የእግዚአብሔርን ቃል የሚያዳምጥ ጆሮ - ቅድስት ቤተሰብ -ዘጥምቀት ፪ኛ

ሉቃ 2፡41-52 (ዘጥምቀት አስተርእዮ 2ኛ)

እዚህ ወንጌሉ ሊያስተምረን የፈለገው ነገር ክርስቲያን ተብለን ልንጠራ የምንችለው በቤተሰባችን እያንዳንዳችን ለእግዚአብሔር ዕቅድ/ ጉዳይ ቅድሚያ የሚሰጥ ሕይወት ስንኖር መሆኑን ነው፤በዚሁ ወንጌል በዚህ በቅድስት ቤተሰብ እናት ሆና የምናገኛት ማርያም የእግዚአብሔርን ቃል የምታዳምጥ ሴት ሆና እናገኛታለን፤እግዚአብሔር ዓለምን ለማዳን ባለው ዕቅድ የዘመኑ ፍጻሜ ሲደርስ ለማርያም ቃሉን ይናገራል፤እሷም ምንም እንኳን ያ ቃል ለመረዳት የሚያስቸግር መስሎ ቢታያትም ‹‹እነሆኝ የእግዚአብሔር አገልጋይ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ›› በማለት ተቀበለችው (ሉቃ 1፡39-45)፡፡ በዚሁ ቤተሰብ አባት የሆነው ዮሴፍም እንዲሁ የእግዚአብሔርን ቃል የሚያዳምጥ ጆሮ ያለው ሰው ሆኖ እናገኘዋለን እግዚአብሔርም በመልአኩ በኩል የተናገረውን ቃል ሰምቶ በፍጹም ልቡ ይታዘዛል (ማቴ 1፡24)፡፡እንዲሁም በዚሁ ቤተሰብ ልጅ የሆነው ኢየሱስ የእግዚአብሔር መገለጫ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ እንግዲህ በዚህ ቤተሰብ እያንዳንዳቸው ለእግዚአብሔር ፈቃድና ዕቅድ ቅድሚያ በመስጠት ይኖራሉ፤የእግዚአብሔርንም ቃል መስማትና በሱም መመራት እግዚአብሔርም በሕይወታቸው በነፃነት እንዲገለጽ ያደርጋሉ፡፡ክርስቲያን የሆነ ቤተሰብም እንዲሁ በተመሳሳይ መልኩ የእግዚአብሔርን ቃል፡ ሕይወቱን የሚመራ ቀዳሚ መንገዱ/ሐሳቡ ሊያደርገው ይገባል፡፡

ክርስቲያን ቤተሰብ በየመደቡ (አባት፣እናት፣ልጅ) የሕይወቱን ራእይ፣ዓላማና ዕቅድ እግዚአብሔር በቃሉ እንዲመራውና እንዲገለጽበት ሊፈቅድ ይገባል፡፡ ከክርስቲያንም ቤተሰብ የሚጠበቀው የያንዳንዱ አባል ሕይወት በእግዚአብሔር መንፈስ የተሞላ ሆኖ እርስ በርሳቸውም ሆነ ከሌሎች ሰዎች ጋር በምሕረት፣ በትዕግስት፣በትሕትናና በየዋህነት በፍቅርም የተሞላ ግንኙነት እንዲሆራቸው ነው፡ቆላ 3፡11-15፡፡ እኛም በየቤተሰባችን እንደ ማርያም ዮሴፍና ኢየሱስ ለእግዚአብሔር ጉዳይ ቅድሚያ የምንሰጥ ከሆነ ትልቁ ቤተሰባችን ማለትም የክርስቶስ አካል የሆነችው ቤተክርስቲያን በሰላምና በቅድስና በፍቅርም የተመሠረተ ሕይወት ይኖራታል፡፡ ስለዚህም በየቀኑ በተለያዩ መንገዶች ለያንዳንዱ ቤተሰብ አባል የሚመጣውን ፈተናና ዕንቅፋት በቤተሰባችን እንዲገዛ በተቀበልነው/በፈቀድነው በእግዚአብሔር ኃይል እየተቃወምንና እየተዋጋን የቅድስት ቤተሰብን አርአያ ተከትለን ለእግዚአብሔር የመታዘዝ ሕይወት እንድንኖር ተጠርተናል፡፡የቅድስት ቤተሰብን አብነት መከተል ቅዱሳን ያደርገናል፤ይህም የቅድስና ሕይወት (እግዚአብሔርን የመስማትና የመታዘዝ ሕይወት) ትንሹም ሆነ ትልቁ ቤተሰባችን እንዳይፈርስ የሚያደርግ ኃይልና መከላከያም ነው፡፡ እንግዲህ የክርስቶስ አካል የሆንን ሁላችን የእግዚአብሔር ፈቃድ በወለደንና ባዛመደን ቤተሰብ ሁሉ ለሱ በመገዛት ሰላማችን የሆነውን የክርስቶስን ሰላማዊ ሕይወት እንኑር ሮሜ 5፡1-2፡፡

ይትባረክ ኢየሱስ ክርስቶስ