በአምስት ፡ ትንንሽ ፡ የገብስ ፡ እንጀራና ፡ በሁለት ፡ ትንንሽ ፡ ዓሣ ፡ ከአምስት ፡ ሺህ ፡ ሰው ፡ በላይ ፡ መመገብ ፡ እውነተኛ ፡ ታምር ፡ ወይስ ፡ አጠራጣሪ ፡ አስማት ?

በአምስት ፡ ትንንሽ ፡ የገብስ ፡ እንጀራና ፡ በሁለት ፡ ትንንሽ ፡ ዓሣ ፡ ከአምስት ፡ ሺህ ፡ ሰው ፡ በላይ ፡ መመገብ ፡ እውነተኛ ፡ ታምር ፡ ወይስ ፡ አጠራጣሪ ፡ አስማት ? (ዮሐ 6, 1-15)

መግቢያ

በመጽሐፍ ፡ ቅዱስ ፡ ውስጥ ፡ ተካተው ፡ ከሚገኙትና ፡ በጌ.ኢ.ክ ፡ ከተከናወኑት ፡ ድንቅ ፡ ድንቅ ፡ ታምራቶች ፡ ውስጥ ፡ አንዱ ፡ ጌ.ኢ.ክ ፡  ከአምስት ፡ ሺህ ፡ ሰዎች ፡ በላይ ፡ በአምስት   ፡ ትንንሽ ፡ የገብስ ፡ እንጀራና ፡ በሁለት ፡ ትንንሽ ፡ ዓሣ ፡ መመገቡና ፡ ዐሥራ ፡ ሁለት ፡ መሶብ ፡ የተረፈ ፡ ምግብ ፡ መሰብሰቡ ፡ ነው ፡፡ ይህንን ፡ ታሪክ ፡ የሚተርከው ፡ የወንጌል ፡ ክፍል ፡ ደግሞ ፡ በአራቱም ፡ ወንጌላውያን ፡ ተብራርቶና ፡ እንደውም ፡ ተደጋግሞ ፡ ተገልጾአል (ማር 6 ፡ 30-44 ማቴ 14 ፡ 13-21 ሉቃ 9 ፡ 10-17 ዮሐ 6 ፡ 1-15) ፡፡ ከዚህም ፡ በላይ ፡ አንዳንድ ፡ ወንጌላውያን ፡ ለዚህ ፡ የወንጌል ፡ ክፍል ፡ ልዩ ፡ ትኩረት ፡ ከመስጠታቸው ፡ የተነሳ ፡ ደጋግመው ፡ ጽፈውታል(ማር 6 ፡ 30-44 ማር 8 ፡ 2-9) ፡፡ ምንም ፡ እንኳን ፡ አራቱም ፡ ወንጌላውያን ፡ ይህንን ፡ የወንጌል ፡ ክፍል ፡ ከሞላ ፡ ጎደል ፡ በተመሳሳይ ፡ መልኩ ፡ ቢተርኩትም ፡ ወንጌላዊው ፡ ዮሐንስ ፡ ግን ፡ የበለጠ ፡ ትኩረት ፡ በመስጠት ፡ ለሚያስተምረው ፡ የክርስቲያን ፡ ማሕበረሰብ ፡ ጥልቅ ፡ የሆነ ፡ መልእክት ፡ ያስተላልፋል ፡ ባለ  ፡ መልኩ ፡ አንዳንድ ፡ ተጨማሪ ፡ ነገሮች ፡ በማካተት ፡ ሰፋ ፡ አድርጎ ፡ ተርኮታል ፡፡ በእርግጥም ፡ ወንጌላዊው ፡ ቅዱስ ፡ ዮሐንስ ፡ የጌታን ፡ እራት ፡ ወይም ፡ የቅዱስ ፡ ቁርባን ፡ አመሰራረት ፡ የሚገልጸውና ፡ በሌሎች ፡ ወንጌላውያን ፡ በደንብ ፡ ተብራርቶና ፡ በሰፊው ፡ ተተንትኖ ፡ የቀረበው ፡ የወንጌል ፡ ክፍል ፡ አልጻፈውም ፡፡ በዚህ ፡ ምትክ ፡ ግን ፡ ከሌሎች ፡ ወንጌላውያን ፡ በተለየ ፡ መልኩ ፡ ጌ.ኢ.ክ ፡ የሓዋርያቶችን ፡ እግረ ፡ በማጠብ ፡ ትህትናን ፡ ያስተማረበትንና ፡ ሌሎች ፡ ከጌታ ፡ እራት ፡ ጋር ፡ ተዛማጅነት ፡ ያላቸው ፡ ታምራትንና ፡ ታሪኮችን ፡ በጥልቀት ፡ አብራርቶ ፡ ጽፎአል ፡፡ ከእነዚህም ፡ ውስጥ ፡ አንዱ ፡ የሆነውና ፡ ከጌታ ፡ እራት ፡ ጋር ፡ በተዛማጅነት ፡ የተጻፈው ፡ ከላይ ፡ በመግቢያው ፡ የተጠቀሰው ፡ ጌ.ኢ.ክ ፡ በአምስት ፡ ትንንሽ ፡ የገብስ ፡ እንጀራና ፡ በሁለት ፡ ትንንሽ ፡ ዓሣ ፡ ከአምስት ፡ ሺህ ፡ በላይ ፡ የሆኑ ፡ ሰዎችን ፡ መመገቡን ፡ የሚገልጸው ፡ የወንጌል ፡ ክፍል ፡ ነው ፡፡

ስለዚህ ፡ ምንም ፡ እንኳን ፡ በዚህ ፡ ታሪክ ፡ ዙርያ ፡ በአራቱም ፡ ወንጌላውያን ፡ የተብራሩት ፡ ነገሮች ፡ ግንዛቤ ፡ ውስጥ ፡ ብናስገባም ፡  ለዚህ ፡ አጭር ፡ የሆነው ፡ የወንጌል ፡ ጥናት ፡ የምናተኩረው ፡ ግን ፡ በወንጌላዊው ፡ ቅዱስ ፡ ዮሐንስ ፡ የተገለጸው ፡ የወንጌል ፡ ክፍል (ዮሐ 6  ፡ 1-15) ፡ ይሆናል ፡፡ ታድያ ፡ ይህንን ፡ የወንጌል ፡ ክፍል ፡ በመጽሐፍ ፡ ቅዱስ ፡ ሊቃውንት ፡ ዘንድ ፡ በስፋትና ፡ በጥልቀት ፡ ከተብራራ ፡ በኃላ ፡ አንዳንድ ፡ ጥያቄዎች ፡ ማስነሳቱ ፡ አልቀረም ፡፡ ይህም ፡ እንጀራና ፡ ዓሣ ፡ አባዝቶ ፡ ማደል ፡ ከዚያም ፡ ዐሥራ ፡ ሁለት ፡ መሶብ ፡ የሚያህል ፡ ትርፍራፊ ፡ መሰብሰብ ፡ እንደ ፡ ታምር ፡ መታየት ፡ አለበት ፡ ወይስ ፡ እንደ ፡ አስማት (ምትሓት) ? እንጀራና ፡ ዓሣ ፡ ቁስአካላዊ ፡ ነገሮቸ ፡ ከመሆናቸው ፡ የተነሳ ፡ ለማባዛት ፡ የሚከብድ ፡ ቢሆንም ፡ ይህንን ፡ ሁሉን ፡ ቻይ ፡ በሆነው ፡ በጌ.ኢ.ክ ፡ እጅ ፡ በመከናወኑ ፡ ላይደንቀን ፡ ይችላል ፤ ነገር ፡ ግን ፡ ከዚህ ፡ ጋር ፡ በተያያዘ ፡ መልኩ ፡ አንዳንድ ፡ ጥያቄዎች ፡ ማስነሳቱ ፡ ግን ፡ አልቀረም ፡፡

ከእነዚህም ፡ ጥያቄዎቸ ፡ መካከል ፡ ጥቂቶቹን ፡ ብናይ ፡ ጌ.ኢ.ክ ፡ ሕሙማን ፡ ቢፈውስ ፡ በሥጋና ፡ በመንፈስ ፡ በሽታ ፡ የሚሰቃዩትን ፡ ለማዳን ፡ ነው ፡፡ ሙታንን ፡ ቢያስነሳ ፡ ሕይወትን ፡ በድጋሚ ፡ እንዲያገኙና ፡ የእግዚአብሔርን ፡ ድንቅ ፡ ሥራ ፡ እንዲያዩ ፡ ነው ፡ ከተባለ ፡ እንጀራና ፡ ዓሣስ ፡ አባዝቶ ፡ ማከፋፈል ፡ ለምን ፡ አላማ ፡ ተደረገ ፡ ሊባል ፡ ነው ?  ምንአልባትም ፡ ረሃብን ፡ ለማስታገስና ፡ ከረሃብ ፡ ጋር ፡ ተያይዞ ፡ ሊመጣ ፡ የሚችለዉን ፡ ድካም ፡ ለማራቅ ፡ ነው ፡ ሊባል ፡ ይችል ፡ ይሆናል ፤ ነገር ፡ ግን ፡ እግዚአብሔር ፡ እንደዚህ ፡ አይነት ፡ ድንቅ ፡ ነገሮች ፡ እነዲከናወኑ ፡ የሚፈቅድ ፡ ከሆነ ፡ ታዲያ ፡ ዛሬስ ፡ በዓለማችን ፡ በተለያዩ ፡ ቦታዎች ፡ የሚበሉትና ፡ የሚጠጡት ፡ አጥተው ፡ በረሃብና ፡ በጥማት ፡ ለሚሰቃዩትን ፡ ልጆቹ ፡ ለምን ፡ እንደ ፡ ጥንቱ ፡ መና ፡ አያዘንብላቸውም ?  በተጨማሪም ፡ ሙሴና ፡ አሮን ፡ ወደ ፡ ፈርዖን ፡ ዘንድ ፡ ሄደው ፡ የመጀመርያው ፡ ታምር ፡ ሲያደርጉ (በትርን ፡ ወደ ፡ እባብነት ፡ ሲቀይሩ) ፡ ፈርዖን ፡ ጠቢባኑና ፡ መተተኞቹን ፡ ጠርቶ ፡ በጥበባችው ፡ ያለ ፡ ምንም ፡ ችግርና ፡ ጭንቀት ፡ ተመሳሳይ ፡ ነገር ፡ እንዳከናወኑ ፡ ተገልጾ ፡ እናገኛለን (ዘፀ 7 ፡ 10-11) ፡፡ በግብጻውያን ፡ ዘንድ ፡ እንጂ ፡ በእስራኤላውያን ፡ የሕይወት ፡ ታሪክ ፡ ውስጥ ፡ አስማትና ፡ መተት ፡ ማድረግ ፡ የተለመደ ፡ ነገር ፡ ባይሆንም ፡ እንኳን ፡ እንደዚህ ፡  ለመሰሉ ፡ ነገሮች ፡ ግን ፡ እስራኤላውያን ፡ ባእድ ፡ ናቸው ፡ ማለት ፡ ግን ፡ አይቻልም ፡፡ ታድያ ፡ አምስት ፡ ተንንሽ ፡ የገብስ ፡ እንጀራና ፡ ሁለት ፡ ትንንሽ ፡ ዓሣን ፡ አባዝቶ ፡ ከአምስት ፡ ሺህ ፡ በላይ ፡ ለሆነ ፡ ሕዝብ ፡ መመገብና ፡ ዐስራ ፡ ሁለት ፡ መሶብ ፡ ትርፍራፊ ፡ መሰብሰብ ፡ ከአስማትና ፡ ምትሃት ፡ ጋር ፡ ሊያገናኘው ፡ የሚችል ፡ ነገር ፡ ይኖር ፡ ይሆን ፡ እንዴ ?  እነዚህንና ፡ የመሳሰሉትን ፡ ጥያቄዎች ፡ በተለያዩ ፡ የመጽሐፍ ፡ ቅዱስ ፡ ሊቃውንቶች ፡ በተለያዩ ፡ ጊዜያት ፡ ሲነሱ ፡ ይደመጣሉ ፡፡ ታድያ ፡ እንደነዚህ ፡ ያሉትን ፡ የመጽሐፍ ፡ ቅዱስ ፡ ታሪኮች ፡ ማስተላለፍ ፡ የፈለጉትን ፡ መልእክት ፡ በሚገባ ፡ ለመረዳትና ፡ ግራ ፡ የሚያጋቡንን ፡ ነገሮች ፡ ለማራቅ ፡ ምን ፡ ዓይነት ፡ የመጽሐፍ ፡ ቅዱስ ፡ ያነባብና ፡ የጥናት ፡ ዘዴ ፡ መጠቀም ፡ ይኖርብናል ? ይህንን ፡ የመጽሐፍ ፡ ቅዱስ ፡ ክፍልስ ፡ እንዴት ፡ እንረዳዋለን ? እንደ ፡ እውነተኛ ፡ ታምር ፡ ወይስ ፡ አጠራጣሪ ፡ አስማት ?