ሁላችሁ የእግዚአብሔር ልጆች በሥራችሁ አሜን በሉ! ዘልደት

እንኳን ለ2005 ብርሃነ ልደቱ አደረሳችሁ!
‹‹ምሕረትና አውነት ተገናኙ፣ጽድቅና ሰላም ተስማሙ፣እውነት ከምድር በቀለች ጽድቅም ከሰማይ ተመለከተች›› መዝ 85፡10-11 ይህ ትንቢት በመድኃኒታችን በአየሱስ ክርስቶስ ልደት ተፈጸመ፤ከድንግል ማርያም በተወለደው በኢየሱስ ምሕረትና እውነት ተገናኙ፤ጽድደቅና ሰላምም በሱ ተስማሙ፤እውነትም ከምድር በቀለች፤ጽድቅም ከሰማይ ወደ ምድር ተመለከተ፡፡ ይህ እውነት ምንድነው ብንል የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ምድሩ ደግሞ ሥጋው ነው፤ ክርስቶስ ከማን ተወለደ ብንል ያችን ምድር እናገኛለን፡ እሷም ምድር ንጽሕት የሆነች ቅድስት ድንገል ማርያም ናት፡፡

በዘላለማዊ አባቱ እቅፍ የነበረው የእግዚአብሔር ልጅ በናቱ እቅፍ ለመሆን ከምድር ወጣ፣ሰማየ ሰማያት ሊይዙት የማይችሉት እውነት በግርግም ለመተኛት ከምድር ወጣ፡፡ ይህንን ያደረገው ለራሱ ጥቅም ሳይሆነ ለኛ ብሎ ነው፡፡ አማኝ የሆነ ሁሉ እዚህ የእምነትን ኃይል ያያል፡ እግዚአብሔር መሆን የማይችለውን ነገር አደረገ ይኸውም ሥጋን ለበሰ፣ እኛም ከአቅማችን በላይ የሆነውን እንድንችል አደረገ፡፡ሁሉን የሚችለው ፍቅሩ የሰው ልጅ አዕምሮ ሊገምተው የማይችለውን አደረገ፤ይኸውም ለትልቅነቱ ወሰን የሌለው እሱ ሕፃን ሆኖ የሰው ልጅ ሁሉ ቤተሰብ ሆነ፡፡ ይህን ሁሉ ማድረግ የቻለ እግዚአብሔር ግን እኔ የልቤን የእምነቴን በር ካልከፈትኩለት ወደኔ ሊገባ አይችልም፤ ሰው እግዚአብሔር በሕወቱ እንዳይገባ ሊያደርግ ይችላል፣ በሕይወቱም እንዳይሠራ የማድረግ ችሎታ አለው፡፡ለመሆኑ አሁን በሕይወታችሁ እየሠራ ያለ ማነው? ምድር ፍሬዋን ሰጠች መዝ. 67፡6 ዱሮ የተረገመችው ምድር አሁን ፍሬ ሰጠች ከሰው እግዚአብሔር ተወለደ፤ በሕይወታችን ፍሬ የምንሰጥበት ጊዜ ነው፡፡ በሱ ሁላችን ፍሬ የሚሰጥ ምድር እንሆናለን፡፡እሱ የሌለው ፍሬ አልባና የተረገመ በለስ ነው፡፡(ቅ.አጎስጢኖስ፣በነዲክቶስ ረ.ሊ.ጳ)፡፡

የገና ወቅት ለእግዚአብሔር እሺ ማለትን የምንማርበት ጊዜ ነው፤ እንደቃልህ ይሁንልን ስንል የእግዚአብሔር ቃል በሕይወታችን ኀይልና ብርሃን ሆኖ በእግዚአብሔር መንግስት እንድንኖር ያደርገናል፤ የእግዚአብሔር መንግስት ልጆችም ያደርገናል፤ እስቲ በምናደርገው ሁሉ አንድ ላይ ሆነን ለእግዚአብሔር መንፈስ ተገዝተን ለሱ እሽ እንበል ክብር ለሱ ይሁን! አሜን?
በዚህ ዓለም ራስ ወዳድነት የሌለው ጥሩና መልካም ምድር አለ፤እግዚአብሔር በኛ መካከል መኖሪያው ያደረው ምድር አለ፤ የድንግል ማርያም ሥጋ የሱ ማደሪያ እንደሆነ ያንተም ያንችም ሥጋ የሱ ማደሪያ ነው፡፡ እናንተም ሕያው መኖሪያው ነችሁ፡፡ ስለዚህ ከእግዚአብሔር ፈቃድ ውጪ ሥጋችንን ልንገለገል አልተፈቀደም ስለሆነም ኢሱስ በሥጋው በፈጸመው ሥራው ሁሉ እግዚአብሔርን እናዳከበረ ሁሉ እኛም በሥጋ በምንፈጽመው ሥራችን ሁሉ እግዚአብሔርን እናክብረው፡፡ እሱ ሰላማዊ ሆኖ በትሑት ሕፃን መልክ እንደተገለጸ ሁሉን ትተን ትሑታን ሆነን የሱ መንፈስ መኖሪያ ሆነን ፈለጉን እንከተል፡፡
በሰማያት ለእግዚአብሔር ክብር ይሁን በምድርም በጎ ፈቃድ ላላቸው ሰዎች ሰላም ይሁን! በቃል ሳይሆን በሥራችሁ ሁላችሁ የእግዚአብሔር ልጆች አሜን በሉ!

በአባ ወልደ ትንሣኤ ባለወልድ - ሲታዊ