በርባን ፡ በእውነቱ ፡ ነፍሰ ፡ ገዳይ ፡ ነበርን ፡ ወይስ ፡ ታጋይና ፡ ጀግና ?

በርባን ፡ በእውነቱ ፡ ነፍሰ ፡ ገዳይ ፡ ነበርን ፡ ወይስ ፡ ታጋይና ፡ ጀግና ?

የበርባንን ፡ ታሪክ ፡ በምናይበት ፡ ጊዜ ፡ አራቱም ፡ ወንጌላውያን ፡ በርባን ፡ ስለተባለ ፡ ሰው ፡ ይተርካሉ ፡፡ ይህም ፡ ኢየሱስ ፡ ለፍርድ ፡ በቀረበ ፡ ጊዜ ፡ አይሁዳውያን ‹‹ኢየሱስ ፡ ይሰቀል ፡ በርባን ፡ ግን ፡ ይፈታ ›› እያሉ ፡ ሲጮሁ ፡ እንደነበረና ፡ በርባንም ፡ ‹‹የሕዝብ ፡ ዐመፅ ፡ በማነሣሣት ፡ በነፍስ ፡ ግድያ ፡ የታሰረ ›› እንደነበር ፡ ይተርካሉ ፡፡ ታድያ ፡ በወቅቱ ፡ የነበረው ፡ ማህበራዊ ፤ ታሪካዊና ፡ ፖለቲካዊ ፡ የኑሮ ፡ ሁኔታ ፡ ግንዛቤ ፡ ውስጥ ፡ አስገብተን ፡ ለመረዳት ፡ ካልሞከርን ፡ በርባን ፡ የተባለውን ፡ ማን ፡ እንደነበር ፣ ለምን ፡ ከእስራት ፡ ነጻ ፡ እንዲወጣ ፡ ሕዝቡ ፡ በሙሉ ፡ በጩኸት ፡ ጲላጦስን ፡ አጥብቀው ፡ እንደጠየቁ ፡ ሳንረዳ ፡ እንቀራለን ፡፡ ከዚህም ፡ ባሻገር ፡ በርባን ፡ ማለት ፡ ለሕዝቡ ፡ ምን ፡ አይነት ፡ መሪ ፡ ወይም ፡ ወዳጅ ፡ ወይም ፡ ጠላት ፡ እንደነበር ፡ ሳንረዳው ፡ መቅረታችን ፡ ብቻ ፡ ሳይሆን ፡ እኛም ፡ ሳንረዳው ፡ ቀርተን ፡ እንደ ፡ ወንጀለኛ ፡ ልንቆጥረው ፡ ይችል ፡ ይሆናል ፡፡ በእርግጥ ፡ ቅ. ማቴዎስ ፡ ‹‹ በርባን ፡ በዐመፅ ፡ የታወቀ ፡ እስረኛ ›› (ማቴ 27 ፡ 16) ብሎ ፡ ሲጠቅሰው ፡ ቅ. ማርቆስ ‹‹ ነፍስ ፡ ከገደሉ ፡ ዐመፀኞች ፡ ጋር ፡ የታሰረ ፡ በርባን ፡ የሚባል ፡ አንድ ፡ ሰው ፡ ነበር ›› (ማር 15 ፡ 6) ይላል ፡፡ ቅ. ሉቃስ ፡ ደግሞ ፡ ‹‹በርባን ፡ ከከተማ ፡ ውስጥ ፡ የሕዝብ ፡ ዐመፅ ፡ በማነሣሣትና ፡ በነፍስ ፡ ግድያ ፡ የታሰረ ፡ ሰው ፡ ነበር ›› (ሉቃ 23፡ 19) ሲለው ፡ ቅ. ዮሐንስ ፡ ደግሞ ፡ በአጭሩ ‹‹ በርባን ፡ ወንበዴ ፡ ነበር ›› በማለት ፡ ያልፈዋል (ዮሐ 18 ፡ 40) ፡፡ እዚህ ፡ ላይ ፡ ማስተዋል ፡ ያለብን ፡ በተለይ ፡ የመጀመርያዎቹ ፡ ሦስቱ ፡ ወንጌላት ፡ በርባን ፡ ‹‹በዐመፅ ፡ የታወቀ ፡ እስረኛ›› እንደሆነ ፡ አበክረው ፡ ይገልጻሉ ፡ እንጂ ፡ ለምን ፡ ዐመፀኛ ፡ እንደነበርና ፡ ማን ፡ ላይ ፡ ያምፅ ፡ እንደነበር ፡ አይገልጹም ፡፡ ነፍስ ፡ ከገደሉ ፡ ዐመፀኛ ፡ ሰዎች ፡ ጋር ፡ ታስሯል ፡ ይላሉ ፡ እንጂ ፡ ነፍሰ ፡ ገዳይ ፡ ነበር ፡ ወይም ፡ በነፍሰ ፡ ገዳይነት ፡ ታስሮ ፡ ነበር ፡ አይሉም ፡፡

በእርግጥ ፡ የገዛ  አገሩን፡ ወረው ፡ ይገዙ ፡ የነበሩትን ፡ የሮም ፡ ቀኝ ፡ ገዢዎችን ፡ ይዋጋ ፡ የነበረው ፡ በርባን ፡ በሮማውያን ፡ ዘንድ ፡ እንደ ፡ ወንጀለኛ ፡ ተቆጥሮ ፡ በእስራት ፡ ላይ ፡ ይገኝ ፡ ነበር ፡፡  አገራችንን ፡ በውጭ ፡ ሀይሎች ፡ (በጨቋኝ ፡ ሮማውያን) መገዛት ፡ የለባትም ፤ ሕዝባችንንም ፡ ከሮማውያን ፡ የቀኝ ፡ ግዛት ፡ የጭቆና ፡ ቀንበር ፡ ነጻ ፡ መሆን ፡ አለባት ፡ በማለት ፡ የገዛ ፡ አገሩን ፡ ወረው ፡ የነበሩትን ፡ ሮማውያንን ፡ ማሳደድና ፡ ሕዝቡንም ፡ ለዐመጽ ፡ በመቀስቀስ ፡ የታወቀና ፡ በሕዝቡም ፡ ዘንድ ፡ እንደ ፡ ወንጀለኛ ፡ ሳይሆን ፡ እንደ ፡ ጀግና ፡ ይቆጠር ፡ እንደነበር ፡ የወቅቱ ፡ የህዝቡን ፡ ታሪካዊና ፡ ማሕበራዊ ፡ ሕይወት ፡ ከሚገልጹ ፡ የታሪክ ፡ መጽሐፍቶች ፡ እንረዳለን ፡፡ በሌላ ፡ መልኩ ፡ ደግሞ ፡ እንደ ፡ አንዳንድ ፡ የመጽሐፍ ፡ ቅዱስ ፡ ሊቃውንት ፡ አገላለጽ ‹‹ በርባን ›› የሚለው ፡ ሥም ፡ ከኢየሱስ ፡ መሞት ፡ ጋር ፡ የተያያዘ ፡ ትርጉም ፡ እንዳለውም ፡ ይገልጹታል ፡፡ ይህም ፡ ‹‹በር-ባን ›› በእብራይስጥ ፡ ቋንቋ ፡ ‹‹የአባት ፡ ልጅ ›› የሚለው ፡ ፍቺ ፡ ሲኖረው ፡ አመፀኛ ፡ የተባለው ፡ በርባን ፡ ነጻ ፡ ወጥቶ ፡ በምትኩ ፡ ኢየሱስ ፡ እንዲሰቀልና ፡ የሞት ፡ ፍርድ ፡ እንዲጎናጸፍ ፡ መደረጉን ፡ ‹‹ በአመፀኞች ፡ ምትክ ፡ የአባት ፡ ልጅ (ኢየሱስ) መሰዋቱን ›› ከሚለው ፡ ጋር ፡ በማያያዝ ፡ ያብራሩታል ፡፡  እነዚህንና ፡ ሌሎችም ፡ ተመሳሳይ ፡ ትንተናዎች ፡ ግንዛቤ ፡ አስገብተን ፡ ስናነበው ፡ የበርባንን ፡ ማንነት ፡ የበለጠ ፡ ግልጽ ፡ እየሆነና ፡ እኛም ፡ መልእክቱን ፡ የበለጠ ፡ ወደ ፡ መረዳት ፡ ልንደርስ ፡ እንችላለን ፡፡

በአጠቃላይ ፡ ከላይ ፡ የተዘረዘሩት ፡ ነጥቦች ፡ ቢያንስ ፡ የተወሰኑትን ፡ እንኳ ፡ ግንዛቤ ፡ ውስጥ ፡ አስገብቶ ፡ አንድን ፡ የመጽሐፍ ፡ ቅዱስ ፡ መልእክት ፡ ማንበብ ፡ ወይም ፡ ካነበቡ ፡ በሁዋላ ፡ በተረጋጋ ፡ መንፈስ ፡ እነዚህን ፡ ሀሳቦች ፡ እየከለሱ ፡ መልእክቱን ፡ ለመረዳት ፡ መሞከር ፡ ለመንፈሳዊ ፡ ሕይወታችን ፡ እጅግ ፡ በጣም ፡ ጠቃሚነት ፡ አለው ፡፡ ከዚህም ፡ በላይ ፡ የመጽሐፍ ፡ ቅዱስን ፡ መልእክት ፡ በጥሩ ፡ ሁኔታ ፡ በተረዳነው ፡ መጠን ፡ እምነታችንም ፡ እየጠነከረ ፡ ከመሄዱም ፡ በላይ ፡ በአንዳንድ ፡ የወንጌል ፡ መልእክቶች ፡ ግራ ፡ ለሚጋቡት ፡ ወገኖቻችን ፡ ብርሃን ፡ ሆነን ፡ ለመምራትም ፡ ይጠቅመናል ፡፡ እንግዲህ ፡ እነዚህን ፡ ነገሮችንና ፡ ሌሎችም ፡ እዚህ ፡ ውስጥ ፡ ያልተጠቀሱትን ፡ የመጽሐፍ ፡ ቅዱስ ፡ አጠናን ፡ ዘዴዎች ፡ ግንዛቤ ፡ ውስጥ ፡ በማስገባት ፡ ከላይ ፡ የቀረበውን ፡ አርእስት (ዮሐ 6፡ 1-15 አስማት ፡ ወይስ ፡ ታምራት ) በዝርዝር ፡ በማየት ፡ ለመረዳት ፡ እንሞክር ፡፡