ቃል ሥጋ ሆነ በእኛም አደረ

ቃል ሥጋ ሆነ በእኛም አደረ

የአዳም ልጆች በሙሉ እዲመጣላቸው በናፍቆት ይጠብቁት የነበረው መሲሕ የተወሰነው ጊዜ ሲደርስ መጣ፡፡ በዚህም ሁኔታ የነቢያት ትንቢት ተፈጸመ፣ ሐቅነቱ በግዙፍ በዓይን ታየ፡፡ እግዚአብሔር ለአባታችን አዳም “አዳኝ እልክልሃለሁ” እያለ አስቀድሞ ሰጥቶት የነበረው የተስፋ ቃል ዛሬ ተግባራዊ ሆኖ በዐይን ምስክር ታይቶአል፡፡ ጊዜው ከደረሰ በኋላ እግዚአብሔር በኦሪት ሕግ ሥር የነበሩትን ለማዳንና ልጆችም እንዲሆኑ መብትን ሊሰጣቸው ከሴት የሚወለድ በሕግም የሚመላለስ ልጁን ላከ፡፡ የመድኃኒታችንና የአምላካችን ደግነትና ሰውነት በይፋ ተገለጠ፡፡ ባደረግነው የጽድቅ ፍሬ ሳይሆን በምሕረቱ አዳነን፤ አምላክ እኛን ለመምሰል እንደ እኛ ምስኪን ድኻ ሰው ሆነ፡፡

በዛሬው ቀን ክርስቶስ አምላካችንም እኛን ለማዳን ተከታዮቹና ወዳጆቹ ሊያደርገን ሥጋችንን ለብሶ እኛንም መስሎ በመካከላችን መጣ፡፡ “ቃል ሥጋ ኮነ ወኃደረ ላዕሌነ - ቃል ሥጋ ሆነ በኛም አደረ”  ይላል ቅዱስ ዮሐንስ 1:14፡፡ አምላክ  ሥነ- ማዕረጉን ሁሉ ትቶ፣ ትልቅነቱን ንቆ ዝቅተኛና ደካማ ባሕርያችንን ተሸከመ፣ የራሱም አደረገው፡፡ በዚህ ጭንቅ የተሞላበት ከባድ ኑሯችን ከኃጢአት በስተቀር ልክ እንደ እኛ እንደ አንዱ ሆኖ ለመኖር ስለ ደኅንነታችን ፍቅር ከሰማይ ወደ ጊዜያዊ መኖሪያችን ወደ ምድር ወረደ፡፡

“ኦ! ፍቅር ዘጠነዝ ፍቀር ኦ! ትሕትና ዘመጠነዝ ትሕተና። ፍቅር ሰሐቦ ለወልድ ኃያል እመንበሩ ወአብጽሖ እስከ ለሞት -ኦ! ይህን የሚያህል  ፍቅር ምን ያህል ፍቅር ነው፤ ኦ! ይህን የሚያህል ትህትናስ ምን ዓይነት ትሕትና ነው! ፍቅር ኀያሉን ወልድ  ከመንበሩ ስቦ እስከ ሞት አደረሰው”

እያለ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይናገራል፡፡

ዓለም ሳይፈጠር ጀምሮ ከእርሱ ጋር በነበረ በአምላክ አንድ ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ አምናለሁ፡፡ በእውነት ብርሃን ከብርሃን እውነተኛ አምላክ ከእውነተኛ አምላክ የተወለደ እንጂ የተፈጠረ አይደለም፡፡ መለኮታዊነቱ ከአብ ጋር እኩል ነው፡፡ ሁሉ በእርሱ የሆነ ያለእርሱ ምንም የሌለ ስለ ደኅንነታችን ከሰማይ ወረደ በመንፈስ ቅዱስ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደ፡፡

ይህ በፊታችን ያለው ትናንት የተወለደ ሰማያዊ ሕፃን ነው፡፡ ፈጣሪ ሆኖ ሳለ እኛን ለማጽናናትና የድኀንነትን ብርሃን ሊሰጠን ሕፃን ሆኖ ወደ እኛ መጣ፡፡ አዳም በልጆቹ አማካይነት ይህን መሢሕ በብዙ ምኞትና ናፍቆት ጠበቀው፤ ቶሎ መጥቶ ከመጥፎ ኑሮው እንዲያድነውም በሙሉ ልብ ተማጠነው፡፡ ቀንም ሌሊትም  ለመነው፡፡ ይኸው ዛሬ ምኞቱን ሊያሟላለት የድኀንነትን ብርሃን ሊያበራለት መሢሕ ወደ እርሱ ቀረበ፡፡ “ደስታዬ ከሰው ልጆች ጋር መሆን ነው” እያለ ከእኛ ጋር ሊቀመጥ ፈለገ፡፡ ከእኛ ጋር በመሆን ሊጠብቀን፣ በሚያስፈልገን ሁሉ ሊረዳን፣ ከጠላት ሊታደገን የምድራዊ የሰው ልጅ መልክ ለብሶ መጣ፡፡ በጸጋዎቹ ሀብታሞች ሊያደርገን የእግዚብሔርን መንገድ ሊመራን ወስኖ ከእኛ ጋር ለመኖር መጣ፡፡

ወልድ ሰው ሆነ በመካከላችንም ደግሞ ተቀመጠ፡፡ ልዑል አምላክ ስለፍቅራችን እኛን መሰለ፤ በፍቅሩና በትሕትናው እያመሰገንነው በክፋታችን ከእኛ እንዲርቅ እንዳናደርገው እንጠንቀቅ፡፡ ልባችንን ከልቡ ጋር ፈቃዳችንን ከፈቃዱ ጋረ እንድናደርገው ቃሉን እንስማ፤ ከሁሉ በላይ ደግሞ እርሱን እንፈልግ፣ ኑሯችንም ከእርሱ ጋር ይሁን፡፡

ምንጭ፡

መንፈሳዊ ማሳሰቢያ