ሴቶችና ፡ ሕፃናት ፡ ለምን ፡ አይቆጠሩም

ሴቶችና ፡ ሕፃናት ፡ ለምን ፡ አይቆጠሩም

ይህንን ፡ የአምስት ፡ እንጀራና ፡ የሁለት ፡ ዓሣ ፡ ታሪክ ፡ በምናነብበት ፡ ጊዜ ፡ ሌላው ፡ ሳናስተውለው ፡ ማለፍ ፡ የሌለብን ፡ ጉዳይ ፡ ቢኖር ፡ ሴቶችና ፡ ሕፃናት ፡ አለመጠቀሳቸው ፡ ወይም ፡ ጭራሽ ፡ ቁጥር ፡ ውስጥ ፡ አለመግባታቸው ፡ ነው ፡፡ ቅ.ማርቆስ ፣ ሉቃስ ፡ እና ፡ ዮሐንስ ፡ ጭራሽ ፡ ሴቶችና ፡ ሕፃናት ፡ በቦታው ፡ እንደነበሩም ፡ አይጠቀሱም ፡፡ እንዲያው ፡ በደፈናው ፡ እንጀራውንና ፡ ዓሣውን ፡ የበሉት ፡ አምስት ፡ ሺህ ፡ ወንዶች ፡ ነበሩ ፡ በማለት ፡ ያልፉታል (ማር 6 ፡ 44 ሉቃ 9 ፡ 14 ዮሐ 6፡ 10) ፡፡ ቅ. ማቴዎስ ፡ ግን « የበሉትም ፡ ከሴቶችና ፡ ከሕፃናት ፡ ሌላ ፡ አምስት ፡ ሺህ ፡ ወንዶች ፡ ያህል ፡ ነበሩ ›› (ማቴ 14 ፡ 21) በማለት ፡ እዚያ ፡ ቦታ ፡ ላይ ፡ ሴቶችና ፡ ሕፃናት ፡ እንደነበሩ ፡ ነገር ፡ ግን ፡ ከበላተኛው ፡ ጋር ፡ እንዳልተቆጠሩ ፡ አበክሮ ፡ ይገልጻል ፡፡ በወቅቱ ፡ ሴቶች ፡ የኢየሱስ ፡ ትምህርት ፡ ለመስማት ፡ አይሄዱም ፡ ነበር ፡ እንዳንል ፡ እጅግ ፡ በጣም ፡ ጎበዝ ፡ የሆኑና ፡ እስከ ፡ መስቀል ፡ ሥር ፡ የተከተሉት ፡ በኋላም ፡ ትንሣኤውን ፡ ለመጀመርያ ፡ ጊዜ ፡ ያወጁት ፡ ሴቶች ፡ እንደነበሩ ፡ በወንጌል ፡ ውስጥ ፡ ተበክሮ ፡ ተገልጿል ፡፡ ሴቶችና ፡ ሕፃናት ፡ ስላልበሉ ፡ አልተቆጠሩም ፡ እንዳይባል ፡ ከማንኛውም ፡ የዕድሜ ፡ ክልል ፡ ውስጥ ፡ ካሉት ፡ ሰዎች ፡ መካከል ፡ ሲርባቸው ፡ ምግብ ፡ ይሰጠን ፡ በማለት ፡ በማልቀስም ፡ ሆነ ፡ በተለያየ ፡ ጉትጎታ ፡ እረፍት ፡ የሚነሱት ፡ ሕፃናቶች ፡ እንደሆኑ ፡ የታወቅ ፡ ነው ፡፡ ስለዚህ ፡ ጎረምሶች ፡ እየበሉ ፡ ሕፃናት ፡ ዝም ፡ ብለው ፡ ረሃባቸው ፡ ዋጥ ፡ አርገው ፡ ቆመው ፡ ይመለከቱ ፡ ነበር ፡ ለማለት ፡ በጣም ፡ ያስቸግራል ፡፡ ሴቶችና ፡ ሕፃናት ፡ ወደ ፡ ኢየሱስ (ወደ ፡ አንድ ፡ መምህር) ፡ ለመቅረብ ፡ አይደፍሩም ፡ ወይም ፡ ባሕሉ ፡ አይፈቅድላቸውም ፡ ነበር ፡ እንዳንል ፡ ኢየሱስ ፡ እራሱ « ሕፃናት ፡ ወደ ፡ እኔ ፡ እንዲመጡ ፡ ፍቀዱላቸው ፤ አትከልክሏቸው ፡ የእግዚአብሔር ፡ መንግሥት ፡ እንደነዚህ ፡ ላሉት ፡ ነውና ›› (ሉቃ 18 ፡ 16) ፡ ብሎ ፡ እራሱ ፡ ተናግሯል ፡፡ ታድያ ፡ ወንጌላውያን ፡ ትኩረታቸው ፡ ለምን ፡ ወንዶቹ ፡ ላይ ፡ ብቻ ፡ ሆነ ? ለምን ፡ ሴቶችንና ፡ ሕፃናት ፡ ከቁጥር ፡ ውጪ ፡ ማድረጉን ፡ ፈለጉት ?

በዚህ ፡ ዙርያ ፡ የኢትዮጵያ ፡ አንድምታ ፡ እንዴት ፡ እንደሚተነትነው ፡ ቃኘት ፡ አርገን ፡ የበለጠ ፡ አሳማኝ ፡ የሆነ ፡ ትንታኔ ፡ ወይም ፡ ትርጓሜ ፡ ወደተባለው ፡ ሀሳብ ፡ እንመለሳለን ፡፡ አንድምታ ፡ ማለት ፡ ኢተዮጵያውያን ፡ የቤተክርስትያን ፡ ሊቃውንት ፡ ከጥንት ፡ ጀምረው ፡ መጽሐፍ ፡ ቅዱስንና ፡ ሌሎችም ፡ የሊጡርጊያ ፡ መጽሐፍት ፡ በሕላችን ፣ ቋንቋችን ፣ የክርስትና ፡ ሐይማኖታች ፣ ታሪካችንና ፡ ባጠቃላይ ፡ የአገራችንን ፡ ማህበራዊ ፡ ሕይወት ፡ ግንዛቤ ፡ ውስጥ ፡ በማስገባት ፡ የእግዚአብሔርን ፡ ቃል ፡ ሕዝባችን ፡ የበለጠ ፡ ሊረዳው ፡ በሚችለው ፡ መልኩ ፡ የሚሰጡት ፡ ትንታኔ ፡ ወይም ፡ የትንታኔ ፡ ዘይቤ ፡ ነው ፡፡ አንድምታ ፡ ማቴ 14 ፡ ላይ ፡ የሕፃናትና ፡ የሴቶች ፡ አለመቆጠር ፡ ሁለት ፡ ምክንያቶች ፡ ይሰጣል ፡፡ እንደ ፡ አንድምታ ፡ አገላለጽ ፡ ሴቶች ፡ ሰው ፡ በተሰበሰበበት ፡ ቦታ ፡ ላይ ፡ ስለሚያፍሩ ፡ ብዙም ፡ አይበሉም ፡ ስለዚህ ፡ በደንብ ፡ ካልበሉ ፡ ደግሞ ፡ እንደበላ ፡ ሰው ፡ አይቆጠሩም ፡፡ ሕፃናት ፡ ደግሞ ፡ ከሚበሉት ፡ ይልቅ ፡ የሚያበላሹት ፡ ይበልጣልና ፡ እንደ ፡ በላተኛ ፡ ሊቆጠሩ ፡ አይገባም ፡ በማለት ፡ አንድምታ ፡ ሴቶችንና ፡ ሕፃናትን ፡ ያልተቆጠሩበት ፡ ምክንያት ፡ ይተነትናል ፡፡ ከዚህም ፡ በተጨማሪ ፡ እንደ ፡ አንድምታ ፡ አገላለጽ ፡ « የተረፈውንም ፡ ከመግደላዊት ፡ ማርያም ፡ ቤት ፡ አኑረውት ፡ በዘመነ ፡ ደዌ ፡ ለፈውስ ፡ በዘመነ ፡ ቀጠና ፡ ለበረከት ፡ ይወስዱት ፡ ነበር ›› ይላል ፡፡

በእርግጥ ፡ አንድምታ ፡ የሚያብራራው ፡ የአገራችንን ፡ ባሕላዊ ፡ አኗኗር ፡ በተለይም ፡ አንድምታ ፡ በተጻፈበት ፡ በአሥራ ፡ ሰባተኛውና ፡ በአሥራ ፡ ስምንተኛው ፡ ክፍለ ፡ ዘመን ፡ የነበረውን ፡ የአኗኗር ፡ ዘይቤ ፡ በመመርኮዝ ፡ ነው ፡፡ ሁላችንም ፡ እንደምንረዳው ፡ በተለይም ፡ በገጠሩ ፡ የአገራችን ፡ ክፍል ፡ የሚገኙ ፡ ሴቶች ፡ እንኳንስ ፡ በሺህ ፡ የሚቆጠር ፡ ሕዝብ ፡ በተሰበሰበበት ፡ ቦታ ፡ ይቅርና ፡ እቤት ፡ ውስጥ ፡ እንኳን ፡ አንድ ፡ እንግዳ ፡ ቢገኝ ፡ ወይም ፡ እንግዳ ፡ ሆነው ፡ ወደ ፡ አንድ ፡ ቤተሰብ ፡ ዘንድ ፡ ቢሄዱም ፡ ብዙ ፡ ከመብላት ፡ ይቆጠባሉ ፡፡ ሰው ፡ ሳያያቸው ፡ ዞር ፡ ብለው ፡ ብዙ ፡ ይበላሉ ፡ ማለት ፡ ሳይሆን ፡ በተፈጥሮ ፡ የማፈርና ፡ በባሕልም ፡ ውስጥ ፡ የአኗኗር ፡ ዘይቤአቸው ፡ እንደዚያ ፡ አይነት ፡ የማፈርና ፡ በይሉኝታ ፡ የመኖር ፡ ጫና ፡ ስለሚፈጥርባቸው ፡ ነው ፡፡  ወንጌሉ ፡ በተጻፈበት ፡ ጊዜ ፡ ከነበረው ፡ የሕዝቡ ፡ ማሕበራዊና ፡ ታሪካዊ ፡ አኗኗር ፡ ጋር ፡ ሲታይ ፡ ግን ፡ ሌላ ፡ ተጨማሪ ፡ ማብራሪያ ፡ እንዳለው ፡ ይገለጻል ፡፡

ይህም ፡ በወቅቱ ፡ ገሊላም ፡ ሆነ ፡ ኢየሩሳሌም ፡ ይገኙ ፡ የነበረው ፡ በሮማውያን ፡ ቅኝ ፡ ግዛት ፡ ሥር ፡ ነበር ፡፡ በዚህም ፡ ምክንያት ፡ ገዢዎቹ ፡ ሮማውያን ፡ ባሕላቸውን ፡ በአይሁዳውያን ፡ ሕዝብ ፡ ዘንድ ፡ በውዴታም ፡ ሆነ ፡ በግዴታ ፡ በደንብ ፡ አስፋፍተውት ፡ እንደነበር ፡ ይታወቃል ፡፡ ወንጌላውያንም ፡ አድማጮቻቸውን ፡ ወይም ፡ ያስተምሩት ፡ የነበረውን ፡ ማህበረሰብ ፡ በሮማውያን ፡ ያኗኗር ፡ ሁኔታ (ባሕል) ፡ ውስጥ ፡ ሰርጾ ፡ ገብቶ ፡ ስለነበር ፡ በሚጽፉትም ፡ ወንጌል ፡ ውስጥ ፡ የሮማውያንን ፡ ያኗኗር ፡ ዘይቤ ፡ ያንጸባርቁ ፡ እንደነበር ፡ ይታወቃል ፡፡ በጊዜው ፡ በነበሩት ፡ ሮማውያን ፡ የኑሮ ፡ ሂደት ፡ ውስጥ ፡ ደግሞ ፡ አንድ ፡ ግበዣ ፡ ካለ ፡ ሴቶችና ፡ ሕፃናት ፡ የራሳቸው ፡ የሆነ ፡ የተለየ ፡ ቦታ ፡ ላይ ፡ ሆነው ፡ ይመገቡ ፡ እንደነበረና ፡ ወደ ፡ ዋናው ፡ የግብዣ ፡ ቦታ ፡ ገብተው ፡ መመገብ ፡ ለእነሱ ፡ የተከለከለ ፡ እንደነበር ፡ ይገለፃል ፡፡ ለምሳሌ ፡ ሄሮድስ ፡ በተወለደበት ፡ ዕለት ፡ ለከፍተኛ ፡ ሹማምንቱ ፣ ለጦር ፡ አዛዦቹንና ፡ በገሊላ ፡ ለታወቁ ፡ ታላላቅ ፡ ሰዎች ፡ ገብዣ ፡ አደረገ ፡፡ የሄሮድያዳም ፡ ልጅ ፡ ገብታ ፡ በዘፈነች ፡ ጊዜ ፡ ሄሮድስንና ፡ ተጋባዦቹን ፡ ደስ ፡ አሰኘቻቸው ፡፡ ንጉሡም ፡ ብላቴናዪቱን ፡ የምትፈልጊውን ፡ ሁሉ ፡ ጠይቂኝ ፡ እሰጥሻለሁ ፡ ሲላት ፡ እሷም ፡ ወጥታ ፡ እናቷን ፡ ምን ፡ ልለምነው ፡ ብላ ፡ እንደጠየቀቻት ፡ ተገልጿል (ማር 6 ፡ 21-24) ፡፡ እዚህ ፡ ላይ ፡ ሁለት ፡ ነገሮች ፡ ማስተዋል ፡ ይኖርብናል ፡፡ በመጀመርያ ፡ የሄሮድያዳ ፡ ልጅ ፡ ለመዝፈንና ፡ እንግዶቹን ፡ ለማስደሰት ፡ ብቻ ፡ ነው ፡ ከውጪ ፡ ወደ ፡ ግብዣው ፡ አዳራሽ ፡ የገባችው ፡፡ ቀጥሎም ፡ እናትዬው ፡ ያለችው ፡ ከግብዣው ፡ አዳራሽ ፡ ውጪ ፡ መሆኑን ፡ ተጠቅሷል ፤ በእርግጥም ፡ ልጅትዋ ፡ እናትዋ ፡ ወደነበረችበት ፡ ከግብዣው ፡ አዳራሽ ፡ ውጪ ፡ ወደነበረው ፡ ለየት ፡ ወዳለው ፡ ቦታ ፡ ወጥታ ፡ በመሄድ ፡ ነው ፡ የጠየቀቻት ፡፡

በአጠቃላይ ፡ የሴቶችና ፡ የሕፃናት ፡ በወንጌሉ ፡ ውስጥ ፡ አለመቆጠራቸው ፡ ከዚህ ፡ የሮማውያን ፡ ባሕል ፡ ጋር ፡ በተያያዘ ፡ መልኩ ፡ ሲብራራ ፡ መልእክቱ ፡ የበለጠ ፡ ትርጉም ፡ እንደሚሰጥ ፡ ይገለጻል ፡፡ ይህም ፡ ማለት ፡ በወቅቱ ፡ ከነበረው ፡ ታሪካዊና ፡ ባሕላዊ ፡ የአኗኗር ፡ ዘይቤ ፡ አኳያ ፡ ሲታይ ፡ ሴቶችና ፡ ሕፃናት ፡ በግብዣ ፡ ቦታ ፡ ላይ ፡ የራሳቸው ፡ የሆነ ፡ የተለየ ፡ ቦታ ፡ ላይ ፡ ይገኙ ፡ ስለነበርና ፡ ወንጌላውያኑ ፡ ደግሞ ፡ የወቅቱ ፡ ባሕል ፡ በጠበቅ ፡ መልኩ ፡ ያስተምሩ ፡ ስለነበር ፡ ምንም ፡ እንኳ ፡ ሕዝቦቹ ፡ ሁሉ ፡ በኢየሱስ ፡ ዙርያ ፡ ሁሉም ፡ በአንድነት ፡ ቢገኙም ፡ ለወንጌላውያኑ ፡ የቁጥሩ ፡ አስፈላጊነት ፡ ለሚያስተምሩት ፡ ማሕበረሰብ ፡ ትርጉም ፡ ሰጪነቱ ፡ እስከዚህም ፡ ስለነበር ፡ ትኩረት ፡ አልሰጡትም ፡ ይሆናል ፡፡ በሌላ ፡ መልኩ ፡ ደግሞ ፡ አምስት ፡ ሺህ ፡ የሚያህሉ ፡ ወንዶች ፡ በልተው ፡ ነው ፡ ከአምስት ፡ እንጀራና ፡ ሁለት ፡ ዓሣ ፡ ላይ ፡ አሥራ ፡ ሁለት ፡ መሶብ ፡ ትርፍራፊ ፡ የተሰበሰበው ፡ ብለው ፡ ወንጌላውያኑ ፡ ቢገልጹ ፡ ነው ፡ አንባቢያቸው ፡ ወይም ፡ አድማጫቸው ፡ በኢየሱስ ፡ ሥራ ፡ የበለጠ ፡ ሊገረም ፡ የሚችለው ፡፡ ከልሆነ ፡ አንባቢው ፡ አሥራ ፡ ሁለት ፡ መሶብ ፡ የተረፈ ፡ ምግብ ፡ ተሰበሰበ ፡ የሚለው ፡ ሲያይ ፡ ይሄኔ ፡ እኮ ፡ ሕፃናት ፡ እና ፡ ሴቶች ፡ ብቻ ፡ በልተው ፡ ነው ፡ ያን ፡ ያህል ፡ ሊተርፍ ፡ የቻለው ፡ ብሎ ፡ ታምራቱን ፡ አቅልሎ ፡ እንዳያየውም ፡ ጭምር ፡ ሊሆን ፡ ይችላል ፡፡