እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

የጻድቅ ሰው ሞት ሕይወት ነው!

የጻድቅ ሰው ሞት ሕይወት ነው!


imagesእ.ኤ.አ ሚያዚያ 2/2ዐዐ5 ዓ.ም ያረፋት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔድክቶስ አሥራ ስድስተኛ እጅ እ.ኤ.አ እሁድ ግንቦት 1/2ዐ11 /ሚያዚያ 23/2ዐዐ3 ዓ.ም/ በመለኮታዊ ምሕረት በዓል ዕለት በቫቲካን ብፁዕ ተብለው እንደሚሰየሙ መገለጹን ምክንያት በማድረግ ከፍቅርና ሰላም ጋዜጣ ያገኘነውን የሕይወት ታሪካቸውንና ለብፅእና እወጃ ሂደት ያገዙ ሁኔታዎችን እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

የካቶሊክ ቤተክርስቲያንን ለሃያ ሰባት ዓመታት ያህል የመሩት ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት እንዳረፉ በቀብራቸው ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙ ምእመናን “ቶሎ ቅዱስ ይባሉ” እያሉ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ሲያስተጋቡ ተስተውለዋል፡፡ ከሮም ዮሴፍ ቮይቲዋ በወዶዊች መንደር በፖላንድ እ.ኤ.አ 18/192ዐ ከአባታቸው ከሮል ቮይቲዋና ከእናታቸው ኤሚሊያ ከቾሮቮሰከ ተወለዱ፡፡ ለቤተሰባቸው ከተወለዱ ከሦስት ልጆች መካከል የሁሉ ታናሽ ነበሩ፡፡

ከአንድ ወር በኋላ እ.ኤ.አ ሰኔ 2ዐ/192ዐ በቁምስናቸው ቤተክርስትያን ተጠመቁ፡፡ እ.ኤ.አ ግንቦት 1938 ዓ.ም በአሥራ ስምንት ዕድሜያቸው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀው በክራኮቭ በሚገኘው ዩኒቨርሲቲ በድራማ ሥነ ጥበብ ተመዘገቡ፡፡ የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ሳያጠናቅቁ እ.ኤ.አ መስከረም 1/1939 ዓ.ም የሁለተኛ ዓለም ጦርነት ተቀሰቀሰ፡፡ የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውም የዘለቀው እሰከ እ.ኤ.አ ኅዳር 6/1939 ብቻ ነበር፡፡ ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ በሕይወት ዕቅዳቸው በሙሉ ተቀየረ፡፡ ከ194ዐ-1944 ድረስ በድንጋይ ቁፋሮ ሥራ ተሠማርተው ኑሮአቸውን መግፋት ጀመሩ፡፡ በቁፋሮ ሥራ የተሠማሩ ጓደኞቻቸው ቀላል ሥራ የሰጧቸው ሲሆን በተጨማሪም ካሮል አንተ ካህን መሆን አለብህ እያሉ ያቆላምጧቸው ነበር፡፡ “እኔ መረጥኋችሁ እንጂ እናንተ አልመረጣችሁኝም” /ዮሐንስ 15፡16/ የሚለው የጌታ ቃልም የክህነት ሕይወትን እንዲመርጡ አነሣሣቸው፡፡

እ.ኤ.አ 1942 ዓ.ም በክራኮቭ ዘርዓ ክህነት ለመግባት ወስነው ጥያቄያቸው ተቀባይነት ስላገኘ በድብቅ ቤት ተከራይተው የዘርዓ ክህነት ትምህርት እያጠኑ እስከ እ.ኤ.አ ጥር 1945 ቆዩ፡፡ በቅዱሳን ሁሉ በዓል ዕለት እ.ኤ.አ ኅዳር 1/1946 በክራኮቭ የክህነት ማዕረግ ተቀበሉ፡፡ የክህነት መዓረግ ከተቀበሉ በኋላ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ሮም ተላኩ፡፡ በዚያም አንጀሊኩም በሚባል ዩኒቨርሲቲ ጉላገራነጅ ከሚባሉ ከአንድ ታዋቂ ዶሜኒካዊ ሊቅ በመማር እ.ኤ.አ በሐምሌ 1948 በዶክትሬት ተመረቁ፡፡

pope-john-paul-IIከሮም እንደተመለሱ አንድ ኒጎዊች በምትባል የገጠር ቁምስና ቢመደቡም ከአንድ ዓመት በኋላ ክራኮቭ ከተማ ወደሚገኝ ቁምስና /ፍሎሪያን/ ተመለሱ፡፡ በ1953 በሞራል ንባበ መለኮት ከሉብሊን ዩኒቨርሲቲ እንደገና በዶክትሬት ተመርቀው በዚያው ዩኒቨርሲቲ ማስተማር ጀመሩ፡፡ እ.ኤ.አ መስከረም 28/1958 በወጣት ዕድሜያቸው በተወለዱ በ38 ዓመታቸው በቫቬል ከቭድራል የክራኮብ ረዳት ጳጳስ ሆነው ተቀቡ፡፡ እ.ኤ.አ ጥር 13/1964 ዓ.ም የክራኮቭ ሊቀ ጳጳስ አድርገው ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ ስድስተኛ ሰየሟቸው፡፡ ከሦስት ዓመት በኋላ እ.ኤ.አ ሰኔ 26/1967 ዓ.ም ካርዲናል አድርገው ሰየሟቸው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በቫቲካን ሁለተኛ ጉባኤ በመገኘት ቤተክርስቲያን በዘመናችን  /Gaudium et Spes/ የሚለው ሰነድ በማዘጋጀት ከፍተኛ አሰተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ የርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ምርጫ ዝግ ጉባኤ እ.ኤ.አ ጥቅምት 16/1978 ፓፓ አድርጐ መረጣቸው፡፡ እ.ኤ.አ ጥቅምት 22/1978 ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የሚል ስያሜ በመውሰድ ሁለት መቶ ስልሳ አራት /264/ የቅዱስ ጴጥሮስ ተከታይ በመሆን በመንበረ ጴጥሮስ ተቀመጡ፡፡ ከርሳቸው በፊት የተመረጡ ዮሐንስ ጳውሎስ ቀዳማዊ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንን ለሠላሳ ሦስት ቀናት ብቻ መምራታቸው ይታወሳል፡፡ እ.ኤ.አ ሚያዚያ 18/2ዐዐ5 ዓ.ም ካርዲናል ዮሴፍ ራዚንገር የተባሉ በትውልድ ጀርመናዊ የሆኑ የቅዱስ ጴጥሮስ መንበር 265ኛ መሪ በመሆን ቤኔድክቶስ አሥራ ስድስተኛ የሚል ስያሜ በመውሰድ ከዮሐንስ ጳውሎስ ቀጥሎ ተመረጡ፡፡ ከጣሊያን አገር ውጭ አንድ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሲመረጡ ከ455 ዓመታት ወዲህ የመጀመሪያ ፓፓ ሆኑ፡፡ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በምድራችን ከኖሩት 265 የቤተክርቲያን መሪዎች መካከል ቤተክርስቲያንን ለረጅም ዓመታት በማስተዳደር ሦስተኛ ናቸው፡፡ ለረጅም ዓመታት ካስተዳደሩት መካከል የመጀመሪያው ሐዋርያ ጴጥሮስ ተብሎ ሲገመት /ስንት ዓመታት እንዳስተደደሩ በትክክል አናውቅም/ ሁለተኛው ደግሞ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ ዘጠነኛ /ከ1948-1978/ ቤተክርስቲያንን ለሠላሳ ዓመታት የመሩ የቤተክርቲያን መሪ ሲሆኑ ሦስተኛው ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እ.ኤ.አ 1978-2005 /እ.ኤ.አ 1971-1997/ ያስተዳደሩ ናቸው፡፡  የርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ሙሉ መጠሪያ ማዕረጋቸው እንደሚከተለው ነበር፡፡

ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፤ የሮም ጳጳስ፤ የክርስቶስ እንደራሴ፤ የቅዱስ ጴጥሮስ ተከታይ፤ የጳጳሳት ጉባኤ መሪ፤ የመላው ዓለም የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ መሪ፤ የምዕራብ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ፓትሪያሪክ፤ የጣሊያን አገር ጳጳሳት መሪ ጳጳስ፤ የሮም ከተማ ሊቀ ጳጳሳት፤ የቫቲካን መንግሥት መሪና የእግዚአብሔር አገልጋዮች አገልጋይ ተብለው ይጠሩ ነበር፡፡

እ.ኤ.አ ግንቦት 13/1981 ዓ.ም የሻቲካን ምእመናን እየባረኩ ሲያልፉ ከተቃጣባቸው የግድያ ሙከራ ተርፈዋል፡፡ ልክ በዓመቱ ወደ ፋጡማ እመቤታችን ማርያም ቤተክርቲያን ፖርቹጋል በመሄድ ምሥጋና አቅርበዋል፡፡ ለመግደል የሞከረውን አጋከ የተባለውን ግለሰብንም ወደ እስር ቤት በመሄድ ከመጠየቃቸው ባሻገር ይቅርታ አድርገውለታል፡፡

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ከመቶ ሃያ አገሮች በላይ በመጓዝ በዓለማችን ረዥም ርቀት ጉዞ በመጓዝ በዓለማችን ረዥም ርቀት ጉዞ በመጓዝም የመጀመሪያው ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነዋል፡፡ በአፍሪካ አህጉር ቢሆንም ከሠላሳ አምስት አገሮች በላይ የጎበኙ ሲሆን ኢትዮጵያ በዚህ ጉብኝት ውስጥ አልተካተተችም፡፡   ተገኝቶ እንደነበር ይነገራል፡፡ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ለካቶሊካዊያን ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም እውነተኛ አባት ነበሩ፡፡

በካቶሊክ ቤተክርስቲያን አንድ ምእመን ብፁዕ እንዲባል ከተፈለገ የብጽዕናን ዑደት ለመጀመር ቢያንስ ካረፈ በኋላ አምስት ዓመታትን ማለፍ ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን ፓፓ ዮሐንስ ጳውሎስ ባረፋ በጥቂት ሣምንታት የቅድስናቸው ዑደት እንዲጀመር ፓፓ ቤኔድክቶስ አሥራ ስድስተኛ በሰጡት ልዩ ፈቃድ መሠረት እ.ኤ.አ ሰኔ 28/2ዐዐ5 የቅድስናቸው ጉዳይ በካርዲናል ከሚሎ ሩዊኒ የሮም ከተማ የፓፓ እንደራሱ አማካኝነት በይፋ ተከፈተ፡፡ አንድ ምእመን ብፁዕ ወይም ቅዱስ እንዲባል ከተፈለገ አንድ ተአምር ይጠበቃል፡፡ በርግጥ አንድን ግለሰብ ብፁዕ ወይም ቅዱስ የሚያሰኘው በፍቅር በእምነትና በተስፋ መኖሩ/ሯ ነው፡፡ ሲስተር ማሪ ሲሞን-ፔሬል የተባሉ የ46 ዓመት የፈረንሳይ ተወላጅ የሆኑ ገዳማዊተ የፓርኪንሶን ሕመምተኛ ነበሩ፡፡ ከበሽታቸው ለመፈወሰ ዮሐንስ ጳውሎስ እንዳረፉ ወዲያው በርሳቸው አማላጅነት ልመና ማቅረብ ጀመሩ፡፡

ዮሐንስ ጳውሎስ ካረፉ በኋላ ለሁለት ወራት ያህል በስማቸው ስትጸልይ ቆይታ መራመድ መጻፍና መኪና መንዳት አቅቷት የነበረች ሲስተር አንድ ቀን ጠዋት ከእንቅልፏ ስትነቃ በሽታው ለሰው ለመግለጽ በሚያዳግት ተአምር ለቅቋት ተገኘች፡፡ ባሁኑ ጊዜ ሲስተር ማሪ በፓሪስ ከተማ በሚገኝ በማኀበራቸው ሥም በሚንቀሳቀስ ማዋለጃ ሆስፒታል ውስጥ በመሥራት ላይ ትገኛለች፡፡ እ.ኤ.አ  ጥር 14/2ዐ11 ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔድክቶስ አሥራ ስድስተኛ ይህ ተአምር ፓፓ ዮሐንስ ጳውሎስ ብፁዕ ለማሰኘት ብቁ ማስረጃ ነው በማለት የብፁዕናቸው ቀን ሚያዚያ 23/2ዐዐ3 እንዲሆን አወጁ፡፡ ሌሎች ተአምራትም በፓፓ ዮሐንስ ጳውሎስ አማካኝነት አግኝተናል የሚሉ መልእክቶችን ለቅድስና ጥናት ጽ/ቤት አቅርበዋል፡፡

john-paul-II-genogramስለ ቅድስናቸው በተደረገው ጥናታዊ መጽሐፍ ሁለት መቶ አሥራ አራት ሰዎች ፓፓ ዮሐንስ ጳውሎስ ቅዱስ ናቸው ሲሉ መስክረዋል፡፡ ቀኑ ሚያዚያ 23/2ዐዐ3 እንዲሆን የተመረጠበት ዋናው ዓመታዊ ዕለቱ የመለኮታዊ ምህረት ዓመታዊ ክብረ በዓል ከመሆኑም ባሻገር የመለኮታዊ ምህረተ መንፈሳዊነትን ለዓለም ያስፋፋች የሀገራቸው ተወላጅ የሆነችውን ሲስተር ፋውስቲና ኮዋልሰከር ለማክበት ጭምር ነው፡፡ በቀብራቸው ዕለት በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ምእመናንና ከመቶ ሰማንያ የሚበልጡ የአገር መሪዎች እንደተገኙ ሁሉ በብፅዕናቸው በዓልም በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶች አድናቂዎቻቸው የፖላንድ ተወደጆችና ከመላው ዓለም የሚመጡ ምእመናን የቅዱስ ጴጥሮንስ አደባባይና የሮም ከተማን ያጥለቀልቃሉ ተብሎ ይገመታል፡፡ ቅዱስ ተብለው እንዲጠሩ ከተፈለገ ከዚህ ሌላ አንድ ተጨማሪ ተአምር እንዲሠሩ ይጠበቅባቸዋል፡፡

አንድ ተአምር ተፈጸመ የሚባለው ተአምር ቅጽበታዊ ዘላቂና በተለያዩ ሐኪሞች ተመርምሮ በማስረጃ የተረጋገጠ የማያጠራጥር ፈውስ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ ከሚያዚያ 23/2ዐዐ3 ጀምሮ ቅድስናቸው እስኪታወጅ ድረስ ብፁዕ ዮሐንስ ጳውሎስ እየተባሉ በመላው ዓለም በዚህ ክብር ይጠራሉ፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ የተከበሩ ወይም የእግዚአብሔር አገልጋይ እየተባሉ ሲጠሩ ቆይተዋል፡፡ የዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ብፅዕና መታወጅ ለመላይቱ ቤተክርስቲያን ትልቅ የደስታ ምክንያት ይሆናል፤ ምክንያቱም ያወቅናቸውና የዘመናችን ሰው በመሆናቸው ነው፡፡ የርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ሕይወት ለሁላችንም ምሳሌ የሚሆን ነው፡፡ ምክንያቱም በስብከት፣ በፈቅር ለሰው አክብሮትና ይቅርታ በማድረግ የተሟላ ሕይወትን ኖረዋል፡፡ ድሆችንና የተረሱ የኅብረሰተስ አካላትን በመድረስና ወደ ሌሎች እምነት ሰዎች በመድረስ የዓለምን ገጽታ የቀየሩ ሰው ነበሩ፡፡

እኛም ከብፅዕናቸው ዕለት ጀምሮ ልመናና ምስጋና በርሳቸው ስም ወደ አምላካችን ማቅረብ እንችላለን፡፡ በርሳቸው ጸሎትና ልመና እግዚአብሔር ለቤተክርስቲያናችን አንድነትን፣ ፍቅርን፣ ዕድገትንና ቅድስናን ይላክልን፡፡

/ከፍቅርና ሰላም ጋዜጣ -በአባ ኃይለ ገብርኤል መለቁ/

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት