በእርግጥ ፡ ዐሥራ ፡ ሁለት ፡ መሶብ ፡ ቁርስራሽ ፡ ተሰብስቧልን?

በእርግጥ ፡ ዐሥራ ፡ ሁለት ፡ መሶብ ፡ ቁርስራሽ ፡ ተሰብስቧልን ?

አምስት ፡ እንጀራና ፡ ሁለት ፡ ዓሣ ፡ ከአምስት ፡ ሺህ ፡ ሰዎች ፡ በላይ ፡ ከተመገቡት ፡ በኋላ ፡ በእርግጥ ፡ ይህንን ፡ ያህል ፡ ቁርስራሽ ፡ ሊሰበሰብ ፡ ይችላልን ? ወይስ ፡ ሌላ ፡ ትርጓሜ ፡ ሊኖረው ፡ ይችላልን ? ብዙዎች ፡ የመጽሐፍ ፡ ቅዱስ ፡ ሊቃውንቶች ፡ ይህንን « ዐሥራ ፡ ሁለት ›› የሚለው ፡ ቃል ፡ በተለያየ ፡ መልኩ ፡ ሲተነትኑትና ፡ የተለያየ ፡ ትርጓሜ ፡ ሲሰጡት ፡ ይታያል ፡፡ ከእነዚህም ፡ ትንተናዎች ፡ መካከል ፡ እንደ ፡ ምሳሌ ፡ አንዱን ፡ እንይና ፡ የበለጠ ፡ ትርጉም ፡ ሊሰጠው ፡ ይችላል ፡ ወደሚባለው ፡ ሀሳብ ፡ እናትኩር ፡፡ አሥራ ፡ ሁለት ፡ መሶብ ፡ ዐሥራ ፡ ሁለቱ ፡ የእስራኤላውያን ፡ ነገዶች ፡ የሚያሳይ ፡ ሲሆን ፡ እነዚህ ፡ ነገዶች ፡ በሙሉ ፡  ማለትም ፡ እስራኤላውያን ፡ በሙሉ ፡ ማለት ፡ ነው ፡ ወደ ፡ እኔ (ወደ ኢየሱስ) ቢመጡ ፡ የተትረፈረፈ ፡ የሕይወት ፡ እንጀራ ፡ ያገኛሉ ፡፡ ስለዚህ ፡ ኢየሱስ ፡ የሁሉም ፡ እስራኤላውያን ፡ አዳኝ ፡ መሆኑንና ፡ ለሁላቸውም ፡ ዘላለማዊ ፡ የሆነ ፡ የሕይወት ፡ እንጀራ ፡ ሰጭ ፡ መሆኑን ፡ ለማመልከት ፡ ነው ፡ በማለት ፡ የሚፈቱት ፡ አሉ ፡፡

ከብዙ ፡ ትንታኔዎች ፡ መካከል ፡ ውስጥ ፡ የበለጠ ፡ መልእክት ፡ አስተላላፊነቱን ፡ የሚታመንበት ፡ ግን ፡ ቀጥሎ ፡ የሚገኘው ፡ ሀሳብ ፡ ነው ፡፡ ዐሥራ ፡ ሁለት ፡ መሶብ ፡ በአሥራ ፡ ሁለቱ ፡ የእስራኤል ፡ ነገዶች ፡ መመሰሉና ፡ የተረፈውንም ፡ ምግብ ፡ ለእስራኤላውያን ፡ በሙሉ ፡ የሚያረካ ፡ የሕይወት ፡ እንጀራ ፡ ኢየሱስ ፡ ነው ፡ ብሎ ፡ መገለጹ ፡ ተገቢ ፡ አይደለም ፤ ምክንያቱም ፡ ኢየሱስ ፡ ለእስራኤላውያን ፡ ብቻ ፡ የመጣና ፡ ትኩረቱ ፡ እነሱ ፡ ላይ ፡ ብቻ ፡ ያደረገ ፡ መስሎ ፡ ያሳያል ፡፡ ይህም ፡ ከእስራኤላውያን ፡ ነገዶች ፡ ውጪ ፡ ላሉት ፡ የኢየሱስን ፡ የአዳኝነት ፡ ተግባር ፡ ወይም « የሕይወት ፡ እንጀራነቱን ›› ለሁሉም ፡ ሕዝቦች ፡ መሆኑን ፡ ይገድባል ፡፡ ስለዚህ ፡ ዐሥራ ፡ ሁለት ፡ መሶብ ፡ ቁርስራሽ ፡ መሰብሰቡን ፡ የሚያሳየው ፡ ኢየሱስ ፡ የሚሰጠው ፡ የሕይወት ፡ እንጀራ ፡ ጊዜያዊና ፡ የሚያልቅ ፡ ሳይሆን ፡ ለዘላለም ፡ የሚኖር ፡ የሕይወት ፡ እንጀራና ፡ እሱንም ፡ የተመገቡት ፡ የሚጠፉ ፡ ሳይሆኑ ፡ ለዘላለም ፡ የሚኖሩ ፡ መሆናቸውን ፡ ለማሳየት ፡ ነው ፡፡ በእርግጥም ፡ ኢየሱስ ፡ ሲያስተምር « አባቶቻችሁ ፡ በምድረ ፡ በዳ ፡ መና ፡ በሉ ፡ ይሁን ፡ እንጂ ፡ ሞቱ ፡፡ ነገር ፡ ግን ፡ ሰው ፡ እንዳይሞት ፡ ይበላው ፡ ዘንድ ፡ ከሰማይ ፡ የወረደ ፡ የሕይወት ፡ እንጀራ ፡ እኔ ፡ ነኝ ፤ ማንም ፡ ሰው ፡ ከዚህ ፡ እንጀራ ፡ ቢበላ ፡ ለዘላለም ፡ ይኖራል ፡ ይህም ፡ እንጀራ ፡ ለዓለም ፡ ሕይወት ፡ እንዲሆን ፡ የምሰጠው ፡ ሥጋዬ ፡ ነው ›› በማለት ፡ አበክሮ ፡ ገልጾታል(ዮሐ 6 ፡ 49) ፡፡