ዘጰራቅሊጦስ

 በዓለ ጰራቅሊጦስ 

የቅዳሴ ንባባት ጥቅሶች

1ኛ ቆሮ.15:33-51 

1ኛ ዮሐ. 2:12-15 

የሐዋ. ሥራ 2:1-12

ወንጌል ዮሐ. 16:7-16


የአንድነትና የፍቅር ቋንቋ - እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ

ጌታ ሞትን ድል አድርጎ ከትንሣኤ 50 ቀናት እንዲሁም ወደ ሰማይ በክብር ካረገበት ደግሞ 10 ቀናት በኋላ በዓለ ጰራቅሊጦስን፡ እናከብራለን።

በዓለ ጰራቅሊጦስ:-

- መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ የወረደበት
- አማንያን በሐዋርያት ስብከትና በምስጢረ ጥምቀት ከክርስቶስ ጋር ተዋህደው የአዲስ ኪዳን አዲስ ሕይወት የጀመሩበት
- በመንፈስ ቅዱስ የምትመራዋ ቅድስት ቤተ ክርስትያን በይፋ የተቆረቆረችበት
- ሕግዋ ፍቅር፤ እውነትም መሠረትዋ የሆነችው ቤተክርስትያን የአማኞች ማኅበር ሆና የተመሠረተችበት ፍጻሜ ነው።

የበዓለ ጰራቅሊጦስ ሁኔታና ክናዋኔዎች ዛሬ ባነበብነው የሐዋርያት ሥራ ሁለተኛ ምእራፍ ላይ የሚከተሉትን ነጥቦች እናገኛለን፦

· በዓለ ኀምሳ የተባለውም ቀን በደረሰ ጊዜ፥ ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው አብረው ሳሉ፥ 

· ሐዋርያት በአንድ ቤት ተሰብስበው ለዘጠኝ ቀናት በጸሎት ላይ እንደነበሩ --ከዕርገት- ጰራቅሊጦስ- (በቤተ ክርስትያናችን የዘጠኝ ቀናት ጸሎት (Novena) የምናደርገው ከዚሁ የጀመረና በዚሁ ምሳሌነት ነው።)

· በድንገት እንደሚነጥቅ ዓውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምፅ መጣ፥ ተቀምጠው የነበሩበትንም ቤት ሁሉ ሞላው። 

· እንደ እሳትም የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዩአቸው፤ በያንዳንዳቸውም ላይ ተቀመጡባቸው።

· በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፥ መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደ ሰጣቸው በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር። 

· ከሰማይም በታች ካሉ ሕዝብ ሁሉ በጸሎት የተጉ አይሁድ በኢየሩሳሌም ይኖሩ ነበር፤

· ይህም ድምፅ በሆነ ጊዜ ሕዝብ ሁሉ ተሰበሰቡ፥ እያንዳንዱም በገዛ ቋንቋው ሲናገሩ ይሰማ ስለ ነበር የሚሉትን አጡ። 

· ተገርመውም ተደንቀውም እንዲህ አሉ። እነሆ፥ እነዚህ የሚናገሩት ሁሉ የገሊላ ሰዎች አይደሉምን? 

· እኛም እያንዳንዳችን የተወለድንበትን የገዛ ቋንቋችንን እንዴት እንሰማለን? (ግሐ 2፡ 1-4)

ይህ የአዲስ ኪዳን ታላቅ ክንዋኔ የተፈጸመው አይሁድ በዓለ ኀምሳቸውን በሚያከብሩበት ዕለት ነው። አይሁዳውያን በየዓመቱ ከግብፅ ባርነት ነፃ የመውጣታቸውን በዓለ ፍሥሐ ካከበሩበት ከሶስት ቀናት በኋላ ምርታቸውን የሚሰበስቡበት ወቀት በመሆኑ የመጀመርያ ፍሬዎችን ይዘው፡ ዝናሙን፡ ነፋሱንና፡ ጸሐዩን አመጣጥኖ በመስጠት በመሬት ለተዘራውም ዘር ሕይወትን ሰጥቶ፡ አብቅሎ፡ አለምልሞ፡ እንዲያብብ በማድረግ በ 30፡ 60፡ እና መቶ እጥፍ አፍርቶ አትረፍርፎ የሰጣቸውን አምለክ የሚያመሰግኑበት በዓልም ነበራቸው። (ዘፀ 34፡22፤ ዘኁ 16፡10) ይህ በዓል እስከ ኀምሳ ቀናት ከተከበረ በኋላ በእርሾ የተጋገረ ቂጣ እንደ የምስጋና መባ የሚያስያስገቡበት ዕለትም ነበር። (ዘሌዋ 23፡ 17-20፤ ዘኁ 16፡9-10)

ይህን በጣም የታወቀ በዓል በከፍ ያለ ሁኔታ ለማክበር አይሁዳውያን ከያሉበት ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም ይሰበሰቡ ነበር።

የጰራቅሊጦስ ተአምር የተፈጸመበት ዕለት ከዚሁ በዓል ጋር የተደራረበም ስለነበር በዚያን ዕለት በኢየሩሳሌም በጣም ብዙ ሕዝብ መገኘት ቻለ። ያ የአውሎ ነፋስ የሚመስል ድምጽ በተሰማ ጊዜ ሕዝቡ ምንድነው? በማለት ሐዋርያቶቹ ወደ ነበሩበት ቦታ አመሩ። ያን ጊዜ ከልዩ ልዩ ቦታዎችና የተለያዩ ቋንቋዎች ተናጋሪ የሆነው ሕዝብ፡ ሐዋርያት በሚያውቁት በገዛ ቋንቋችው ሲናገሩ፤ በሐዋርያት አንደበት ተናጋሪ፡ በሕዝቡ ጆሮ ሰሚ በሆነው መንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ሁሉም በየቋንቋቸው ይረዱት ነበር። (ግሐ 2፡ 7-13)

ሁሉም ተገረሙና አመንትተው እርስ በርሳቸው እንጃ ይህ ምን ይሆን? አሉ። ሌሎች ግን እያፌዙባቸው። ጉሽ የወይን ጠጅ ጠግበዋል አሉ። (ግሐ 2፡ 12-13)

ያን ጊዜ ሊቀ ሐዋርያት “ጴጥሮስ ከአሥራ አንዱ ጋር ቆመ፥ ድምፁንም ከፍ አድርጎ እንዲህ ሲል ተናገራቸው። አይሁድ በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሁላችሁ፥ ይህ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን፥ ቃሎቼንም አድምጡ።” (ግሐ 2፡14…) በማለት በብሉይ ኪዳን ስለ መንፈስ ቅዱስ የነበረውን ትንቢት ጠቅሶ ይሰብክ ጀመረ። ስለ ጌታ ኢየሱስ ስለ ሕማማቱና ትንሣኤው በሰፊው አስተማረ። ሕዝቡም ይህንን ሐቅ በሰሙ ጊዜ በልባቸው ሠረፀና በአምላክ አመኑ። “ይህንም በሰሙ ጊዜ ልባቸው ተነካ፥ ጴጥሮስንና ሌሎችንም ሐዋርያት። ወንድሞች ሆይ፥ ምን እናድርግ? አሉአቸው። ጴጥሮስም። ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ። የተስፋው ቃል ለእናንተና ለልጆቻችሁ ጌታ አምላካችንም ወደ እርሱ ለሚጠራቸው በሩቅ ላሉ ሁሉ ነውና አላቸው። በብዙ ሌላ ቃልም መሰከረና። ከዚህ ጠማማ ትውልድ ዳኑ ብሎ መከራቸው። ቃሉንም የተቀበሉ ተጠመቁ፥ በዚያም ቀን ሦስት ሺህ የሚያህል ነፍስ ተጨመሩ” (ግሐ 2፡ 37-41)

የክርስትያን ሕይወት አርአያ መሆን የሚገባውንና መንፈሳዊ ቅናትን በውስጣችን መጫር ያለበትን ሃሳቦች ሲተርክ እንዲህ ይላል... ያመኑት ደግሞ፦

· ያመኑትም ሁሉ አብረው ነበሩ፤ 

· ያላቸውንም ሁሉ አንድነት አደረጉ። 

· መሬታቸውንና ጥሪታቸውንም እየሸጡ፥ 

· ማንኛውም እንደሚፈልግ ለሁሉ ያካፍሉት ነበር።

· በየቀኑም በአንድ ልብ ሆነው በመቅደስ እየተጉ በቤታቸውም እንጀራ እየቈረሱ፥ 

· በደስታና በጥሩ ልብ ምግባቸውን ይመገቡ ነበር፤ 

· እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ 

· በሕዝብ ሁሉ ፊት ሞገስ ነበራቸው። 

· ጌታም የሚድኑትን ዕለት ዕለት በእነርሱ ላይ ይጨምር ነበር። (ግሐ 2፡ 45-47)

የጰራቅሊጦስ ዕለት የተከሰተው ሁኔታ ሁሉ በፊት በባቢሎን ላይ የተለያየውን ቋንቋና ሕዝብ ወደ አንድነት የሚመልስ ፍጻሜ ነው። በባቢሎን ሕዝቡ ከእግዚአብሔር ስለሸፈተ ቋንቋቸውን በተነባቸው። ሊረዳዱም አልቻሉም። በአንጻሩ በጰራቅሊጦስ ደግሞ የተበታተነውን ሰብስቦ አንድና አዲስ ሕዝብ አድርጎ ሐዋርያት ባንድ ቋንቋ የተናገሩትን ሁሉም ሊረዱት እንደሚችሉ አደረገ። 

ክርስቶስ በሞቱና በትንሣአው ዓለምን አድሶ የጽድቅ ፍሬ እንድናፈራና ለዘላለም የህይወት ጎተራ በሆነው በመንግሥተ ሰማያት ሊሰበስበን ፈቅዶ አይሁዳውያን የምርት በዓላቸውን በሚያከብሩበት በበዓለ ኀምሳ ሐዋርያቱን ልኮ የመጀመርያ የመዳን ፍሬ የሆኑትን 3000 ምእመናንን አፈሩ።

ስለዚህ እኛም በጥምቀታችን ምክንያት ራሱ አማላክና የእግዝአብሔር ታላቅ ስጦታ የሆነው መንፈስ ቅዱስን ተቀብለናልና ከሱ ጋር ሆነን እግዚአብሔር በሚከበርበት እኛም በምንድንበት መንገድ እንጓዝ። 

የእግዚአብሔር ልጆች የአንድነት ቋንቋ በሆነው በእግዚአብሔር ፍቅርና በእርስ በርሳችን ፍቅር ተዋህደን የአዲስ ኪዳን ሕዝብና መንፈስ ቅዱስ የሚመራው ሕዝብ ሆነን እንጓዝ።

አባ ዓውተ ወልዱ ሲታዊ 
{play}Mezmur/Track22.mp3{/play}