3ኛ ጰራቅሊጦስ

3 ሰንበተ ጰራቅሊጦስ

የቅዳሴ ንባባት

1 ቆሮ.12:1-12

1 ዮሐ. 2:20-ፍጻሜ

የሐዋ. ሥራ 2:14-22

ወንጌል ዮሐ. 14:22-ፍጻሜ

ሰላማችን ክርስቶስ ነው

ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም። ልባችሁ አይታወክ አይፍራም። (ዮሐ. 14 27)

መጽሐፍ ቅዱስም ስለ ሰላም በብዙ ቦታና መልክ ይናገራል። ለምሳሌ ያህል ጥቂቶቹን ለመጥቀስ፦

ኢሳ 9 6 ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል

ማቴ 5 9 የሚያስተራርቁ ብፁዓን ናቸው፥ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና።

1 ቆሮ 14 33 እግዚአብሔርስ የሰላም አምላክ ነው እንጂ የሁከት አምላክ አይደለምና፤ በቅዱሳንም አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እንዲህ ነው።

ገላ 5 22 የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ቸርነት፥ በጎነት፥ እምነት፥ የውሃት፥ ራስን መግዛት ነው።

የሰው ልጅ በሰላም እየኖረ ነው ለማለት በሶስት አቅጣጫ በሰላም ላይ መገኘት አለበት።

1. ሰላም ከእግዚአብሔር ጋር- ከእግዚአብሔር ጋራ በሰላም የምንኖርበት ሰላም

2. ሰላም ከገዛ ራሳችን- ከገዛ ራሳችን/ከኅሊናችን/ ጋር በሰላም የምንኖርበት ሰላም

3. ሰላም ከባልንጀራችን- ከባልንጀራችን ጋር በሰላም የምንኖርበት ሰላም

1. ሰላም ከእግዚአብሔር ጋር

መጀመርያ ከእግዚአብሔር ጋር የምናተሳስረው ሰላም አለ። የዚህ ዓይነቱ ሰላም እንዲገኝ በእግዚአብሔር ማመን፣ እግዚአብሔርን በሕይወታችን ላይ ማስገባት፣ እግዚአብሔርን ማወቅ፤ መውደድና መታዘዝ ያስፈልጋል። እግዚአብሔር ከኛ ጋራ መሆኑንና ሰላማችን እሱ ራሱ መሆኑን መረዳትና መቀበል ይኖርብናል። ከዚህ ውጪ በሆነ መንገድ ውስጣዊና ዘላቂ ሰላም ሊገኝ አይችልም። ሰላም የምትገኘው በሕይወታችን ላይ አንደኛውን ስፍራ ለእግዚኣብሔር ስንሰጥ ብቻ ነው። እግዚአብሔርን ከልብ መውደድ፡ የእግዚኣብሐርን ፈቃድ እየፈጸሙ መመላለስ፡ የማያሳስት የሰላም ጐደና ነው።

2. ሰላም ከገዛ ራሳችን ጋር

ከእግዚኣብሔር ጋር በሰላም በምንገኝበት ጊዜ ቀስ በቀስ ውስጣዊ ሕይወታችንም መንገዱን እየያዘ ሰላምን እንደ የሕይወታችን ዓላማ እያደረግን እንመጣለን። ሰላማችን የሆነው እግዚአብሔር በሕይወታችን ላይ ሲነግሥ፡ ክርስቶስን የሕይወታችን ንጉሥ አድርገን በምንመላለስበት ጊዜ፡ ንጉሠ-ሰላም የሆነው ክርስቶስ ከኛ ጋራ ስላለ በገዛ ራሳችን፡ በሕይወታችን ሰላም ይነግሣል። በዚሁ መልክ ከገዛ ራሳችን ጋር በሰላም እንገኛለን። ይህ ግን የሕይወታችን የመጨረሻ ፍጻሜ አይደለም። የሰው ልጅ ዓላማው ከሆነው ከእግዚአብሔር ጋር ለአንዴና ለዘለዓለም በሰማያዊትና የማትለዋወጠው የሰማይ ሰላም ላይ እስኪደርስ ድረስበቃ አሁን ከዚህ በላይ የምፈልገው ነገር የለኝምብሎ ማረፍ አይገባውምም አይችልምም።

4. ሰላም ከባልንጀራችን ጋር

ከባልንጀራችን ጋር ሰላም ሊኖረን የሚችለው ከእግዚአብሔርና ከገዛ ራሳችን ጋር ሰላም ሲኖረን ብቻ ነው። ከሰዎች ጋር ያለን ግንኙነት ከእግዚአብሔር ጋርና ከገዛ ራሳችን ጋር ያለንን ሰላም ያንጸባርቃል። በውስጡ የታወከና ከእግዚአብሔርም የተለየ ሰው ከሌሎች ጋር በሰላም ሊኖር ኣይችልም።

ክርስቶስ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ ብሎናል። ክርስቶስ ሰላም ሰጪአችን ብቻ ሳይሆን ሰላማችን ራሱ ስለሆነ፡ ሰላሙን ሲሰጠን የሚሰጠን የገዛራሱን ነው ለዚህም ነው መላእክተ ሰማይ ክርስቶስ በተወለደልን ጊዜክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድብለው የዘመሩት። እንዲሁም ክርስቶስ እኛን ለማዳን ሞቶ ከሞት በተነሣ ጊዜ የመጀመርያ ሰላምታውሰላም ከእናንተ ጋር ይሁንየሚለው ነበር። ስለዚህም ነው ደግሞ ቅድስት ቤተ ክርስትያን የክርስቶስ አባሎች ለሆኑት ምእመናን፡ በቃሉና በሥጋሁ ወደሙ ገበታ ላይ ለመካፈል ሲሰባሰቡሰላም ከእናንተ ጋር ይሁንበማለት ክርስቶስ ከያንዳንዳችን ጋር የሚሆንበትን ምሥጢር በሚገልጽ መንገድ ሰላምታ የምታቀርብልን።

ስለዚህ ከእግዚአሔብር ጋር ሰላም እንዲኖረን ሕጉን እንጠብቅ፤ ከገዛ ራሳችን ጋር ሰላም ሊኖረን የምናምነውንና የምንሠራውን እናስማማ፤ ከባልንጀሮቻችን ጋርም ሰላም እንዲኖረን ደግሞ እነሱ ለኛ ሊያደርጉልን የምንፈልገውን እኛም ለእነርሱ እናድርግላቸው።

በመጨረሻምየሰላም አምላክ ራሱ ሁለንተናችሁን ይቀድስ፤ መንፈሳችሁም ነፍሳችሁም ሥጋችሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ያለ ነቀፋ ፈጽመው ይጠበቁ።” (1 ተሰሎ 5 23) አሜን።

አባ ዓውተ ወልዱ ሲታዊ

{play}Mezmur/Track17.mp3{/play}