በመጥቀስ ፡ ከኢየሱስ ፡ ጋር ፡ እንዲወያዩ ፡ የሚያደርጋቸውና ፡ ኢየሱስ ፡ ላይ ፡ ያላቸውን ፡ እምነት ፡ ምን ፡ እንደሚመስል ፡ ለማሳየት ፡ የሚሞክረው ፡፡